ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ መስተዳድር ውሳኔ “ሰነድ አልባ” በመሆናቸው ሕገ ወጥ የተሰኙ ቤቶች እንዲፈርሱ ተደርገዋል። ይህንን እና ተዛማች የአዲስ አበባ ጉዳዮችን በማንሳት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ፈተናዎች ምን ምን ናቸው የሚሉትን መሐመድ አሊ እንደሚከተለው ዘርዝረዋቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከታችም ከላይም በሚቀጣጠል የፖለቲካ ትኩሳት እንደቡሄ ዳቦ የሚጠበሱ ይመስለኛል።ባንድ በኩል ከአዲስ አበባ መስፋፋት ጋር በተያያዘ በከተማዋ ዙሪያ የነበሩ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸው አስተዳደሩን ክፉኛ ሊንጠው የሚችል የፖለቲካ አጀንዳ ሆኗል።በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ሕዝብን ለማሰለፍና ለማንቀሳቀስ ታዋቂ አክቲቪስቶች ጭምር በተቀናጀ መልኩ ውስጥ ለውስጥ እየሠሩ እንደሆነ ይወራል።በሌላ በኩል በከተማዋ ዙሪያ በሕገ ወጥ መንገድ የተገነባ ነው በሚል ቤታቸው እንዲፈርስ ተደርጎ ሜዳ ላይ የተበተኑ ዜጎች ጉዳይ ሌላ የፖለቲካ ትኩሳት ሆኗል።አንዳንድ ወገኖች ይህን እርምጃ የአዲስ አበባን የሥነ ሕዝብ ሁኔታ (demography) ለመፐወዝ ያለመ አድርገው ይወስዱታል።በዚህ መሐል ያደፈጠው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ሌላ ስጋት አርግዞ ቀኑን የሚቆጥር ይመስላል።እነዚህን ሁኔታዎች ደምሮ ማሰብ ትልቅ ራስ ምታት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ይቻላል።
አዲስ አበባ የማናት?
ይኸ ጥያቄ ከጅምሩ ግራ የሚያጋባና ግራ የሆነ ጥያቄ ነው። ለዚህ ጥያቄ እስካሁን ድረስ ሁሉንም ወገን ሊያስማማ የሚችል ምላሽ የተገኘ አይመስልም። አወዛጋቢው የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ድንጋጌም ቢሆንከአዲስ አበባ መገኛ ቦታ በመነሳት ከኦሮሚያ መንግሥት ጋር ስለሚኖረው መስተጋብርና የኦሮሚያ መንግሥት ሊያገኘው የሚገባው ልዩ ጥቅም መጠበቁን ከማመልከት ባለፈ በዝርዝር የሚለው ነገር የለም። ይልቁንም ዝርዝሩ ወደፊት ሊወጣ በሚችል ሕግ እንደሚወሰን በጥቅሉ ገልጾት ያልፋል። ለማንኛውም የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 49(5) ድንጋጌ እነዲህ ይላል፦
“የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”
ለመሆኑ የዚህ ድንጋጌ አንደምታ ምንድነው? “የአገልግሎት አቅርቦት” ሲባልስ ማነው አቅራቢና ተቀባዩ? “የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም” ሲባልስ ምን ምንን ያካትታል? የመሬት አጠቃቀምን ይጨምር ይሆን? “ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችስ” ከምን የሚመነጩ ናቸው? “ልዩ ጥቅም” የተባለውስ በምን ይገለፃል? “ዝርዝሩን በሕግ” የሚወስነውስ ማነው? የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች ፍላጎትስ (the intention of the drafters) ምን ይሆን?
