‹‹አሁን ኢትዮጵያ ካለፈው የባሰ የሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ ነች ብዬ አላምንም››

0
1633

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ነበር ያገኙት። ቀጥለውም በ‹ዴቨሎፕመንት ስተዲስ› ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። በዚህ አላበቁም፣ ከኢንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በዓለም አቀፍና ሰብአዊ መብቶች ሕግ ኹለተኛ ዲግሪ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በመሥራት የዶክትሬት ማዕረግ ጭነዋል፤ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)።

ዳንኤል በተማሩበት የሕግ ሙያ አማካሪና ጠበቃ፣ በኅብረት ኢንሹራንስ የሕግ ክፍል ዳይሬክተር እንዲሁም አክሽን ኤይድ በተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የፖሊሲ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። በተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ውስጥ በአማካሪነት ሠርተዋል።

ከ1997 ምርጫ በኋላ ለእስር ከተዳረጉ ሰዎች መካከል የነበሩት ዳንኤል፣ ከእስር ከወጡ በኋላም የሰብአዊ መብት ተሟጋች በመሆን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ውስጥ አገልግሎት ሰጥተዋል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ከፍተኛ አማካሪ በኋላም የሂውማን ራይስት ዋች የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተር ነበሩ። አሁን ላይ ያሉበትን የሰብአዊ መብት ኮሚሽነርነት ኃላፊነትና ሥልጣን ሲረከቡ፣ በከፍተኛ የአደራ ስሜት እንደተረከቡ በተለያየ ጊዜ ገልጸዋል። የሰብአዊ መብት ጉዳይና ሙግት ለእርሳቸው እንግዳ ነገር ባይሆንም፣ ቦታው ላይ ሲቀመጡ ብዙ እንደሚጠባቅበቸው ሳይረዱ አልቀሩም።

አሁን ባሉት የኮሚሽኑ እንቅስቃሴዎች፣ በወደፊት ሐሳቦችና የኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታን በሚመለከት የአዲስ ማለዳው ተወዳጅ ስንታየሁ ከኮሚሽነሩ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን በሥራ ከተቀላቀሉ በኋላ፣ የገጠሞትና ያልጠበቁት ነገር ካለ፣ በጥሩ ወይም በመጥፎ?
አመሠግናለሁ። ውጪ አገር የነበረኝን ሥራ አቋርጬ ነው ለዚህ ሥራና ኃላፊነት የመጣሁት። ግን ያ ማለት ባለፉት ዓመታት ሁሉ ከኢትዮጵያ ርቄ ቆይቼ ነበር ማለት አይደለም። በሥራም በግል ምክንያትም እመላለስ ስለነበር፣ ያን ያህል ተራርቄ አልቆየሁም።

ወደ ኮሚሽኑ ሥራ ከመጣሁ፣ በተግዳሮት ደረጃ ባስቀምጠው፣ አንድ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ያገኘሁት፣ ከዚህ ቀደም በነበረው የፖለቲካ አስተዳደር የተነሳ የተቋሙ ብቃት ከምጠብቀውም በላይ አነስተኛ ሆኖ ማግኘቴ ነው። ይህ ደግሞ ለዚህ ተቋም ብቻ ሳይሆን ብዙ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ያለ ችግር ሊሆን ይችላል። አንደኛ ከነበረው የፖለቲካ ተጽዕኖ አንጻር፣ ኹለተኛ ብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከሚከተሉት አደረጃጀት፣ አወቃቀር፣ የሰው ኃይልና የገንዘብ ስርዓት አንጻር፣ ለአንድ ሥራ ብቃት ያላቸውን ሰዎች የሚስብና ለማቆየት የሚያስችል አይደለም።

ለአንድ ሥራ ደግሞ በጣም ወሳኝ የሚሆነው ለሥራው በቂ ትምህርት፣ በቂ ልምድና በቂ ዝግጅት እንዲሁም በቂ ዝግጁነት ያላቸውን ሰዎች መሳብና ሥራ ላይ ማቆየት መቻል ነው። ስለዚህ ተቋሙ ባለፉት ዓመታት ይህን ማድረግ አለመቻሉ አንዱ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ከዚሁ ተቋም ሳንወጣ፣ በዚህ በአስቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን ሙሉ ዝግጁነትና መሰጠት ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች አሉ። በውስን የሰው ሀብትና የገንዘብ አቅም፣ በአስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ሊሠሩ የሚገባውን የሰብአዊ መብት ሥራዎች ለመሥራት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች መኖራቸው፣ በኮሚሽኑ የሚያበረታታና ተስፋ የሚሰጥ ነው። እና ኮሚሽኑ ውስጥ ከተግዳሮትም ከመልካም አጋጣሚም አንጻር መጥቀስ እችላለሁ።

የበፊት ሥራዎ ሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት ነበር። አሁን ያሉበት ቦታ ደግሞ ችግሩን ማስተካከልም ይጠይቃል። ልዩነቱን እንዴት አገኙት?
እንዳልከው ከውጪ [ከመንግሥት መዋቅር ወጪ] ሆነህ ስለ ሰብአዊ መብት ስትሠራ፣ የሰብአዊ መብት ችግሮችን መመርመር፣ ማጣራት፣ መረጃ መሰብሰብ፣ ትንተና መስጠት፣ ከዛ ሊስተካከል በሚችለው የሚወሰድ የእርምጃ ሐሳብ ታቀርባለህ። አሁንም በተወሰነ መልኩ ሥራው ተመሳሳይነት አለው።

እርግጥ የምንሠራቸው ሥራዎች ሰፊ ናቸው። ሰብአዊ መብት ማስከበርና ማስፋፋት የሚል ነው። ስለ ሰብአዊ መብት የማስተማር፣ የማሳወቅ፣ ግንዛቤ የማስፋፋት፣ አቅም የመገንባት የመሳሰሉ ሥራዎች አሉ። የእስር ቤቶችን አያያዝ፣ የታሳሪዎችን መብት መከበር በቅርብ የመከታተል ሥራ አለ። አንዳንድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲኖር ደግሞ ያንን መመርመር፣ ማጣራት፣ ማስረጃ መሰብሰብ፣ ትንተና መሥጠት አለ።

ይህን ለየት የሚያደርገው፣ አንደኛ ለጉዳዩ ለችግሩና ለሁኔታው በጣም ቅርብ ትሆናለህ። በጣም ቅርብ ሆኖ መሥራት የበለጠ መረጃዎችን ለማግኘት እድል ይሰጣል። ኹለተኛ ለሚመለከታቸው አካላት የምትሰጠው ምክረ ሐሳብ አሁን ባለው አስተዳደር መደመጡ፣ ከዛም አልፎ ለእርምጃ መሠረት መሆኑ ያበረታታል።

ለምሳሌ አለአግባብ የታሰሩ ሰዎችን በሚመለከት ሊለቀቁ ይገባል የሚል ሐሳብ ስናቀርብ መንግሥት ያንን ምክረ ሐሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ ሲያደርገው ለማየት ችያለሁ። እስር ቤት ውስጥ መሻሻል የሚገባውን ሄጄ አይቼና ተመልክቼ፣ ይሄ መሻሻል ይገባል ብዬ ኃላፊዎችን ስናገር ለማሻሻል ፈቃደኛ ሆነዋል። በሕግ ማውጣት ሂደት ውስጥ፣ ሕግ አውጪዎች በሚያዘጋጁት ረቂቅ ላይ ሊስተካከል፣ ሊለወጥና ሊሻሻል ይገባል ብለን በምንሰጠው አስተያየት፣ ተቀብለው በዛ ሐሳብ መሠረት ሲያሻሽሉ አይተናል።

