ከፖለቲካ እንዲሁም ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የሴቶች የእኩልነትና የመብት ጥያቄ ብዙ ነው። ለብዛቱና ሳይፈታ ለመቆየቱ ለሴቶችና በሴቶች ዙሪያ ያለው የማኅበረሰብ አመለካከት ክፍተት ተጠያቂ ሊሆን ይችላል። ሕሊና ብርሃኑ የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ በማተኮር፣ ፖለቲከኞች የሴቶችን ጉዳይ ማንሳት ካለመምረጣቸው በላይ ጉዳዩን ያነሱ እንደሆነ እንኳ መዝጊያና መቋጫ ሐሳብ እንደሚያደርጉት ያመላክታሉ። በኢትዮጵያ ከሚስተዋሉ ከሴቶች ጋር የተገናኙ የተዛቡ አመለካከቶች በመነሳትም፣ የታዩ ንፍገቶችን ዘርዝረው፣ ነጥቦቹን ያላማከለ የፖለሲ አቅጣጫና አሠራር፣ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት አያግዝም አልፎም ውጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል ሲሉ ይሞግታሉ።
‹‹ሥልጣን ተሰጣችሁ። አሁን ደግሞ ምን ቀራችሁ? ይሄ በዚህ ሰዓት መቅረብ ያለበት ጥያቄ ነው? እሺ ቆይ ምን ይሁን ነው የምትይው?”
ብዙ የፖለቲካ ሰዎችን ያገናኘ ስብሰባ ላይ የሴቶች ጥያቄን በተመለከተ አንዳንድ አስተያየቶችን ሰጥቼ፣ ስብሰባውም ተገባዶ ስንወጣ በር ላይ ያገኘኋቸው የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች (ሁሉም ወንዶች ናቸው) ያነሱልኝ ጥያቄ ነበር።
ለነገሩ እነርሱ የፖለቲካ ውይይት ላይ ‹‹አገር ልትፈርስ ነው እየተባለ ይሄን ጥያቄ (እኩል ውክልናና የሴቶች መብት) ምን ስትሆኚ ታነሺያለሽ?›› ዓይነት የአጀንዳ ደረጃ ማውጣት አባዜና ግሰፃም ጭምር ነበር። እናም ከብዙ አሰጣ-አገባ በኋላ፣ ከዚህ ቀደም የተወሰዱ የእኩልነት እርምጃዎች በቂ ናቸው ብለው ማሰባቸው፣ ‹‹እኩልነት ዛሬ የለችም ነገ ተመለሱ›› በሚመስል መልክ የሴቶች ፖለቲካን ለይደር መተው መፍቀዳቸው ከልብ አስከፋኝ። በዚህ አካሄድ ማንን ይሆን የምመርጠው?
‹‹የሚያውቁት ሰይጣን›› ወደሚለው ላመራ ይሆን? ብዬ እንዳስብም ሳያደርገኝ አልቀረም። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥያቄ ማንሳት የሚያስደነብራቸውና የሚያቅለሸልሻቸው እንዳሉ ሳላውቅ ቀርቼ አይደለም። ኧረ እንዲያውም ‹‹ሴቶችን አካቱ ተብለናል፣ ምን ግዴታ አለብን?” ያሉ በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን በፓርላማ ውይይት ላይ ሲያቀርቡም ሰምቻለሁ። ነገሩ ይህን ያህል አፍጦ፣ በተቃውሞ መልክ ይመጣል ብዬ አላሰብኩም ነበር እንጂ። መራጭ መሆናችንን ዘንግተውት ይሆን?
