ኦሮምያ እንደ ትግራይ- ጅማም እንደ ዓድዋ??!!

0
759

በኢትዮጵያ የተካሄዱ አገራዊ ምርጫዎች በየጊዜው የየራሳቸውን አይረሴ ኩነቶች አስተናግደው አሳልፈዋል። ግዛቸው አበበ እነዚህን ይልቁንም የ1997 ምርጫና የ2002 ምርጫን በማንሳት፣ በትግራይ ክልል የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ በምርጫዎች ዋዜማ፣ በምርጫ ወቅትና በምርጫ ማግስት እንደ አገር ካስተናገደችው ግርግር ውስጥ በትግራይ ክልል የነበረውን ክስተት የጠቃቀሱ ሲሆን፣ አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በማነጻጸር ያስቀምጣሉ። ካድሬዎችና ባለሥልጣናት ይመረጣል ብለው የጠበቁትና የፈለጉት ብቻ እንዲመረጥ ለማድረግም በተፎካካሪ/በተቃዋሚ ፓርቲ፣ አባላት ወይም ግለሰቦች ላይ የሚያሳርፉትን መከራም በማሳያ ያነሳሉ። ይህም ብዙዎች ለምርጫ መቅረብን እንዲፈሩ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ጊዜው ግንቦት የ2002 የአገር አቀፍ ምርጫ መዳረሻ ወቅት ነበር፤ ቦታው ደግሞ መቀሌ። ወግ ነውና ምርጫ ደረሰ ተብሎ ቅስቀሳዎች በተለያየ መንገድ ይካሄዳሉ። ጥቂት የግል ተወዳዳሪዎች ፖስተር አዘጋጅተው በየቦታው ለጥፈዋል። ከመቀሌው ሐውዜን አደባባይ ወደ ደጀና (ወደ ክልሉ መንግሥት ጽሕፈት ቤት) በሚወስደው መንገድ ግራና ቀኝ በሚገኙ ሕንጻዎች እና የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ እዚያና አዚህ የተለጠፈች የአንድ የግል ተወዳዳሪ ፖስተር የብዙዎችን ትኩረት ስባለች። ዐይኑን የጣለባትን ሁሉ ዘና ስለምታርግ ለሳቅና ለስላቅ ታነሳሳለች።

የግል ተወዳዳሪው የመረጡት የምርጫ ምልክት በየግቢአችን የሚተከለው የውሃ ቧንቧ ነው። ተወዳዳሪው ‹ለመቀሌ ከተማ የራስ ምታት የሆነውን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር የምፈታው እኔ ነኝና ምረጡኝ› ማለታቸው ነው። በፖስተሯ ላይ ያረፈው ጽሑፍ ደግሞ የተወዳዳሪውን ስጋት ያስተጋባል። ተወዳዳሪው የሕወሐት ተቀናቃኝ ሳልሆን ከሕወሐት ጋር አብሮ ለመሥራት ነው ወደ ምርጫ የገባሁት የሚሉ የሚያስመስል ጽሑፍ ፖስተሩ ላይ ይነበባል።

‹‹…ሕወሐት በመቀሌም ሆነ በመላ ትግራይ የሕዝብን ችግር ለመፍታት በርካታ የልማት ሥራዎችን ሠርቷል። ውሃንም በሰፊው አዳርሷል፣ የውሃ ምንጮችን ከመቆፈር ጀምሮ ዋና ዋና የውሃ መስሮችን እስከ መዘርጋት ጥሩ ሥራ በሕወሐት ተሠርቷል… የቀረው ነገር ከትልልቆቹ መስመሮች ውሃውን እየሳቡ ወደየቤቱ ማስገባት ነው… እኔ ከተመረጥኩ ይህን ቀሪ ሥራ እሠራዋለሁ….›› ይላል ፖስተሩ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ። ይህ አባባል የሰውየውን እየፈሩ ወደ ምርጫ መግባት ስለሚያሳብቅ አንባቢውን ሁሉ ለሳቅና ከዚያም ለስላቅ ይገፋፋዋል። ‹ከፈሩ ለምን አርፈው አይቀመጡም?› የሚሉም አልታጡም። አንዳንዶች ደግሞ ሰውዬው ቀድሞውንም ቢሆን ምርጫው ውድድር ያለበት ለማስመሰል በሕወሐት የተመለመሉ የግል ተወዳዳሪ ናቸውና ምን አብረከረካቸው ሲሉም ተሰምተዋል።

በእርግጥ ሰውዬው በግላቸው ተነሳስተው ከሕወሐት ጋር የምክር ቤት ወንበር ለመናጠቅ ወደ ምርጫው የገቡ ከሆነ በእሳቸው መፍረድ ከባድ ነው። በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሲሆን እንደታየው የምርጫ 1997 ዋዜማ በትግራይም ደስ የሚል የዴሞክራሲ ሽታ ነበረው። ብዙ ተወዳዳሪዎች ተመራጭ ለመሆን ተነሳስተው ታይተዋል። በተለያዩ መንገዶች ቅስቀሳዎችን አካሂደዋል። ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ደግሞ እንደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል የዴሞክራሲና የእውነተኛ ምርጫ ሞት መርዶ በትግራይም ይስተጋባ ዘንድ ግድ ሆኗል። በምርጫ 1997 ወቅት ትግራይ ውስጥ ችግር የተፈጠረባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ብቻ ሳይሆኑ የግል ተወዳዳሪዎችም ጭምር ነበሩ።

