ልማት ባንክ ከ 900 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

0
1103

ልማት ባንክ ከኪሳራ በመውጣት በ 2012 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ ከ951 ሚሊዮን ብር ማትረፉን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
ባንኩ በ2011 በጀት ዓመት ከነበረበት ኪሳራ በማገገም፣ በአጠቃላይ በስድስት ወሩ ብር 951 ሚሊዮን ወይም የዕቅዱን 483 በመቶ ሊያተርፍ መቻሉን ኤጀንሲው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2011 የተበላሸ ብድር መጠኑ ማሻቀቡን ተከትሎ ኪሳራ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል። በተለይ ለግብርና የሰጠው ብድር ውስጥ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ሊመለስ አልቻለም ነበር። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፈው በጀት ዓመት የተበላሸ የብድር መጠኑ 40 በመቶ መድረሱ ይታወሳል።

የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች በ2012 በጀት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከታክስ በፊት 10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን የገለፀው ኤጀንሲው፣ ልማት ባንክ በስድስት ወራት ውስጥ 9 ነጥብ 33 ቢሊዮን ወይም ከዕቅዱ 103 በመቶ ካተረፈው ንግድ ባንክ በመቀጠል ኹለተኛው ከፍተኛው አትራፊ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ደግሞ በመንፈቀ ዓመቱ ብር 427 ሚሊዮን ወይም የዕቅዱን 101 በመቶ አትርፎ ለዘርፉ ትርፍ አፈጻጸም የ4 በመቶ ድርሻ በማበርከት ሦስተኛ ደረጃ ይዟል።
ልማት ባንክ ከኪሳራ ለመውጣት የብድር አሰጣጣ ስርዓቱ ላይ ለውጦቸን ማድረጉ የተገለፀ ሲሆን፣ የሌሎች አገራትን ባንኮች ልምድ በመወሰድ ላይ እንደሚገኝ መግለፁ ይታወሳል።

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ስር በፋይናንስ ዘርፍ የሚገኙ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2012 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከታክስ በፊት በድምሩ 10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችለዋል።

ይህ የገቢ የልማት ድርጅቶቹ አቅደውት ከነበረው የብር 9 ነጥብ 67 ቢሊዮን ብር ትርፍ አንጻር ሲታይ፣ ክንውናቸው ከዕቅዳቸው ከ11 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ኤጀንሲው አስታውቋል።
ድርጅቶቹ ይህንን ትርፍ ሊያገኙ የቻሉት የባንክና የመድን አገልግሎቶች በመስጠት በግማሽ ዓመቱ 34 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅደው፣ 37 ቢሊዮን ወይም የእቅዳቸውን 107 በመቶ ማግኘት በመቻላቸው ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here