አዋጁ የጥላቻ ንግግርን እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር ምርጡ አማራጭ አይደለም!

0
1048

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለፈው ሐሙስ፣ የካቲት 5/2012 የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በ23 ተቃውሞና በኹለት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

ይህ ረቂቅ አዋጅ ኅዳር 2012 ለዚሁ ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ከተመራ ጀምሮ፣ በይበልጥ የመገናኛ ብዙኀንን ቀልብ ከመሳብ ባሻገር የውይይት እና የክርክር ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ከርሟል። በመደበኛ እንዲሁም ማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ቃላት ሲያሰናዝርና የጦፈ ክርክር ሲያስነሳ መክረሙንም ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉት ያውቁታል።

ብዙዎች ወሳኝ ያሏቸውን እና ሐሳባቸውን የሚደግፍላቸውን አመክንዮ በመዘርዘር ክርክር አድርገዋል። ተቃውሟቸውን በከፍተኛ ድምጽ የሚያሰሙት ሕጉ በተለይ የሰብዓዊ መብቶች አንዱና ዋነኛው መብት የሆነውን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን የሚገድብ አዋጅ መሆኑን በማንሳት የመከራከሪያቸው መሰረት አድርገውታል። ሌላው ከዚህ ቀደም በጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ ይደረግ እንደነበረው፣ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚከለክለው ሕግ መጽደቅ፣ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ተቀናቃኞቹን ለማጥፋት እንደ መሣሪያ ሊጠቀምበት ይችላል ከሚል ሥጋት የመነጨ ነው።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ባለሙያ እንደሚሉት፣ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን ሕግ እንዲያዘጋጅ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር የሚገኘው ነጻ የመገናኛ ብዙኀን የሥራ ቡድን ነበር። ነገር ግን ይህን ነጻነት በሚጥስ መንገድ ዐቃቤ ሕግ ሥራውን ከቡድኑ ነጥቆ ራሱ የሠራው መሆኑ ገለልተኛ አመለካከት ሳይሆን የመንግሥትን ጥቅም ታሳቢ አድርጎ እንደተቀረጸ የሚያሳስብ ነው ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ልዩ ራፖርተር የሆኑት ዴቪድ ኬይ፣ ሕጉን የማርቀቁ ሥራ ነጻ ከሆነው የመገናኛ ብዙኀን ቡድን መነጠቁ ተገቢ አይደለም ሲሉ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ጊዜ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸው ነበር።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ባለሙያም፣ ሕጉ የምርጫው መቃረብን ግምት ውስጥ በማስገባት ተጣድፎ የተሠራ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ አውሮፓ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አገሮችም መሰል ሕጎችን እያወጁ እንደሆነ የገለጹት ባለሙያው፣ በኢትዮጵያ ሁኔታው የሚለየው እንደ አደጉት አገራት የጥላቻ ንግግርን በግልጽ ሊለይ የሚችል የሕግ ፈጻሚና ተርጓሚ መዋቅር ያለመኖሩ ነው ብለው ያምናሉ። የአገራችን ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶች እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት የጥላቻ ንግግርን ግልጽ በሆነ መንገድ የመለየት ችግር እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ባለሙያው፣ ይህ ትልቁ የአተገባበር ተግዳሮት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሕጉ ተግባራዊ መደረግ አለበት በሚል ድጋፍ የሚያሰሙት ወገኖች በራሳቸው የሚያነሷቸው ምክንያቶች አሏቸው። በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግሮችም ሆነ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ሲሉም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱትን ግጭቶች፣ መፈናቀሎች ብሎም ግድያዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ጋር በማያያዝ ለአብነት ይጠቅሳሉ። እነዚህ በሕዝብ መካከል የሚነዙ የጥላቻ ንግሮችም ሆኑ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች በጊዜ ሃይ ካልተባሉ ደግሞ የአገር ሕልውና ላይ ሥጋት እንደሚደቅኑ ያምናሉ።

በእርግጥ አዲስ ማለዳ ከወራት በፊት በማኅበራዊ ድረ ገጿ ላይ “ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት እና የጥላቻ ንግግርን መግራት” በሚል ላሰናዳችው ሐተታ ዘ ማለዳ ግብዓት ለመጠቀም ለማኅበራዊ ድረ ገጿ ተከታታዮች “በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች ዘንድ ‘የጥላቻ ንግግር’ ሕጋዊ ክልከላ ሊደረግበት የሚገባው ደረጃ ላይ ደርሷል ብለው ያስባሉ?” በሚል ላቀረበችላቸው ጥያቄ፣ ከ1812 መልስ ሰጪዎች መካከል 92 በመቶዎቹ “አዎን፣ በሕግ መከልከል አለበት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ይህም የጥላቻም ሆነ የሐሰት ንግግሮችን የሥጋት ምንጭነት የሚያመላክት ነው።

በጸደቀው ሕግ ውስጥ የተከለከሉ ተግባራት ተብለው ከተዘረዘሩት መካከልም ማንነትን መሰረት አድርጎ ቡድንን ወይም ማኅበረሰብን እኩይ አድርጎ በመሳል መድልዖ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ መልዕክትን መናገር፣ ጽሑፍን መጻፍ፣ የኪነ ጥበብ እና እደጥብብ ውጤት መሥራት፣ በድምጽ ቅጂ ወይም በምሥል ወይም በቪዲዮ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት፣ በብሮድካስት እና በማንኛውም መገናኛ መንገዶች ለሕዝብ መልዕክቱን እንዲደርስ ማድረግ ይገኙበታል።