አገራችን ባለችበት የለውጥ ሂደት ውስጥ የሴቶች እኩልነት ጥያቄዎችን በተመለከተ ፖለቲካዊ ውይይትን ያነሳሱ፣ ለምሳሌነት የሚተርፉ መልካም ጅማሮዎች መኖራቸው የማይካድ ነው። ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስህተቶች ሲኖሩም የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በኅብረተሰቡ ከፍተኛ ውትወታ ሲደረግ፣ ይህን ተከትሎም ፈጣን የሚባል ምላሽ ሲሰጥ ይታያል። ይህ የሚበረታታ ተግባር ነው። ይሁን እንጅ በሴቶች መብት ላይ የተደረጉ ለውጦችና ንቅናቄዎች ላይ ግን ግትር የፖለቲካ ዳኝነት ይታይባቸዋል።
በማኅበረሰባችን እይታ የሴቶች ፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄን የሚያነሱ ቡድኖችና ግለሰቦች የልሂቃን የቅብጠት ጥያቄ እንዳነሱ ይቆጠርባቸዋል። ይባስ ብሎም በለውጡ ሒደት ‹‹የት የተዋጋሽውን፣ መቼ የተሰዋሽውን›› የሚሉ የሴቶችን ሚና የሚክዱና የመብት ጥያቄን መስዋዕትነት ከመክፈል ጋር የሚያቆራኙ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይስተዋላል። ‹‹አሁን የእገሌ ብሔር ተራ ነው፤ ተራሽን ጠብቂ›› የሚል አልያም ‹‹ሴትነትሽን አውልቂና ብሔር ብትሆኚ ይበጅሻል። አለበለዚያ እነ እንትና ሊገድሉሽ ነው፣ መጡብሽ›› ዓይነት ማስፈራሪያ የሚጠቀሙም አይጠፉም።
‹‹ሴቷ ለምን ሥልጣን ተሰጣት? በበጎ አድራጎት ሥራ ችግሯ በቅድሚያ ይቀረፍ፤ ሴቶች ከቡና ማፍላትና ስብሰባ ማድመቅ ያለፈ ተግባር እንደሌላቸው እያወቁ፣ የአስተናጋጅ ዳሌ ቸብ ከማድረግ ልምድ ሳንላቀቅ ጠሚው ምን ሲሉ ወደሥልጣን አመጧቸው?›› ብለው በመጽሐፍ ደረጃ ጭምር ይህን ፆተኝነት ያሳተሙ እንደ ኢያሱ ገብረመስቀል አይነት ‘ጸሐፊዎች’ እንዳሉ ሳንረሳ ማለት ነው። በዚህ አገላለፅ ስለ አንዱ ብሔር ጽፎ ቢሆን ኖሮ ‹ስውር መፈንቅለ መንግሥትና የዐቢይ ቀጣይ ስጋቶች› የሚለው መጽሐፉ ከያለበት ይለቀም እንደነበር ጥርጥር የለኝም።
ከማኅበረሰባዊ እይታ ወደ ገዥው ፓርቲ ስንመጣም የፆታ እኩልነት ላይ የሚሠሩ ሥራዎችን ተከታትሎ የማረምና ተጨማሪ የመሥራት ፍላጎቱ የተዳከመ ነው። አበረታች መነሻዎቹ እንደ መድረሻ ግብ ተወስደው በጅምሩ የተቀጩ ይመስላሉ። ሴቶች እኩል ውክልና እንዲኖራቸው በጥቂቱ የተሠራ ቢሆንም፣ ወደ ሥልጣን ቀረብ ሲሉ ግን ‹ከዚህ ግድም አትለፊ› ዓይነት መስመር የተሰመረላቸውም ጭምር። ሌላውን እንኳ ትተን የሴቶች ፖለቲካ ውክልና ላይ የተሠሩ ሥራዎችን ብንመለከት የሴቶች እኩል ተሳትፎ ሲባል የወሰዱትን ኃላፊነት ለመወጣት አቅማቸውን አሟጠው መሥራት ይችሉ ዘንድ ምቹ የሆነ የሥራ ከባቢን መፍጠር እንደሚጠይቅ ገዥው ፓርቲ የዘነጋው ይመስላል።
እናም ይህን ለማስተካከል ታዋቂዋ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር Drude Dahlerup ‘Has Democracy Failed Women?’ በሚለው መጽሐፏ እንዳስቀመጠችው፣ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ስኬታማ ሆኖ እንዲዘልቅ ከተፈለገ ከስር [ከዚህ አንቀጽ ስር] የምተነትናቸውን የፖለቲካ የወንዶች የበላይነትን ልብ ሊል፣ ትኩረት ሰጥቶም ሊያርም ይገባል። ከታች የተዘረዘሩትን ፍሬ ነገሮች ያላማከለ የፖለሲ አቅጣጫና የአሰራር ሒደት፣ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ላይ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዳይሆንና ለሕገሥመንግሥቱ ዓላማ እንዳይገዛ ያደርገዋል።