ምናልባትም የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎችን ፍላጎት ማግኘት የሚቻለው በቀደሙት የዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፆች ነው። አንቀፅ 49 (1) እና (3) ተጣምረው ሲነበቡ “አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰከተማ ስትሆን ተጠሪነቷም ለፌዴራሉ መንግሥት” እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ። አንቀፅ 49 (2) እና (4) በፊናቸው “አዲስ አበባ ከተማ ሙሉ በሙሉ ራሱን የሚያስተዳድር ሲሆን ነዋሪው ሕዝብ በቀጥታ በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት” እንደሚወከል በማያሻማ አኳኋን ይገልጻሉ። ከዚህ በመነሳት በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ወሳኙ የከተማው ነዋሪ መሆኑን አስረግጦ መናገር ይቻላል። ይህም ሆኖ ግን ጉዳዩ አሳሳቢና አነጋጋሪ (sensitive & controversial)መሆኑ አልቀረም።
የአዲስ አበባ ዙሪያ ፖለቲካ
የአዲስ አበባ ዙሪያ ፖለቲካ መልኩን እየቀያየረና በየጊዜው እያደገ የሚሔድ ነው ማለት ይቻላል። በ1993 የመጫና ቱለማ መረዳጃ ማኅበር መሪዎችን ጨምሮ የኦሮሞ ተወላጅ ለሆኑ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እስርና እንግልት ምክንያት የሆነው የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ አዲስ አበባ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ነበር። ሆኖም ግን፣ ያሁሉ መስዋዕትነት ተከፍሎም የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ወደ አዳማ/ናዝሬት መዛወሩ አልቀረም ነበር። የክልሉ መቀመጫ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው በ1997 ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የተመረጠውን ቅንጅትን ፈተና ላይ ለመጣል ነበር። ይሁንና ቅንጅት የከተማውን አስተዳደር ባለመረከቡ በሕገ መንግሥቱ የተጠበቀው “የልዩ ጥቅም” ጉዳይ ሳይነሳ ቆዬ።
የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደገና አነጋጋሪ ሊሆን የቻለው አወዛጋቢው የአዲስ አበባ ማተር ፕላን በ2008 ይፋ መደረጉን ተከትሎ ነበር። ጉዳዩ በመላው ኦሮሚያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጣ በማስነሳቱ ማስተር ፕላኑ ሥራ ላይ ሳይውል ቀርቷል። የማስተር ፕላኑ አጀንዳ ከተዘጋ በኋላ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ሊያገኝ የሚገባውንና በሕገ መንግሥቱ የተጠበቀለትን “ልዩ ጥቅም” በሚመለከት ለፓርላማው የቀረበው የሕግ ረቂቅ ነበር። ረቂቅ ሕጉን ተከትሎ “አዲስ አበባ የማናት?” የሚለው ጉዳይ እስካሁንም አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል። አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የድሆች መፈናቀልና እሮሮ ሰሞነኛና/አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኗል።
የአርሶ አደሮች መፈናቀል
በየትኛውም አገር ቢሆን ከተሞች ሲስፋፉ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸው የማይቀርና የተለመደ ሒደት (pattern)ነው።በአገራችን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመቀሌ፣ በባሕርዳር፣ በአዋሳና በሌሎችም(ትላልቅና መካከለኛ ዕድገት ባላቸው) ከተሞች ዙሪያም ከከተሞቹ መስፋፋት ጋር በተያያዘ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸው የግድና የሚጠበቅ ነው። ምናልባት በሌሎች ከተሞች ዙሪያ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የሚቆረቆርላቸውና የሚጮህላቸው ጠፍቶ ነው? ወይስ አርሶ አደሮቹ ከከተሞቹ መስፋፋት የሚያገኙት የተለዬ ትሩፋት ይኖር ይሆን? ወይስ ከዚህ ጀርባ ሌላ የተደበቀ አጀንዳ አለ?
በርግጥ በሌሎች ከተሞች ዙሪያ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የሚጮህላቸው ወገን አለመኖሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች መጮህን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት በቂ መነሻ ሊሆን አይችልም። በተለይም ደግሞ ከሌሎች አንፃር ሲታይ የአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት በብዙ እጥፍ ስለሚልቅ የሚፈናቀሉት አርሶ አደሮች ቁጥርም ያንኑ ያህል ያሻቅባል። ይሁንና በግለሰብ ደረጃ ካየነው በእያንዳንዱ አርሶ አደር ላይ የሚደርሰው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። ስለሆነም ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ስለሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች አንድ ወጥ አገር አቀፍ ፖሊሲ መከተል አስፈላጊ ነው።
አርሶ አደሮቹን ማን አፈናቀላቸው?