በምርጫ 1997 ማግስት በየምርጫ ጣቢያው የተለጠፉ ውጤቶች የሕወሐት ተወካዮች በቀላሉ በከፍተኛ ድምጽ መመረጣቸውን የሚናገሩ ቢሆኑም ምርጫውን ተከትሎ ከፍተኛ ግርግር መከተሉ ብዙዎችን ግራ አጋብቶ ነበር። መቀሌ ውስጥ ትልልቅ የድምጽ ማጉያ በጫኑ መኪኖች ላይ ሆነው ‹‹… የትግራይ ሕዝብ ሆይ! ትምክህተኞችና ጠባቦች (አማራዎችና ኦሮሞዎችን ነው) ተባብረው ተነስተውብሃል፣ ትግራይን የጦርነት አውድማ አድርገዋት የነበሩትና አሸንፈህ ከትግራይ ያባረርካቸው የዘወትር ጠላቶችህ በምርጫ ሥም ተመልሰው ሊመጡና ሊገዙህ ተነስተዋል…›› እያሉ የሚቀሰቅሱ ካድሬዎች ተሰማርተው ነበር።

በምርጫው ማግስት ‘ለቅንጅት ድምጽ የሰጡ እነማን ናቸው?’ በሚል ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቶ፣ በየቀበሌውና በየመሥሪያ ቤቱ ስውር የማጣራት ሥራ መሠራቱ ገልጽ ነበር። የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ተወዳዳሪዎችና ደጋፊዎችም ሰፊ የጥቃት ማዕበል ተከፍቶባቸዋል። በሰበብ አስባቡ ከየሥራቸው የተባረሩና ተሸማቅቀው እንዲኖሩ የሚያደርግ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውም ጥቂት አልነበሩም። ኅብረተሰቡ ከነ ቤተሰባቸው ያገላቸው ዘንድ ተጽዕኖ ይደረግ ነበረ።

እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ትግራይ ውስጥም በምርጫ መወዳደር ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚዎች በምርጫ ጣቢያዎች በታዛቢነት መቆምም ለድብደባ፣ ለእስርና ለሞት ሰበብ የሆነባቸው አጋጣሚዎች በጣም ብዙ ናቸው። ዓረና የተባለው ትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ነባር ተቃዋሚ ፓርቲ፣ በዚህ ዓይነት ጥቃት ጥቂት የማይባሉ አባላቱንና ደጋፊዎቹን አጥቷል፣ ብዙዎችም ተጎድተውበታል።

ምርጫ 1997ትን ተከትሎ አንዳንድ ፈጣን የትግራይ ዘፋኞች ምርጫውን ለማጣጣልና በምርጫው ዋዜማ የተካሄዱት (በቴሌቪዥንና በሬዲዮ በቀጥታ ሲተላለፉ የነበሩት) ክርክሮች የፈጠሩባቸውን የብስጭት ስሜት በሚገልጽ መልኩ ‘በጠላ ቤት ወሬ ሥልጣን አይገኝም’ የሚልና የመሳሰሉ ነጠላ ዜማዎችን ለቅቀዋል። እነዚህ ዘፈኖች የአንዳንድ የሕወሐት ባለሥልጣናትና ታጋዮችን ‘እኛ ሞተንና ቆስለን ያገኘነውን ሥልጣን እንዴት በምርጫ አሳልፈን እንሰጣለን? … ሥልጣን አንዴ ከሕወሐት እጅ ከወጣ መቼም ቢሆን እንደገና አይመለስም!’ እያሉ ከሚያንሾካሹኩትና አንዳንዴም በየስብሰባው ከሚናገሩት ነገር የተቀዱ ናቸው።

ትግራይ ውስጥ ምርጫ 1997ትን ተከትሎ የግል ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበው በነበሩ ሰዎች ላይም ከፍተኛ ችግር እንዲደርስ መደረጉ ሊታወስ ይገባል። ይህን በሚመለከት የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች በተለይ ከሐውዜን አደባባይ አስከ ሮማናት አደባባይ በንግድ ሥራ የተሰማሩ የጽሕፈት ማሳሪያዎች እና የመኪና መለዋወጫ እቃዎች መሸጫ ሱቅ ያላቸው ነጋዴወች፣ በሚገባ የሚያስታውሱት አንድ ታሪክ አለ። ከእነዚህ ነጋዴዎች መካከል የሆኑ አንዲት ወይዘሮ፣ በግል ተወዳዳሪነት ለምርጫ 1997 ቀርበው ነበር። የምርጫ ምልክታቸውን መሶበ-ወርቅ ያረፈበት፣ በሹሩባና በሐበሻ ልብስ ተውበው የሚታዩበትን ምስላቸውን የሚታይበት ፖስተር በሚወዳደሩበት አካባቢ ለጣጥፈው ቅስቀሳ አካሂደዋል።