ንፍገት አንድ – ውክልና
በተለምዶ ‹ከሞላ ጎደል ሕዝቡን ይመስላሉ› በሚል አገላለፅ ታጅበው ለሕዝብ የሚገለጹ ሹመቶች፣ የኮሚቴ አወቃቀሮች በወንዶች የተያዙ ናቸው። ይህን ለማየት ብዙም ሳንሄድ የጠቅላይ ሚኒስትር ገፅን ፎቶዎች ማየት ብቻውን በቂ ነው። የተለያዩ የመንግሥት ጉዞዎችና ስብሰባዎች ላይ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን በሚመስል መልኩ ተደርድረው ለሚያዩ ሴቶች 51 በመቶ የሕዝቡ አካል መሆናቸውን እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ነው።
ከሴቶች የእኩል ውክልና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ሕገ-መንግሥታዊ መብት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አጋጣሚዎች ብዙ የተባለ ቢሆንም፣ ከሁሉም ግን የሴቶች ተሳትፎ ጥያቄን ከብቃት አለመኖር ጋር አንድ አይነት ወሬ አድርገው የሚያቀርቡ ብዙዎች ምላሽ ያሻቸዋል። በቅድሚያ አገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ተምሳሌታዊ ሴቶች መኖራቸው የማይካድ ሃቅ ነው። ስለዚህም ‹ሴቶች አጣን፣ የሉም፣ ብቃት የሌላቸው ሴቶች ይምጡ ነው የምትይው?› የሚለው አጓጉል ምክንያት አይሠራም።
በየሥራ ዘርፉ ብቃት ያላቸው ሴቶች ነበሩ፣ አሉ፣ ይኖራሉም። ይህን ፈልፍሎ ማውጣት፣ ከያሉበትና ታሪካቸውን ከሚያጋሩ መዋቅሮች ተከታትሎ መመልመል የመንግሥትና መንግሥት ለመሆን የሚጥሩ ተፎካካሪ ፖርቲዎች ግዴታ ነው። ሲቀጥል የብቃት ማነስን ጥያቄ ለምን ሴቶች ላይ ብቻ? ስንት የሥራ መደቡን/ሹመቱን የማይመጥን ወንድ አመራር ባስተናገደች፣ አሁንም ቢሆን እያስተናገደች ባለች አገር አንዱ ፆታ ላይ ብቻ ተጠያቂነትን ማኖር ለምን? እዚህ ጋር ታዋቂው የእንግሊዝ ፈላስፋ ጆን ስቱዋርት ሚል ‘The subjection of women (1869)’ በሚለው መጽሐፉ እንዲህ ይላል፤
‹‹… የአንድ አገር የፖለቲካ ስርዓት ብቁ ያልሆኑ ወንዶችን ገሸሽ ካደረገ፥ ብቁ ያልሆኑ ሴቶችንም መግፋቱ አይቀሬ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ብቃት የሌለውን ግለሰብ ወንድም ይሁን ሴት ሥልጣን ቢወስድ የሚያመጣው ተጨማሪ ክፋት የለም።››
ይህም ሲሆን መታወቅ ያለበት የሴቶች ሥልጣን ላይ መኖር የችግር ሁሉ መዳኛ ተደርጎ ያለምንም በቂ ማስረጃ ከሙስና ቁጥብ፣ እናትነትና የመንግሥት ኃላፊነትን ያቀላቀለ ሩህሩህነት ባለቤት አድርጎ የሚስል ትርክት ሰለባዎች እንዲሆኑ አይደለም። እንዲህ ያለው ትርክት ለጊዜው በጎና ሴቶችን ደጋፊ ቢመስልም ቀጣይ ውጤቱ ግን ‹ይሔው ሴቶችን አስገብተን መች ወርቅ ዘነበልን› የሚል ተአምራት ጥበቃ መሆኑ አይቀሬ ነው። ይህም ሴቶችን የአንድ አይነት ባህሪይ ባለቤት አድርጎ በጎራ ከመጨፍለቁ ባሻገር፣ የሥልጣን ጥያቄያችንን ከመብት ጉዳይ ወደ ጥቅም ላይ ያተኮረ ችሮታ ይቀይረዋል።
