ኔዘርላንድስ ሲራክ አስፋው በተባሉ ግለሰብ እጅ ለ21 ዓመታት የቆየው ጥንታዊ ዘውድ ዛሬ የካቲት 12 /2012 ለኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡
በ18ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰራ የሚነገርለት ዘውድ፤ በኔዘርላንድስ ኤምባሲ በኩል ለኢትዮጵያ የተመለሰ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ቅርሱን ተረክበዋል።
ዘውዱ ለተወሰነ ጊዜ በብሔራዊ ሙዝየም ቆይቶ በትግራይ ክልል ከመቀሌ 16 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ከሚገኘውና ረዥም ዕድሜ ካስቆጠረው ሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስቲያን ይመለሳል ሲሉ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ ፍስሐ (ዶ/ር) ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል።
ቅርሱ የሚመለስበትን ቀን ገና ባንወስንም በአድዋ በዓል ላይ ለማስረከብ አስበናል ሲሉ ሙሉጌታ ገልጸዋል።
“ቅርሱ የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን በፎቶ ማስረጃዎች ካረጋገጥን በኋላ እንዲመለስ ተወስኗል” ሲሉም አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ቅርሱ ከተሰረቀ በኋላ ለማስመለስ ደብዳቤዎች ይጻጻፍ እንደነበር እና ቅርሱ ከመዘረፉ በፊት የነበረበትን ሁኔታ የሚያሳዩ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች እንዳሉም አክለዋል።