በክልል ያሉ መንግሥታትም ሲያማክሩን ሲያወያዩን ተመልክቻለሁ። ይህም ያበረታታል።

ይህን ሁሉ ያልኩት፣ በምንሠራው ሥራ ውጤት ለማግኘት የበለጠ እድል አለ። ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋም ውስጥ ስትሠራ አንዱ ትልቁ እድል፣ በሰብአዊ መብት ላይ ልትሠራ የምትፈልገው ነገር ውጤት ማምጣቱ ነው። መብት አያያዝ ላይ የእውነት ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ለማምጣት ነው የምትፈልገው። ስለዚህ ከዚህ አንጻር የሚያበረታታና ደስ የሚል ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

እነዚህ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች በዜጎች ጥቆማ ሊሠሩ የሚችሉ በመሆኑ ኮሚሽኑ በሕዝብ ተዓማኒነት ሊኖረው ይገባል። አሁን ያለው ኮሚሽን በሕዝብ የመታመን ደረጃው ምን ይመስላል?
እንደሚታወቀው ግልጽ በሆነ ምክንያት፣ ተቋሙ ከዚህ በፊት በነበረው ታሪክ የተዓማኒነትና የተቀባይነት ችግር የነበረበት ተቋም ነው። በፖለቲካ ቁጥጥር ስር ነበር፣ ነጻ አልነበረም፣ ውጤታማ ሥራ አልሠራም፣ ስለዚህ ተዓማኒነቱና ተቀባይነቱ በጣም ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቶ ነበር።

ለዚህ ተቋም ብቻ ሳይሆን ምንአልባት በብዙ ተቋማት ተመሳሳይ ነበር ማለት ይቻላል፣ ምርጫ ቦርድም ይሁን ሌሎችም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ጭምር ማለት ነው። እና አዲስ በተጀመረው የፖለቲካ ምዕራፍ የታየው የፖለቲካ ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት እነዚህን ተቋማት ለማሻሻልና ለመለወጥ ነው።

ከዛ አንጻር ገና አንድ የመጀመሪያ እርምጃ ተወሰደ እንጂ ሥራው አልተጠናቀቀም። ለዚህ ኮሚሽን አዲስ አመራር መሰየም ጥሩ ነው፣ ግን የኮሚሽኑ ተዓማኒነት መረጋገጥ መቻል ያለበት በሥራው ነው። እና ያ ደግሞ ገና ነው። በእርግጥ እኔ ወደዚህ ሥራ ከመምጣቴ ጋር በተያያዘ፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን እህቶችና ወንድሞች ድጋፋቸውን ገልጸውልኛል። ያ ያበረታታል። በእለት ተእለት ሥራ ሂደትም ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በማደርገው ግንኙነት የተሻለ ቀና ስሜት እንዳላቸው እረዳለሁ።

ግን ገና ሥራችንን አጠናቀን አልጨረስንም። ያ ማለት ኮሚሽኑ አሁን ባለበት ሁኔታ የማስፈጸም አቅሙ የተዳከመ ስለሆነ፣ ስር ነቀል ለውጥ ማካሄድ አለብን፣ መዋቅሩ ላይ ለውጥ መደረግ አለበት። ስርዓቶች መቀየር አለባቸው። የአሠራር ባህል መቀየር አለበት። ብዙ መለወጥ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ለምሳሌ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ራሱ መሻሻል መለወጥ አለበት። አሁን እሱን እየሠራን ነው።

መሻሻል የሚገባቸው ነጥቦች ላይ መሻሻያ እየሠራን ነው። ከዛ ደግሞ አዲስ ኮሚሽነሮች ምርጫ መካሄድ አለበት። ኮሚሽኑ ውስጥ ያለሁት ኮሚሽነር እኔ ብቻ አይደለሁም፤ ሌሎችም አሉ። የእነርሱ የአብዛኛዎቹ የአገልግሎት ዘመናቸው እያበቃ ስለሆነ፣ ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ ለማዋቀር ከተፈለገ፣ ከሐሳብ ጋር አብሮ በሚሄድ መልክ አዲስ ኮሚሽነሮች ምርጫ መደረግ አለበት።

ምርጫው እንደ በፊቱ ሳይሆን፣ በደንብ በሙያና በሙያ ዝግጅት፣ በትምህርት ዝግጅት፣ በሥራ ልምድ በጉዳዩ አስፈላጊ የሚሆኑ ሰዎችን፣ ግልጽ በሆነ የምርጫ ሂደት እናስመርጣለን ብለን እናስባለን። ስለዚሀ አዲስ ኮሚሽነሮች እናገኛለን። ከዛም የድርጅቱን መዋቅር ለሥራው አመቺ በሚሆን መልኩ እንቀይራለን። ያ እንግዲህ የሰው ኃይል ስርዓቱን በአዲስ መልክ መሥራት ማለት ነው።

በተለይ ሠራተኞችን ለመሳብና ለመያዝ እንቅፋት ሆኖ የነበረውን የክፍያ ስርዓታችንን እንፈትሻለን/ እናስተካክላለን። እንዲሁም ኮሚሽኑ ውስጥ ያሉትን ሠራተኞች አቅም እንገነባለን። ይህን ሁሉ በማድረግ ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈጸም የሚያስችል ብቃት ያለው ቁመና እንዲኖረው መስጠት ማለት ነው። አቅም መፍጠር አለብን። አንድን ሥራ ለመሥራት የተቋም አቅም ያስፈልጋል። ያንን አቅም ከፈጠርን በኋላ ወደ ሥራ ገብተን በምናሳየው ውጤት፣ የኮሚሽኑ ተዓማኒነትና ተቀባይነት እየጨመረ ይሄዳል ብዬ አምናለሁ።

ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታም ቢሆን፣ እንደ በፊቱ ሳይሆን እስረኞችን ሄደን በመጎብኘት፣ አንዳንድ በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊ አስተያየታችንን በመስጠት፣ በሕግ መሻሻል ሂደት ጠቃሚ ተጽዕኖ በማሳደርና በመሳሰለው በምናደርገው አስተዋጽኦ፣ ስለኮሚሽኑ ያለው አስተያየት ከዚህ በፊት እንደነበረው እንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። የማገኘው ግብረ-መልስም እንደዛ ነው። ስለዚህ ያ ያበረታታኛል። ግን እጅግ በጣም ይቀረናል።

አሁን ላይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አለመረጋጋቶች ሲከሰቱ ይታያል፤ በአብዛኛው ግን መንግሥት በቸልታ ነው የሚያየው። ከዚህ ጋር በተያያዘስ በኮሚሽኑ ምን ያህል ወቅቱን የጠበቀ ሪፖርት እየወጣ ነው?
አሁን አንዱ ትልቁ ችግራችን እንዳልኩት የተቋሙ አቅም በዛ ደረጃ ስላልሆነ፣ ይህን ያህል ትርጉም ያለው ሪፖርት እያወጣን አይደለም። እያወጣን ያለነው በፈጣን ዳሰሳ ጥናት ምክንያት የደረስንባቸውን አንዳንድ ግኝቶች ወይ በሚድያ ኢንተርቪው ወይም በጋዜጣዊ መግለጫ ዓይነት እናሳውቃለን፤ እንጂ የተሟሉ ሪፖርቶች ገና በአግባቡ መውጣት አልተጀመረም። እኔም ይህን ሥራ ከጀመርኩ አምስትና ስድስት ወር ላይ ነው ያለሁት።

