የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ መሠረታዊ የምጣኔ ሀብት አስተሳሰቦች (ክፍል አራት)

0
993


ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) ባለፉት ሦስት መጣጥፋቸው የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥት እና ሕዝብ አስተዳደር” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ተመሥርተው፣ የገብረሕይወት ምጣኔ ሀብታዊ ኀቲት ግንባር ቀደም መሆኑን እንዲሁም የጀመርናዊው ሔንሪ ቻርለስ ኬሪ ትንታኔ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው በተጨማሪም ገብረሕይወት ውስጣዊ እና ውጪያዊ የምጣኔ ሀብት ተግዳሮቶች አድርገው ያሰፈሯቸውን አትተዋል። በዚህ ማጠቃለያቸው የገብረሕይወት ትንታኔ ተፅዕኖን በኢትዮጵያን ምሁራን ዘንድ ተመልክተው ጽሑፋቸውን ይቋጫሉ።

(የመጨረሻ ክፍል)

በመጨረሻም ነጋድራስ ይህንን ውጫዊ የልማት መሰናክል ያልኩትን (የወጪና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን) ለማጠቃለል ዓለማቀፍ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ይዳስሳሉ። በዚህ ትንታኔያቸዉ ካፒታል (ገንዘብ) ከአገር አገር የሚዞረው የተሻለ ትርፍ ፍለጋ መሆኑን በመተንተን በኢኮኖሚክስ ጥናቶች ውስጥ ገንኖ የታወቀውን የፕሮፌሰር መንደልና ፍላሚንግ ሞዴል (ምንም እንኳ የእንገሊዙ ሊቅ ዴቪድ ሪካርዶና ካርል ማርክስ ቀደም ብለው ያሉት ጉዳይ ቢሆንም) ነጋድራስ ቀድመው ጠቁመውታል። እነመንደል ይህንን ሐሳብ አገኙ የተባለው ከ50 ዓመት በኋላ በ1960ዎቹ ነበር።
እንደ ገብረሕይወት አተናተን ይህ ዓይነቱ ትርፍ ፈላጊ ካፒታል ተጠናክሮ እንዲመጣ በጊዜው ያለው የሥራ ክፍፍል ደረጃ ዋንኛው ምክንያት ሲሆን፥ ይህ ግን ያገር ውስጥ ኢንደስትሪ እንዳያድግ ዕንቅፋት እደሚፈጥር አትተዋል። ይህ ትንተና ከመሠረተ ልማት ግንባታ ጋር የተቆራኘ መሆኑን የገብረሕይወት ሞዴል ያሳያል። ይህም ለየት ያደርገዋል። በገብረሕይወት አስተሳሰብ ዕወቀት በሌለው ኅብረተሰብ የመሠረት ልማት መስፋፋት ካፒታል ወደ አገሩ ዘልቆ እንዲገባ በማድረግ የአገር ውስጥ ዕደ-ጥበባትን በማኮስስ እና የብድር ጫናን በማጠናከር ያላደገውን አገር በአደገው አገር የመበዝበዝ ሁኔታ ያጠናክራል። ከዚህ ትንትኔ በመነሣት ያገር ውስጥ ምርትን በማጠናከር ራስን በራስ የመቻል ዓላማ ሊኖር እንደሚገባና ይህም የሚከተሉትን የፖሊሲ አቅጣጫዎች በመከተል ሊተገበር እንደሚገባ አስረድትዋል።
እነዚህም አንደኛ፣ ተገቢ የሆኑ የቀረጥ ፓሊሲ፦ የአገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርትን የሚያበረታታና ከወጪ የሚመጠትን ምርቶች የሚገድብ፤ ሁለተኛ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ ማካሔድ፤ እና ሦስተኛ፣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን በአግባቡ በመቆጣጠር ማበረታታት ናቸው።
የመጨረሻውን ነጥብ ሲያጠናክሩም ገብረሕይወት የሚከተለውን ብለዋል፦ “መቼም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገውን ዕቃ ሁሉ የሚገዛው ከውጭ አገር ሰዎች ነው። ሠራተኞቹ ያሉበት ቦታ ሩቅ ስለሆነ ግን እቃውን አገኛለሁ ሲል ብዙ ትርፍ እና ድካም ይሔድበታል። ጥቅሙን የሚያገኙት ግን ነጋዴዎች ናቸው። ስለዚህ የውጭ አገር ሰዎች ድካማችንን መውሰዳቸው ላይቀር አጠገባችን እየሠሩ ቢወስዱት ይሻላል።” (ገጽ 98)