ወይዘሮዋ ድህነትን እዋጋለሁ፣ ልጆቻችን የሞቱለትን ዴሞክራሲ ዕውን አደርጋለሁ ብለው ነበር የቆሙት። የመቀሌ መሀል ከተማ ነጋዴዎችም ሆኑ የዚያ አካባቢ ነዋሪዎች የወይዘሮዋን ፖስተር ካዩ ሰዎች መካከል ‘ጀግኒት’ እያሉ እያደነቋቸው ነው ግንቦት 7/1997 የደረሰው። ምን እንደተከሰተ ግልጽ ባይሆንም በምርጫው ማግስት ሴትዮዋ በሕወሐት ጥርስ እንደተነከሰባቸው መሰማት ጀመረ። ወይዘሮዋ የተወዳደሩበትን የምርጫ ጣቢያ የአዲስ አበባዎቹን የምርጫ ጣቢያዎች አስመስለውት ነበረ የሚል ጭምጭምታ ተሰማ። በምርጫ 1997 ገዥው ቡድን የድምጽ ድርቅ እንደመታው ሁሉ ወይዘሮዋ በተወዳደሩበት የመቀሌ ምርጫ ጣቢያም ሕወሐት የድምጽ ድርቅ ሳይመታው እንዳልቀረ የብዙዎች ግምት ሆነ።

ከተወሰደባቸው እርምጃ አንጻር ወይዘሮዋ በምርጫው ስለተሳተፉ ብቻ ቂም ተቋጥሮባቸዋል ማለት ስለሚከብድ ነው ሕወሐትን በዜሮ ዘረሩት የሚለው ወሬ የተወራው። የተወሰደባቸው እርምጃ ከወይዘሮዋ ንግድ ቤት ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ግዥ እንዳይፈጽሙ መከልከል ነበር። ይህ ክልከላ የተደረገው በቀጥታ ከክልሉ ምክትል ፕሬዘደንት ጽሕፈት ቤት ወደ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች በወረደ ደብዳቤ ነው። በወቅቱ አደረጃጀት የክልሉ ምክትል ፕሬዘደንት የክልሉ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊም ነበር። ስለዚህ ይህንን እና ሌላውንም የሕወሐት እርምጃ የታዘቡት ባለ ቧንቧ ምልክቱ የግል ተወዳዳሪ ፍርሃታቸውን የሚያስተጋባ ፖስተር ቢለጥፉ የሚገርም ነገር ይሆናልን?

ከመቀሌ ወደ ዓድዋ እንሂድ። ምርጫ በመጣ ቁጥር አቶ መለስ ዜናዊ ለምርጫ የሚቀርቡት ዓድዋ ከተማ ውስጥ እንደነበረ አይዘነጋም። ዓድዋ ውስጥ በተቃዋሚነት ለመወዳር ሲሞከር ነገሮች በጣም ይከብዱ ነበረ። የሕወሐት ካድሬዎችና ጭፍን ደጋፊዎቻቸው ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር በምርጫ ለመፎካከር ማሰብን ብቻ እንደ ትልቅ ወንጀል፣ እንደ ትልቅ ድፍረት አድርገው ነው የሚያዩት። ተወዳዳሪ ነኝ የሚለውን ወዲያውኑ በጠላትነት ይፈርጁታል። ከአቶ መለሰ ጋር በምርጫ መወዳደርን እንደ ትልቅ ኃጢያት አድርገው የሚያዩ ካድሬዎች ደግሞ የተፎካካሪው ጤንነት ወደ መጠራጠር የደረሰ አዝማሚያ ይታይባቸዋል።

ስለዚህ እነዚህ ካድሬዎች ለተወዳዳሪው ነገሮችን ሁሉ ከባድ ያደርጉበታል። በተቻላቸው መጠን ሁሉ መለስ ዜናዊን ብቸኛ ተወዳዳሪ ለማድረግ ይሠራሉ። የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ፣ ሕዝብን ሰብስቦ ማነጋገር፣ ፖስተር መለጠፍ ወዘተ… አይቻልም። ስብሰባዎች ይታወካሉ፣ ከተማው ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ቅስቀሳ ለማካሄድ የሚሞክሩ ለጥቃት ይዳረጋሉ፣ ፖስተሮች ይቀዳደዳሉ፣ ባነሮች ከየተሰቀሉበት ይወርዳሉ። በመጨረሻዎቹ ምርጫዎች በአድዋ ዓረናን ወክለው የቀረቡት ተወዳዳሪ የቀድሞዋ ታጋይ የኋላዋ ተቃዋሚ ወይዘሮ አረጋሽ ናቸው። አረጋሽ ይህ ሁሉ ደርሶባቸው ‹ለዚህ ነበረ እንዴ የታገልነው!› ለማለት ተገድደዋል።

