ሲጋራ በፓኬት የ15 ብር ጭማሪ አሳየ

0
1073

በኢትዮጵያ የሚመረቱ የሲጋራ ምርቶች ላይ ኻያ ፍሬ የሚይዝ አንድ ፓኬት ሲጋራ ከዚህ ቀደም ሲሸጥበት ከነበረው 25 ብር ዋጋ ወደ 40 ብር፣ የ15 ብር ጭማሪ አሳየ።

ምንም እንኳን የምርት ዋጋ ላይ ጭማሪ ባይኖርም፣ አከፋፋዮች በኤክሳይስ ታክስ ምክንያት በሚኖረው የዋጋ ጭማሪ ላይ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት በሚል ምርት በመያዛቸው የተፈጠረ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ከተለያዩ አካላት አረጋግጣለች።

ከኹለት ወር ጀምሮ የተወሰነ ጭማሪ ማሳየት የጀመረው የአገር ውስጥ የሲጋራ ዋጋ፣ አንድ ፍሬ ሲጋራ ላይ የሃምሳ ሳንቲም ጭማሪ እንዲያሳይ አድርጓል። ነገር ግን በኮንትሮባንድ የሚገቡ የሲጋራ ምርቶች ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ ያልታየ ሲሆን፣ አገር ውስጥ ካሉት የሲጋራ ምርቶች የረከሱ በመሆናቸው ተመራጭ መሆን መጀመራቸውንም አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ኪሎ ካምፓስ አካባቢ ሲጋራ የሚሸጠው ወጣት እንደሚለው፣ ሲጋራ ተወደደብኝ ብሎ ሲጋራ መግዛቱን የሚተው ወይም የሚቀንስ ደንበኛ እስከ አሁን የለም። በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ ጫማ ከመጥረግ ጎን ለጎን ሲጋራን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚሸጡ ወጣቶችም፣ በእነርሱ አጠራር ‹የውጪ ሲጋራዎች› ወይም በኮንትሮባንድ የሚገቡ ሲጋራዎች ፍላጎት እየጨመረ ነው።

ከውጪ የሚገቡ ሲጋራዎች በኮንትሮባንድ ገብተው በፓኬት እስከ 25 ብር ይሸጣሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቶባኮ ኢንተርፕራይዝ በበኩሉ፣ የዋጋ ንረቱን መመልከቱን እና ለዚህም አከፋፋዮች ምርት በማከማቸታቸው የተፈጠረ እንደሆነ ገልጿል።
የኢንተርፕራይዙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ከአምራች ድርጅቱ ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳልተደረገና የዋጋ ጭማሪ የሚኖረው በዓመት አንድ ጊዜ በአንድ ፓኮ የአንድ ብር እንደሆነ ገልፀዋል። በኤክሳይስ ታክሱ መጨመር ምክንያት ከዚህ በላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖር ግን እሙን መሆኑን ገልጸዋል።

የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ የካቲት 5/2012 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀ ሲሆን፣ በፀደቀዉ የኤክሳይስ ታክስ በሲጋራ ላይ የተጣለዉ የኤክሳይዝ ታክስ በቀደመዉ ረቂቅ ላይ በአንድ ፖኬት ሲጋራ የሶስት ብር ጭማሪ ተደርጎበት 8 ብር ሆኖ ፀድቋል፡ማሻሻያ የተደረገበት ምክንያትም ሲጋራ የኅብረተሰቡን ጤና ከሚጎዱትና ማኅበራዊ ችግር ከሚፈጥሩት ምርቶች የሚመደብ በመሆኑ እንደሆነ የገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠቅሷል።

