መንግሥት ማዳበርያ አስኪያስገባ አስመጪዎች የወደብ እንዲከፍሉ ተገደዱ

0
590

ማዳበሪያውን ማስገባት ለሚቀጥሉት ኹለት ወራት ይቀጥላል

የኢትዮጵያ መንግሥት 1.5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ እያስገባ መሆኑን ተከትሎ በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ የነበሩ ኮንቴይነሮች የወደብ ኪራይ እየከፈሉ በጅቡቲ ወደብ እንዲቆዩ ተደርገዋል።

ማንነታቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ በአስመጪ እና ላኪነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ጅቡቲ ወደብ የደረሱት እቃዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረግ ከተጀመረ ሦስት ሳምንት ሆኖታል። ይህም በመሆኑ ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ እና ኪሳራ መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

አስመጪዎቹ እንደተናገሩት፣ አንድ ኮንቴይነር ሲገባ በወደብ ሊቆይ የሚችለው ሰባት ቀን ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ሲቆይ በየቀኑ የሚከፈልበት በመሆኑ ኮንቴይነሮቻቸው ከማዳበሪያው ጋር አብረው እንዲገቡ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትን ቢጠይቁም፣ ምንም መፍትሄ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ይህ በቅርቡ የተከሰተው ችግር ከመፈጠሩ በፊት አንድ ኮንቴይነር ለማስገባት ከ8 አስከ 14 ቀን ይፈጅ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ከ40 አስከ 50 ቀናት መፍጀት መጀመሩን አስመጪዎቹ ገልፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ የገንዘብ እጥረት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ችግሩ ሊፈጠር እንደቻለም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አሸብር ዳዲ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ማዳበሪያው በትራንስፖርተሮች እንዲገባ እየተደረገ ሲሆን ከእነሱም መካከል እንደ ቢሳንሳ እና ዲ ኤች ኤል ያሉት ከፍተኛ እቃ የማመላለስ አቅም ስላላቸው የማጓጓዙ ሂደት እንዲፈጥን እየተሠራ ነው።

ማዳበሪያ የማስገባት ሂደቱ አስከ ኹለት ወር ሊዘልቅ እንደሚችል ኃላፊው ገልፀው፣ አጋዥ ድርጅቶች ከበዙ ከኹለት ወር በፊት የሚያልቅበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል።
በኮንቴይነር በቀን 11 ዶላር የወደብ ኪራይ ለኹለት ሳምንታት ከተከፈለ በኋላ የማይነሳ ከሆነ ክፍያው ወደ 22 ዶላር ከፍ የሚል ሲሆን፣ በሦስተኛው ሳምንት ደግሞ ወደ 33 ዶላር እንደሚያድግ እና ከዚያ በላይ እየቆየ ሲሔድ ንብረቶቹን መውረስ ድረስ የሚደርስ ሥልጣን ለወደቡ እንደሚሰጥ የሎጂስቲክ ድርጅት የሆነው የማርስክ ባልደረባ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ከዚህ በፊት ማዳበሪያ በሌሎች ወደቦች በኩል ይገባ የነበረ ሲሆን፣ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ ታስቦ በጅቡቲ ወደብ መደረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ይህ 1.5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ እየገባ ያለው በጊዜ ለአዝመራ እንዲደርስ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ ሁኔታ መደበኛውን የምልልስ ሂደት ማዛባቱንም አክለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት እቃዎች መጠን መጨመሩን ያስረዱት ኃላፊው፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ማዳበሪያ በዚህ ላይ መታከሉ ተጨማሪ የሎጂስቲክስ አቅም አስፈላጊ እንዲሆን አድርጓልም ይላሉ። በመሆኑም አጋዥ የትራንስፖርት ማኅበራትን ማሳተፍ እየጀመሩ መሆኑን እና ውል ተፈፅሞ በፍጥነት ማዳበሪያው እየተጓጓዘ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ጫናውን ለመቀነስ በመኪና ብቻ ሲመላለስ የነበረውን ማዳበሪያ በባቡር ማመላለስ መጀመሩን ኃላፊው ገልፀዋል።
ለጊዜው እንዳይገቡ ጫና እየተደረገባቸው ያሉት የሸቀጣ ሸቀጥ እቃዎች እና የተለያዩ የመለዋወጫ እቃዎች ላይ እንጂ እንደ መድኃኒት እና ከጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸው እየገቡ መሆኑን አሸብር ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here