ቀጣዩ ምርጫስ ለትግራይ ተቃዋሚና የግል ተወዳዳሪዎች ምን ይዞ ይመጣል?
አዲስ ማለዳ ከሳምንታት በፊት እንዳስነበበችን፣ ምርጫውን በሕወሐት እጅ የማስገባት ሰፊ ሥራ ተሠርቷል። እውነተኛ ተቃዋሚ ቡድኖች በባንዳነት፣ በተላላኪነትና የትግራይን ሕዝብ አንድነት ለማናጋት የሚሠሩ ጠላቶች ተብለው ተፈርጀዋል። እረፉ! ካልሆነ ግን ከእኔ የሚያስጥላችሁ ማንም የለም ተብለውም በይፋ ማስጠንቀቂያ ተሰንዝሮባቸዋል። በዚህ ሳምንት የተቃዋሚው የዓረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መካካል አንዱ የሆኑት ዶክተር ማርቆስ ገሰሰ ከፍተኛ ድብደባና ማንገላታት ደርሶባቸው፣ በግል ሆስፒታላቸው ላይ ዝርፊያ ሊፈጸም ተሞክሮ ነበር።

ይህን በሚመለከት ዓረና ለጋዜጠኞች በሰጠውና ማክሰኞ የካቲት 1/2012 በዶቸ ቨለና በቪኦኤ በተላለፈው መግለጫ ላይ፣ የሕወሐት ባለሥልጣናት በይፋ ዛቻ መሰንዘራቸውን ተከትሎ በአባላቱና በአመራሮቹ እንዲሁም በሌሎች ከሕወሐት ጋር በማይሞዳሞዱ ዜጎች ላይ እስራቶች፣ ድብዳባዎች፣ በመርዝ የመግደል ሙከራን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች እየተፈጸሙባቸው መሆኑን፣ ‘…በምርጫው መካፈል አደገኛ ነው…’ የሚል ስሜት አሳድረው ራሳቸውን ከምርጫው ያገልሉ ዘንድ ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን አሳውቀዋል።

በትግራይ የተለመደው ተቃዋሚዎችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችና የማሸማቀቅ ሥራዎች በመላ ኢትዮጵያ ሲፈጸሙ የኖሩ ናቸው። በዚህ ወቅት በትግራይ የሚታየው ዓይነት ጥቃትና ማሸማቀቅ በኦሮምያም በመፈጸም ላይ ያለ ይመስላል። በእርግጥ ትግራይ ውስጥ ሕወሐት በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍልም የቀድሞዎቹ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ካድሬዎችና ፖለቲከኞች ናቸው ያሉት። የመቀሌዎቹም ሆነ ብልጽግናዎች ግምገማ አካሂደው ለለውጡ፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ለመልካም አስተዳደር ወዘተ…. የማይበጁትን ለይተው አልመነጠሩም። ሁሉም እንዳሉ ነው ያሉት ማለት ይቻላል።

ስለዚህ በትግራይ የለየለት አፈና ቀጥሎ እየታየ ሲሆን በኦሮምያ ደግሞ የተመለደ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ባህሪ የሆነው ሕዝብን እያሰለፉ ድራማ መሥራትና ተቃዋሚዎችን መወንጀል የተጀመረ ይመስላል። የኦሮምያ ብልጽግና ፓርቲ ራሱን እንደ ሕወሐት አድርጎ፣ ኦሮምያን እንደ ትግራይ ሊያደርጋት እየቃጣው ነው ለማለት የሚያስደፍሩ ድርጊቶች እየታዩ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ካድሬዎች የተለመደውን ሪፖርት የማድረግና ነጥብ ለማስመዝገብ ሥራ በመሥራት ላይ ያሉ ይመስላሉ። ሕወሐት/ኢሕአዴግ በ2010 እስኪከረበት ድረስ የስርዓቱ ካድሬዎች ስርዓታቸው የሰልፍና የስብሰባ ድርቅ እንዳይገባው ማድረጉ ላይ ሰንፈው አያውቁም። የሚያዝያ 29 እና 30/1997 ሰልፎችን አይተው እንኳ ሰልፍ ማምለካቸውን አላቆሙም።