ሐሰተኛ መረጃዎች በተመለከተ አዋጁ አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑ የታወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ኹከት ወይም ግጭት ለማነሳሳት ዕድሉ ከፍ ያለ መረጃን ሆነ ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትን ከልክሏል።

በወንጅል ተጠያቂነት ዙሪያ አዋጁ ለጥላቻ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት እንዲሁም የሐሰተኛ መረጃን ማሰራጨትን በተመለከተ ደግሞ ከኹለት ዓመት እስከ አምስት ዓመት የእስር ቅጣት ጥሏል። በተጨማሪም የሐሰት መረጃዎችን በማኅበራዊ ድረገጾች፣ በብሮድካስት አገልግሎት፣ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ያስተላለፈ አካል ላይ እስከ 100,000 ብር ቅጣት ተጥሏል። ቅጣቱ በተለይ በማኅበራዊ ገፆች ከአምስት ሺሕ በላይ ተከታዮች ያሏቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለክታል።

ካርድ የተባለው ሰብዓዊ መብቶች እና ዴሞክራሲን ለማጠናከር የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት በፍቃዱ ኃይሉ አዋጁ ሆነ ብሎ ለመጉዳት በማሰብ የሚደረግ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት ያለመ መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሩ ታቅዶ ይሁን ሳይታቀድ እንዴት እንደሚለይ መወሰኑ ላይ ነው ብለዋል። አተገባበሩ ላይም ይህ እንደ ትልቅ ችግር ሊነሳ የሚችል ጉዳይ ሆኖ እናያለን።

እንደ እርሳቸው አባባል የጥላቻ ንግግርንም ሆነ ሐሰተኛ መረጃን ሆነ ብለው የሚያሰራጩን ሰዎች መንግሥት መያዝ አይችልም። ምክንያቱም ተደብቀው ስለሚያደርጉት ወይም ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ገደብ የሌለበት አገር ላይ ተቀምጠው ስለሚያደርጉት ነው፡፡ በመሆኑም ሐሰተኛ መረጃን እና የጥላቻ ንግግርን በሕግ መከላከል አይቻልም ይላሉ። ነገር ግን በሕግ መከላከል ቢያስፈልግ እንኳን በቂ የሕግ ማዕቀፍ እንዳለ የጠቆሙት በፍቃዱ፣ በአገሪቷ ውስጥ አመጽ ማነሳሳት የሚከለከል በመሆኑ ያንን በተገቢው ሁኔታ መተግበር ላይ ትኩረት ቢደረግ ሲሉ ምክረ ሐሳብ ያቀርባሉ።

መንግሥት የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት አሳስቦኛል ብሎ ካመነ ሦስት መፍትሔዎች አሉ ይላሉ በፍቃዱ። የአንባቢያን፣ የአድማጮች እና ተመልካቾችን የመገናኛ ብዙኀን ግንዛቤ መጠን ከፍ ማድረግ የመጀመሪያው መፍትሔ እንደሆነም ጠቁመዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከመንግሥት በላይ አቅሙም ብቃቱም ያለው የለም ብለው ያምናሉ።

ይህም በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሠሩ መገናኛ ብዙኀን ያሉት በመሆኑ ግንዛቤን ለማሳደግ ጥሩ አቅም አለው ከሚል የመነጨ ነው። ኹለተኛ መፍትሔ ብለው የሚያምኑት ደግሞ መገናኛ ብዙኀን እውነታን ማጣራት ላይ ከዚህ በፊት ተሠርቶ በማይታወቅ መጠን ሊረባረቡ ማስፈለጉን ነው። ሦስተኛው መፍትሔ የመንግሥት ግልጽነትን መጨመር ነው ያሉ ሲሆን፣ የሐሰተኛ መረጃዎች ተአማኒ እንዲሆኑ የሚያደርገው የመንግሥት ግልጽነት መጓደል እንደሆነ በፍቃዱ ያስረዳሉ።

የመንግሥት ባለሥልጣናት መረጃ አንሰጥም በሚሉበት ጊዜ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ይህ ሕግም ሐሳባቸውን የሚገልጹ ንጹሀን ዜጎች ሊያስጠይቀኝ ይችላል በሚል ራሳቸውን እንዲሰበስቡ የሚያደርግ ሲሆን ሆን ብለው የሚያደርጉት ግን ተደብቀው ስለሆነ የሚያግዳቸው አይደለም። በመሆኑ ተግባራዊነቱ ንጹሀን ላይ ነው የሚሆነው ይላሉ በፍቃዱ።

አዲስ ማለዳ በነጻ ቡድን እንዳይረቀቅ መደረጉን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌሎች ሕጎች እንዴት ዜጎችን ለማፈን ያገለግሉ እንደነበር፣ ሆን ብለው ጥላቻን የሚነዙን በሕጉ ለመያዝ በጣም ከባድ መሆኑን፣ የሚያስፈራራው ንጹሐንን መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ተግባራዊነቱ በችግሮች የተሞላ እንደሚሆን ትገነዘባለች፡፡ ምንም እንኳን የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ሥር የሰደዱ ቢሆንም፣ መንግሥት እነሱን ለመቆጣጠር ምርጡን አማራጭ ወስዷል ብላ አዲስ ማለዳ አታምንም። ነገር ግን ሕጉ ወደ ተግባር እየገባ ስለሆነ፣ አፈጻጸሙ በከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ስትል ታሳስባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here