ይህን ጥያቄ ማንሳት የሚያስፈልገው አርሶ አደሮች ሊፈናቀሉ የሚችሉት በተለያዩ ምክንያቶችና መንገድ ስለሆነ ነው።በኛ አገር ሁኔታ ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ገበሬዎች የተፈናቀሉት በሁለት መንገድ ነው ማለት ይቻላል። በአንድ በኩል መንግሥት “መሬቱ ለልማት ይፈለጋል” በሚል አነስተኛ የካሳ ክፍያ በመስጠት ገበሬውን አስገድዶ የሚያፈናቅልበት ሁኔታ አለ። ገበሬው ከመሬቱ ብቻ ሳይሆን ከኖረበትና ከሚያውቀው የግብርና ሥራ ሲፈናቀል ከባሕር የወጣ ዓሣ መሆኑ አይቀርም። ወደ ከተማ ገብቶ በሌሎች የሥራ ዘርፎች ለመሠማራት ምንም በቂ ልምድና ክኅሎት የሌለው ከመሆኑም በላይ የሚሰጠው የካሣ ክፍያም ሕይወቱን ሊቀይር የሚችል አይደለም። ገበሬው ከመሬቱ ሲፈናቀል ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ መሠረቱም ይናጋል። ስለሆነም መንግሥት በልማት ሥም ገበሬውን ሲያፈናቅል ተያያዥ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ታሳቢ በማድረግ ዘላቂነት ያለው የመፍትሔ አቅጣጫን አብሮ መቀየስና ማስቀመጥ ነበረበት።
በሌላ በኩል ግን በተለይ በከተሞች ዙሪያ የሚገኘው ገበሬ ወዶና ፈቅዶ መሬቱን እየሸነሸነ የሚሸጥበት ሁኔታ መኖሩን መካድ አይቻልም። በሕገ መንግሥቱ መሬትን በግል መሸጥና መለወጥ የማይፈቀድ ቢሆንም ገበሬዎች በይዞታቸው ሥር የሚገኙ መሬቶችን እየሸነሸኑ በሽያጭ ግን በሥጦታና ዕዳ መክፈል ባለመቻል ንብረታቸውን በመያዣነት ማስተላለፋቸው የተለመደና የሚታወቅ ነገር ነው። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ከገበሬዎች ላይ የሚገዛ (እስከ 200 ካ.ሜ. የሚደርስ) የቤት መሥሪያ (ሰነድ አልባ) ቦታ ዋጋ እስከ ብር 600,000.00 (ስድስት መቶ ሺሕ ብር) እንደሚደርስ ይነገራል። በዚህ ሒሳብ በሄክታር የሚገመት የመሬት ይዞታ ያላቸው ገበሬዎች ምን ያህል ገንዘብ ሊያገኙ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። በዝቅተኛ ግምትና የካሳ ክፍያ እየተሸነገሉ በልማት ሥም ከተፈናቀሉት አንፃር ሲታይ በግላቸው (በሕገ ወጥ መንገድም ቢሆን) መሬታቸውን እየሸነሸኑ የሸጡት ገበሬዎች ይበልጥ ተጠቃሚዎች ናቸው ለማለት ያስደፍራል።
ይህም ሆኖ ግን፣ የከተሞች መስፋፋት ለአካባቢው ነባር ማኅበረሰብ ይዟቸው የሚመጣ ትሩፋቶች መኖር አለባቸው። ከተሞች ሲስፋፉ የመሠረተ ልማትና የተለያዩ የማኅበራዊ አገልግሎቶች አብረው ይስፋፋሉ። ሆኖም ግን ከተሞች ሲስፋፉ ገበሬው ከመሬቱ ተፈናቅሎ የትም ከተጣለ ልማቱ መጣብኝ እንጅ መጣልኝ ሊል አይችልም። ስለሆነም አርሶአደሮች ከመሬታቸው ሲፈነቀሉ ለወደፊቱ ሊያቋቁሟቸውና ሕይወታቸውን ለቀይር የሚችል ተገቢ ካሣ ማግኘታቸው መረጋገጥ አለበት።እንዲሁም የየከተሞቹ አስተዳደሮች ቢያንስ በሚይዟቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ውስጥ የአርሶ አደሮቹን ጉዳይ ማካተት እንዳለባቸው ማሰብ ያስፈልጋል። ከዚህም ባለፈ አርሶ አደሮቹ ወደሌሎች የኢኮኖሚ/የሥራ ዘርፎች ሊሸጋገሩ የሚችሉበትን የገንዘብና የሙያ (financial & technical) ድጋፍ መስጠትም አብሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን፣ ይህ አካሔድ ቀደም ሲል በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ተመዝግበው ገንዘብ ሲቆጥቡ የቆዩና ዕጣቸውን የሚጠባበቁ የከተማ ነዋሪዎችን መብት የሚያጣብብ መሆን እንደሌለበት ሊሠመርበት ይገባል። አሁን በመገንባት ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ወጭ የሚሸፈነው እነዚህ ዜጎች ባዋጡት ገንዘብ መሆኑም መዘንጋት የለበትም።
“ሰነድ አልባ” ቤቶችን የማፍረስ እርምጃ