በዚህ በያዝነው የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ጅማና አጋሮ ላይ ስብሰባና ሰልፍ ተካሂዷል። የስብሰባውና የሰልፉ ተሳታፊዎች የከተሞቹና የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ናቸው ተብሏል። ፋና የተባለው ‘የአገዛዞች’ መገናኛ ብዙኀን፣ የመንግሥት ሚዲያዎች፣ ዶቸ ቨለ እና ቪኦኤ ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል። ሰልፉና ስብሰባው ለውጡን በመደገፍ የተካሄደ መሆኑ ተዘግቧል። በሰልፉ በለውጡ የተገኙት መልካም ነገሮች ተጠቅሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወድሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን የነካ የዐይኔን ብሌን ነካ ዓይነት የጥብቅና መቆም አነጋሮችም ተሰምተዋል። ተመሳሳይ መፈክሮችም ለንባብ በቅተዋል። ሰልፎቹ ግለሰብ ተኮር ነበሩ። የጅማ ከንቲባ ንግግር ያሰሙበት የጅማውና አጋሮው ሰልፍ የቀድሞው ኦሕዴድ የአሁኑ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ካድሬዎች የጠሩት ሰልፍ ነው። ተቀናቃኞች የሚጠሩት ስብሰባና ሰልፍ እስካልተከለከለ ጊዜ ድረስ በገዥው ቡድን ካድሬዎችና ባለሥልጣናት ትብብር ይህን መሰል የድጋፍ ሰልፍና ስብሰባ መጠራቱ ችግር የለውም።

የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን በዘገባቸው ሰልፉ ለውጡን ለመደገፍ መጠራቱን የዘገቡ ቢሆንም፣ ዶቸቨለና ቪኦኤ ላይ ለቃለ ምልልስ የቀረቡት ታዳሚዎችና የሰልፉ አዘጋጆች ግን አሳሳቢና ‹ቀጥሎስ በኦሮምያ ምን ይመጣ ይሆን?› ብሎ መጠየቅን የግድ የሚል ነው። ሰልፉን ያስተባበሩት ካድሬዎችና የብልጽግና ደጋፊዎች መረራ ጉዲናን (ዶ/ር) እንደ ግለሰብ፣ ኦፌኮን ደግሞ እንደ ድርጅት ሲያወግዙና ‘የጅማን ሕዝብ ተሳድበዋል’ እያሉ ሲወነጅሉ ተሰምተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ድጋፍ በሚል ተካሄደ በተባለለት ሰልፍ፣ ይህን መሰሉ ውንጀላ መሰማቱ ምርጫዎች በመጡ ቁጥር በመለስ ዜናዊ የትውልድ ቦታ በዓድዋ ሲፈጸም የነበረውን የካድሬዎች ነገር የሚያስታውስ ነው። በተመሳሳይ ለብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ በሚል ሰልፎች፣ የጽዳት ዘመቻዎችና መዋጮዎች በጅግጅጋና በምዕራብ ሐረርጌና በአዳማ ተካሂደዋል። በምዕራብ ሐረርጌ በ15 ወረዳዎችና በኹለት የከተማ አስተዳሮች ለአንድ ወር ተኩል የተፋሰስ ልማት ሥራ ሲሠራ መሰንበቱን ተከትሎ፣ ተካሄደ የተባለውን የድጋፍ ሰልፍ በሚመለከት ቪኦኤ ላይ መግለጫ የሰጡት የዞኑ የኮምንኬሽን ጽሕፈት ቤት ሐላፊ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስል ያረፈበት ቲ-ሸርት የለበሱ ተሳታፊወች ‘የስድብና የዘለፋ ፖለቲካ ይቁም!’ የሚሉና የመሳሰሉ ጽሑፎች የሰፈሩባቸው ባነሮች መያዛቸውን አሳውቀዋል።

በምዕራብ ኦሮምያው ሰልፍ ላይም ቀደም ብሎ በዚሁ አካባቢ ሰልፍ በጠሩት በእነ ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ ኦብፓና አቶ ጃዋር ላይ ጣትን የመቀሰር ዘመቻ ተካሂዷል ማለት ይቻላል። የጅግጅጋና የምዕራብ ሐረርጌ ሰልፎችም እንደ ጅማና አጋሮ ሰልፎች በግለሰብ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በዕለተ ረቡዕ የካቲት 11/2012 ተመሳሳዩ ሰልፍ በለገጣፎ ለገዳዲ መካሄዱ በፋና ብሮድካስቲንግ ተዘግቧል። በዚያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወድሰዋል።

የእነኦፌኮ አብሮ ለመሥራት መጣመርና ትኩረታቸውን በቀጣዩ ምርጫ ላይ አድርገው እንቅስቃሴ መጀመር፣ የኦሮምያ ብልጽግና ፓርቲን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሊከትተው እንደሚችል አዲስ ማለዳ ጋዜጣ፣ በጥር 16 ቀን 2012 እትሟ ጠቆም አድርጋ ነበረ። በእርግጥም የኦሮምያ ብልጽግና ፓርቲ ስጋት ውስጥ እንደገባ የሚያስገምቱትን እርምጃዎች እየወሰደ ነው። በጅማና በምዕራብ ሐረርጌ በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ጸጉር ስንጠቃ በሚመስል አኳኋን ‘የጅማ ሕዝብ ተሰደበ….ጅማ ላይ መሬት እንጂ ሰው የለንም ተባለ….’ እና የመሳሰሉት ነገሮችን እያስተጋቡ፣ ተቃዋሚ/ተፎካካሪ ቡድኖችንና አመራሮቻቸውን በሥም እየጠቀሱ የጥላቻ ዒላማ የማድረግ ሥራ በግልጽ መሠራቱ፣ ዓድዋ ብሎም ትግራይ ላይ ለምርጫ መቅረብን ብቻ አስፈሪ የሚያደርግ መንፈስ ሰፍኖ እንደነበረው ሁሉ ጅማ ብሎም ኦሮምያ ላይ ተመሳሳይ መንፈስ ለማስፈን እየተሞከረ ሊሆን እንደሚችል ለመጠርጠር የሚጋብዝ ነው።

