አምስቱ የመከራ ዘመን – በየካቲት 12 መነጽር

0
1203

በጋዜጠኝነት አገልግሎቱ የሚታወቀው ጳውሎስ ኞኞ የተለያዩ የታሪክ መጻሕፍትንም ለአንባብያን አድርሷል። «የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት» የተሰኘው መጽሐፉ አንዱ ነው። ይህ መጽሐፍ ጣልያን ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር ተጠቃሽ ሰበብ የሆናትን የወልወል ግጭት ጉዳይን ያነሳል።

«ማንኛውም የጣልያን ወታደር የረገጠው መሬት ሁሉ የጣልያን ቅኝ ግዛት መሆን አለበት። የምኒልክ ጊዜ በ1898 እና ግንቦት 16 ቀን 1908 ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው የወሰን ስምምነት መፍረሱን የጣልያን ሹማምንት ሁሉ እንዲያውቁት» የሚል ትዕዛዝ ከሮም ተላለፈ።

ቀጥሎ የሆነውን ጳውሎስ በመጽሐፉ እንዲህ አስፍሮታል፤ «ኅዳር 26 ቀን ረቡዕ ልክ ከቀኑ 9 ሰዓት ተኩል ሲሆን በድንገት ባንዳዎቹ በኢትዮጵያ ወታደር ላይ አደጋ ጣሉ። ወዲያው በሰማይ አውሮፕላኖች፤ በምድር ታንኮች ደርሰው በጣሊያኖቹ መድፍና ቦምብ መሬቷ ተርገበገበች። ኢትዮጵያውያኑም ያሉበትን ስፍራ ሳይለቁ ባላቸው አሮጌ መሣሪያ እስከ ሌሊቱ 5 ሰዓት ድረስ በጀግንነት ተዋጉ። በዚያም ጦርነት 94 ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ሲወድቁ 45 ቆሰሉ።»

የነገሩ መነሻ ይህ ነው ይባል እንጂ ጉዳዩ ከአድዋ ድል ጋር የሚገናኝ ነው። ጣልያን በአድዋ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል ቀን ቆጠራ ጊዜ ጠብቃ ነበር ኢትዮጵያን የወረረችው። በርካታ ጸሐፍትም በዚህ ይስማማሉ። ጥላሁን ጣሰው «የኢትዮጵያና የጣሊያን ኹለተኛው ጦርነት» በተሰኘ መጽሐፉ ይህን ነጥብ ያነሳል።

በመጽሐፉም ኢትዮጵያ ከአድዋ ድል በኋላ በቀጣይ 40 ዓመታት ከመጠነኛ መሻሻል በቀር የተለየ ለውጥ ያስመዘገበች አለመሆኑ፣ ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ሞት በኋላ የነበረው የሥልጣን ፍትጊያ የኢትዮጵያን ማእከላዊ መንግሥት እያዳከመው መሄዱ፣ በጥቅሉ ኢትዮጵያ በሽግግር ላይ የነበረችበት ወቅት መሆኑ ለጣልያን ጥሩ አጋጣሚ ሆነ። የንጉሡ ከአገር መውጣት ደግሞ ጉዳቱ እንዲከፋ አድርጓል።

አምስቱ ዓመታትና የካቲት 12
በአምስቱ ዓመት የጣልያን ወረራ ዘመን፣ የኢትዮጵያውያን መከራ ቀላል አልነበረም። በአምስቱ ዓመታትም የማይረሱ ጦርነቶችና አሳዛኝ እልቂቶች አልፈዋል። በደብረ ሊባኖስ የደረሰው መከራ ቀላል የሚባል አይደለም። በዚህ ሁሉ ውስጥ ታድያ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ እንደዘመን ያለእርጅና እንደ አዲስ የሚነሱና የሚወሱ፣ የሚከበሩና የሚሞገሱ ሰማዕታትን ለኢትዮጵያ አሳይቷታል።

