መታጠፊያው መንገድ

0
470

የ2012 አገራዊ ምርጫ ቀኑ ተወስኗል። ከወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲሁም ምርጫው ይደረግበታል ከተባለው ሰሞን የአየር ጸባይ ጋር በተገናኘ፣ የፖለቲካ ሰዎች አስተያየት ሲሰጡ ነበር። ሆነም ቀረ፣ ያም ሆነ ይህ ምርጫው መካሄዱ እንደማይቀር ቁርጥ ሆኗል። ይህም እንደ አገር ለኢትዮጵያ፣ እንደ ዜጋ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ ብርታት ካለ፣ ለይተን ስንመለከት፣ ለኢትዮጵያውያን ሴቶች መብትና እኩልነት ጥያቄም ወሳኝ መታጠፊያ መንገድ ነው።

በአገራችን ከመቶ ሰዎች መካከል ሀምሳ አንዱ ሴቶች ናቸው። አንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለባት አገር፣ በዚህ ምርጫ ላይ ሃምሳ ሚሊዮን የሚሆኑት ለመራጭነት ካርድ ይወስዳሉ፣ ይሆነናል ይወክለናል ያትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ውስጥ ምን ያህሉ ወንዶች እና ምን ያህሉ ሴቶች እንደሚሆኑ በግምት ማወቅ ባይቻልም፣ ግምት ቢኖር እንኳ ያንን ለመቀየር ጊዜው ገና ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክራቸው የብሔር ግጭትን፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትን፣ በየቦታው የሚነሱ የሰላም እጦቶችንና አለመረጋጋቶችን ወዘተ መፍታት ነው። የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ፣ የክልልነት ጥያቄዎች፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የሕግና ስርዓት አለመከበር፣ የደኅንነት ነገርም በማስታወሻቸው ከሚይዙት አጀንዳ ላይ የሚገኙ ነጥቦች ናቸው። የሴቶችን ጉዳይስ ይዘውታል?

የሴቶች የመብትና እኩልነት ጥያቄ እንደ ተጨማሪ ወይም ‹ቦነስ› ነጥብ የሚያሰጥ ተደርጎ ይቆጠራል። ፓርቲዎች እናራምደዋለን ከሚሉት ርዕዮት ላይ እንደ ቅመም ‹የሴቶች ተሳትፎ› የምትል ሐሳብ ጣል ያደርጋሉ። እንደ ማሟሻ፣ እንደ ‹አልረሳነውም› ማስታወሻ በትንሹ ያነሱታል። ከአሁን ወዲህ ግን ያ እንዳይሆን የ2012 የምርጫ ካርድ በእጃችን ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚጠበቁ የክርክር መድረኮች ላይ ሐሳቦችን አንስተው እንዲነጋሩና እንዲከራከሩ ይጠበቃል። በዛ የሚያቀርቡት ሐሳብ ከወደድን በካርዳችን እንገዛቸዋለን፣ ካልወደድን ትተናቸው እናልፋለን። ከሐሳብ አውድ ገበያው ላይ የሚጥመን፣ የሚሆነን፣ የወደድነው፣ ይሆነናል የምንለውን ካጣን፣ ተጽእኖ መፍጠር ሥልጣኑ አሁንም በዛው ካርዳችን ላይ አለ። ምርጫውን እስከማስደገም አይደርስም ብላችሁ ነው?

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ መንግሥት ሆኖ በማገልገል ላይ ያለው ፓርቲ፣ በሴቶች ጉዳይ ላይ ግልጽ ፖሊሲና አሠራር ሊኖራቸው ይገባል። ይህንን እንዲያደርጉም የምርጫ ካርዱ በሴቶችም እጅ የሚገኝ ነው። ጫና ማሳደር ይቻላል።

እንደምናውቀው የካቲት 23 የአድዋ ድልን እናከብራለን። አድዋ በተነሳ ቁጥር ደግሞ የኢትዮጵያውያት የኩራት ምንጭ፣ ዓለም የተደመመባቸውን ሴት፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡልን አለማስታወስና አለማነሳሳት አይቻልም። ጣይቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የአገር ፖለቲካ ላይ ትልቅ ድርሻና አስተዋጽኦ ነበራቸው።

በኢትዮጵያ ዛሬ ድረስ የጥላቻ ሐውልት እየቆመ ስናይ፣ የጀግኖችን ሐውልት መገንባት አፈር ከለበሰ 30 ዓመት ሆነው እንጂ፣ ጣይቱ ብጡል ቋሚ ሐውልት የሚያስፈልጋቸው ሴት ነበሩ። አልታደልንም። ሆኖም በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ የእቴጌይቱ ማንነት በድንጋይና በሲሚንቶ ተስማምቶ ከተሠራ ሐውልት በተሻለ ተቀርጾ አለ። እናም የአገራችን ፖለቲካ ላይ ሁላችን ጣይቱን ሆነን ማብራት ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ የባላባት ልጅ፣ የባለተራ ወገን፣ የነገሥታት ዘር፣ ዝነኛና ታዋቂ ወዘተ መሆን አይጠበቅብንም። ለምርጫ የምንወስዳት ካርድ ብቻ በቂ ናት።

እንግዲህ የሴቶች መልእክት የሚሆነው ይህ ነው። ‹‹ሐሳብህን ይዘህ የምትመጣ ፖለቲካ ፓርቲ ሆይ! እንደ አገር ካሰብከው ውስጥ ለሴቶች የሰፈርክበት ቁና መጠን በቂ ካልሆነ፣ ገዢ አይኖርህም።››
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here