የዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች ፋይዳ በሰብኣዊ መብቶች ቀን ዋዜማ

0
887

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ስለፈጸማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማው ፊት ቀርበው በግልጽ ባመኑ ማግስት፤ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር በተለቀቁበት፣ የቀድሞ የማረሚያ ቤት አስተዳደር ኃላፊዎች ከቦታቸው በተነሱበት፣ እንዲሁም ወደ አርባ የሚጠጉ የደኅንነት እና የፖሊስ ኃላፊዎች በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉበት፣ ከሰብኣዊ መብቶች መከበር እና ከፖለቲካ ምኅዳር ማስፋት እንዲሁም ከሕግ የበላይነት መከበር ጋር የሚያያዙ አጀብ ሊያሰኙ የሚችሉ አስገራሚ ሰበር ዜናዎች በቀናት ልዩነት ውስጥ ለሕዝብ በሚደርሱበት፣ የአብዛኛው ኅብረተሰብ ዓይኖች እና ጆሮዎች ተከፍተው ቀጣዩን የፖለቲካ ክስተት በጉጉት በሚጠባበቁበት፣ ከዚህም በተቃራኒ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚከሰቱ ግጭቶች እና መፈናቀሎች ሳቢያ የሕዝቦች ሰብኣዊ መብት መከበር ጥያቄ ምልክት ውስጥ በገባበት፣ ጥቂት የማይባሉ ወረዳዎችና ዞኖች ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደርን መብት አንስተው ‹ክልል እንሁን› ባሉበት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ወሳኝ ሊባል በሚችል ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ታድያ የፊታችን ሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 ቀን 2011 የሰብኣዊ መብቶች ቀን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተከብሮ ይውላል፡፡
መነሻውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ጠቅላላ ጉባኤ ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌን እ.አ.አ. በ1948 ያፀደቀበትን ቀን ያደረገው ዓመታዊው የሰብኣዊ መብቶች ቀን፥ ከ1950 ጀምሮ ዲሴምበር 10 እየተከበረ አሁን 68ኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ የተ.መ.ድ. መሥራች አባል ከመሆኗም ባሻገር ድንጋጌው በተ.መ.ድ. ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ቁጥር 217 ሆኖ እንዲፀድቅ በድምፅ ከደገፉ 48 አገራት መካከል አንዷ ነች፡፡ ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ በዚህ ዓመት 70ኛ ዓመቱን የሚያከብር ሲሆን መሠረታዊ የሰብኣዊ መብቶችን ከመደንገጉም ባሻገር ለመንታያዎቹ ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብት ሥምምነቶች እንደ መነሻ አገልግሏል፡፡ ድንጋጌው በአገራት መካከል የተደረገ የሰብኣዊ መብቶች ሥምምነት ባለመሆኑ ምክንያት አስገዳጅነት ያለው ባይሆንም እ.አ.አ. ከ1948 በኋላ ለፀደቁት የተለያዩ አገራት ሕገ መንግሥቶች እና ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ተቋማት እንደመነሻ አገልግሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም ድንጋጌው በብዙ የዓለም ዐቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ዘንድ የልማዳዊ ዓለማቀፍ ሕግ አካል ሆኖ በመቆጠሩ ምክንያት አስገዳጅነት ሊኖረው እንደሚችል ይጠቆማል፡፡
ኢትዮጵያ በሰብኣዊ መብቶች ጥበቃ ረገድ ባሉ ዓለም ዐቀፍ ሥምነቶች ለመገዛት ያደረገችው ተሳትፎ ከፍተኛ ቢሆንም፥ ሥምምነቶቹ አገር ውስጥ ለነበረው ተግባራዊ የሰብኣዊ መብቶች ጥበቃ የነበራቸውን ሚና እምብዛም እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ መሠረታዊ ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች መዘርዝር (ቢል) ናቸው ከሚባሉት 9 ሥምምነቶች መሀል 7ቱን አፅድቃለች፡፡ አገሪቱ ካፀደቀቻቸው 7ቱ ሥምምነቶች ውስጥ ከሁለቱ በስተቀር ሁሉም ከደርግ መንግሥት ውደቅተ በኋላ የፀደቁ ናቸው፡፡ ይህም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለሰብኣዊ መብቶች መከበር ጥሩ እርምጃዎችን ወስዷል ሊያስብል ቢችልም የአፍሪካ ሰብአዊ መብት ምሁር የሆነው ፍራንስ ቪሊዮን እንደሚለው አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የሰብኣዊ መብቶች ሥምምነቶችን የሚፈርሙት ለይስሙላ እና በዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ መልካም ሥም ለመገንባት በመሆኑ ሥምምነቶቹ መፅደቃቸው ብቻውን ምንም የተለየ ቁርጠኝነትን ላያንፀባርቅ ይችላል፡፡ ፍራስን ቪሊዮን ይህንን አቋሙን ለማስረዳት በማሳያነት የሚጠቀመው አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ዕውቅና የሚሰጡትን እናት ሥምምነቶች ከማፅደቅ ባሻገር ለእነዚህ ሥምምነቶች ተግባራዊነት ማረጋገጫ የሚሆኑትን፥ መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን ሲፈፅሙ በዓለም ዐቀፍ ‹ፍርድ ቤቶች› ፊት እንዲጠየቁ የሚያደርጉትን አባሪ ሥምምነቶችን አለማፅደቃቸውን ነው፡፡ ኢትዮጵያም እነዚህን ዓይነት የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የደረሰባቸው ሰዎች መንግሥትን በመክሰስ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያደርጉ ሥምምነቶችን አልፈረመች፡፡ ይህም መንግሥት የተሟላ የሰብኣዊ መብቶች ጥበቃን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው ይነገራል፡፡
የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የደረሰባቸው ግለሰቦች በዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ኮሚቴ ፊት የኢትዮጵያን መንግሥት መክሰስ እና ፍርድ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርገውን አማራጭ ሥምምነት (1st Optional Protocol to the ICCPR) ኢትዮጵያ እንድትፈርም የሰብኣዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ተቋም ‹ሂውማን ራይትስ ዋች› ኢትዮጵያ የዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ሥምምነት (Rome Statute of the International Criminal Court) በማፅደቅ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የፈፀሙ ግለሰቦችን ተጠያቂ እንድታደርግ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ለእነዚህ ሁሉ ውትወታዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከርሟል፥ አለፍ ሲልም ሥምምነቶቹን እንደማይቀበል በይፋ አስታውቋል፡፡
በቅርቡ ከስደት ወደ አገር ቤት የተመለሰችው የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ እና የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ቡድን አባል የሆነችው ሶልያና ሽመልስ ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ አላት፡፡ “ዓለም ዐቀፍ ተፅዕኖዎች መንግሥት በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ረገድ ያለውን ባሕሪ እንዲቀይር የማድረግ አቅማቸው አነስተኛ ነው” የምትለው ሶልያና፥ “ከዛ ይልቅ አገር ውስጥ ያለውን የሰብኣዊ መብቶች ጥበቃ ስርዓት ማጠናከር የበለጠ ውጤት ይኖረዋል”፡፡ “ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ጥበቃ ስርዓቶች ከአገር ውስጥ ካለው ስርዓት በተጨማሪ ድጋፍ ሆነው ሊያገለግሉ ቢችሉም ዜጎችን በስፋት በማንቀሳቀስ መንግሥት ለሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ እና እንደ ፍርድ ቤት፣ የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን እና የሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴን ማጠናከር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው” ስትል ለአዲስ ማለዳ አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብኣዊ መብቶች መምህር እንደሚሉት ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ችሎቶች በአገር ውስጥ ያሉ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲዳኙ ሥልጣን መስጠት የመንግሥትን ተጠያቂነት የሚያጠናክር ቢሆንም የተፈፃሚነት ደረጃው አገር ውስጥ እንዳሉ ፍርድ ቤቶች እና ሌሎች ስርዓቶች ላይሆን ይችላል፡፡ ይሁንና የዓለም ዐቀፍ ችሎቶቹ ተፅዕኖ የሚናቅ እንዳልሆነ የአውሮፓ የሰብኣዊ መብቶች ፍርድ ቤት ውሳኔዎች አምባገነን የሆኑትን የምሥራቅ አውሮፓ እና የቀድሞ ሶቪየት ኅብረት አገራት አፋኝ ሕጎቻቸውን እና የሰብኣዊ መብቶች አያያዛቸውን እንዲያሻሽሉ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ለምሳሌ ያህል ጠቅሰው ይናገራሉ፡፡
ሶልያና ሽመልስ እንደምትለው ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ስለሚታይባቸው መንግሥታት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመስጠት ሲያቅማሙ ይስተዋላል፡፡ ኢትዮጵያ በብቸኝነት የዳኝነት ሥልጣኑን የተቀበለችው ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ችሎት የአፍሪካ የሰብኣዊና የሕዝቦች መብት ኮሚሽን ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ በኮሚሽኑ ፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ 12 ጉዳዮች የቀረቡ ሲሆን ከአንዱ በስተቀር ሁሉም በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡ ውሳኔ የተሰጠበት ብቸኛው መዝገብ የኢትዮጵያ መንግሥት የደርግ ባለሥልጣናት ለፍርድ ባቀረበበት ወቅት የፍርድ ሒደቱን ከሚገባው በላይ አጓትቷል፤ የተጠርጣሪዎቹንም ከፍርድ በፊት እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብት ጥሷል በሚል መንግሥት ለቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት ካሳ እንዲከፍል ቢወሰንበትም ውሳኔው ሳይፈፀም ቆይቷል፡፡ ሶልያና አገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ምኅዳር ዝግ እስካልሆነ ድረስ አገር ውስጥ ያሉ ስርዓቶችን ተጠቅሞ ለሰብኣዊ መብቶች ጥበቃ መታገል የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን ትናገራለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንግሥት የተጀመረው የሕግ እና ፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ እንደ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን እና የእንባ ጠባቂ ተቋም ያሉ አገራዊ የዴሞክራሲ ተቋማትን ችግሮች ለመፍታት፣ እንዲሁም አፈፃፀማቸውን እና ተአማኒነታቸውን ለማጠናከር እየሠራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ማሻሻያው ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብቶች ችሎቶችን ሥልጣን የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲቀበል የሚያደርጉ ሥምምነቶችን በማፅደቅ የሕግ ማዕቀፉን የማጠናከር ሒደትን እንደማያካትት ከሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ፍኖተ ካርታ መረዳት ይቻላል፡፡ ቀድመን የጠቀስናቸው የሰብኣዊ መብቶች ምሁር ግን ማሻሻያው ከአገራዊ የሰብኣዊ መብቶች እና የዴሞክራሲ ተቋማት ለውጥ በተጨማሪ ይህን ጉዳይ ማካተት ይገባው ነበር ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here