የማይጨው ጦርነት በተመሳሳይ የሚጠቀስ ሲሆን፣ የአሸንጌ ሐይቅ እልቂትም ይነሳል። በአሸንጌ የነበረውን እልቂት በሚመለከት ጥላሁን በመጽሐፉ እንዲህ ሲል ከትቦታል፤
«በሰሜን በኩል አርባ የሚሆኑ አይሮፕላኖች ከመስመሩ መጨረሻ ጀምረው በአንድ ጊዜ ሰልፈኛው ላይ ኤፕሪት ጋዝና የቦንብ መብረቅ ያወርዱበት ጀመር።… እንደገና ጋዙን ሊሞሉ ሲሄዱ ሌሎች ደግሞ ወዲያውኑ እነርሱን የሚተኩ ጋዝ የሞሉ አውሮፕላኖች በቦታቸው ይመጣሉ።…በጥቂት ሰዓታት ቆይታ የአንድ ትልቅ ሰልፍ ሙሉ ወታደር ድምጥማጡ ጠፍቶ አፈር ለበሰ።…በማግስቱ ጎህ ሲቀድ የአሸንጌን ሐይቅ ባየነው ጊዜ የሚያሰቅቅ ትዕይንት ተደቅኖ አገኘን። የሐይቁ ዙሪያ በሬሳዎች መቀነት ተከቧል። የሴት የወንድና የእንስሳት ሬሳ አብሮ ተደባልቋል።…ከሬሣው ብዛት የተነሳ ሐይቁ ትልቅ የመቃብር ቦታ ይመስላል…»

የካቲት 12 ቀን 1929 የሆነው ክስተትም በተመሳሳይ ተጠቃሽ ነው። ይህም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገ ሙከራ መነሻነት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ሁሉ ሲገደሉ የነበረበትና መከራ የተቀበሉበት ነው። ይህንንም አሳዛኝና አይረሴ ክስተት ዛሬ ድረስ እየተነሳ የሰማዕታቱ መታሰቢያም እየተደረገ ዘልቋል።

የካቲት 12 በአምስቱ ዓመት በኢትዮጵያን ላይ የደረሰው ግፍ በአንድ ቁልጭ ብሎ እንደሚታይበት መስታወት ነው። ምክንያቱም በእለቱ ያልተፈጸመ ድርጊት አለመኖሩ፣ ብዙዎች ለሰማዕትነት መነሳታቸውና አርበኝነትንም እንዲጋጋል ያደረገ ክስተት በመሆኑ ነው።

በዚህ ላይ አበበ ሐረገወይን (ዶ/ር) አባታቸው የነገሯቸውን የተጋድሎ ታሪክ በማስታወስ ያነሳሉ። ካህን የነበሩና አንድም ቀን ጦር መሣሪያ ይዘው የማያውቁት አባታቸው፣ በጣልያን እጅ ወድቀው ከሞት መትረፋቸውን ተከትሎ፣ ከዛን እለት በኋላ ወደ አርበኝነቱ ዘልቀው ገብተዋል። አዲስ አበባ በደም ጎርፍ በተጥቀለቀችበት እለተ አርብ የካቲት 12/1929፣ እንደ አበበ አባት ያሉ ከሞት የተረፉ ደግሞ ለአገራቸው ሕይወታቸውን በአርበኝነት ከመስጠት የሰሰቱ አልነበሩም።

ጋዜጠኛና የታሪክ ባለሞያ ጥበቡ በለጠ ክስተቱን ምን ያህል አሳዛኝ እንደነበር፣ ልጆች ያለ እናት፣ እናቶችም ሕጻናት ልጆቻቸውን ተነጥቀው ለብቻቸው የቀሩበት መሆኑን ያነሳሉ። ደራሲና አርበኛ ተመስገን ገብሬን ያነሱት ጥበቡ፣ የተመስገንን ‹ሕይወቴ› የተሰኘ መጽሐፍ በመጥቀስ፣ የካቲት 12ን በሚመለከት ስላሰፈሩት እውነት ገልጸዋል።

እንደሚታወቀው ተመስገን ገብሬ ከጦርነቱ መነሳት አስቀድሞ ስጋታቸውን ያቀረቡ፣ ሲልቪያ ፓንክረስት (የሪቻርድ ፓንክረስት እናት) በኢንግሊዝ ለሚያሳትሙት ጋዜጣም፣ ጣልያን ኢትዮጵያ ላይ ያደባችውን ደባ በሚመለከት መረጃ ሲያቀርቡ የነበሩ አርበኛ ናቸው፤ ከድርሰት ሥራቸው ጎን ለጎን።

የካቲት 12 አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒን ለመግደል ያደረጉት ሙከራ ዋና አቀነባባሪ ተመስገን ናቸው በሚል ጣልያኖች ሊገድሉ ከሚፈልጓቸው ሰዎች መካከል ነበሩ፤ ተመስገን ገብሬ።

