“አልቀመስ ያለው” የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ዋጋ

0
1514

. 41 በመቶ የከተማዋ ነዋሪዎች ግለሰቦች በሚያቀርቧቸው የኪራይ ቤቶች ይኖራሉ
. ከ3 ዓመት በፊት ለሚንስተሮች ም/ቤት የተላከው “የመኖሪያ ቤት ልማትና ግብይት ረቂቅ አዋጅ” እስካሁን አልፀደቀም

የሚከራይ ቤትን እያማተረ መገናኛ አካባቢ ወደሚገኝ ደላላ ቤት የደረሰው መርድ ሙሉጌታ በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ የመሪ አካባቢ ነዋሪ ሲሆን በቤት ኪራይ ውድነት ከተማረሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ነው:: ከሦስት ዓመት በፊት በ850 ብር ጠባብ ክፍል ቤትን ተከራይቶ በአዲስ አበባ መኖር የጀመረው መርድ አከራዩ በየጊዜው የሚጨምሩት የኪራይ ዋጋ ሁለት ሺህ ብር ሲደርስ ቤት ለመቀየር እንደተገደደ ይናገራል:: መርድ “ምንም እንኳን መጀመሪያ የተከራየሁትን ቤት ከለቀቅኩ በኋላ መሪ አካባቢ በአንድ ሺህ 800 ብር አንድ ክፍል ቤት አግኝቼ ከዓመት በፊት የተከራየሁ ቢሆንም አከራዬ በዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የቤት ኪራይ ዋጋ እንድጨምርላቸው ጠይቀውኛል:: የኪራይ ዋጋውንም ሁለት ሺሕ 400 ብር አድርሰውታል” በማለት ምሬቱን ከትካዜ ጋር ይገልጻል::
የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሬ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች መባባሱ እየተገለጸ ነው:: በተለይ ከባለፉት ስድስት ወራት ወዲህ በግለሰብ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኙ ቤቶች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በእንግዳ ማረፊያዎች እንዲሁም በሙሉ ግቢ ኪራይ ቤቶች ላይ የዋጋ ጭማሬው ታይቷል:: ለጭማሪው ዋና ምክንያት ናቸው ከሚባሉት መካከል የኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር መጨመር እንዲሁም በአነስተኛ ዋጋ እየተከራዩ ለሌሎች በውድ ማከራየትን እንደንግድ እየቆጠሩ የመጡ አዲስ አበቤዎች መበራከት ይገኙበታል፡፡
ጭማሬው ከተስተዋለባቸው አካባቢዎች አንዱ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም ነው:: ነፋስ ስልክ ክፍለ የሚገኘው መብራት ኃይል አካባቢ ‹ስቱዲዮ› በቅርቡ ከሦስት ሺሕ ወደ አራት ሺሕ ብር ያደገ ሲሆን ባለአንድ መኝታ ደግሞ ከነበረበት አማካይ አራት ሺሕ ወደ ስድስት ሺሕ ብር አድጓል:: በጎተራ ኮንዶሚንየም አካባቢም ስቱዲዮ ወደ አራት ሺሕ 500 ሲከራይ፣ ባለአንድ መኝታ ከነበረበት አራት ሺሕ 500 ወደ አምስት ሺሕ 500 ብር፣ ባለሁለት መኝታ ቤት ከሰባት ሺሕ ወደ 10 ሺህ አሻቅቧል፡፡ ባለ ሦስት መኝታ ከስምንት ሺህ 500 ወደ 11 ሺህ ማደጉን ደላሎች ይናገራሉ፡፡ ባልደራስ አካባቢም እንዲሁ ባለሁለት መኝታ ኮንዶሚንየም እስከ 11 ሺህ ድረስ እየተከራየ ነው:: የእንግዳ ማረፊያ የኪራይ ዋጋ በበኩሉ ባለሁለት መኝታ ከ13 ሺህ ወደ 18 ሺህ፣ ባለሦስት መኝታው ደግሞ ከ20 ሺህ ወደ 25 ሺህ አድጓል፡፡
በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ መብራት ሀይል ኮንዶሚንየም አካባቢ በድለላ ሥራ ላይ የተሰማራው መለስ ገሰሰ የአዲስ ማለዳ እህት የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ለሆነ ‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው› እንደገለጸው ከሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ኤርትራዊያን በአዲስ አበባ ለመኖር ያላቸው ፍላጎት መጨመር ለቤት ኪራይ ዋጋ መናር ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ይህንን ምክንያት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሌሎቸ የከተማዋ የቤት ደላሎችም ይጋሩታል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ እርቅ ማውረዳቸውን ተከትሎ በተከፈተው ድንበር በርካታ ኤርትራዊያን ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ:: የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሸን የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ከተከፈተ በኃላ በየቀኑ ከ200 በላይ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሚገኙ ገልጿል::