መንግሥት ሕግና ስርዓትን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት እሙን ነው። ይሁንና ሕግና ስርዓትን በማስከበር ረገድ አስቀድሞ የመከላከል መርሕን መከተል ያስፈልጋል። ግለሰብ ዜጎች ሕግና ደንብን ተላልፈው ሲገኙም፣ በተለይ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት ተራ የፖለቲካ ሀሁ ይመስለኛል። ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት በተለምዶ “ሕገ ወጥ” የሚባሉ ግንባታዎችን (“ሰነድ አልባ”) ቤቶችን ለማፍረስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሊያስከትሉ የሚችሉት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ግንዛቤ ውስጥ የሚገባ አይመስልም። ውሎ አድሮም ፖለቲካዊ ቀውስ ሊፈጥርና ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ሊጤን ይገባዋል።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ግለሰብ ዜጎች “ሕገ ወጥ” የሚባሉ ቤቶችን ለመሥራት ቦታውን ከገበሬዎች በውድ ዋጋ እንደገዙ ይታወቃል። ጥረው ግረው ባጠራቀሙት ገንዘብ ቦታውን ከገዙም በኋላ እንደገና ያላቸውን ጥሪት አሟጥጠው ጎጆ በመቀለስ ኑሯቸውን መግፋት ይጀምራሉ። በዚህ መንገድ ለአንገታቸው ማስገቢያ ጎጆ ሲያገኙ ቀሪው ሐሳብና/ጭንቀታቸው ልጆቻቸውን ማስተማርና “ከእጅወደ አፍ” የሚሉትን የዕለት ቀለብ ማሟላት ይሆናል። መቼም በዚህ ዘመን ጥሮ፣ ተፍጨርጭሮ በየጊዜው እያሻቀበ የሚሔደውን የኑሮ ውድነት ተቋቁሞ መኖር ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ መገመት ይቻላል። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በጭንቀት ተወጣጥሮ የሚኖርን ቤተሰብ ቤቱን አፍርሶ ሜዳ ላይ መበተን ምን ሊባል ይችላል? እንደምግብና መጠጥ ሁሉ የመጠለያ ጉዳይ ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚመደብ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ስለሆነም መንግሥት በሚችለው መንገድ ሁሉ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግ ሲገባው በራሳቸው ጥረት/ጥሪታቸውን አሟጥጠው የሠሩትን ቤት አፍርሶ ሜዳ ላይ መበተን ከሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ባለፈ ሞራላዊ ጥያቄዎችን ያስነሳል።
የታከለ ኡማ ፈተና
የታከለ ኡማን ፈተና ለመረዳት በእርሳቸው ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ ያስፈልጋል። ትናንት የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን በመቃወም ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሰው ናቸው።ያኔ የከተማዋን መስፋፋት የተቃወሙት ከአካባቢው አርሶ አደሮች መፈናቀል ጋር በተያያዘ ነው ተብሎ ይገመታል። ከዚህም ባለፈ የሕወሓት አመጣሹስርዓት በተለይ መሬትን በመቀራመት ረገድ ሲያሳየው የነበረው ከልክ ያለፈ ስግብግብነትና ይሉኝታ ቢስነት የማንንም ሰው ትዕግስት ሊፈትንና ሊያስቆጣ እንደሚችልም መረሳት የለበትም። ትናንት ግን ዛሬ አይደለም።ዛሬ ያለፈውአገዛዝ መልሶ ማንሰራራት በማይችልበት ሁኔታ በሽንፈት ተዘርሮ ታከለ ኡማም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆነዋል፤ስለሆነም የአዲስ አበባን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች መፍታት መቻል ታከለ ኡማ እንደከንቲባናፖለቲከኛ የሚፈተኑበት ይሆናል።
ታከለ ኡማ እንደከንቲባ በአዲስ አበባ የራሳቸውን አሻራ ትተው ማለፍ እንደሚፈልጉ መገመት ይቻላል። በተግባርም በርካታ በጎ ተግባራትን ሲያከናውኑ ተመልክተናል።ወጣቱ ከንቲባ ከሚያደርጉት በተጨማሪ በትህትና የታጀበና ጨዋነት የተሞላበት አነጋገራቸውና አስተሳሰባቸው ሰብዕናቸውን ብቻ ሳይሆን ግብራቸውንም ጭምር ገላጭ ነው። ስለሆነም አንዳንድ ወገኖች በታከለ ኡማ ዙሪያ ያላቸውን አጉል ጥርጣሬ፣ አሉታዊ አመለካከትና መሠረተቢስ አሉባልታ እንደወረደ ለመቀበል ያስቸግራል።ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ሆነው የተሾሙበትን አግባብ ጥያቄ ውስጥ ማስገባትም አሁን ካለንበት የሽግግር ሒደት አንፃር ጭራ ከመሰንጠቅ ያለፈ ትርጉም የለውም።ይሁንና ታከለ ኡማ በተለይ የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም የሚያቀነቅነው የኦህዴድ/ኦዴፓ አባል መሆናቸው አይዘነጋም። ዛሬ ላለበት ቦታ የበቃውም በዚሁ የአስተሳሰብና የአደረጃጀት መሥመር መሆኑም እሙን ነው።
