የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አዲስ መልክ ፡ የኢትዮጵያ ቀን

0
1167
“በብዝኃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ ለ13ኛ ጊዜ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በአዲስ አበባ ከተማ አዘጋጅነት ከቀደሙት ዓመታት በተለየ መልኩ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበተረ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ፕሬስ ሴክረተሪ የሆኑት ፌቨን ተሾመ 13ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል በዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ እንደመከበሩ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከቀድሞ ለየት ያሉ መሰናዶዎችን እንዳደረገ እና በተለይም ሠላም እና አገራዊ አንድነት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ከቀናት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። በበዓሉ ውስጥ ከተካተቱ መርሓ ግብሮች መካከል ‹ኑ ለሠላም ቡና እንጠጣ› በሚል ኅዳር 27 የተዘጋጀው ላይ 10 ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች የታደሙበት በመስቀል አደባባይ የተካሔደው የቡና ሥነ ስርዓት ነው። ሥነ ስርዓቱን በ‹ጊነስ ወርልድ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ› ለማስመዝገብ ጥረት መደረጉን ፕሬስ ሰክሬተሪዋ ገልፀዋል። በተጨማሪም ‹ኅብር ኢትዮጵያ› በሚል የሙዚቃ ድግስ በጊዮን ሆቴል የተዘጋጀ ሲሆን፣ አንጋፋው አርቲስት አሊ መሐመድ ቢራን ጨምሮ ሚካኤል በላይነህ፣ ሮፍናን፣ ዳዊት ነጋ እና ጋጋ ስዩም የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል። ዝግጅቱ ለታዳሚዎች በነፃ የቀረበ ሲሆን ወደ ሙዚቃ ድግሱ ለመግባት የኢትዮጵያ ባሕላዊ ልብሶችን መልበስ ብቻ በቂ ነበር። በሙዚቃ ድግሱ ላይ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተለያዩ ብሔረሰቦችን ባሕላዊ ልብሶች በመልበስ የታደሙ ሲሆን ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ በተለያዩ ባሕላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች ሲዝናኑ አምሽተዋል። ለአዲስ ማለዳ አስተያየቷን የሰጠች ሐና የተባባለች የዝግጅቱ ታዳሚ ‹ሁሌም ቢሆን የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን እንደ ባሕል ቀን የባሕል ልብሶችን ለብሼ አሳልፈው ነበር› ብላለች። ሐና እንደምትለው በዓሉ ካለው ፖለቲካዊ እንደምታ ይልቅ በትምህርት ቤቶችም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የባሕል ልብሶች እና ሙዚቃዎች የሚቀርቡበት ቀን ሆኖ ይከበራል። በዚህ ዓመትም መግቢያው የባሕል ልብሶችን ለብሶ መቅረብ የሆነበት ነፃ የሙዚቃ ዝግጅት መደረጉ ለከተማው ልዩ ድባብ እንደፈጠረ ጠቅሳለች። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዓመታት በፊት በወሰነው መሠረት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የፀደቀበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ዛሬ ቅዳሜ፣ ኅዳር 29 ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም 30ሺሕ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ከ200 ሺሕ በላይ ከሁሉም ክልልች የመጡ ተወካዮች በተገኙበት በይፋ ይከበራል። በዝግጅቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የከተማው ከንቲባ ታከለ ኡማ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚገኙ ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here