ሌላው በሚኒስቴር ደረጃ የተስተካከለው የሥርዓተ ፆታ ጉዳይ ወደ ታች ወርዶ እያንዳንዱን የመንግሥት ተቋማት ካላዳረሰ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ይህን ስንል ከከፍተኛ ባለሥልጣን አካላት ተነስቶ እስከ ወረዳ እና ቀበሌ የአስተዳደር ቦታዎች ላይ ሴቶች እኩል ተሳትፎ ሲያገኙ ማለት ነው። ስለዚህ ከመንግሥት የበለጠ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል እንጂ የዘጠኝ ሴት ሚኒስትር ውክልና የእያንዳንዷን ሴት ሕይወት ሊቀይር አይችልም።
ወደ ኹለተኛ ሐሳቤ ላምራ፤
ንፍገት ኹለት – አመራር ላይ ባሉ ሴቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጅምላ ፍረጃዎችና ፆተኛ አመለካከቶች
ብዙ ጊዜና በተደጋጋሚ ሴቶች ወደ ፖለቲካው ዓለም ለመቀላቀል ፍላጎት እንደሌላቸውና እንደሚፈሩ ሳይቀር ሲነሳ እንሰማለን። አመራር ላይ ያሉ ሴቶች ከሚገጥሟቸው ከባድ ፈተናዎች መካከል በማኅብረሰቡ እንዲሁም በሚዲያዎች የሚሰጡ ጅምላ ፍረጃዎችና ፆተኛ አስተያየቶች ይባስ ብሎም ፆታን መሰረት ያደረጉ ማስፈራሪያዎችም እንደሆኑ የተለያዩ ጥናቶችና ከሴት ፖለቲከኞች አንደበት የሰማናቸው ምስክርነቶች ይጠቁማሉ።
ለሴቶች የማኅበራዊ መደብ የማውጣት አባዜ፤ ‹‹የቤቱንስ ለማን ትተሽ፣ የእድሩን ወጥ ማን ሠርቶልሽ›› ዓይነት ፍረጃ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉ ሴቶችም ጭምር የሚገጥማቸው ጥያቄ ነው። እንደውም በቅርቡ አንድ ይህ ባህሪይ የተጠናወተው የፋና ጋዜጠኛ፣ በስትራቴጂካዊ አመራርነት ላይ ለሴት ሚኒስትሮች የተሰጠ ሥልጠናን ‹‹ሴት አመራሮች የቤት ውስጥ ኃላፊነታቸውን ከውጪው ጋር እንዴት ሊያጣጥሙ እንደሚችሉ የተዘጋጀ ሥልጠና›› ሲል ዘግቦታል። የሥልጠና መርሃ ግብር ላይ የሌለውን ያልተጻፈውን ሲያነብ ማለት ነው።
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው የቤትና የውጪ ተብሎ የተቀመጠው የሥራ ክፍፍል አሁንም ብዙ ሴቶችን እየጎተተ ያለ እሳቤ ነው። የትምህርት አቅርቦትን እኩል የማግኘት፣ ‹ተምራ የት ልትደርስ› ከሚለው አመለካከት ጀምሮ ሴት ልጅ በምርጫዋ እንዳትኖርና ሕይወቷን እንዳትቀይር የሚያደርጉ እክሎች የሚወለዱትም ከመሰል አስተሳሰቦች ነው።
ከዚህም አልፎ በቅርብ ጊዜ እንኳ ፖለቲካ ውስጥ በተሳተፉ ሴቶች ላይ እንዳየነው፣ ከወንድ የሥራ አጋሮቻቸው በተለየ የወሲብ ነክ የጥላቻ ንግግር፣ በሥራ ላይ ስላለው አፈፃፀም ትችት ሳይሆን ውበታቸው ላይ፣ ግለሰባዊ ምርጫቸውንና የግል ሕይወታቸውን የሚጋፉ አስተያየቶች ይሰጣሉ። በሴቶች የጋብቻ ሁኔታ፣ ከሌሎች ወንዶች ጋር የነበራቸውን የሥራ ቅርርብ አልያም እድሜያቸው ላይ በመመርኮዝ ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኛ ነን ባዮች እነዚህን ሴት አመራሮችን ‹ቆሞ ቀሮች› ‹ጋለሞታዎች› ‹መውለጃ ጊዜዋ ያለፈባት› በማለትም ሲያንጓጥጡ ሰምተናል።