እና ለምክር ቤቱም ባቀረብነው ሪፖርት፣ በአብዛኛው ስለ ሰብአዊ መብት ያለንን ግምገማ እና መደበኛ ሥራዎቻችን በሚመለከት፣ በየቀኑ የሚመጡ በየቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻችን በኩል ጭምር የሚመጡ አቤቱታዎች አሉ፣ እነዛን እንመረምራለን፣ የመፍትሄ ሐሳብ እናሰባስባለን፣ አንዳንዶቹም ላይ መፍትሔ እናፈላልጋለን።

እንዲህ ያሉ ምርመራዎች ይካሄዳሉ፣ ቶሎ ቶሎም ይስተናገዳሉ። ግን አንዳንድ ትልልቅ ግጭቶች ጋር የተያያዘ ሁኔታን ሄዶ በወቅቱ መረጃውን ሰብስቦና አጣርቶ ሪፖርቶችን ማዘጋጀት በሚመለከት፣ ገና ነው። የዚህ ዓይነት ብቃት በደንብ አልተገነባም ማለት ይቻላል። ግን በመንግሥት በኩል፣ ቸልተኝነት ወይ ግዴለሽነት ያለ አይመስለኝም።

አላውቅም፤ ከውጪ ስትመለከተው እንደዛ ሊመስል ይችላል። እኔ እንደታዘብኩት ግን ችግሮች ሲከሰቱ የማነጋግራቸው የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ይህን ቸልተኝነት አላይም። ይልቁንም ጉዳዩ አሳስቧቸው ጥረት ሲያደርጉ እመለከታለሁ።

ለምሳሌ ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ስንመለከት፣ እውነት ለመናገር በእነዛ ቦታዎች ላይ በተለይ የፌዴራል ጸጥታ አስከባሪዎች፣ በወቅቱ ወደ ቦታው ሄደው ምላሽ ባይሰጡና ሁኔታዎችን ባያረጋጉ ኖሮ፣ አንዳንድ ግጭቶች የባሰ የከፋ ሊሆኑ ይችሉ ነበር። ከማነጋግራቸው ሰዎች በማገኘው ምላሽ፣ በአካባቢያቸው የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት ዋነኛ ግብዐት ብለው የሚወስዱት የፌዴራል ጸጥታ አካላት በቦታው መሰማራታቸውን ነው።

ይህን ብዙ ቦታ አይቼዋለሁ። በአፋርና ሶማሌ ክልል፣ በኦሮምያ፣ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ክልል በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ቀደም ብሎ በተከሰተው ችግር በተያያዘ፣ አብዛኛው ግጭት የተፈጠረባቸው ቦታዎች ላይ፣ ጉዳዩ ከክልሉ የጸጥታ አስከባሪ ኃይል በላይ ሲሆን፣ እንደውም የፌዴራል ጋር መሄዳቸው ነው ነገሩን ለማረጋጋት ሲረዳ የማየው። ያ ቸልተኝነት አይደለም። እንደውም በኃላፊነት ስሜት ቶሎ መልስ የመስጠት ነገር አለ።

አብሬ የምታዘበው ችግር ግን፣ የአቅም ውስንነት አለ። በፖሊስ ይባል በፌዴራል ሠራዊት ወይም በዐቃቤ ሕግ፣ በጣም የአቅም ውስንነት አለ። በውስን አቅም ስለሆነ የሚሠራው፣ ያለው የማኅበራዊ አገልግሎት ፍላጎት መጠንና መንግሥት ተደራሽ እያደረገ ያለበት አቅም ብዙ ጊዜ አይገናኝም። ያ ትልቅ ችግር ይመስለኛል።

ኹለተኛ ደግሞ አንዳንዴ ጸጥታ በማስከበር ሂደት ውስጥ፣ የሕግ ማስከበር ሥራው ከታቀደለት ዓላማ አልፎ ይሄድና ለሰዎች ያለአግባብ ሕይወት መጥፋት፣ መታሰርና አለአግባብ መጉላላት ምክንያት ሲሆን ተመልክተናል።

ከዚህ በቀር ቸልተኝነት አይመስለኝም። ሌላው ትንሽ ክፍተት ግንኙነት ላይ ነው። አሁን የመንግሥት የኮምዩኒኬሽን አሠራር የተቀየረ ይመስለኛል። እንደ ድሮው በአንድ ማእከል አይመራም። በአንድ ማእከል ባለመሆኑ፣ በሚገባው መጠን እና ፍጥነት የኮምዩኒኬሽን ሥራ የሌለ ይመስለኛል።

በዛ ላይ ያለመናበብም እየተፈጠረ አንዳንዴ የተጋጩ መረጃዎችም ሊደመጡ ይችላሉ። ከዛ በተረፈ ሙሉ ቸልተኝነት አይመስለኝም። እኛም በተቻለ መጠን ጥረት የምናደርገው መንግሥት የሚገባውን ትኩረት እንዲሰጥና በየጊዜውና ወቅታዊ በሆነ መልኩ ለችግሮች መፍትሄ እንዲፈልጉ ማበረታታችንን እንቀጥላለን።

የፌዴራል ፖሊሶች በተላኩበት ትዕዛዝ አልመጣልንም በሚል፣ ጥፋት ሲደርስ እየታየ ምንም ምለሽ ሳይሰጡ የታዩበት ግጭት አለ። በአንጻሩ ለተወሰኑ ጉዳዮች ደግሞ ፈጣን ምላሽ መስጠት ይታያል። ለአንዱ ጉዳይ ለመገናኛ ብዙኀን መግለጫ ሲሰጥ ሌላው ደግሞ ምንም ሳይባል ያልፋል። በዚህ ሁኔታ የኮምዩኒኬሽን ችግር ነው ማለት አያስቸግርም?
ገብቶኛል። የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ለምንድን ነው በዚህ መልክ እየሠሩ ያሉት የሚለውን ራሳቸው መልስ መስጠት ይኖርባቸዋል። እንዳልኩት ግን እኔ በምመለከተው ሐሳብ፣ ፍላጎትና ጥረት እንዳለ አያለሁ። ግን በሚፈለገው መጠን እንዳልሆነ እኔም እስማማለሁ። እናንተም እንደ ሚድያ ጫና መፍጠር አለባችሁ። በዛ መልክ ነው እየተሻሻለ የሚሄደው።

በሌላ መልኩ ደግሞ ትንሽ ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባው ነገር፣ አሁን በመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች መካከል ብዙ አሳሳቢ ነገር እጃቸው ላይ ሲኖር፣ ለየትኛው ቅድሚያ እንደምትሰጥ ይቸግር ይሆናል። ብዙ ጉዳይ ሲኖርብህና ያለህ ሀብት፣ ጊዜና አቅም የተወሰነ ሲሆን፣ በሁሉ ነገር ላይ በምትፈልገው መጠን ላትሠራ ትችላለህ።

