15 ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በምሥረታ ላይ ናቸው

0
1224

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ተቆጣጣሪ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 15 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በምሥረታ ላይ መሆናቸውን ይፋ አደረገ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የተለያዩ ማሻሻያዎች ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ፣ በርካታ የፋይናንስ ተቋማት በምሥረታ ላይ ሲሆኑ፣ አዳዲሶቹ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከተመሠረቱ ቁጥራቸው ወደ 53 ከፍ እንደሚል ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አንድ ማይክሮ ፋይናንስ ለመመሥረት 10 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በቂ ሲሆን፣ በሥራ ላይ ያሉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ ካፒታል ወደ 15 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

የማይክሮ ፋይናንሶች ማኅበር ፕሬዘዳንት ተሾመ ከበደ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ በምሥረታ ላይ ያሉት አዳዲሶቹ ማይክሮ ፋይናንሶች እስከ አሁን ከነበሩት የተሻለ አቅም ይዘዉ ሊመጡ እንደሚችሉና ያለውን የአሠራር ሁኔታ እና ክፍተት አጥንተዉ ስለሚመጡ አገልግሎታቸዉ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ድህነትን ከመቀነስ አንፃርም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መብዛት በፋይናንስ አቅርቦት እጥረት የሚፈጠረውን የብድርና የገንዘብ አቅርቦት ችግር በመፍታት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖረውን ማኅበረሰብ አቅም ፈጥሮ እንዲሠራ እድል እንደሚፈጥርም ተሾመ አብራርተዋል።

በአሁኑ ስዓት ማይክሮ ፋይናንሶች በሕዝብ የንግድ ድርጅቶችና በግለሰቦች ባለቤትነት ተመስርተዉ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማኅበረሰብ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመላክተው የማይክሮ ፋይናንሶች ተበዳሪ ደንበኞች ቁጥር አምስት ሚሊዮን ደርሷል። በአሁኑ ስዓት በሥራ ላይ የሚገኙት የ38 ማይክሮ ፋይናንሶች ጠቅላላ ብዛታቸውን ወደ 76.5 ቢሊዮን ብር አሳድገዋል። አጠቃላይ ብድርም 51.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ከ2011 የንብረት ዕድገት ጋር ሲነፃፀር የ26 በመቶ ለውጥ አሳይቷል።

ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ጐን ለጐን በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ዓይነተኛ ሚና እንዳላቸው የሚጠቀሱት ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ናቸው። በተለይ አነስተኛ ቢዝነሶች የብድር አቅርቦት ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ያሉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ ከሚሰጡት አገልግሎት አንፃርም በተለይ በገጠራማ አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብ የተሻለ የብድርና የቁጠባ አገልግሎት ከማይክሮ ፋይናንሶች ነው። በአሁኑ ጊዜ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቁጥር 38 ደርሷል። አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች አንድና ከአንድ በላይ የሚሆኑ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ይንቀሳቀሳሉ።

በሌላ በኩል ተሾመ የማይክሮ ፋይናንሶች ወደ ባንክ የመሸጋገር አዝማሚያ ትክክለኛ እና ወቅታዊ ነው ያሉ ሲሆን፣ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አሁን ካሉት ባንኮች ከሚሰጡት አገልግሎት በተሻለና ተደራሽነቱ በተቀላጠፈ ሁኔታ ሥራዎችን የማከናወን አቅም እንዳላቸዉ ጠቁመዋል። ‹‹ባንኮች ያልደረሱባቸውን ቦታዎች ማይክሮ ፋይናንሶች በድህነት ለሚኖሩ ዜጎች አገልግሎት ስለሚሰጡ፣ የታችኛውን ማኅበረሰብ ወርዶ የመሥራት ልምዳቸውን እና ትስስራቸውን ተጠቅመው አሁን ካሉት ባንኮች የተሻሉ መሆን ይችላሉ›› ሲሉ ገልፀዋል።

ተሾመ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ አሁን ያለው የፋይናንስ አገልግሎት በጣም ዝቅተኛ እንደሆነና በመቶኛ ሲታይም ከ50 በመቶ በታች እንደሆነ ተናግረዋል። አሁን እየታየ ያለው የፋይናንስ ተቋማት መበራከት የአገልግሎት አሰጣጡን የተቀላጠፈ እንደሚያደርገውና በኅብረተሰቡ እጅ ላይ ያለው ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲገባም አስተዋፅኦ እንዳለዉ ፕሬዝዳንቱ አክለዉ ገልፀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here