እንደ አዲስ አበባ ከንቲባ፣ የአዲስ አበባ ከተማን ኗሪ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች/ፍላጎቶች መሠረት አድርጎ መሥራት ይጠበቅበታል። ይህን ሲያደርጉ፣ በተለይ ከከተማው መስፋፋት ጋር በተያያዘ፣ ምናልባትም ትናንት ሲያራምዱት ከነበረው አቋም ጋር በቀጥታ ሊያጋጯቸው የሚችሉ ፈታኝ ሁኔታዎች (conflict of interest) ውስጥ ሊገቡይችላሉ። ሁኔታውን ይበልጥ ፈታኝ የሚያደርገው ደግሞ፣ ትናንት እነታከለ ወደ ሥልጣን የመጡበትን አጀንዳ ነጥቀውና እነሱን አውርደው ሊፈጠፍጧቸው ያሰፈሰፉ ኃይሎች መኖራቸው ነው። ታከለ በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እነዚህን የሚጋጩ ፍላጎቶች እንዴት (tactically)አስታርቀውና አጣጥመው ማለፍና ብቃታቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉየምናየው ይሆናል።
እንደመንግሥት ባለሥልጣን፣ ታከለ ኡማ ሕግና ስርዓትን ማስከበር ይኖርባቸዋል።ሕግና ደንብን በሚተላለፉ ወገኖች ላይም ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የተገነቡና በተለምዶ “ሰነድ አልባ” የሚባሉ ቤቶችን ማፍረስ ከሕግ አንፃር ትክክለኛ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከዜጎች መሠራታዊ መብትና ከሞራል አንፃር ግን የድሆችን ቤት አፍርሶ ቤተሰብን ሜዳ ላይ መበተን አነጋጋሪና ቁጣን ሊቀሰቅስ የሚችል ነው።
ታከለ ኡማ እነዚህ ቤቶች እንዲፈርሱ በቀጥታ ትዕዛዝ ላይሰጡ ይችላሉ። ምናልባትም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የለውጥ ሒደቱን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች መሣሪያ የሆኑ ወገኖችም ሊኖሩ ይችላሉ። በተለይ አሁን ባለንበት የሽግግር ጊዜ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚኖራቸውን ፖለቲካዊ አንደምታና ሊፈጥሩ የሚችሉትን ክፍተት በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር በሕገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን ለማፍረስ ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ሲጀመር ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የቤት መሥሪያ ቦታ የሚያገኙበት አማራጭ ቢኖር ኖሮ ገንዘባቸውን አውጥተው ሕጋዊነቱ ያልተረጋገጠ ቦታ የሚገዙበት፣ በድሀ አቅማቸው የሚገነቡበትና በስጋት (ከዛሬነገ ሊፈርስ ይችላል በሚል) የሚኖሩበት ምክንያት አይኖርም። ሲቀጥል ድርጊቱ ሕገ ወጥ ነው ከተባለ፣ ግንባታ ከመካሔዱ በፊት ማስቆምና መከልከል እየተቻለ፣ የግለሰብ ብቻ ሳይሆን የአገር ሀብት የፈሰሰበትን ቤት፣ ንብረት ማፍረስ ማንንም የሚያሳምን አይደለም። ይህም ሆኖ፣ “ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም” እንዲሉ ቤታቸው የፈረሰባቸውና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ሜዳ ላይ የተበተኑ ቤተሰቦች ዕጣፈንታ ምን ይሆናል? የሚለው ጉዳይ ታከለ ኡማ የሚፈተኑበት ይሆናል።
መሐመድ አሊ መሐመድ ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው። ፖለቲከኛ ሲሆኑ ከ1998 እስከ 2002 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡ በኢሜይል አድራሻቸው mohalim2@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011