በሌሎች አገራት መንግሥት ሰፊ አቅም አለው። ለሁሉም ጉዳዮች የሚሠሩ ሰዎች ይኖራሉ። አቅም ውስን ሲሆን ግን፣ ለምሳሌ የእኛን ኮሚሽን እንውሰድ። ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ አቅም ቢኖር ኖሮ ብዙ የምንሰማቸው ጉዳዮች ላይ በወቅቱ ምርመራ ማካሄድ፣ መወሰድ የሚገባውን እርምጃ መውሰድ ይገባን ነበር። ነገር ግን ያንን ለማድረግ ሳንችል አንቀራለን። ምክንያቱም ያለው አቅም ውስን ነው።
ይህ ስለሆነ የምትመልስበትን ጉዳይ ለመምረጥ ትገደዳለህ። ግን በተቻለን መጠን፣ በተለይ ከሚድያ ጋር እኔም በግሌ፣ ሚድያዎችን በማግኘት ቢያንስ እየሠራን ያለውን፣ ያገኘነው ግኝት ወይም የገጠመን ችግር ካለም ያንን ለማሳወቅ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት እናደርጋለን። ሌሎች መሥሪያ ቤቶችም እንደዚህ ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ሪፖርቶችን በየጊዜው ይፋ እንዳታደርጉ የአቅም ችግር አለ ብለዋልና፣ ያንን ለማስተካከል ምን እየተሠራ ነው?
የተቋሙን አቅም ለመሻሻል መጠነ ሰፊ ጥናት ስናደረግ ቆይተናል። ይህ ጥናት በእኛ ብቻ የሚሆን አይደለም። ብሔራዊ ሰብአዊ መብት ኮሚሽኖች በሁሉም አገራት አሉና፣ በዓለም አቀፍና በአኅጉር ደረጃ ከአገራት ተመሳሳይ ልምድ ለማግኘትና የእኛንም እንዴት ማሻሻል እንደምንችል በእውቀት ላይ የተመሠረተ የአቅም ግንባታ ሥራ ለመሥራት ባለሞያዎች አግኝተን፣ ከውጭ አገር፣ ከአፍሪካ ውስጥና ከአውሮፓ ካሉ የአገር ውስጥ ባለሞያዎችም የተውጣጡበት፣ ኮሚሽኑም የተሳተፈበት የአቅም ፍላጎት ምን እንደሆነ ለይቶ ማውጣት የሚያስችል ጥናት ነው።
ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም፣ ግን ዋና ዋና ግኝቶች አሉን። ይህም የአቅም ፍላጎቶቹ በምን ዘርፍና በምን ጉዳዮች ላይ እንደሆኑ ለይቶ የሚያመለክት ነው።

አሁን ያንን ጥናት እያጠናቀቅን ነው። በዛ መሠረት አቅም ለመገንባት የሚያስችል እቅድ ነድፈን ሥራ ላይ እናውላለን። ከዚህ ሥራ ውስጥ አንዱ መከናወን የሚገባው የተቋሙን የማቋቋያ አዋጅ ማሻሻል ጭምር ነው። ይህ ያስፈለገበት ምክንያት ኮሚሽኑ ነጻ ተቋም ሆኖ ቢቋቋምም፣ በጀቱና የሰው ኃይል አስተዳደሩ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ነው። ይህ ተቋሙ ነጻ እንዳይሆን እንቅፋት ይፈጥርበታል።

በዚህ አዋጅ ማሻሻያ የምናደርገው ተቋሙ የአሠራር፣ የፋይናንስ፣ የአደረጃጀት፣ የሰው ሀብት አስተዳደርም ነጻነቱ እንዲረጋገጥለት ነው። ከዛም በምናወጣው እቅድ መሠረት የሰብአዊ መብት የማስፋፋት የመጠበቅ መጠነ ሰፊ ሥራ እንሠራለን።

ይህን ለማድረግ ደግሞ አገር ውስጥ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተመካከርን ነው። ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ማጠናከር እኛ ለብቻችን የምንሠራው ስላልሆነ። ሌላው ለዚህ ሥራ ሊያግዙን የሚችሉ ዓለማቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ አገራትና መንግሥታት፣ የተባበሩት መንግሥታት ጭምር፣ የአውሮፓ ኅብረትን የመሳሰሉ ድርጅቶችንም እያነጋገርን፣ ከእነርሱ የቴክኒክና የፋይናንስ እገዛ እያፈላለግን ነው።

ሌላው አገር ውስጥ ያሉና ለዚህ ሥራ ሊረዱ የሚችሉ ኢትጵያውያን ባለሞያዎችን ወደዚህ ሥራ ለመሳብ ጥረት እያደረግን ነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፣ በዚህ ሥራ ላይ ቢሰማሩ ጥሩ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ። ስለዚህ እንዲህ ያሉ እያከናወንናቸው ያሉ ሥራዎች አሉ። እነዚህም በጠቅላላው የተቋሙን አቅም መገንባት እና ትርጉም ያለው ውጤታማ የሆነ ሥራ ውስጥ በፍጥነት መግባት በሚል ነው።

የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች አዲስ አበባ ላይ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ማለት ይቻላል። ጥያቄዎችም ቀርበው የተከለከሉበት ሁኔታ አለ። እነዚህ ዓይነት ነገሮችን ለማቆም ምን ሠራችሁ?
ትክክል ነው። ይህ ችግር አዲስ አበባ ከተማ ላይ ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልሎችም ያለ ነው። እንዳልከውም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው። በተለይ የመሰብሰብ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ከማድረግ መብት ጋር በተገናኘ፣ በተደጋጋሚ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ችግሮች ታይተዋል። በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች በጸጥታ ኃይል አንዳንዴም በተደራጁ ቡድኖች ሲሰናከሉ አይተናል።

በአጠቃላይ በሰላማዊ መንገድ መሰብሰብ መብት ላይ በተደጋጋሚ እንቅፋት ሲፈጠር ተስተውሏል። ይህ የሚያሳዝን ክስተት ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ለምርጫ እየተዘጋጀች እንደመሆኑ፣ በጣም ሊከበር የሚገባ ሰብአዊ መብቶች ውስጥ አንዱ በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ የመንቀሳቀስ፣ በፖለቲካ የመሳተፍ ወሳኝ መብቶች ናቸው።

እነዚህ መብቶች አደጋ ላይ እየወደቁ ከመጡ አሳሳቢ ነው የሚሆነው። የዚህ ምልክቶች እየታዩ ስለሆነ፣ ከአሁኑ ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ ነው። እኔም ያሳስበኛል። አንዳንድ እቅዶችም አሉን። በተለይ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጋር በቀጥታ ተገናኝተን መነጋገርና መወያየት እንዳለብን ይሰማኛል። ምንአልባት የተሳሳተ የሕግ አተረጓጎም ወይም የግንዛቤ እጥረት ያለባቸው ጉዳዮች ላይም እንዲታረሙ ምክር መስጠትና ማስተካከል ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል።

ለምሳሌ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ማንኛውም ሰው ለሰላማዊ ጉዳይ አንድ ቤት ውስጥ ለመሰብሰብ ምንም ዓይነት ፈቃድ አያስፈልገውም። የቤት ውስጥ ስብሰባ ፈቃድ አያስፈልገውም። ግን አንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገጥማቸው ችግር፣ ቤት ውስጥ ወይም ሆቴል አዳራሽ ተከራይተው ለሚያደርጉት ስብሰባ፣ ፈቃድ ካላመጣችሁ እየተባሉ ችግር ይገጥማቸዋል። ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። ቤትህ ውሰጥ ለምታደርገው ስብሰባ ፈቃድ ማውጣት አለብህ የሚል ሕግ የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ከመሠረታዊ የሰብአዊ መብት ጋር የሚጻረር አሠራር ነው።

