የጎንጂ ቆለላ አዲስ ዓለም መንገድ በአስፓልት ደረጃ ለማስገንባት ከተቋራጮች ጋር ውል መፈፀሙን የፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።
ይህ መንገድ ጠቅላላ 10 ነጥብ 74 ኪሎ ሜትር ርዝመት ኖሮት በአስፋልት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን፣ በገጠር በአማካይ 10 ሜትር ስፋት ሲኖረው በከተማው 21 ነጥብ 5 ሜትር ተጨማሪ ስፋት እንደሚኖረው ታውቋል።
የመንገዱ ግንባታ በ 333.3 ሚሊዮን ብር የሚገነባ ሲሆን፣ ግንባታውን ለማከናወን ጨረታዉን አሸንፎ የውል ስምምነቱን የፈረመው የአማራ መንገድ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ የተባለ ሥራ ተቋራጭ ነው። የመንገዱ ግንባታ በአንድ ዓመት ተኩል ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የመንገዶቹ ግንባታ ለትራፊክ ደኅንነት ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር፣ ከዚህ ቀደም ይወስድ የነበረውን የጉዞ ጊዜ በማሳጠር በቂ የሆነ የመንገድ መሰረተ ልማት የሌለውን የአካባቢው ኅብረተሰብ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ተጠቃሚ በማድረግ የነበረውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል እንደሚያግዝ ተገልጿል።
መንገድ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ገበሬዎች እና የአካባቢው ነጋዴዎች የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለማድረስ እና አርሶ አደሮች የሚያመርቷቸውን የግብርና ምርቶች ለገበያ ለማቅረብ ያግዛቸዋል ተብሏል። በዚህም ምክንያት በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች እና ወረዳዎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ባለሥልጣኑ አስታውቋል።
የመንገዱ ግንባታ በሚካሄድባቸው መስመሮች ላይ የሚገኙ የአካባቢው ኅብረተሰብ፣ የመስተዳድር አካላት እንዲሁም የመንገዱ ተጠቃሚዎች በሙሉ የመንገዱ ግንባታ ተጀምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ባለሥልጣን መሥሪያ ጥሪ አቅርቧል።
ከእዚህ የመንገድ ግንባታ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት መንገዶችን ለማስገንባት ባለሥልጣኑ ውል የተፈራረመ ሲሆን፣ የቆሼ ሚጦ ወራቤ፣ የጋምቤላ አቦቦ ጎግ፣ ዲማ – ሎት ኹለት፣ የፑኝዶ ጎግጊሎ ወንዝ፣ የግሸን መገንጠያ ፕሮጀክቶች ናቸው።
ለእነዚህ አራት የመንገድ ኘሮጀክቶች የሚውለው አጠቃላይ የግንባታ ወጪ ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ የአራቱም መንገዶች ርዝማኔ በአጠቃላይ 169 ኪሎ ሜትር ነዉ። የግንባታዉ ሙሉ ወጪም የሚሸፈነዉ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012