በኦሮምያ መታየት የጀመረው አሳሳቢ ነገር በጅማና በምዕራብ ኦሮምያ የተከሰቱትን ዓይነት ተቃዋሚዎችን የማብጠልጠልና ተቃዋሚዎችን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት ሴራ መሸረብ ብቻ አይደለም። ኦፌኮና ኦነግ አባሎቻቸው እየታሰሩባቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ጅምላ በሚባል ደረጃ ወደ እስር ቤት የሚወረወሩትም አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ቤት ረዥም ጊዜ እንዲያሳልፉ ከመደረጋቸው በተጨማሪ፣ አንዳንዶቹ ጠያቂ ቤተሰብ እንዳያያቸው ክልከላ እንደተደረገባቸውም ይናገራሉ። ታሳሪዎቹ ክስ ስለማይመሰረትባቸው የታሰሩበትን ምክንያት ይህ ነው ለማለት መቸገራቸውንም አሳውቀዋል።

አርብ የካቲት 6/2012፣ ኦነግ በሰጠው መግለጫ የአባላቱ እስራት ለአንድ ዓመት ከአምስት ወራት ያለማሰለስ የተካሄደ መሆኑን ገልጾ በቅርቡ ግን በአንድ ሳምንት ውስጥ መጠነ ሰፊ የማሰር ዘመቻ እንደተካሄደበት አሳውቋል። ኦነግ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙት በሰበታ፣ አዋስ፣ ለገጣፎ፣ ቡራዩና በሌሎች ሰባት ዞኖችና 26 ከተሞች በተካሄዱ የማሰር ዘመቻዎች፣ በትክክል የተመዘገቡ አባላቱ የሆኑ፣ ሥልጠናም የተሰጣቸው ወደ 400 የሚሆኑ ሰዎቹ እንደታሰሩበት ገልጿል። ‹መንግሥት ቃሉን አጥፏል› ያለው ኦነግ፣ ጅምላ እስራቱ የሚካሄደው በኦሮምያ ፖሊስ ነው ብሏል። ኦነግ በመግለጫው ላይ አገሪቱ ወደ ምርጫ ስትቃረብ እስራቱ መበራከቱ እንዳሳሰበው ገልጾ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነገሩን አጣርቶ ይፋ ያደርገው ዘንድ ጥሪ አቅርቧል።

በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በምሥራቅ ጉጅና በሻምፑ መጠነ ሰፊ እስራቶች እንደተካሄዱ መረጃ አለኝ የሚለው አምነስቲ፣ የኦነግ አቤቱታ ተቀባይነት ያለው ነው ይላል። የአምነስቲ ተወካይ በጉጂ ብቻ ቢያንስ 75 ከኦነግ ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን ገልጿል። አምነስቲ የኦሮምያው የማሰር ዘመቻ አገሪቱ ዝግጅት በምታደርግበት ቀጣይ ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችልም ጠቁሟል። እስራቱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽን፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስንና የመደራጀትን መብት ገድቦ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ እንዳይሆን ሊያደርገው እንደሚችልም ስጋቱን አስተጋብቷል።

የኦሮምያ አለመረጋጋት ያሳሰበው የአባ ገዳዎች ኅብረት የሚሳተፍበት፣ የኦሮሞና የኦሮምያ ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊ የተባለው ኮሚቴ ባለ ስድስት ነጥብ መፍትሔ የያዘ ነው የተባለለትን ሰነድ ለክልሉና ለፌዴራሉ መንግሥት አቅርቧል። አባ ገዳዎቹና ኅብረቱ ኦሮምያ ወደ ለየለየት ችግር አንዳትዘፈቅ ስጋት አድሮባቸዋል። ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ መግባት የማይችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ሲሉም ጭንቀታቸውን አስተጋብተዋል።

ምርጫው በኦሮምያ ይህን በመሰለ የአሳዳጅና የተሳዳጅ ጨዋታ ታጅቦ የሚካሄድ ከሆነ ነጻና ፍትሐዊ መሆኑ ላይ ጥርጣሬ መዘራቱ አይቀሬ ነው። ሁሉም ተፎካካሪዎች እኩል መወዳደሪያ ቦታ ካላገኙና ‘በወረዳችንማ/በአውራጃችንማ ሌላ ሰው እንዴት ይወደዳራል’ የሚል ግርግር ከተጀመረ፣ በአንድ በኩል መንግሥት አልባ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ባለ ብዙ ትንንሽ መንግሥታት ሆና የምትታየው ኢትዮጵያ፣ ወደ ከፋ ችግር ልትዘፈቅ ትችላለች። አንድ ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ከሊቢያና ከሶርያ አስከትሎ ስጋት ያንዣበበባት አገር ሲል ያስቀመጠላት ትንቢትም እውን ሊሆን ይችላል።

የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ መንግሥት ምዕራብ ኦሮምያ ብዙ ፈተናዎች እየገጠሟቸው መሆኑ ግልጽ ነው። የኦሮምያ ፖሊሶች፣ ባለሥልጣናትና የባለሥልጣናት ቤተሰቦች በተደጋጋሚ የጥቃት ዒላማ ተደርገዋል። ግድያና አፈናዎችም ይካሄዱባቸዋል። ‘አባ ቶርቤ’ (ባለ ሳምንት) የተባለው ቡድን እስከ ታኅሳስ 2012 ባካሄደው የግድያ ዘመቻ፣ በምዕራብ ኦሮምያ ብቻ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውና ከነዚህ ውስጥ 12 ፖሊሶች እንደሚገኙበት በወቅቱ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

‘አባ ቶርቤ’ የኦነግ ክንፍ እንደሆነ ይታመናል። ታኅሳስ 2012 ላይ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “…. በምዕራብ ዞን የሚገኘውም ይሁን በሌሎች ዞኖች ውስጥ የሚገኘው የኦነግ ሠራዊት በሙሉ ተጠሪነቱ፣ የሚመራውም፣ ትዕዛዝ የሚቀበለውም ከኦነግ ሊቀመንበር ከዳውድ ኢብሳ ነው። ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀመንበር ናቸው። የኦነግ ጦር ደግሞ ካሉት የኦነግ ዘርፎች አንዱ ነው። ስለዚህ [ጦሩ] ተጠሪነቱም ለሊቀመንበሩ ነው…..” ብሎ መናገሩ የሚዘነጋ አይደለም።

መንግሥት አሁንም ቢሆን የሕግን የበላይነት ማስከበር ይገባዋል። ፖሊሶች፣ የወረዳና ከተማ አስተዳዳሪዎች፣ የመሥሪያ ቤቶችና የትምህርት ተቋምት ኃላፊወች ወዘተ… ዒላማ መደረጋቸው በቃ ሊባል ይገባል። ፖሊስ ወይም የወረዳ ባለሥልጣን ነው ተብሎ አባት ልጁን ይዞ እየሄደ በመንገድ ላይ መገደሉ፣ በማታ በር ተንኳኩቶ አባት በልጅና በሚስቱ ፊት በጥይት መመታቱ ወዘተ…. የመንግሥት ተቃዋሚ ነን ባይ ታጣቂዎችን አረመኔነት፣ ወደ አደገኛ አዝማሚያ ውስጥ እየገቡ መሆኑንም አመላካች ነው። በተመሳሳይ መንገድ ዜጎች በጥርጣሬና በስህተት በመንግሥት ታጣቂዎች መገደላቸው፣ መታሰራቸውና ለስደት መዳረጋቸው በቃ ሊባል ይገባል።

መንግሥት ዱር ውስጥ መሽጓል በሚለው ኦነግና መሣሪያውን አውርዶ ከተማ ገብቷል በተባለው ኦነግ መካከል ዝምድና (ግንኙነት) መኖርና አለመኖሩ ላይ ግልጽ አቋም ያለው አይመስልም ወይም ‘እንደየ አመጣጡ ይስተናገዳል’ ብሎ ስለ ዝምድና መኖርና አለመኖሩ መጨነቅ አልፈለገም። ዳውድ ኢብሳን ‘በሳሎን’ ጃል መሮን ‘በጓሮ’ አስቀምጦ ሕግን ማስከበር የሚቻል አይደለም። በየወረዳውና በየገጠሩ ያሉ የመንግሥት ወኪሎችን፣ ፖሊሶችንና ሚሊሻዎችን ለተቃዋሚ ለታጣቂዎች ስስ ዒላማዎች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ይህን መሰሉ የተዛነፈ አሰራር ሊሆን ይችላል። ታዲያ እነዚህ የወረዳና የዞን ባለሥልጣና፣ ፖሊሶችና ሚሊሻዎች በዝምታ ነገሮችን ማስተናገድ ይችላሉን? ለብቀላ ይሁን ራስን ለማዳን መተኮሳቸው ይቀራልን?