በነገራችን ላይ ሴቶችም ቢሆኑ ከወንድ የበላይነት ስርዓት ነጻ የወጡ አይደሉምና ይህን መሰል አስተያየቶች በሴቶችም ጭምር ይሰጣሉ። በጅምላው ‹‹አይ እንዲህ ያለችዋን ማን ያገባል?፣ እስካሁን ሳታገባ ለአገር ተረፍኩ ምን ይበጃል? አርፋ ለወንዶቹ አትተውም? እኛ እኮ በተፈጥሯችን ይሄ አይሆነንም›› የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ወደ ኃላፊነት የሚመጡ ሌሎች ሴቶችን ያለአግባብ መጠራጠር ብሎም ሰዋዊ ያልሆኑና ከሌሎች ወንዶች የማይጠብቁትን እንከን የለሽ፣ እግዜራዊ ሥራ መጠበቅም የተለመደ ነው።
ሴቶች ይበልጥ የተማሩ ከሆነም፣ የልሂቅነት ማዕረግን አልብሶ ልክ የኢትዮጵያን ችግር የማትረዳ አድርጎ መተቸትም እንዲያው፤ በተቃራኒው የተማሩ ወንዶችን በየቦታው እያሞገሱና የአዋቂነት ካባ እያለበሱ ማለት ነው።
አድናቆት እንዲቸራት የምትፈልግ፣ ተወዳጅ መሆን የተመኘች ሴት በማኅበረሰቡ ልክ የምታስብና የምትንቀሳቀስ እንድትሆን ይጠበቅባታል። በተለይ በተለይ የሃይማኖትና የብሔር ካባዋን ከፍ አድርጋ የለበሰች ቀን አሞጋሿ ብዙ ነው። ከሃይማኖት ጋርም ተያይዞ ሙስሊም ሴት ስትሆን ደግሞ ድርብርብ በደል ይስተዋላል። ከአለባበሷ ምርጫ እስከ አዋዋልዋ እና የእውቀት አቅሟ፣ እስከ ምግብና መጠጥ ምርጫዎቿ ጭምር አግባብነት የሌላቸው ትችቶች ይቀርቡባታል። ይህ ዓይነቱ የፖለቲካ ትንኮሳ በጊዜ ሂደት ሴቶች ከፖለቲካ ሕይወት ራሳቸውን እንዲያገሉ በመጫን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን አደጋ ላይ ይጥላል።
ንፍገት ሦስት – ተዋረዳዊ የሥነ-ፆታ መድሎ
ተዋረዳዊ መድሎ በድርጅት ወይም አውድ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን የሚይዙ ሴቶችንና ወንዶችን ይመለከታል።
በርካታ የመንግሥት ሥራዎች በኮሚቴዎች ይሠራሉ። እኚህ ኮሚቴዎች በፓርላማም ይሁን በእያንዳንዱ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ውስጥ፣ የፖለቲካ ውይይቶችና ውሳኔዎችን የሚያስተናግዱ ቁልፍ ስፍራዎች ናቸው። በዚህ ውስጥ ታዲያ በቀጥታው መስመር ተዋረድ ስንመለከት አብዛኛውን የሊቀመንበርነት፣ የምክትል ሊቀመንበርነትና የመሳሰሉት ከፍተኛ ቦታዎች በወንዶች የተያዙ ናቸው።
እነዚህ በወንዳዊው ስርዓት የተሻለ ዕድል የተሰጣቸው ወንዶች የኮሚቴ፣ የሥራ አመራር የመሳሰሉት መሪ በመሆናቸው ምክንያት ብቻ የተለያዩ የሥራ ልምዶች፣ የስብሰባና የውይይት ተሳተፉልን ግብዣዎች፣ የውጭ አገራት ጉዞን ጨምሮ የገንዘብና የእውቀት ጥቅማጥቅሞች የመጀመሪያ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ‹ላለው ይጨመርለታል› ነውና የጥቅም ትስስሩ ለሌላ ትልቅ ሹመት እና ጥቅማ ጥቅም የሚያበቃ ነገር ይጨምርላቸዋል።
ሴቷ ግን እነዚህን ቦታዎች ቀድማም አትታደልም፤ ከዚያም በኋላ ቦታውን ባለማግኘቷ ተጨማሪ እሴቶቹን አታገኝም። በመሆኑም መነሻው ላይ ከሷ ትይዩ አቅም የነበራቸው ወንዶች ሲያድጉና ሲመነደጉ፣ እሷ ባለችበት እንድትረግጥ ወይም ዝቅ እንድትል ትደረጋለች።
ንፍገት አራት – ስርዓተ ፆታዊ የአግድመት መድሎ