የብሔራዊ ትንባሆ መንግሥት በጣለው ኤክሳይስ ታክስ መጠን ላይ እንደማይስማማ እና ታክሱ የታሰበለትን የኅብረተሰብ ጤና ማሻሻል የማያስችል፤ ሕጋዊ የሲጋራ ምርቶችን አዳክሞ ለኮንትሮባንድ በር የሚከፍት ነው ሲሉ ተናግረዋል። በሕገ ወጥ የንግድ መስመር የሚገቡትን ሲጋራዎች መቆጣጠር ካልተቻለም እንደታሰበው የኅብረተሰብን ጤና ከሲጋራ መጠቃት ሊያስቆመው እንደማይችልም ተናግረዋል።

ኃላፊው ድርጅቱ ወደፊት እንደየገብያ ሁኔታዉ የዋጋ ጭማሪ እንደሚደርግ እንዲሁም የምርትና የሠራተኛ ቅነሳ ሊደርግ እንደሚችል ጠቁመዋል። አያይዘውም በዚህ ምክንያትም የሲጋራ ተጠቃሚዎች ሕጋዊ የሆነውን ሲጋራ ትተዉ ወደ ኮንተሮባንድ ስለሚገቡ ችግሩን መከላከል አያስቻልም ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የህብረተሰብ ጤና ባለሞያ እና በትንባሆ ጉዳይ አስተያየት በመስጠት ላይ ሰፊ ልምድ ያካበቱት ደረጄ ሽመልስ እንደሚሉት በጃፓን ቶባኮ ከፍተኛ ድርሻ የያዘው ብሄራዊ ትንባሆ በብስጭት እንዲህ ሊል ይችላል ይላሉ፡፡ ይህ ማስፈራሪያ ሊሆን ይችላል እንጂ በ 100 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ አምስት በመቶ አጫሽ ያለበትን ገበያ በብቸኛ የበላይነት ላለው አምራች አሁን በተጣለው የኤክሳይስ ታክስ ጉዳት ይደርስበታል ብሎ ማሰብ ጥቂት የንግድ እውቀት ላለው ሰውም ቢሆን የማይታሰብ ነው እንደ ደረጄ ገለፃ፡፡

‹‹ድርቶ ወደ አገር ሲመጣ የተገባለት የፖለቲካ ቃል ኖሮ እንኳን በአለም ላይ ካሉ ታላላቅ ኩባኒዎች መሀል የሆነው ጃፓን ቶባኮ ኢትዮጵያ የአለም የጤና ድርጅት የትንባሆ ቁጥጥር ኮንቬክሽንን አፅድቃ እያለ የኤክሳስ ታክሱ አይጨመርም ብለው ሊያምኑ አይችሉም›› ሲሉ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካሪ የሆኑት ደረጃ ይናገራሉ፡፡

ጃፓን ቶባኮ ወደ ኢትዮጵያ በገባ ጊዜ በኢትዮጵያ የነበረው የፖለቲካ ስርአት አስተማማኝ አልነበርም ለውጥም ሊኖር እንደሚችል መገመት ይገባል የሚሉት ባለሞያው ይሄም የማይገመት አይደለም ይላሉ፡፡ የቶባኮ ኢንዱሰትሪ ያለው ተቀጣሪ ሰው 1200 አካባቢ ነው የሚሉት እኚሁ ባለሞያው ከነሚያስተዳድሩት ቤተሰብ ጋር ታይቶ አጠቃላይ 15 ሺህ ሰው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን 17 ሺ ሰው በትንባሆ ምክኒያት ህይወታቸው አልፋል ይህም የተፈጠረዉ የስራ እድልና የሚመጣዉ ጉዳት የማይወዳደር ነዉ፡፡

አንድ አገር የህግ ማስከበር አቅሟን ተማምና እንጂ በአገር ውስጥ ከኮንትሮባንድ የረከሰ ምርት አቅርቤ ህገ ወጥነት እከላከላሁ ብላ አታስብም፣ መንግሰት በድነበር ላይ ያለውን ቁጥጥር በማጠናከር እና መሰል የጉምሩክ ስራዎቹን በማጠናከር ነው ኮንትሮባንድን መከላከል ያለበት፤ እደ ደረጄ ገለፃ፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here