ሰላማዊ ሰልፍን በሚመለከት ቢያንስ አስቀድሞ ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ የሚያላክት ሕግ አለ። ያ ሕግ ራሱ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችና ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጋር የተጣጣመ ነው አይደለም የሚለው አከራካሪ ነው፤ የተጣጣመ ነው ተብሎም አይታመንም። ያ ሕግ ራሱ እንዲሻሻል የተጀመረ ሂደት አለ። ለዛም ራሱን የቻለ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር የተቋቋመው የሕግ አማካሪዎች ስር ያለ ቡድን ያንን ሥራ እየሠራ ነው። ይህ ጥሩ ነው። አንድ ውጤት ላይ ቶሎ ይደረሳል ብዬ አስባለሁ።

ግን እስከዚያም ቢሆን በኢትዮጵያ አሁን በተፈጠረው የፖለቲካ ምዕራፍ እና በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ እነዚህን ሕጎች የሚያስፈጽሙና የሚያስተዳድሩ አካላት በሙሉ፣ ሕጉን በዚህ መንፈስ መተርጎም አለባቸው። ሕጉ ለማሰናከል ሳይሆን ለማስተባበር፣ ለማሳለጥ ለማገዝ ነው መሆን ያለበት እንጂ፣ ለመከልከል መሣሪያ መሆን የለበትም። በዚህ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ስለሚያስፈልግ፣ ጥረት እያደረግን ነው። ቀስ እያልንም ይህን ግንዛቤ እንፈጥራለን ብዬ አስባለሁ። ግን ገና ብዙ ሥራ ይቀራል።

በክልሎች የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤቶች አቅም ምን ይመስላል?
በክልሎችም ተመሳሳይ ነው። በየክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉን፣ እነርሱም የዚህ መሥሪያ ቤት አካል ናቸው እንጂ የተለየ ሕልውና የላቸውም። እና በሁሉም ክልሎች ብቻ ሳይሆን ወደፊት በብዙ ከተሞችና አስፈላጊ በሆነ ቦታ ሁሉ ብዙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ይኖረናል።

የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዋነኛ ዓላማ አገልግሎት ለምንሰጠው ሕዝብ ተደራሽ ለመሆን ነው። ለምሳሌ አቤቱታ ማቅረብ የሚፈልግ ሰው፣ አዲስ አበባ ድረስ መምጣት ሳያስፈልገው በአቅራቢያው አቤቱታ የሚያቀርብበት ቦታ እንዲያገኝ ነው።

ግን እንዳልኩት ዋናው መሥሪያ ቤት ሆነ ቅርንጫፎቹ በውስን አቅም ነው የሚሠሩት። አቅም ገና ረጅምና ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ይሄ በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያለ ችግር ሊሆን ይችላል። ግን የተቋማት አቅም እና ብቃት ውስን ስለሆነ፣ መሠረታዊ የአቅም ግንባታ ይፈልጋል።

ነገር ግን ከክልል መንግሥታት ጋር ባለን ግንኙነትና በሄድኩባቸው አጋጣሚዎች፣ በነበረን ንግግርም፣ እስከ አሁን አዎንታዊ መልስ ነው የምመለከተው። ለምሳሌ ድንገተኛ ጉብኝት እናካሂዳለን። እኔ ራሴ ሄጃለሁ።አልከለከሉንም፣ ተቀብለውናል፣ አስገብተውናል። የእስር ቤቶች ውስጡን ለማየት ችለናል። ሐሳብ ስንሰጥም ሐሳባችንን ሲቀበሉና አንዳንድ ቦታዎች ሥራ ላይ ሲያውሉ ተመልክተናል። ያ ያበረታታኛል።

የሰብአዊ መብት ሁኔታውን መሬት ላይ ምን ያህል በተግባር እየቀየረው ነው ለሚለው፣ ገና ነው። ግን አንዳንድ ትንንሽ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች አሉ ማለት ይቻላል።

ለተጋላጭ ቡድኖች የተለየ ትኩረት እንደምትሰጡ ይታወቃል። እነዚህ ተጋላጭ ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? በየጊዜውስ ተቀያያሪ ናቸው?
እውነት ነው። ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብለን የምናስባቸው አሉ። እነዚህ ክፍሎች ለምሳሌ ሴቶች ወይም ሕጻናት፣ የአካል ጉዳተኞች ሊሆኑ ይችላሉ። አልያም አንድ ብሔር፣ ሃይማኖት ወይም መሰል ቡድን በብዛት ካለበት ቡድን ውስጥ አነስ ያሉ የተለየ ብሔር፣ ሃይማኖትና መሰል ያላቸው ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሚባሉት ቡድኖች ከቦታ ቦታና በሁኔታ ይለያያሉ።

በአጭሩ ግን ከቡድኑ ጠባይ እና ከጠቅላላ አገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የተነሳ፣ ለመብት ጥሰት ከሌላው ኅብረተሰብ ክፍል የበለጠ ተጋላጭ የሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለት ነው።

በዚህ ሁኔታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በዚህ ማካተት አይቻልም?
ትንሽ ያከራክራል። በሰብአዊ መብት አውድ በተለምዶ ተጋላጭ የምንላቸው ውስጥ ያንን አይጨምርም።

በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በየጊዜው ያታሰራሉ፣ ይገደላሉ፣ ቢሯቸው የተዘረፈ እንዳለም ሪፖርት ተደርጓል። እንዲህ ያሉ ነገሮች ስናይ አባላቱን በተጋላጭ እንዲካተቱ አያደርግም?
እንዳልኩት በተለምዶ በሰብአዊ መብት ጽንሰ ሐሳብ ተጋላጭ ማኅበረሰብ ውስጥ አንከታቸውም። አሁን ባልከው አተረጓጎም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ ለሕዝብ ሐሳብን የሚገልጹ ሰዎች፣ሰብአዊ መብት ታጋዮችና ተሟጋች የሚባሉ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ሠራተኞች፣ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና አባላት ተመሳሳይነት አላቸው። በተለይ የፖለቲካ ከባቢው ምቹ ባልሆነበት አገር፣ ተጋላጭነታው ይጨምራል።

ከሥራቸው ጸባይ የተነሳ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭነታቸውን ግን እውቅና እንሰጣለን። በሥራው ምክንያት የመብት ጥሰት ሲደርስባቸው ቶሎ ትኩረት ሰጥተን ለማጣራት ጥረት የምናደርገውም ለዚህ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታ ያለው ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው። እናም ችግሩን ተጋፍጠው የሚሠሩ ናቸው። ስለዚህ ያንን እየሠሩ በሚደርስባቸው ችግር ምክንያትም ልዩ ጥበቃ ስለሚያስፈልጋቸው፣ በዛ መንፈስ የተለየ ትኩረት እንሰጠዋለን።