የአግድመት መድሎ ማለት በሚኒስቴር ደረጃ ወይም በኮሚቴዎች ውስጥ ሴቶች እና ወንዶች የሥልጣን ማዕረጋቸው አንድ አይነት ይሆንና፣ ሥራቸው የሚከፋፈልበትን የፆተኝነት ዕይታን ይገልፃል። ይህ የፆተኝነት እይታ ሴቶች በተፈጥሮ ‹አይችሉም› ወይም ‹ቀለል ያለውን የሥራ ድርሻ ቢወስዱ ይሻላል› ከሚል በሳይንስ ያልተረጋገጠ ፆታን መሰረት ያደረገ ፍረጃ የሚነሳ ሲሆን፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ ወንዶች ‹ይችሏቸዋል› ተብለው የሚታሰቡትን የሥራ ክፍሎች የበለጠ አስፈላጊ እንደሆኑ የሚቆጠርበት ስርዓትም ጭምር ነው።
ለምሳሌ ኢኮኖሚያዊ፣ መሠረተ ልማት፣ ባንኮችን ጨምሮ የተለያዩ የገንዘብ ተቋማትን፣ መከላከያን፣ ስፖርት እና የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮችን መምራትና ማስተዳደር በብዛት በወንድ የተያዙ ናቸው። ሴቶች በዋነኛነት ከማኅበራዊና ባህላዊ ጉዳዮች ጋር የሚገናኙ ቦታዎች ላይ በብዛት ሲወከሉ ይታያል። ማለትም ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ሴቶችና ሕጻናት፣ ትምህርት እና ባህል የመሳሰሉት የሚኒስትርነትና የኮሚቴ ሰብሳቢነት ኃላፊነቶች። ይህ ሲባል ትምህርትን ወይም የማኅበራዊ ጉዳይ ሥራዎችን ለማሳነስ አይደለም። በማኅበረሰቡ ቅድሚያ እና ክብደት የሚሰጣቸውን የትኞቹ ዘርፎች እንደሆኑ ለማሳየትና ሴቶች ይህን ማኅበራዊ አጥር ፈንቅለው ወደ ሌላው (ወንዶች በተለምዶ ወደሚይዟቸው) መሻገር ቢፈልጉ የሚገጥማቸውን ትችትና ፈተናዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
‹‹ሴቶችን የመከላከያ ሚኒስቴር ማድረግ ርህራሄ የተሞላው ተፈጥሮአቸውን መጋፋት ይሆናል›› ከሚሉ ተራና መሰረተ ቢስ አስተያየቶች እስከ በመንግሥት ደረጃ ለእነዚህ የተለያዩ ሥራዎች የሚኖሩ የበጀት ድልድሎች ስንመለከት፣ ለወንዶችና በተለምዶ ወንዶች ይይዙታል ለሚባሉ የሥራ ክፍሎች ያደሉ ሆነው እናገኛቸዋለን።
በነገራችን ላይ ከለውጡ በኋላ በመጡ የሚኒስቴር ማዕረጎች እነዚህ ዘልማዳዊ ድንበሮች የተገፉ ቢመስልም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየን እንደመጣነው ግን እነዚህ ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ሴቶች በአግባቡ እንኳ አቅማቸውን ሳይጠቀሙ፣ ችሎታቸውን ሳያሳዩ፣ ያለ በቂ ምክንያትና የሥራ ግምገማ የሹመት ቅያሪ የሚያደርጉበት እድል ከፍ ያለ ነው።
ንፍገት አምስት – ወንዴ ሰራሽ የፖለቲካ አሠራርና ልማዶች
ፖለቲካ በአሠራሩ ወንዳዊ ነው ስል በግልፅ ያልተጻፉ ፆተኛ አሰራሮች ላይ የማተኩር ይሆናል። ከላይ እንደጠቀስኩት አብዛኞቹ የፖለቲካ አደረጃጀቶች ሴቶች ለፖለቲከኝነት ብቁ እንዳልሆኑ፣ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸውና ቢሳተፉም ሴቶች ሌሎች ሴቶችችን አይደግፉም፣ አይመርጡም የሚል ድምዳሜን ይዘው የሚነሱ ናቸው። ይህንም ሰበብ በመጠቀም የምልመላ መረቡን ራሳቸውን ለሚመስሉ ወይም ለእነሱ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ያመቻቻሉ።
