የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ፖለቲካ!

0
871

ከሰላም ማጣት፣ ሽብርተኝነትና የአየር ንብረት ለውጥ ጎን ለጎን የዓለም አራትን ጭንቅ ውስጥ የከተተው ኮሮና ቫይረስ አሁንም እየተስፋፋ ይገኛል። አገራትም በየራሳቸው መንገድ ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግና ሕዝባቸውን ለመጠበቅ የየበኩላቸውን ያሉትን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ግዛቸው አበበ ታድያ የኢትዮጵያን ሁኑታ አንስተው የአየር መንገዱን ‹በረራ አላቆምም› የሚል ውሳኔን እንዲሁም ቻይና የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚለው እንቅስቃሴ ላይ ማተዋልና ትኩረት ሊደረግ ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ። ማኅበራዊ ሚድያውም ነገርን ከማግነን መቆጠብ አለበት ሲሉ ያሳስባሉ። ኢትዮጵያም በሽታውን ለመቋቋም ከፍተኛ አቅም የሌላት መሆኑን አያይዘው አንስተዋል።

በቻይና የተቀሰቀሰውን በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ የመተንፈሻ አካል በሽታ ተከትሎ፣ በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጉዳይ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ከ” እና “ወደ” ቻይና የሚደረጉ በረራዎቹን አለማቆሙ ያለ እረፍት መነጋገሪያ እየሆኑ ያሉ ጉዳዮች ናቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሽታው በ24 አገራት መታየቱ እንደታወቀ ወደ ቻይና በረራ ከሚያደርግባቸው አምስት ከተሞች ውስጥ፣ ወደ አራቱ የሚደረጉ ሳምንታዊ በረራዎቹን በ33 በመቶ መቀነሱ፣ በቦይንግ 777 እና በኤርባስ A-350 የሚደረጉ አንዳንድ በረራዎችን በቦይንግ 787 መተካቱን፣ ‘ኳርትዝ አፍሪካ ዊክሊ’ (Quartz Africa Weekly) እና ‘ሲምፕል ፍላይንግ’ (Simple Flying) የተባሉ የመረጃ ምንጮች ወርሐ የካቲት ላይ ዘግበዋል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ በረራዎች መቀጠላቸው፣ አየር መንገዱ በረራዎችን ማቆም የሚለውን አስተሳሰብ አምርሮ በመቃወም የተለየ አቋም መያዙ በግልጽ እየታየ ነው።

በየሳምንቱ 35 በረራዎችን ወደ ቻይና የሚያደርገው አየር መንገዱ፣ በየቀኑ ለ24 ሰዓታት የመንገደኞቹን የሰውነት ሙቀት በኢንፍራሬድ ጨረር ክትትል እያደረገበት መሆኑ እና ከተለመደው ላቅ ያለ የሰውነት ሙቀት የሚታይባቸውን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑ ይታወቃል። አየር መንገዱ አጠቃላይ እገዳ ካልተጣለ፣ በአንድ አገር የሚጣል አገዳ ብቻውን ውጤታማ አያደርግም ባይ መሆኑን ‘አፍሪካን ኤሮ-ስፔስ’ (African Aero-Space) በተባለ ድረ ገጽ ላይ የቀረበ ቃለ ምልልስ ያሳያል።
ከዚህ በተጨማሪ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወልደ ገብረማርያም “… ቻይናን ማግለል አይኖርብንም። የቻይና ተሳፋሪዎችን ማራቅ አይገባም። ማድረግ ያለብን በዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ መሰረት ለመንገደኞቹ የጤና ምርመራ ማድረግ ነው…” ማለታቸው በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ መዘገቡን ተከትሎ፣ አየር መንገዱ ቫይረሱ የሚያስከትለውን ችግር ሳይሆን ዲፕሎማሲን ያስቀደመ ውሳኔ እየተሰጠ እንዳይሆን የሚል ስጋት እንዲሰፍን አድርጓል። በእርግጥ እዚህ ላይ የላቀ ኃላፊነትና የመወሰን መብት ያለው የጤና ሚኒስቴሩን ተጠቅሞ ትዕዛዝ መስጠት የሚችለውና የሚገባው መንግሥት እንጅ አየር መንገዱ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል።