የሰብአዊ መብት ጥሰት ከመከሰቱ በፊት ሊጠቁሙ የሚችሉ ምልክቶች ይኖራል። ለምሳሌ የሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ከመካሔዱ በፊት ብዙ ቆንጨራ ወደ አገሪቱ ሲገባ ነበር። ያንን ቀድሞ ለማስቆም ቢሞከር ጥፋቱን መቀነስ ይቻል ነበር። ጥሰቶች ከመከሰታቸው በፊት በእናንተ በኩል የመከላከል ሁኔታችሁ ምን ይመስላል?
የሰብአዊ መብት ክትትል እና ጥበቃ ሥራ ሰብአዊ መብት ተጥሶ ሲገኝ ሔዶ መዘገብና ሪፖርት ማድረግ ሳይሆን ዋነኛ ዓላማው የሰብአዊ መብት ጥሰትን መከላከል ነው። የዚህ ኮሚሽን ኃላፊነት በጠቅላላው ሰብአዊ መብቶችን ማስፋፋት እና መከላከል ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። በማስተማርም ይሁን በሌሎች የመከላከል ሥራዎች የሚከናወነው የተከሰተውን ጥሰት የማረምና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ እንዲሁም የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያ ተግባር የሚፈለገው ውጤት የሰብአዊ መብት ጥሰት ወደ ፊት እንዳይከሰት ለመከላከል ነው።

ስለሆነም ስለ ሰብአዊ መብት ስናስተምር፣ ምርመራ ስናደርግ፣ እስር ቤቶችን ስንከታተል፣ ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብት ክትትል ስንሠራ፣ ዓላማው አንዳንድ መረጃዎችን አስቀድሞ በማግኘት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስቀድሞ ለመከላከል፣ ምክረ ሐሳብ ለመስጠት እና መረጃው ለሚመለከታቸው ወገኖች ለማሳወቅም ነው። በመሆኑም የሥራችን ዓላማ የሰብአዊ መብት ጥሰትን ቢያንስ ለመቀነስ ቢቻል ሙሉ ለሙሉ ለመከላከል ነው።

ከማስተማሩ ውጪ የመከላከሉ እንቅስቃሴዎች ምን ምንን ያካትታሉ?
መከላከሉ አንደኛ የሚቀርቡትን አቤቱታዎች መመርመር እና መፍትሔ መስጠትን ያካትታል። ሰብአዊ መብቴ ተጥሶ በዚህ ሁኔታ ላይ ነኝ የሚል ሰው ሲኖር፣ የመከላከል ሥራው ይህንን ሁኔታ መቀልበስና ያላግባብ የታሰረ ከሆነ ማስለቀቅ፣ ያጠፋ ሰው ካለ ማስጠየቅ ነው። ኹለተኛው ጥሰቱ ሳይደርስ በፊትም መከላከል ነው። ለምሳሌ በምናካሂደው ክትትል የእስር ቤት አያያዝ ሁኔታ የእስረኞችን ሰብአዊ መብት እንዳይጥስ በዝቅተኛ መስፈርትነት ያሉት ነገሮች እንዲሟሉ ይሠራል።

ለእኛ በሚቀርብልን አቤቱታ ብቻ ሳይሆን በራሳችን አነሳሽነት ምርመራ እናካሂዳለን፣ እናጣራለን፣ አጥፊዎች እንዲጠየቁ እናደርጋለን። የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመፈጸም ምክንያት የሆነው ፖሊሲ ወይም ሕግ ሊሆን ይችላል፤ ያ ደግሞ እንዲሻሻል ምክረ ሐሳብ እንሰጣለን።

ማስተማሩ የሰውን ግንዛቤ ስለሚቀይር ጥሰቱ ከመከሰቱ በፊት የሚደረግ ነው። ቁጥጥሩም ከጥሰት በፊት የሚደረግ ነው። ነገር ግን ቆንጨራ መግዛት ዓይነት ነገሮች ተግባራት ናቸው። እነዚህን ለመከላከል የምትሠሯቸው ሥራዎች አሉ?
አዎ በትክክል እንሠራለን፣ መሥራትም አለብን። ምክንያቱም ለሰብአዊ መብት ጥሰት አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል የፖለቲካ ሁኔታ ሲከሰትም ሆነ የቅስቀሳ ንግግሮች ሲደረጉ ወይም ሰፊ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊያስከትሉ የሚችሉ ዝግጅቶች ከታዩ መመርመር፣ መጣራት እና ቶሎ ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ መወሰድ አለባቸው። ተገቢው ጥናት፣ ምርመራ እና ምክረ ሐሳብ መሰጠት አለበት።

አሁን ያልከውን ነገር ሰምቻለሁ። አንድ ወቅት ተከስቶ የነበረ ነገር ነው። ከዚያም የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች እርምጃ ወስደዋል የሚባል ነገር አለ። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ነገር ሲከሰትም ቢሆን ምርመራ ማድረግ ይጠይቃል። ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊያስከትል የሚችል የወንጀል ሥራ ዝግጅት አለ የሚባል ከሆነ፣ ወንጀሉን የመከላከል ኃላፊነት የፖሊስ ስለሆነ የእኛ ሚና የሚሆነው ያገኘነውን መረጃ ለመንግሥት የፀጥታ አካላት መስጠት ነው።

ከቆንጨራ ጋር የተያያዘ ያነሳኸው ነገር ሰፋ ያለ ጥሰት የሚያስከትል ቢሆንም የወንጀል ዝግጅት ማለት ነው። ይህ ደግሞ ያስጠይቃል። ወንጀልን ለመከላከል የሚሠራውም ክፍል ደግሞ ኃላፊነቱን ለመወጣት መሥራት አለበት። ከዚያ ያለፈ ደግሞ በንግግር የሚደረግ፣ ወደ ግጭት ሊመራ የሚችል እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊያስከትሉ የሚችሉ ንግግሮች በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሊኖር ይችላል።

ስለዚህ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። ደጋግሜ እንዳልኩት ኮሚሽኑ አሁን ባለበት ሁኔታ አቅሙ ውስን ስለሆነ ነው እንጂ በርካታ ክትትል ሊደረግባቸው የሚገቡ ዘርፎች እንዳሉ ይታየኛል። እናንተ ጋዜጠኞች ለምሳሌ በሥራ አጋጣሚ ልታገኟቸው የምትችሏቸው መረጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እነዚያን መረጃዎች በበለጠ መመርመር ማጣራት ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አቅም መፍጠር ነው ሕልማችን፣ እየደከምን ያለነውም ለዚሁ ነው።

በተለይ ኦሮሚያ፣ ትግራይና አማራ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቡድኖች ሕጻናትን መሣሪያ በማስታጠቅ ወይም በማሠልጠን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እያስገቡ ነው። በዚህ ረገድ የሕጻናቶችን መብት ለመጠበቅ በተለይ በእነዚህ ክልሎች ያሉት የእናንተ ቢሮዎች ምን እየሠሩ ነው?
ይሔ ቅድም ካነሳኸው ጋር ይያያዛል። ልጆች ለዚህ ዓይነት የመብት ጥሰት ተጋላጭ ይሆናሉ። በተለይ የታጠቀ ቡድን የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች፣ አንዳንድ ጊዜም ከዚያ ውጪ የሆኑ ቦታዎች ልጆችን ወደ ጦርነት ለማሰማራት የሚደረግ እንቅስቃሴ ካለ “ሕጻናት ወታደሮች” ማሰማራት በዓለም አቀፍ ሕግ እጅግ በጣም የተወገዘ እና የሚያስጠይቅ ከባድ ወንጀል ነው። ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ከባድ ወንጀል ነው። ይህንን ያደረጉ ሰዎችም ለሕግ ሊቀርቡ ይገባል።