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢትዮጵያ በደቻ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኤርትራዊያን ወደ አዲስ አበባ መምጣት ለቤት ኪራይ መጨመር አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ:: ኢትዮጵያ የማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲን ጥናት መነሻ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ከተሜነት እየተስፋፋ ነው ይላሉ:: ይህም በቀጣዮቹ ዓመታት የሚጨምር ሲሆን በ2012 በአማካይ 15 ነጥብ አምስት ሚሊየን ሕዝብ በከተማ ይኖራል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን በ2037 42 ነጥብ ሦስት ሚሊየን ይደርሳል ተብሎም ይገመታል፡፡ የአዲስ አበባ እጣ ፈንታም ይኸው በመሆኑ ለቤት ኪራይ መጨመር የራሱን ተጽዕኖ አሳድሯል ተብሏል::
የመሠረተ ልማት መስፋፋት፣ ተደራሽነትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስፋፋት ሰዎች ከገጠርና የከተማ ዳርቻዎች ወደ መሐል ከተማ እንዲመጡ ምክንያት ስለመሆኑ የሚያነሱት ኢትዮጵያ፣ በከተማ ያለውን የቤት ኪራይ ፍላጎት በመጨመር ለኪራይ ዋጋ መናር የራሱ አስተዋጾ እንዳለው ያነሳሉ፡፡
አያይዘውም 41 በመቶ የሚሆኑት የከተማው ነዋሪዎች በግለሰቦች ለኪራይ በሚቀርቡ ቤቶች ውስጥ እንደሚኖሩ በመጥቀስ አከራዮች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በየጊዜው ለሚጨምሩት የኪራይ ዋጋ መጋለጣቸውን ያክላሉ፡፡ ተከራዮችም ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የተከራዩትን ቤት በመጠቀማቸው ‹‹ለሚከተለው የንብረት ጉዳት ለማካካስ›› በሚል አከራዮች በነባሮችም ሆነ አዳዲስ ተከራዮች ላይ የዋጋ ጭማሬ እንደሚያደርጉም ይጠቁማሉ፡፡ ሕገወጥ ደላሎች ሆን ብለው ከተገቢው በላይ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ተከራዮች ከተገቢው በላይ ኪራይ እንዲከፍሉ ማድረግ ለቤት ኪራይ ዋጋ መናር ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑም አክለዋል:: የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጓተት ሌላው ምክንያት እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
የቤት ኪራይ ዋጋ በየጊዜው ማሻቀብን ለመቀነስ፣ የተከራይና አከራይ መብቶችንም በሚያስጠብቅ መልኩ ችግሩን ይፈታል በሚል እምነት ከሦስት ዓመት በፊት የተዘጋጀ ‹‹የመኖሪያ ቤት ልማትና ግብይት ረቂቅ አዋጅ›› እንደነበር ኃላፊው ተናግረዋል:: ሚንስቴሩም ረቂቁን ለሚንስትሮች ምክር ቤት ከሦስት ዓመት በፊት የላከ ሲሆን እስካሁን የአዋጁን መጽደቅ እየተጠባበቀ ይገኛል:: እንደ ኢትዮጵያ ገለጻ የመኖሪያ ቤት ልማትና ግብይት በተለየ የሕግ ስርዓት እንዲዘጋጅ ያስፈለገው የሪል እስቴት ግንባታ፣ በመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ተገንብተው ለተጠቃሚዎች በኪራይ የሚተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና በግለሰብ ለኪራይ የሚቀርቡ ቤቶች የሕግ አግባብን ተከትለው ለተጠቃሚው እንዲደርሱ በመታሰቡ ነው:: ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን በተጠቀሱት ሦስት የመኖሪያ ቤት ዘርፎች የሚታየውን ብልሹ አሰራር ያስወግዳል የሚል እምነትም ተጥሎበታል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በጀርመን ፍራንክ ፈርት ላይ በነበራቸው ውይይት መንግሥታቸው ሁሉንም ቤት ፈላጊ የግል ቤት ባለቤት ማድረግ ባይችልም ዜጎችን በአቅማቸው ልክ ቤት ለመከራት እንዳይሳቀቁና እንዳይቸገሩ ለማስቻል እንደሚሠራ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት የተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤት ፈላጊ ያለ ሲሆን በየዓመቱም ተጨማሪ 100 ሺህ ቤት ፈላጊ ይፈጠራል፤ አብዛኛውም አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ በሌላ መልኩ በ2005 በተደረገ የኮንዶሚኒየመ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ከተመዘገቡት ውስጥ እስካሁን 974 ሺሕ በላይ ቤት ያላገኙ ሲሆን አስተዳደሩ ምዝገባው አሁን ላይ ቢደረግ የቤት ፈላጊው ቁጥር ከዚህ እጥፍ እንደሚሆንም እረዳለሁ ብሏል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here