አየር መንገዱ የመንግሥትን አቅጣጫ ካልሆነም ትዕዛዝ እየተከተለ የሚወስን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ከዚህ በኋላ ደግሞ ‘የሚታገደው በረራ “ከ” እና “ወደ” ቻይና ብቻ ነው ወይስ ቫይረሱ ተገኘባቸው የሚባሉ አገራትን ሁሉ እየተከታተሉ ተጨማሪ በረራዎችን ማገድ?’ ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ነው።

ዞሮ ዞሮ የአየር መንገዱ ኹለተኛ ውሳኔ የፖለቲካ (የካድሬዎች) ውሳኔ እንጂ በሕክምና ባለሙያዎች ዕውቀት ላይ የተመረኮዘ አይደለም የሚል ውዝግብ ተከፍቷል። በሦስትና ከዚያ በላይ በሚሆኑ የአገራችን ቋንቋዎች ስርጭት ያላቸው ቪኦኤና ቢቢሲ እንዲሁም በአማርኛ ስርጭት የሚያደርገው ዶቸቨለ፣ በየዕለቱ በሚባል ሁኔታ ስለ በሽታውና ከበሽታው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ሲያወሱ የአገር ቤት መገናኛ ብዙኀን በተለይም የመንግሥት እና የኢሕአዴግ ሚዲያዎች እየተባሉ የኖሩት ፋና እና ዋልታ ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ ነው ማለት ይቻላል።

ከበሽታው አስከፊነትና አደገኛነት አንጻር ሲታይ በተለይም በሽታው እንዴ ከተከሰተ በኋላ ለቁጥጥር አስቸጋሪ፣ ሕመምተኞችን ለማዳንም ከፍተኛ ሀብትና እውቀት የሚጠይቅ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ፣ በሽታው የዕለት ከዕለት ትኩረት መሰጠቱ የሚበዛበት አይሆንም። ነገር ግን በምዕራቡ ዓለም በተለመደው መንገድ፣ የተገኘውን ነገር ሁሉ ቻይናን ማጥቂያና ማብጠልጠያ ለማድረግ እንደሚሞከረው ሁሉ ይህን በሽታ ለዚያ ዓላማ ማዋል ለኢትዮጵያችን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። በእነዚህ የውጭ ንብረት የሆኑ መገናኛ ብዙኀን ላይ ‘….ታላቋ አሜሪካ የቻይና በረራዎችን በከለከለችበት ጊዜ ድሃዋ ኢትዮጵያ በረራዎችን ለማቋረጥ ዳተኛ መሆኗ ጥገኝነት የወለደው የፖለቲካ ውሳኔ ነው….’ የሚሉ ወገኖች፣ የትራምፕ መንግሥት ውሳኔ በቻይና ላይ ምክንያት እየፈለገ ከሚጥለው ማዕቀብና የቀረጥ ጭማሪ ጋር ተደምሮ ሊታይ የሚገባው የፖለቲካ ውሳኔ ላለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ሰዎች በቀጥታ ከቻይና ወደ አሜሪካ ምድር እንዳይገቡ በረራዎችን ቢያግድም፣ አሜሪካውያን ከቻይና ተነስተው በሌላ አገር አቋርጠው ወደ አገራቸው እንዳይመሰሉ መከልከል ስለማይችል፣ በሩን ሙሉ በሙሉ መዝጋት እንደቻለ ተደርጎ መታየቱ በጉዳዩ ውስጥ ፖለቲካ መጨመሩን ካለማስተዋል የሚመጣ ድምዳሜ ነው ሊሆን የሚችለው።