ይሄኔ የሥርዓተ ፆታ ተመራማሪዎች ‘አሃዳዊ ማኅበራዊነት’ (homosociality) የሚሉትን ማለትም የአመለካከት ወጥነት ያለውና የማኅበራዊ መደቦችን በመመርኮዝ በተለይም ፆታዊ ትስስሮችን መሰረት ያደረገ ሌሎችን አግላይ የሆነ የጥቅም ኢ-መደበኛ ግንኙነት መዋቅርን ሲገነቡ ይስተዋላል። ይህ መዋቅር እንደ መደበኛ ማኅበራት ግልፅ ሥምና ሎጎ ባይኖረውም፣ የዛን ቡድን ጥቅም ሕጋዊ ባልሆነና ወጥነት በጎደለው መልኩ የማስቀጠል አቅሙ ግን የሚናቅ አይደለም።
ለምሳሌ ያህል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልያም አንድ የሚኒስትር ቢሮ ሙያዊ አማካሪ መቅጠር ቢፈልጉ ለነማን ያሳውቃሉ? እነማን ቀድሞ የኤሌክትሮኒክስ መልእክት ያላክላቸዋል? እነማንስ ይጠራሉ? የትኛው የፆታ ቡድን በብዛት ይህ መልዕክት ይደርሰዋል? ብሎ ማሰብ ነው። ከቅጥር ውጪም ቢሆን በመንግሥት ተቋማት የሚታተሙ ጽሑፎች፣ የሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች ከተጋባዥ ተናጋሪዎች እስከ ዝግጅት ታዳሚዎች በወንድ የሚሞሉት እነዚህ መረጃዎች በቅድሚያና በብዛት ለወንዶች ሲለሚላኩ ሲሆን፣ የተላከላቸውም ወንዶች ቢሆን በአብዛኛውም የሚያጋሩት እነርሱን ለሚመስሉ ሌላ ወንዶች ስለሆነ የትስስር ሰንሰለቱን ሰብሮ ለመግባት እጅግ አዳጋች ይሆናል።
ሴቶችን ያካተቱ ጊዜም ቢሆን (በአብዛኛው ሴቶችን የሚያካትቱት ከምር የፆታ እኩልነትን የተረዳ ሥርዓት ኖሮ ሳይሆን በሕዝብ ዐይን ሥልጡን፣ ዘመናዊ ሆኖ ለመታየት መሆኑን ሳንረሳ ማለት ነው) ወደ ሥልጣን የሚመጡ ሴቶችን አጎብዳጅ የሚያደርጉ ያልተጻፉ አሠራሮችን አኑረው ይጠብቃሉ። ይህም ሲሆን ሴቶች ሆን ብለው ግር እንዲሰኙ አልያም በወንዶች ችሮታ የገቡ መሆናቸውን እንዳይረሱ የሚደረጉ ወንዳዊ መጥለፎች እና አሉታዊ ተፅእኖዎችም ይኖራል።
እነዚህ የአሠራር እንቅፋቶችን ችለው ቅሬታ ለማሰማት እንኳ በማያመች መልኩ በኖረ ስርዓት ውስጥ እንዲሰሠሩ ይገደዳሉ። አልያም ‘የተሰጠው’ ሊወሰድ እንደሚችል እንዲታወሱ ይደርጋል። የውስጥ አሠራሩ ይህን መስሎ በጎን ደግሞ ማኅበረሰቡ ለውጥን፣ በተሰማሩበት የመሪነት የሥራ ድርሻና ዘርፍ ውጤትን መጠበቁ አይቀሬ ነውና፣ ይህን ለማድረግ ተመሳስሎ መሥራቱን፣ ለወንዳዊ ስርዓት መገዛትን የመሰንበቻ አማራጫቸው አድርገው ይቀበሉታል።
ንፍገት ስድስት – የፆታ እኩልነትን ያላገናዘቡ ፖሊሲዎችና ሕጎችን በወንድ ዐይን መንድፍ
ብዙውን ጊዜ በተለያዩ የፖሊሲ ውይይቶች ወይም መድረኮች ላይ ስለፆታ እኩልነት የሚነሳው በስተመጨረሻና ከሌሎች የፖለቲካና ልማት ጥያቄዎች ተነጥሎ እንደ ተቀጥያ ሐሳብ እና እንደትርፍ አጀንዳ ነው። ይህም የሆነው በንፍገት አምስት ላይ እንዳስቀመጥኩት፣ በብዙ ቆይታ የተገነባ ወንዳዊ ስርዓት በመኖሩና የስርዓተ ፆታ እኩልነት ለፖለቲካ ወይም ለልማት አስፈለጊ እንደሆነ መሰረታዊ ሐሳብ ስለማይታይ ነው። ስለዚህም በአብዛኞቹ በመንግሥት አመራርነት የሚካሄዱ ችግርን የመፍታት ሙከራዎች፣ ሁሉን ከሠሩ በኋላ የሚያስቀምጡት ስለሆነ የእኩልነት ጥያቄ በአግባቡና ስትራቴጅካዊ በሆነ መልኩ እንዳይመለስና እንደው የይድረስ ይድረስ ለይስሙላ እንዲሠራ ያደርገዋል።
