ብልፅግና ፓርቲ በ40 ሚሊዮን ብር አዲስ ጽሕፈት ቤት ሊገነባ ነው

0
722

ብልፅግና ፓርቲ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ከ 40 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ባለሦስት ወለል የጽሕፈት ቤት ሕንፃ ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጠ።
ግንባታው በያዝነው ዓመት ተጀምሮ በቀጣይ ኹለት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል የተባለ ሲሆን፣ የፓርቲው የዞን ኃላፊዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ቢሮዎች፣ ሦስት አዳራሾች እና መዝናኛ ክበቦች እንደሚኖሩት ታውቋል።

ለግንባታው የሚሆነውን ወጪ የፓርቲውን ዓላማ እና ሐሳብ በሚደግፉ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ድጋፍ እና ሀብት በማሰባሰብ ለመሸፈን ታቅዷል ያሉት የዞኑ የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፀሐይ ወራሳ፣ ከክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። በዋነኝነት ግን በፓርቲው አባላት ወጪ ለመገንባት እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።

አያይዘው ፓርቲው በዞኑ በርካታ ደጋፊዎች እንዳሉት የጠቆሙ ሲሆን፣ አሁን የሚገነባው ሕንፃ ፓርቲው በዞኑ ያለበትን የጽሕፈት ቤት እጥረት ለመቅረፍ እንደሚያግዘው ጠቅሰዋል። ለቀጣዩ ምርጫ እንደ ዞን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን ያሉ ሲሆን፣ ፓርቲው በዞኑ ምን ያህል አባላት እንዳሉት ግን ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

ብልፅግና ፓርቲ ከኢሕአዴግ ወደ ብልፅግና ውህድ ፓርቲ ከተሸጋገረ በኋላ በየደረጃው ለሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች እና ከክልል እስከ ዞን ለሚገኙ ቢሮ ኃላፊዎች ከጥር 16 እስከ የካቲት 2/2012 ሥልጠና መስጠቱ የሚታወስ ነው።

ሥልጠናው ከብልፅግና ፓርቲ ምንነትና አስተሳሰብ ዙሪያ የተዘጋጀ እንደሆነ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ የሕዝቡን የሕግ የበላይነት፣ የማኅበራዊ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲሁም በቀጣይ የጋራ አቅጣጫዎች ላይ ለመግባባት የሚያስችል የሐሳብ ልውውጥ እንደተካሄደበት ለማወቅ ተችሏል።

በአዳዲስ እና ነባር አመራሮች መካከል የነበረውን የልምድ እና የእውቀት ከፍተት በመሙላት ኹለቱም በፓርቲው ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች እና እሳቤዎች ላይ እኩል እንዲሰለፉና በትኩረት እንዲሠሩ ለማድርግ እንደሆነም ፓርቲው አስታውቋል።

ብልፅግና ፓርቲን የመሠረቱት የቀድሞው የኢሕአዴግ አባል ሦሰት ፓርቲዎች እና ሕወሓት የንብረት ኦዲት እንዲያደርጉ በምርጫ ቦርድ በታዘዙት መሰረት፣ የንብረት ኦዲት እየተሠራ መሆኑን በሚኒስትር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የውጪ እና የአገር ውስጥ ግንኙነት አስተባባሪ አወሎ አብዲን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያለውን የቀድሞው ኢሕአዴግ ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታን ጨምሮ በመላው አገሪቱ የተለያዩ ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። አሁን ግን ትኩረቱ ኦዲት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም እነዚህ ንብረቶች እዳ ካለባቸው አጠቃላይ ግምት እየተሠራ ሲሆን፣ የዲላው ግንባታም ከዚህ እንደማይለይ ገልፀዋል።
‹‹ቀደም ሲል ኢሕአዴግ በነበረ ጊዜ ለመሥራት የታሰበ በመሆኑ እንጂ አሁን ኦዲት ተደርጎ ገና ብልፅግና ጋር አልደረሰም፤ ግን ኦዲት እየተደረገ ነው›› ብለዋል። ‹‹ፓርቲው ድሮውንም ከሕዝብ በሰበሰበው መዋጮ እና በስጦታ ያገኘው ስለሆነ፣ ወይ ለሕዝብ ወይም ለፓርቲው ይሆናል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here