የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 7.5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ብድር ከንግድ ባንክ ወሰደ

0
599

ተቋሙ በገንዘብ እጥረት የተነሳ ፕሮጀክቶች ለማቆም ጫፍ ደርሶ ነበር

ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ወድቆ የነበረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2012 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ያለበትን የብድር ወለድ ለመክፈል እንዲሁም ለህዳሴ ግድብ ግንባታ እና ለሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማስገንቢያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር መበደሩን ይፋ አደረገ። ይህንንም ተከትሎ ድርጅቱ ከንግድ ባንክ የወሰደው ብድር ወደ 271 ቢሊዮን ብር ገደማ ሲደርስ፣ አጠቃላይ ዕዳውን ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሞገስ መኮንን ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ኤሌክትሪክ ኃይሉ ብድሩን የተበደረዉ ለህዳሴ ግድቡ የግንባታ ፕሮጀክት ማስኬጃ፣ ለኃይል ማመንጫ ለተቋራጮች የሚከፈልና ኤሌክትሪክ ኃይሉ ያለበትን የብድር ወለድ ለመክፈል ነው። እንደ ኃላፊዉ ገለፃ፣ ተቋሙ ብድሩን ባይወስድ ከተለያዩ ተቋማቶች የሚያገኘዉን ሌሎች ብድሮች ሊያጣ እንደሚችልና በሥራ ላይ ያሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊጓተትና ሊቆም እንደሚችልም ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዉ ‹‹ተቋሙ ከዛሬ ሦስት ዓመታት በፊት ሊወጣው ወደማይችለዉ የእዳ ጫና ገብቶ ነበር›› ብለው የነበሩት ሞገስ፣ ባለፈዉ አንድ ዓመት ከነበረዉ የመመሥረቻ ገንዘብ በማሽቆልቆል የ13 ቢሊዮን ብር እዳ (ኔጌቲቭ) ገብቶ እንደነበር ኃላፊዉ ተናግረዋል።

ተቋሙ የነበረበትን የእዳ ጫና ለማቃለል ከአበዳሪ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር የብድር ወለድ መቀነስና የመክፍያ ጊዜ ማራዘሙንም ሞገስ ተናግረዋል።

ያለበትን የዕዳ ጫና ለማቃለል አዲስ ብድር መውሰድ ሁሌም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጤናማ ሆኖ ለመቆየት የሚጠቀመው ስትራቴጂ ነው ያሉት የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ፣ ተቋሙ በእጁ ያሉትን የግንባታ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ብድር መውሰዱ አይቀሬ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የከፋ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የብድሮቹን የመክፈያ ጊዜ ማራዘም እንዲሁም ተጨማሪ ካፒታል ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ማድረግ እና ሌሎች የረጅም ጊዜ የገንዘብ ምንጮችን መፈለግ ለንግድ ባንክም ሆነ ለኤሌክትሪክ ኃይሉ እንደሚበጅ የፋይናንስ ባለሙያው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ሞገስ እንደሚሉት ኤሌክትሪክ ኃይሉ ያለበትን የእዳ ጫና ለማቃለል ባለፈው ዓመት ማሻሻያዎችን እንዳደረገና አላስፈላጊ ያላቸዉን ፕሮጀክቶች እንዳቋረጠ አስታውሰዋል። ከተቋረጡ ፕሮጀክቶች ውስጥ በአፋር ክልል ይሠራ የነበረዉ መጤ አረምን አቃጥሎ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ፕሮጀክት አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ እስከዛሬ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎችን አገልግሎትና ክፍያ ኤሌክትሪክ ኃይሉ ከባለፈዉ ዓመት ጀምሮ በራሱ ማስተዳደር መጀመሩ ገቢው እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ደ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በመንግሥት ሊገነቡ ታቅደው የነበሩ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ከግሉ ዘርፍ ጋር በአጋርነት እንዲተገበሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት፣ ኤሌክትሪክ ኃይሉ የኃይል ማመንጫዎችን እንደማይሠራና ከዚህ በኋላ የሚገነቡ የኃይል ማመንጫዎች በግል ድርጅቶች እንደሚሠሩ መግለፁ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here