ይህ አተናተንና የፖሊሲ ምክር ለአሁኑ መንግሥታችን ጭምር (ወይ ሐሳቡ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ ወይ እኛ ባለንበት ቆመን) ትምህርት መሆኑን ሳላሠምርበት አላልፍም።
የገብረሕይወት ምስለ ኢኮኖሚ ተፅዕኖ
ሁለት የዘመኑ ምሁራን ከገብረሕይወት ሥራ ጋር ባላቸው ቁርኝነት ሊጠቀሱ የሚገባ ነው። እኚህም ብላታ ደሬሳ አመንቴና አቶ ሚካኤል ተሰማ ናቸው። እኚህ ምሁራን በዘመኑ ዕውቅ በነበረው የ“ብርሃንና ሠላም” ጋዜጣ ላይ ከኢትዮጵያ የዕድገት ችግር ጋር የተያያዙ ብዙ ቁም ነገሮችን ተንትነዋል። ሆኖም እዚህ የጠቃቀስኩት ከገብረሕይወት ጋር የሚያያዘውን ብቻ ነው።
ከብላታ ደሬሳ ብንጀምር ከጃፓን ልምድ በመማር በኢትዮጵያ ልማት ለማምጣት ዕውቀት (ትምህርት) ማስፋፋት ቁልፍ እንደሆነ ያብራራሉ። ይህ ግን ዘላቂነት እንዲኖረው ተቋማትና ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ እንደሆኑ ተንትነዋል። ለዕውቀት የሠጡት ቦታ በገብረሕይወትም የተተኮረበት ሲሆን ገብረሕይወትም ስርዓት ያላት ትንሽ አገር ስርዓት ከሌለው ትልቅ አገር ሙያ ትሠራለች። ኃይል ስርዓት እንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም ሲሉ ይህንኑ የብላታ ደሬሳ ሐሳብ ተንትነውት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ለመሠረተ ልማት መስፋፋት የሰጡት ትኩረት እና በዕቃዎች ዋጋና በገንዘብ አጠቃቀም ላይ ያለው ተፅዕኖ ትንተናቸው ሁለቱም የሚገናኙበት ጉዳይ ነው። ብላታ ስለ አንፃራዊው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ጥቅም በተለይም ከአውሮፓው አቻው ጋር ሲታይ የማሽቆልቁሉ አዝማሚያ ላይ ያረጉት አሐዛዊ ትንታኔም በገብረሕይወት ሐሳብና ቀደምት ተመሳሳይ ሥራ ላይ ተንተርሰው የሠሩት ይመስላል።
ከብላታ ደሬሳ በተጨማሪ የገብረሕይወት ሐሳብ ከሚካኤል ተስማም የ“ብርሃንና ሠላም” ትንተና ጋር ይያያዛል። ሚካኤልና ገ/ሕይወት ለዕወቅት ያላቸው ትኩረትና ስንፍናን በማስወገድ ላይ ያላቸው አመለካከት ተመሳሳይ ነው። በሌሎች አቅጣጫ ግን ሰፋ ያለ ልዩነት አላቸው። ለምሳሌም ሚካኤል ዓለም ዐቀፍ ንግድ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑን ሲከራከሩ ገብረሕይወት በታቀራኒው የቆሙ ነበሩ። ገብረሕይወት የገቢ ስርጭት ሁኔታ ሲያሳስባቸው ሚካኤል ግን ይህ ፍታሐዊ የክፍያ ስርዓት ነው ይላሉ። በአጠቃላይ ሲታይ ሚካኤል የኢኮኖሚ ፅንፀ ሐሳቦችን በሕዝቡ ውስጥ በሚገባው ቋንቋ ለማስረፅ ቢጥሩም (ለመጀመሪያ ጊዜ የምጣኔሀብት አስተሳሰቦችን በስዕላዊ ሰንጠረዥ ባማርኛ ጋዜጣ ላይ በመሥራት ጭምር)፣ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ለማዛመድና ጠለቅ ብለው ለመተንተን እንደ ገብረሕይወት የደከሙ አይመስልም።