በኦሮምያ እርምጃዎች በዘፈቀደና በየወረዳው ባሉ ኃላፊወች ስሜትና ፍላጎት ብቻ እየተወሰዱ መሆንና አለመሆኑን መንግሥት ሊያጣራ ይገባዋል። በዕለተ ቅዳሜ የካቲት 7/2012 በቡራዩ ከተማ በአንድ ሆቴል የመመረቅ ስነስርዓት ላይ ችግር ተፈጥሮ ነበር። በፖሊስ ተደብድበናል የሚሉት አርቲስቶች አንዷ ችግሩ የተፈጠረው ስነ-ስርዓቱ ከተጠናቀቀና ሰው መበተን ከጀመረ በኋላ መሆኑን ገልጻ “…ኦነግን የሚያሞግስ ዘፈን ዘፍናችኋል…” እያሉ ፖሊሶች ያለ ርህራሄ እንደደበደቧቸው ተናግራለች። ግጭት እንደነበረ ያመኑት የቡራዩ ፖሊስ መምሪያ ምክትል ኃላፊ፣ ችግሩ የተፈጠረው በተጠሩት አንግዶች መካከል ከዘፈን ምርጫ ጋር በተገናኘ በተቀሰቀሰ አለመግባባት መሆኑንና ፖሊስ በቦታው የደረሰው ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ሁከቱን ለማብረድ ነው ብለዋል። እዚህ ላይ በፖሊስና በአርቲስቶች መካከል ወይም በታዳሚዎች መካከል የኦነግ ጉዳይ መግባቱ ልብ ሊባል ይገባል።

የካቲት 10/2012 ደግሞ ሌላ እሮሮ ተሰምቷል። በኦሮምያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ አዲስ የኦነግን ጽሕፈት ቤት ለመክፈት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ፖሊሶችና የመከላከያ አባላት ተኩስ ከፍተው፣ አንድ ሰው ገድለው ሦስት ማቁሰላቸውን፣ የዐይን እማኞችንና የሟቹን እናት ያነጋገረው ቪኦኤ ዘግቧል።

የወረዳው አስተዳዳሪ ከእውቅና ውጭ ሊከፈት የነበረ የኦነግ ጽሕፈት ቤትን በሚመለከት የተዘጋጀን ስነ-ስርዓት ለማስቆም ሲሞከር በተፈጠረ ግጭት ተኩስ መከፈቱን፣ ሟችና ቁስለኛ መኖሩንም አምነዋል። ጥቃት አድራሾቹንና ተኩስ የከፈቱትን ሰዎች ማንነት ለማወቅም እያጣራን ነው ብለዋል። አስተዳዳሪው ይህን ቢሉም በስነ-ስርዓቱ ላይ ለመገኘት ከአዲስ አበባ ወደ ቦታው የተጓዙት የኦነግ ተወካይ ድርጅታቸው ሦስት ደብዳቤዎችን አዘጋጅቶ ለወረዳው አስተዳደር፣ ለወረዳው ፖሊስ እና አካባቢውን ለሚያስተዳድረው ቀበሌ መስጠቱን አውስተዋል። ማናቸውም አይቻልም ወይም አቁሙ የሚል ምላሽ እንዳልሰጧቸውም ተናግረዋል። የወረዳው አስተዳዳሪ ግን ማንም ምን ነገር እንዳላሳወቃቸው፣ ሰዎቹ እርስ በእርስ ተጠራርተው በምስጢር ጽሕፈት ቤቱን ሊከፍቱ መሆኑ ሲታወቅ ሕግ-አስከባሪወች ወደ ቦታው መሄዳቸውንና ግጭት መቀስቀሱን ተናግረዋል።

እንደየ አመጣጡ ማስተናገድ የሚለው አሰራር በኦሮምያ ለሚካሄዱ የዘፈቀደ እርምጃዎች በር ከፍቶ ሊሆን ይችላል። በዚህ ደግሞ ፍትሕ በየግለሰቦች እጅ ትወድቃለች። ካድሬው፣ ትልቁ ባለሥልጣን፣ ትንሹ ባለሥልጣን የማሰር የማሳደድ ብሎም የመግደል መብት ያገኘ ሊመስለው ይችላል። በዚህ መብቱ ደግሞ ሁሉም ምርጫውን ለራሱ በሚጠቅመው መንገድ ለመጠምዘዝ መሞከሩ አይቀሬ ነው። የመለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ በተካሄደው ምርጫ (ምርጫ 2007) ሕወሐት/ኢሕአዴግ መቶ-በ-መቶ የደፈነው ለዚህ ነው።

ሁሉም አለቃ የለኝም ባይ እና ራሱን የመለስ ዜናዊ ምትክ አድርጎ በመሾሙ ነው ተሸናፊ የታጣው። የወረዳዎች መለስ ዜናዊዎች፣ የአውራጃዎች መለስ ዜናዊዎች፣ የክልሎች መለስ ዜናዊዎችና የፌደራሎቹ መለስ ዜናዊዎች ተረባርበረው እያንዳንዱን የምርጫ ጣቢያ ሌላ ተወዳዳሪ በመቅረቡ ብቻ ጥፋተኛ ሆኖ የሚሸነፍበት ‘የዓድዋ ምርጫ ጣቢያ’ አድርገውት አረፉ። በቀጣዩ ምርጫስ ምን ይከሰት ይሆን?

ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here