አሁን እስካለኝ መረጃ ልጆችን በቀጥታ ጦርነት ውስጥ የማስገባት የተስፋፋ ችግር አለ ባይባልም፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ይህን ዓይነት አዝማሚያ መኖሩ አሳሳቢ ነው። እድሜያቸው አነስተኛ የሆኑ ልጆች አንዳንድ ቦታ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ቡድኖችን ተቀላቅለው ታይተዋል የሚሉ መረጃዎች አሉ። ይህ በጣም አሳሳቢ ነው። ታጥቀው ከመንግሥት ኃይል ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ቡድኖች ቢሆኑም በዚህ ላይ የተሰማሩትን ሰዎች ሊደረግ የሚገባው ነገር መያዝ፣ መቆጣጠር እና ሕግ ፊት ማቅረብ ነው። ከትጥቅ ትግል ውጪ በሆነ ሁኔታም ቢሆን ልጆችን ለዚህ ዓይነት ነገር መጠቀም ተገቢ ነገር አይደለም። ለጨዋታ በሚመስል ነገርም ቢሆን ልጆችን ጦርነት ውስጥ እንዳሉ አድርጎ እዛ ስሜት ውስጥ መክተት ተገቢ ነገር አይደለም።

በዚህ ረገድ በየክልሎች ያሉ ቢሮዎች ምን እያደረጉ ነው?
ክትትል ለማድረግ ጥረት ይደረጋል። ቅድም እንዳልኩት በጣም ብዙ ዓይነት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ነው ያሉት። ሁሉም ላይ በሚፈለገው መጠን መልስ ሰጥተናል አልልም። ነገር ግን በምናያቸው እና በምንታዘባቸው ችግሮች ላይ ሁሉ ባገኘነው አጋጣሚ ለሚመለከታቸው ሰዎች ሁሉ መልዕክት ለማስተላለፍ እና እርምት እንዲደረግ ለማድረግ ጥረታችንን እንቀጥላለን።

ከለውጡ በኋላ በሰብአዊ መብቶች ረገድ መሻሻሎች እንዳሉ ከቪኦኤ ጋር በነበረዎት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር። አሁን ላይ ግን ወደኋለእ እየተመለሰ እንደሆነ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ዳይሬክተር ፍስሃ ተክሌ ለአዲስ ማለዳ ገልጸው ነበር። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ይሔ የእኔ እና የጓደኛዬ የፍስሃ አስተያየት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሰው አስተያየት ይመስለኛል። በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አስተያየት እንደሚነሳ አውቃለሁ። ሌላውንም ሐሳብ አከብራለሁ። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የፖለቲካ አመለካከታችን በጣም ጫፍ እና ጫፍ የቆመና ስሜታዊ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ አሁን የባሰ ቀውስ ውስጥ ነች፣ ከመጣንበት ሁኔታ አሁን ያለንበት የባሰ ነው የሚል አስተያየት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። ሐሳቡንም አከብራለሁ።

ነገር ግን በግሌ አልስማማበትም። ኢትዮጵያ ካሳለፍነው ታሪክና የፖለቲካ አስተዳደር የባሰ የሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ አሁን አለች ብዬ አላምንም። ነገር ግን አሁን ያለን የሰብአዊ መብት ቀውስ እና ችግር ቀላል ነው ማለቴ ግን አይደለም።

ግጭቶች ግን የተስፋፉት አሁን ነው። አሁን ማንም ሰው ወይም ቡድን የማንንም ሰው ወይም ቡድን መብት ሊጥስ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ያልቻለበት እና ዜጎች የራሳችንን መብት በራሳችን ልናስጠብቅ ይገባል በሚል ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚረዱበት ሁኔታ ያለ አይመስልም?
አሁን ያለንበት የፖለቲካ ሁኔታ ያልከውን ዓይነት ስሜት የሚፈጥር መሆኑ ይገባኛል። በእኔ አስተያየት ይኼ የሽግግር ወቅት ጠባይ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተከሰት ያለመረጋጋት ሳይሆን ብዙ ከአንድ አምባገነናዊ ከነበረ የፖለቲካ ስርዓት ወጥተው የዴሞክራሲ ሽግግር ሊያደርጉ በሚፈልጉ አገሮች ውስጥ ተመሳሳይ ዓይነት ቀውስ ውስጥ ገብተው ነበር። ምክንያቱም አንድ አምባገነናዊ ስርዓት ሲወድቅ በተወሰነ መልኩ የደኅንነት ክፍተት ይፈጥራል።

በፊት የነበረው ሕግና ስርዓት የሚጠበቅበት መዋቅር ስለሚፈረካከስ በድሮው ዓይነት ልቀጥል ካልተባለ በቀር ሕጋዊ የሆነ የሕግ ማስከበር ስርዓት ተፈጥሮ ሥራ ላይ እስኪውል ድረስ የተወሰነ ጊዜ ይወስዳል። በሚፈጠረው የደኅንነት ክፍተት ሕገ-ወጥነት እና የሕግና ስርዓት መናድ ይከሰታል። ከዚያ ጋር የተያያዘ ምስቅልቅል፣ ግጭት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ንብረት መውደም፣ ከሥራ መፈናቀል የመሳሰሉት አሳዛኝና ውስብስብ ይኼ ነው የማይባል ችግር ይፈጠራል። በመሆኑም በዚያ ደረጃ ሊገለጽ የሚችል የሰብአዊ መብት ቀውስ ውስጥ ገብተናል።

ነገር ግን ካሳለፍነው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ልዩነት ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ ዋነኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚው መንግሥታዊ መዋቅር ነው። አሁን ግን ሰብአዊ መብት ፈጻሚ እና አስፈጻሚ መንግሥታዊ መዋቅር አይደለም። አሁን በመንግሥት ላይ የሚደርሰው ቅሬታ ተገቢውን ጥበቃ ያለማድረግ ነው። ይህንን ሽግግር እስክናልፈው ጊዜ ድረስ የዚህ ዓይነት ምስቅልቅል ለተወሰነ ጊዜ አሳዛኝ ውጤት ይዞ ይቀጥላል። ይህንን ለመቀነስ ነው ጥረት የሚደረገው።

የሰብአዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ የሚሆነው መንግሥት ሕዝብን ለመጠበቅ በተቋቋሙ የፀጥታ መዋቅሮቹ ዋነኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚ እና አስፈጻሚ ሲሆን ነው። ሌላው ነጥብ ደግሞ እኛ በታሪካችን ኢትዮጵያ ውስጥ የምናውቀው በጣም ከፍተኛ ቁጥጥር የሚጭን ጨቋኝ የሆነ መንግሥት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት እና ሕዝብ መካከል የነበረው ግንኙነት ሕዝብ መንግሥትን የሚፈራበት ነበር። የሚፈራው ጠመንጃ ስለያዘ እና ሕግ አስከባሪ ስለሆነ ሳይሆን፣ እንደ ልቡና ከአግባብ ውጪ [መንግሥት] ስለሆነ ነው። ከሕግ ውጪ በጠመንጃው ሕዝብን ስለሚያጠቃ፣ ስለሚያስር፣ ስለሚገድል ነበር የሚፈራው። በድምጹ ተማምኖ ሊያነሳው እና ሊቀይረው የሚችለው መንግሥት ስላልነበር ነው።