በዚህም ምክንያት ሕግና ፖሊሲዎች ሲነደፉ እንዲሁም የመንግሥት በጀት ሲያዝ፣ በወንድ ዐይን ልኬት የሚመዘን ይሆናል። ለምሳሌ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተሟላ መልኩ የሕጻናት ማቆያን የሚመለከት ግልፅ ፖሊሲ ለረጅም ጊዜ አለመኖሩ፣ ሶፍትና ሳሙና የሚያድሉ መሥሪያ ቤቶች ሥርአተ ፆታን ያገናዘበ የበጀት አሠራርን ዘይደው ሞዴስ ለማደል አለማሰባቸውን መጥቀስ እንችላለን። ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወደ አጠቃላይ ሕግ ስንሄድም፣ መሠረታዊ የሴቶች ስጋቶች የሆኑትን ለምሳሌ ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን፣ በሥራ ላይ የሚደርሱ ትንኮሳዎችን ጨምሮ ሁሉን አቀፍና ፍትሃዊ ሕግ አልወጣላቸውም። የወጡትም አጥጋቢ ያልሆኑ ሕጎች በትክክል ሲተገበሩ አይታይም።
ይልቁንስ የሴቶችን የተለየ ፍላጎትና ጥቅምን የሚያስከብሩ ሕጎች ይቅርና ከጊዜ ወደ ጊዜ ያለውንም የሚቀንሱ፣ በተለይ የማኅበረሰብ ሞራልን ታከው የሚወጡ ሴቶችን የበለጠ የሚጨቁኑ ወንድ ተንከባካቢ ሕጎችንም እናያለን። እዚህ ጋር ለምሳሌ በቅርቡ ለሕዝብ ውይይት የቀረበውን የጎዳና ልመናና የወሲብ ንግድን ለማገድ የወጣውን ረቂቅ ሕግ መመልከት እችላለን።
እርግጥ ይሄ ሕግ የእነዚህ ሴቶች ኑሮና ፍላጎት በሚገባ ለመረዳት ሞክሯልን? እንኳን ሕግ ወጥቶ ድሮውንም በወንድ ፖሊስና በጉልበተኛ ወንዶች ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች፣ ብር እንዲካፈሉ የሚገደዱ፣ በደንበኛ የሚደርስባቸውን ጥቃት ለማምልከት ሲሄዱ ‹ከኔም ጋር ካልተኛሽ› የሚል ጥያቄ የሚገጥማቸውን ሴቶች ሕይወት፣ በእርግጥስ ታሳቢ አድርጓልን? ለመሆኑ ተጠቃሚው ወይም ገዢው በተለምዶ ወንዶች ናቸው፣ ለምንስ ተጠያቂ አልሆኑም? ወይስ የማኅበረሰብ ሞራል ኃላፊነትን መወጣት እነርሱን አይነካም?
ሥርዓተ-ፆታ በማንኛውም ማህኅበረሰብ ውስጥ ልብ ሊባሉ ከሚገባ ማኅበራዊ ስሪቶችና የማኅበራዊ ሥልጣን እርከን ክፍፍል መንስኤዎች አንዱና ዋነኛው ነው። መንግሥትም ይህን በመረዳትና ፆታን መሰረት ያደረጉ ኢ-ፍትሃዊ አሰራሮችን ለመቀየር ማቀዱ መልካም ሆኖ ሳለ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካና ማኅበራዊ ዲ ኤን ኤ ውስጥ ሰርፆ የገባው የወንድ የበላይነት ባህል ጥቂት ሴት ሚኒስትሮችን ከመሾም በላይ ሥራ እንደሚጠይቅ ልብ ሊባል ይገባል። እርግጥ ነው የሴቶች ኃላፊነት ላይ መሆን የማይካድ ምሳሌያዊ እና ተጨባጭ ዕድሎችን ይፈጥራል። ነገር ግን ፆተኝነት የመሰሉ ስር የሰደዱ አመለካከቶች ጠንካራና ሁሉን አቀፍ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ይጠይቃሉ።
ከላይ የጠቀስኳቸው ንፉግነቶች የፖለቲካ ጥያቄ ላይ በተደጋጋሚ ከሚስተዋሉት ነው እንጂ ከዚህ በላይ ብዙ ሌላም ብዙ ቀዳዳዎች መኖራቸው እሙን ነው። ለጊዜው ግን እነዚህ ላይ ማኀበረ-ባሕላዊ እንዲሁም ሕጋዊና የፖሊሲ እርማቶች ቢወሰዱ መልካም ነው እላለሁ።
ሕሊና ብርሃኑ የሥርዓተ-ፆታና የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ በዚህ አድራሻ ይገኛሉ bhilina.degefa@gmail.com
ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012