ጥበቡ ታድያ እኚህን ሰው በማንሳት፣ ያንን አሳዛኝ ክስተት የዛሬ ትውልድ መዘንጋት እንደሌለበት በተማጽኖ አሳስበዋል።
እንደሚታወቀው ጣልያን ኢትዮጵያን ከአድዋ ድል በኋላ ለመውረር የተመለሰችው በ1928 ነው። ኢትጵያውያንም ሰማዕትነትን የተቀበሉት በዓመቱ ነው። ከየካቲት 12 ክስተት በኋላም፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ጣልያንን መቀመጫና መቆሚያ ማሳጣታው እንጂ፣ እስከ 1933 ድረስ መከራው አላበቃም ነበር። ከሠላሳ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በተከታታይ ሦስት ቀናት ለሞት ሰለባ የሆኑበት ሁኔታ ግን፣ ከኋላም ከፊትም እንደ መሻገሪያ ማእከል ሆኗል።

ዘንድሮ የሰማዕታት መታሰቢያ 83ኛ ዓመቱን ይዟል። በብዙ ወቅታዊ ውጥረቶች መካከል ያለችው ኢትዮጵያ፣ ለዛሬ ያደረሷትን ሰማዕታት ለመዘከርና ለማሰብ ብዙ የተሰናዳችም ሆነ ክዋኔዎችን አላዘጋጀችም። ነገር ግን ታሪኩን የሚዘክሩ ተተኪ ልጆች ነበሩና፣ ቀኑ በተለያዩ ክዋኔዎች ታስቦ ውሏል።

የካቲት 12 በ83ኛው የካቲት
ሐሙስ እለት የዋለው 83ኛው የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ እንደተለመደው ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሃውልት ስር ታስቦ፣ ሰማዕታቱም ተዘክረዋል። በእለቱም በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ የሚገኙ ባለሥልጣናት ባይገኙም፣ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ በርካታ ዜጎች ሰማዕታቱን ለማሰብ በመታሰቢያ ሃውልቱ ስር ተገኝተዋል። ጉዳዩንም መገናኛ ብዙኀን የዜና ሽፋን ሰጥተውት መመልከት ችለናል።

የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ ሰማዕታቱን በዘከረው በዚህ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከቀደሙት አባቶች በብዙ መስዋዕትነት የተቀበሏትን አገር፣ ሰማዕታቱን በማሰብና ሰላምን በመጠበቅ የአሁኑ ትውልድም ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ‹‹ከአባቶቻችንን የተረከብናትን አገር ለልጆቻችን ማስተላለፍ የምንችለው አንድ ስንሆን ነው።›› ያሉት ልጅ ዳንኤል፣ ሰማዕታቱን በማሰብ ስርዓቱ በየዓመቱ የሚታዩ ለውጦችን አድንቀዋል፤ አመስግነዋልም።

ሄኖክ ደሳለኝ በዓሉን ጠዋት በአደባባዩ ተገኝተው ካከበሩ ወጣቶች መካከል ይገኛል። ይህን ማድረግ የጀመረው ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ ጀምሮ ከወላጅ አባቱ ጋር በመምጣት እንደሆነ የሚያስታውሰው ሄኖክ፣ አሁን ላይ የየካቲት 12 ሰማዕታት ከቀደመው ይልቅ በስፋት እየታሰቡ እንደሆነ ይሰማኛል ይላል።

ለዚህም የራሱን ቅኝት እንዳደረገ የሚገለጸው ሄኖክ፣ መታሰቢያውን ሊያደርጉ በሃውልቱ ዙሪያ በፊት ይገኙ የነበሩ አርበኞችና ጥቂት በአካባቢው የተገኙ ግለሰቦች እንዲሁም ማርች ባንድ ብቻ ናቸው ይላል። አሁን ላይ የከተማዋ ነዋሪዎችም ይልቁንም ወጣቶች በብዛት በሃውልቱ ዙሪያ ተገኝተው ትኩረት መስጠትና ሰማዕታቱን ማሰባቸው ደስ የሚያሰኘው እንደሆነም ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸው።
‹‹የዓድዋ ድል በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ አከባበሩ እየደመቀና መንግሥትም ትኩረት እየሰጠው ነው። ይህም የሆነው ወጣቶች ለጉዳዩ ትኩረት ስለሰጡ ነው።›› ያለው ሄኖክ፣ የየካቲት 12 ሰማዕታትና አምስቱ ዓመት ጦርነትም ለዓድዋ ድል ራሳቸውን ከሰጡ ኢትዮጵያውን ልክ ሊታወሱ ይገባል ሲል ይሞግታል።