ከዚህ ሌላ አገራችን የሴራ ፖለቲካንና አናርኪዝምን እንደ መሣሪያ እየተጠቀሙ ‘የመታገል’ ልምድ ያዳበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከዓመታት በፊት የጀመሩትን በየሰበቡ ትርምስና ግጭት የመፍጠር አካሄድን አሁንም ለማቆም ያልቻሉና ለማቆምም የማይፈልጉ ሆነው ይታያሉ። እናም ይህን በሽታ ተመርኩዞ የሚፈጠሩ ወሬዎችን በመጠቀምም ትርምስ ሊፈጥሩ እየሞከሩ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።

በአሁኑ ጊዜ የአየር መንገዱ በረራ አለማቆሙን፣ በቻይና ውኀን ግዛት የሚገኙ ተማሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመመስ መንግሥት ፈቃደኛ አለመሆኑን፣ ወደ ቻይናና አካባቢዋ በሚደረጉ በረራዎች ላይ የሚሠሩ የአየር መንገዱ ሠራተኞች የሚያሰሙትን ቅሬታ በመጠቀም ፖለቲካዊ ቁማር ለመጫወት የሚፈልጉ ወገኖች መኖራቸው በግልጽ የሚታይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ማኅበራዊ ሚዲያው እየተጫወተው ያለው ሚና በእጅጉ ከፍ ያለ ነው። ነገር ግን አየር መንገዱ በረራ ቢያቆምና ተማሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ቢደረግስ፣ እነዚህ የሶሻል ሚዲያ ታጋዮች ዝም ይላሉን? የተማሪዎችን በገፍ መመለስ ተመርኩዘው አስበርጋጊና አሸባሪ የፈጠራ ወሬዎችን ከመንዛት ይቆጠባሉን?

እዚህ ላይ በዩክሬን በቅርቡ ያጋጠመውን ጉዳይ መመልከት ተገቢ ነው። ዩክሬን በቀለም አብዮት መንግሥት የቀየረች አገር ናት። ቻይና ውስጥ የተከሰተውን በሽታ ተከትሎ ዩክሬን ውስጥ የተቀሰቀሰው አመጽ በቀለም አብዮቶቹ ወቅት የሰፈነውና በለውጡ ማግስትም የቀጠለው ራስን ከሕግ የበላይ ማስቀመጥ የወለደው ጉዳይ ነው። ሐሙስ የካቲት 12/2012 ዩክሬን ከቻይና ውሃን ግዛት የወጣቻቸውን 45 ዜጎቿንና 27 የሌሎች አገራት ዜጎችን ወደ ምድሯ አስገብታ፣ በማእከላዊ ዩክሬን ፖልታቫ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኖቪ-ሻንዛሪ መንደር ወደተዘጋጀላቸው ማቆያ ያጓጓዘችበት ዕለት ነው።

‘አሶሲየትድ ፕረስ’ ይፋ ባደረገው ዜና በዕለቱ ተመላሾቹን የጫኑ አውቶብሶች ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው ዘግቧል። ዘገባው እንደሚያሳየው፣ የሰዎቹ ወደ አገራቸው መመለስ በእነሱ ላይ አደጋ የሚደቅን ሆኖ የተሰማቸው ዩክሬናውያን ወደ አውቶብሶቹ ድንጋይና ቤት ሠራሽ ተቀጣጣይ ፈንጅዎችን በመወርወር ተመላሾቹ ክትትል እየተደረገላቸው 14 ቀናትን ያሳልፉበት ዘንድ ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ እንዳይገቡ ለመከላከልም ሞክረዋል። ጉዞው እንዳይስተጓጎል፣ ተመላሾች ጉዳት እንዳይደርስባቸውና ተመላሾቹ ራሳቸውን ከአጥቂዎች ለመከላከል ሲሉ ከቦታው ሸሽተው (ተበታትነው) በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዳይደበቁ ለማድረግ በቦታው የተገኘው የፖሊስ ኃይልም የአመጸኞቹ ዒላማ ሆኗል።

በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው የተባሉት ሰዎች የመኪና ጎማዎችን በማቃጠል፣ ትራክተሮችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን መንገድ ላይ በመደርደር፣ መንገድ ለመዝጋት ሞክረዋል። አመጸኞቹ ያህን ጥቃት የተቀላቀለበት ተቃውሞ ያካሄዱት፣ የአገሪቱ ፕሬዘዳንትና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ ሰዎቹ ቻይና ውስጥ ለጉዞ ከመነሳታቸው በፊት ምርመራ ተደርጎላቸው ቫይረሱ ያልተገኘባቸው መሆናቸውን፣ ለሚቀጥሉት 14 ቀናትም ለብቻቸው ተቀምጠው እንደሚቆዩና ሙሉ ጤነኞች መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ ወደ ኅብረተሰቡ የሚቀላቀሉ መሆኑን እያሳወቁ ባሉበት ጊዜ ነው።

ግብታዊውንና ቆም ብሎ ማሰብ ያልታከለበት የዩክሬን አመጽ ምን ቀሰቀሰው? የአሜሪካው ‘ኤቢሲ ኒውስ’ ኃይል የቀላቀለው አመጽ የተቀሰቀሰው በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሰተራጨ ሐሰተኛ መረጃ ከፍተኛ ስጋትን በማስፈኑ ነው ብሏል። የዩክሬን ባለሥልጣናት አሳሳቹና አስፈሪው የፈጠራ ወሬ ማዕበል በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቀው፣ እንደተለመደው ሆነ ተብሎ ዩከሬንን የብጥብጥ ዒላማ ለማድረግ ነው ማለታቸውን ኤቢሲ ገልጿል። ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ በዩክሬን አምስት በኮሮና ቫይረስ የተለከፉ ሰዎች እንደተገኙ፣ ይህን መረጃ ያገኙት ከአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በተላከ ኢ-ሜይል እንደሆነ አስመስለው ወሬውን ስለነዙት፣ ወሬውን የሰማው ዩክሬናዊ ሁሉ በያለበት ለድንጋጤ ተዳርጓል።

ይህ ደግሞ ዓመጹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ብዙ ከተሞች እንዲዛመትና ተመላሾቹ ወደ እነዚህ ከተሞቹ ሊመጡ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬን ወልዶ አመጸኞች በየከተሞቻቸው የሚገኙ ሆስፒታሎች መግቢያዎችን በመቆጣጠር በመደበኛ ሥራቸው ላይ እክል እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ፖሊሶች ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እገዛ ያስፈልጋቸው ሲሆን፣ ከፖሊስ ጋር የተደረገው ግብግብ ቀኑን ቀጥሎ ለሊቱንም ያጋመሰባቸው አካባቢዎች ነበሩ።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ መረጃዎችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኀንና ልበ-ቅን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በኮሮና ቫይረስ የሚቀሰቀሰው በሽታ አስፈሪና አስቸጋሪ የመሆኑን ያህል፣ ስለ በሽታው መረጃዎችን ሲያሰራጩም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግና ለሕክምና ባለሙያዎች ሊተው የሚገባውን ለእነሱ መተው እንዳለባቸው ከዩክሬን ተሞክሮ መረዳት ይገባቸዋል። ተማሪዎች ለምን አልተመለሱም ብለው ብዙ ትችት የሚሰነዝሩና መንግሥትን በ‹ችላ ባይነት› የሚወቅሱ ሰዎች፣ ቻይና ውኀን የሚገኙ ወገኖቻችን ሲመለሱ ስለሚያወሩት ቀጣይ ወሬም ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል። የተማሪዎች መመለስና አለመመለስ ፈጽሞ የፖለቲካ ግብግብ ግብአት መሆን የለበትም።