ይህ ከላይ የጠቀስኩት ገብረሕይወት በዘመኑ ከነበሩ ኢትዮጵያዊ የምጣኔሀብት ተንታኞች ጋር ያለው ቁርኝት መሠረታዊ ገጽታ ሲሆን ጽሑፌን ከማጠቃላሌ በፊት ግን የገብረሕይወት አስተሳሰብ ከጊዜ ሒደት አንፃር ሲታይ ምን መልክ እንደሚይዝ ለመጠቆም እወዳለሁ። እስካሁን ባየነው የገብረሕይወት ሞዴል ገለጻዬ ውስጥ ዛሬ ወይም ዘንድሮ የሆነው ነገር፣ ነገና ተነገ ወዲያ ወይም በሚቀጥለው ዓመት/ጊዜ ሊያመጣ የሚችለውን ተፅዕኖ (ፈረንጆቹ ‹ዳይናሚክስ› የሚሉትን በአማርኛ “ተገሳጋሽነት” ልንለው የምንችለው) ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። እውነታው ግን የገብረሕይወት ሥራ የጊዜ ሒደት በልማት ላይ ያለውን ተፅዕኖ (ተገሳጋሽነትን) በአንክሮ ያጤነ ነው።
ሙሉዕ በሆነው የገ/ሕይወት ምስለ ኢኮኖሚ የዛሬው ግጭት በሰው ኃይል ሀብት ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ዛሬ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን መጪውን ጊዜ/ዓመታት ያካትታል። በተመሳሳይም የዛሬው የንግድ ልውውጥ መዛባት ተፅዕኖ ዛሬ ላይ ብቻ ሳይወሰን ለሚቀጥሉት ዓመታትም የሚዘልቅ ነው።
የነዚህ ድምር ውጤት (የኢኮኖሚው ተገሳጋሽነት) የዛሬውን ምርታማነትና ምርት ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ብቻ ሳይሆን የመጪው ጊዜ ምርትና ምርታማነትም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ስለሆነም የመፍትሔ ሐሳብ ፍለጋው ዘመን ተሻጋሪ መሆን አለበት ማለት ነው። ይህ አስተሳሰብ ከአንዱ ተማሪዬ (ከአብረሃም አበበ) ጋር በቅርቡ እንዳደረግነው ጠለቅ ባለ የሒሳብ ቀመር ሲሠራ የገብረሕይወትን የጠለቀ አስተሳሰብ ጥርት አድርጎ ያሳያል። በተጨማሪም ገብረሕይወት ያነሱትን መሠረታዊ የልማት ችግሮች አጥጋቢ መፍትሔ ለመስጠት መንገዱን ይከፍትልናል። አጥርቶ ማየት ደግሞ የመፍተሔ ፍለጋ ‹ሀሁ› ነው።
ማጠቃለያ
ለማጠቃለል ያህል፣ በዚህ አጭር ጽሑፌ አንባቢ የነጋድራስ ሥራ ምን ያህል ጥልቅና ድንቅ እንደሆነ እንደሚረዳልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በተለይም ደግሞ ‘ልማታዊ የምጣኔሀብት ትንታኔ” በሚባለው የምጣኔሀብት ትምህርት ፈርጅ ድንቅ የተባሉትን ግኝቶች ነጋድራስ ገብረሕይወት ግኝቶቹ ተገኙ ከተባለበት 40 ና 50 ዓመት በፊት እንደጻፏቸው አንባቢው ይገነዘባል።
በሁለተኛ ደረጃ የነጋድራስ አስተሳሰቦች ድሮ ተሠርተው ታሪክ ሆነው የሚቀሩ ሰነዶች ብቻ እንዳልሆኑ ለማሳየት ሞክሪያለሁ። ነጋድራስ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች ብለው ምሁራዊ ትንታኔና የፖሊሲ አቅጣጫን ያሳዩባቸው ጉዳዮች በሚያሳዝንና በሚያሳፍር መልኩ ዛሬም ከእኛ ጋር ያሉ፥ ዛሬም ምክራቸውን ያልተጠቀምንበት መሆኑ ነው። እንግዲህ ይሄንንም ሐሳብ በተቻለኝ አቅም ለማሳየት ሞክሬያለሁ።
በመጨረሻም የነጋድራስ ሐሳቦች የረቀቁና የመጠቁ ስለሆኑ ለብዙ ምርምሮችና የፖሊስ ሐሳቦች በር ከፋች መሆናቸውን ላሠምርበት እፈልጋለሁ። ተመራማሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ይህንን አቅጣጫ ቢከተሉና የፖሊሲ አቅጣጫቸውንም በዚህ ተንተርሰው ቢያዩ ዛሬም ፍሬያማ ሥራ ሊሠሩበት እነደሚችሉ በማስገነዝብ ጽሑፌን በዚሁ አጠቃልላለሁ።

ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በአ.አ.ዩ. የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው ag112526@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here