የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ሕንጻ ግንባታ ተጀመረ

0
768

በ1 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር ወጪ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ሕንጻ ግንባታ ተጀመረ።
ሕንጻው ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ለተጠሪ ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤት አገልግሎት የሚውል ሲሆን፥ ለተጠሪ ተቋማት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች እንደሚኖሩት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኮምዩኒኬሽን ለአዲስ ማለዳ በላከዉ መረጃ ጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪም እንግዳ መቀበያ፣ የሥልጠና መስጫና የጥናት ሥራዎች ማከናወኛ ምቹ ክፍሎች፣ በአንድ ጊዜ ከ600 በላይ ሰዎችን የሚይዝ ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና የትራንስፖርት ሙዚየም ማእከላትን ያካትታል።

በተለይም ሕንጻው ዘመናዊ የኤሌክትሪክ፣ የውሃና ሜካኒካል መስመሮች ብልሽቶች ሲኖሩ፣ በወቅቱ መረጃ የሚሰጥ ቴክኖሎጂ የሚገጠምለት በመሆኑ የሕንጻው የአገልግሎት ደረጃና የአገልግሎት ዘመን ከፍ እንዲል ተብሏል።

ሕንጻው ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃት ከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፍ ተቋማት በአንድ ጣራ ስር እንዲገኙ ከማድረጉ ጋር ተያይዞ፣ ባለጉዳዮች ሳይጉላሉ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ እንደሚገመትም ተመላክቷል።

በፕሮጀክቱ ግንባታ ወቅት ከ500 ላላነሱ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ደግሞ ከ600 ላላነሱ ዜጎች የመሥሪያ ቦታ በመሆን የሚያገለግል ይሆናል።

ሕንጻው ከመሬት በታች ሦስት ወለሎች እና ከመሬት በላይ ደግሞ 21 ወለሎች ያሉት ሲሆን፥ በኹለት ዓመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል። ስምምነቱ ከዞንግ-ያንግ ኮንስትራክሽን ግሩፕ ኩባንያ ጋር እንደተፈረመም ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here