ዳሰሳ ዘ ማለዳ (የካቲት 18/2012)

0
683

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስድስት ወራት ውስጥ 7 ነጥብ8  ቢሊዮን ብር አተረፈ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2012 ዓመት፣ በስድስት ወራት ውስጥ 7ነጥብ7 ቢሊዮን ብር ማትረፉን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።ኤጀንሲው እንደገለጸው ከሆነም ትርፉ ከባለፈው ዓመት ስድስት ወራት ጋር ሲነጻጸር ተመሳሳይ  እንደሆነም  አስታውቋል።በስድስት ወራት ወስጥ ትርፋማ ከሆኑት የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከልም  የኢትዮጵ ንግድ ባንክ ቀዳሚው ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ ኹለተኛ ደረጃ መያዙ ታውቋል። (ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በኮድ ሁለት ሲሰሩ የነበሩ የዶልፊን ቫን ተሽከርካሪዎች ጥያቄ ምላሽ መገኘቱ ተገለጸ ሲሆን በ2008 ባገለገሉ የዶልፊን ቫን ተሽከርካሪዎች የታሪፍ ውዝግብ ምክንያት ኤክሳይስ ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ያቀረቡት ቅሬታ መፈታቱን የጉሙሩክ ኮሚሽን ገለጸ። የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር  ደበሌ ቃበታ፣ ምንም እንኳን ባለንብረቶቹ የተወሰነውን ውሳኔ የተላለፉ ቢሆንም ኮሚሽኑ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተሽከርካሪዎቹን ወደ ኮድ ሶስት ወይም ኮድ አንድ እንዲቀይሩና የህዝብ ወይም የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ ጊዜ በመስጠት ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ አስቀምጧል ብለዋል።(ገቢዎች ሚኒስቴር)።

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር በአሜሪካ ሊካሂድ የታሰበው ስብሰባ ላይ እንደማትገኝ አስታወቀች። በአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ ሴክሬተሪ የተጠራውና በአውሮፓውያኑ የካቲት 27-28/2020 በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ ሊካሂድ ታስቦ የነበረው የሦስትዮሽ የድርድር መድረክ ኢትዮጵያ አትሳተፍም። የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባላማጠናቀቁ በተጠቀሰው ጊዜ በአሜሪካ በመገኘት ውይይቱን ማድረግ እንዳልተቻለ ጥሪውን ላደረገው የአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ ማስታወቁን የውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታውቋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የኮሮና ቫይረስ (ኮቪዳ 19) የስርጭት መጠን በየጊዜው የሚለያይ ቢሆንም ስጋቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ(ዶ/ር) የኮሮና ቫይረስ የስርጭት መጠን ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም የስጋት ደረጃው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ኢንስቲትዩቱ ቫይረሱን በተመለከተ በፅህፈት ቤቱ ትናንት በሰጠው ሳምንታዊ መግለጫ ላይ ገልፀዋል።ቫይረሱ የተስፋፋባቸው አገራት ከ28 ወደ ቁጥር ወደ 34 መድረሱን አስታውቀዋል። ይህም የቫይረሱ ስጋት ደረጃው ምን ያህል እጨመረ እንደመጣና ለኢትዮጵያም እየቀረበ መምጣቱን ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

“የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን” በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ለሚከናወኑ ተግባራት 10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ። ድጋፉ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ጋር በጋራ ለሚሠሩ ድርጅቶች የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የሚረዳ ነው ተብሏል። የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ፋውንዴሽን ድጋፍ አገራቱ የአንበጣ መንጋውን ለመዋጋት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።(ቢቢሲ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በተደራጀ ሁኔታ የኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ በሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት መሠረተ ልማት ላይ ዝርፊያ ሲፈጽሙ ነበሩ የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዙን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ገለጸ። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን የያዘው ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ አልማዝየ ሜዳ አካባቢ በደረሰው የኅብረተሰቡ ጥቆማ መሆኑንም አስታውቋል። (ኢቢሲ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ 104 ኢትዮጵውያን በዛሬው ዕለት የካቲት 18/2012 ከታንዛኒያ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ተመላሾቹ ኢሪንጋ በሚባለው ግዛት በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ የቆዩ መሆናቸውን በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል። በቅርቡ ሞሮጎሮ፣ ሩቩማ፣ ንጆም፣ ቤምቤያ እና ሶንግዌ በሚባሉ የታንዛኒያ ግዛቶች ታስረው የነበሩ 294 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል። (ፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ከ2012 ዓመት ጀምሮ የወረቀት ፈተና እድሜ እንደማይኖረውና ማርክ ወይም ውጤት  አስተካክሉልኝ የሚል ጥያቄም ቦታ እንደሚያጣ የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። በፈተና ዙሪያ እርማት ፣ፈተናውን ማስተዳደር፣ መፈተንና ውጤት አገላለጽ ድረስ ያሉ ሂደቶችን ዘመናዊ በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ የወረቀት ፈተና እድሜ እንደሚያጥር የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አርአያ ገብረእግዚአብሔር ገልፀዋል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here