አዲስ ማለዳ ሄኖክን ያገኘችው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በ‹የእምዬ ምኒልክ ወዳጆች ማኅበር› በተዘጋጀ የየካቲት 12 መታሰቢያ ክዋኔ ላይ ለመሳተፍ ወደስፍራው ሲያቀና ሲሆን፣ እርሷም ማኅበሩ ባዘጋጀው ክዋኔ ላይ ለመሳተፍ እድሉን አግኝታለች። በክዋኔውም ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ አበበ ሐረገወይን (ዶ/ር)፣ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ ሐሳባቸውን ሲካፍሉ፣ ወጣት ገጣምያንና በርካታ የመገናኛ ብዙኀን ተገኝተዋል።

የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ የእምዬ ምኒልክ ወዳጆች ማኅበር አባል እንቁጣጣሽ ኃይለማርያም፣ ማኅበሩ ተረሱ ተዘነጉ ያላቸውን ታሪካዊ ክስተቶችና ሁነቶች በማስታወስ የሚዘክር እንደሆነ ጠቅሳለች። ‹‹የካቲት 12 ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ታሪካዊ በዓላት በቅርቡ ነው በደንብ መከበር የጀመሩት።›› የምትለው እንቁጣጣሽ፣ በወጣቶች ተሳትፎ እና ተነሳሽነት ግን በፊት አድዋ የሚከበርበት መልክና የሚሰጠው ትኩረት እንደተቀየር ትጠቁማለች።

በእርግጥም የአድዋ ድል በዓል አከባበር ከቀደመው ጊዜ ይልቅ የአሁኑ ደማቅ ነው። እንቁጣጣሽ መለስ ብላ ስታስታውስም፣ ከአራት ዓመት በፊት ማኅበሩ እንቅስቃሴውን ሲጀምር፣ የድል በዓሉ ታስቦ ዋለ ብቻ ይባል እንደነበር ታነሳለች። ‹‹መጀመሪያ ይህ እንቅስቃሴ ሲጀመር አድዋ ታስቦ ዋለ ብቻ ነበር የሚባለው። ትኩረት እንዲሰጠው የተለያየ ሥራ ሠርተናል። አሁን አድዋ በድምቀት እየተከበረ ስለሆነ ትኩረት ወዳልተሰጣቸው ነው ትኩረታችንን ያደግነው።›› ስትል የሰማዕታቱን መታሰቢያ ለማድረግ ምክንያታቸውን ትገልጻለች።

አዲስ ማለዳ ለእንቁጣጣሽ ያነሳችው አንዱ ጥያቄ፣ የዛሬ ወጣት በተለየ እነዚህ የታሪክ በዓላት ለማክበር ተነሳሽነት ያሳየው እንዴት ነው የሚል ነበር። እርሷም የግል አስተያየቷን ስትሰጥ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የታሪክ መዛባት መስተዋሉና በተሳሳተ መልኩ መተርጎሙ፣ ወጣቱም ይህን ለማተካከል ካለው ፍላጎት የተነሳ ሊሆን እንደሚችል እይታዋን ገልጻለች። ያም ሆኖ እነርሱ እንደ ማኅበር እርሷም እንደ አንዲት ኢትዮጵያዊት፣ ታሪክን ማንሳታቸው ዛሬን የተሻለ ለማድረግ እንደሆነ ጠቅሳለች። እርስ በእርስ ለመጋጨት ከሆነ ምን ይሠራልናል ስትል ትጠይቃለች።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የሰማዕታቱ መታሰቢያ በወጣቶች መደረጉን በእጅጉ ያደነቀ ሲሆን፣ ‹‹ኢትዮጵያ ራሷን ወጣቶች ላይ ተክላለች። የቀደሙ አባቶች ድካማቸውና የፈሰሰው ደማቸው ፍሬ ስለሚያፈራ፣ ኢትዮጵያ ተተኪ ትውልድ አታጣም›› ሲል ስሜቱን በንግግሩ ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here