አሁን ግን በተፈጠረው የፖለቲካው አዲስ ምዕራፍ የገባነው መንግሥት ድሮ የምናውቀው ዓይነት ሳይሆን ሕዝብን የሚፈራ መንግሥት ነው እየተፈጠረ የመጣው። እንደ ከዚህ በፊቱ በኃይል ለማስቆም የማይቸኩል መንግሥት ሲሆን በትክክለኛው አቅጣጫ ነው እየተጓዘ ያለው ማለት ነው። በቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴው ግን ይህ አካሄድ ብዙ ያስከፍላል። እንዲያውም አሁን ያለው ሕዝብ መንግሥት በኃይል እንዲያስቆም ጥሪ እያደረገ ይመስለኛል። የመንግሥት ይህንን ጥሪ ላለመቀበል ማንገራገር ደግሞ ወደ ድሮው ዓይነት መንገድ ላለመመለስ ይመስለኛል። ይህንን ሚዛናዊ ለማድረግ ደግሞ የጸጥታ ኃይሎች አዲስ ዓይነት ባህል፣ አሠራር እና የሕግ ማስፈፀም ስልት መለማመድ መቻል አለባቸው።

እዚያ ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም። ስለዚህ በዚህ ሽግግር ወቅት ውስጥ የዚህ ዓይነት ችግር ማየታችን ለተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ይችላል ብዬ አስባለሁ። እንጂ አንዳንዶች እንደሚሉት ከነበርንበት የበለጠ የሚወገዝ ነው የሚያሰኝ አይመስለኝም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የተፈጠረው የፖለቲካ ምህዳር፣ የተወሰደው እርምጃ እና የተፈጠረው የመገናኛ ብዙኀን የመንቀሳቀሻ ቦታ ተስፋ ሰጪ ነው ብዬ አምናለሁ።

የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ኃያላን አገራት ሌሎች አገራት ላይ ወታደራዊ ረገጣ ለማድረስ እና ለማውገዝ የሚጠቀሙበት መሣሪያ ሲሆን ይስተዋላል። እነዚህ ነገሮች ዓለማቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች እንቅስቃሴዎች በኃያላን ተይዘው ሌላውን ለመጨቆን መሣሪያ ናቸው ማለት አንችልም?
አሁን ያልከው ዓይነት ትንታኔ፣ ትርጉም እና መደምደሚያ አደምጣለሁ። ይህን አስመልክቶ ኹለት ነገር ለማለት እወዳለሁ። አንደኛው ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የሰብአዊ መብት ሥራም ይሁን ሌላ የትኛውም ሥራ (የኢኮኖሚም ይሁን፣ የቢዝነስ፣ የባህል፣ የትምህርትም ይሁን የጤና ሥራ) ከዓለም አቀፍ የፖለቲካ ግንኙነት ውጪ አይደለም። ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ግንኙነት ደግሞ መንግሥታት የየአገራቸውን ጥቅም ማራመድ የሚሞክሩበት መድረክ ነው።

ስለዚህ አገሮች በዓለም አቀፍ፣ በንግድ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል ግንኙነቶቻቸው ጥቅማቸውን ለማራመድ ሲሞክሩ ማየት የሚያስገርም ዜና አይመስለኝም። ሁሉም አገር ብሔራዊ ጥቅሙን ለማራመድ ጥረት ያደርጋል። ይህን ሲያደርግ ደግሞ የሚያገኘውን መሣሪያ ሁሉ ይጠቀማል። ሰብአዊ መብትንም በዚሁ መንገድ ሊጠቀምበት ይችላል። ስለዚህ ይኼ የዓለም እውነታ ነው።

ነገር ግን ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሚና ሙሉ በሙሉ መርህ አልባም ነው ብዬ አላምንም። እኔ በግሌ የዚያ ዓይነት አሉታዊ የዓለም አመለካከት የለኝም። እንደዚያ ብለን ካሰብነው በቀላሉ የሴራ መላምት ይሆናል። እንደዚያም ሲሆን ያ የአሜሪካ አጀንዳ ነው፤ ያኛው የቻይና አጀንዳ ነው፣ እንደዚህ ዓይነት ድርጅቶች የሆነ ነገር አስፈጻሚዎች ናቸው ማለት ይጀመራል።
በተወሰነ መልክ እውነታ ሊኖራቸው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጅ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ልምድና ታሪክ የሚያሳየው ነገር በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት የሰው ልጅ መብትና ጥቅም በእንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳዎች ተጠልፎ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው። ያልከውን ዓይነት ተግባር ላይ ያሉ መንግሥታት እንዳሉ ቢታወቅም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አከባበር ስልቶችን በመጠቀም ጥረት ይደረጋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የፖለቲካ መብቶች ላይ ማተኮር እና የኢኮኖሚ መብቶች እና የሀብት ክፍፍል አጀንዳዎችን ያለማንሳት ነገርስ በምን ይታያል?
የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት እንቅስቃሴው የግድ በሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም መብቶች ላይ ሁሉ ነው መሆን ያለበት። እኛ አገር በደንብ አልተስፋፋም እንጂ በዓለማቀፍ ደረጃ ሁሉም መብቶች ተነጣጥለው ሊታዩ አይገባም። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዴት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶችን አብሮ ማስኬድ እንደሚቻል የሚያሳዩ ሰነዶች እና መሣሪያች አሉ። በብዙ አገሮችም ይህን እውን ለማድረግ ጥረት ይደረጋል።

በኮሚሽናችን ከምናስባቸው ነገሮች አንዱ ሥራዎቻችን ለወደፊት ወደ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ማስፋፋትን ነው። ብዙ ጊዜ አምባገነን መንግሥታት ባሉበት አገራት ውስጥ የሕዝብ ጥያቄ በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ላይ ያጠነጥናል። የዚህ ምክንያት ደግሞ ከነጻነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው። ከዚያ ውጪ የአደጉትን አገራት በኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች መሟላት ብንፈትሻቸው የተሻለ እየፈፀሙ ሊሆን ይችላል። በብዛት አይታይም እንጂ ባደጉት አገራት ይኼ ይሠራል።

ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም አንዱ ትልቁ ሥራው ይኼ ነው። በዚህ አንጻር ያደጉት አገሮች ከእኛ ጋር ሲነጻጸር ያሉበት ሁኔታ ክፉ የሚባል አይደለም። እነዚህ የኢከኖሚ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ብዙ ሲሠራባቸው የማይታይባቸው ምክንያት በተፈጥሯቸው ከሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ጋር ሲነጻጸሩ ሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቁ መሆናቸው ነው።

ሲቪል እና የፖለቲካ መብቶችን ማስከበር ሀብት አይጠይቅም። በመሆኑም ለመብት ተሟጋች ድርጅቶች ሥራ ይቀላል። ያለመደብደብ መብትን ማክበር ሀብት አይጠይቅም። በመሆኑም መንግሥት ብር ስለሌለኝ ነው ያለመደብደብ መብቱን ያላከበርኩለት ሊል አይችልም። በሌላ በኩል ግን መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን መንግሥት ሙሉ በሙሉ ማቅረብ ካልቻለ ገንዘብ እንደሌለው ጠቅሶ ለማሻሻል ይሠራል እንጂ ያንን መብት ባለማክበሩ ምንም ሌላ የሚፈጠር ነገር የለም።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here