አሁንም ቢሆን በአንዳንድ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በሽታውን የሚመለከቱት የተሳሳቱ መረጃዎች እየተነዙ ነው። ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንደገባና ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በአገራችን ውስጥ መኖራቸውን መንግሥት መደበቁን፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ እየተላከ የሚካሄደው የቫይረሱ ምርመራ ውጤታማ እንዳልሆነና ተጠርጣሪዎች ወደ ኅብረተሰቡ የሚቀላቀሉት በዘፈቀደ መሆኑን ወዘተ የመሳሰሉትን አደገኛ ውዥንብሮች የሚነዙ ወገኖች አልታጡም። ኅብረተሰቡ ማንነታቸው የማይታወቅና ከሙያው ጋር ትውውቅ የሌላቸው ሰዎች የሚነዙትን ወሬ ሰምቶ ከመደናገጥ ሊጠበቅ ይገባዋል። በወሬዎች መደናገጥና በተሳሳተ (በአሳሳች) መረጃዎች መጨነቅ ለማንም ለምንም አይበጅም። መፍትሔም አይሆንም። አንዳንድ ጊዜ ቪኦኤንና ዶቸቨለን በመሳሰሉ ሚዲያዎች የግል አስተያየታቸውን የሚሰጡ ባለሞያ ያልሆኑ አድማጮች የሚሰነዝሩትን አስተያየትም ወደ ሕዝብ ከመርጨታቸው በፊት ተገቢነቱን በጥንቃቄ ሊያጤኑት ይገባል።

የአገራችን አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች ተራ ወረርሽኞችን መከላከልና የዜጎቿን ሕይወት መታደግ አስቸጋሪ ሲሆኑባት በተደጋጋሚ የታየችው ኢትዮጵያችን፣ ይህ ሕመም በስፋት ቢከሰትባት ምን እንደሚውጣት ማሰብ ያለብን ከወዲሁ ችግሩ ወዲያ ማዶ እያለ ነው ሲሉ ይመክራሉ። ጣሊያን በምድሯ ላይ 79 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ስለተገኙና ኹለት ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው ሕይወታቸው በማለፉ፣ እየወሰደችው ያለችው እርምጃ ሲታይ የአገራችንን የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡት ምክር ውሃ የሚያነሳ ነው ማለት ይቻላል። በጣሊያን ሰሜናዊ አካባቢዎች የሚገኙ ኹለት ግዛቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል። ከተፈቀደላቸው ሰዎች በቀር ወደ ከተሞቹ መግባትና መውጣት አይቻልም።

በከተሞቹ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፣ ሊደረጉ የነበሩ የሴሪ-አ ጨዋታዎችም በዚሁ ምክንያት አልተካሄዱም። በአሁኑ ጊዜ የጣሊያን መንግሥት ይህን እገዳ በፖሊስ እያስከበረ ሲሆን፣ አስፈላጊ ከሆነ የጣሊያን ጦር ኃይልም ሊጨመርበት እንደሚችል ተነግሯል። በሽታው ይህን ሁሉ ጥንቃቄ ተሻግሮ መጠነኛ መስፋፋት ከማሳየቱ ግን አልቀረም። በትንሽ ቁጥር ቢሆንም የታማሚዎችና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውና የሚስተናገድባቸው ቦታዎች ተዘግተዋል። የስፖርት ውድድሮች ተመልካች በሌለበት ስቴዲዮም መካሄድ ጀምረዋል። ከዚህ ምን ትምህርት ይገኛል? የባለሙያ፣ የገንዘብ አቅም፣ የቴክኖሎጂና አስፈላጊ ግብአቶች እጥረት የሌለባት ጣሊያን እንዲህ ከተወጣጠረች፣ ብዙ ችግርና እጥረት ያለባት ኢትዮጵችን ችግሩ ቢከሰት የምትይዘውና የምትጨብጠው አታጣምን?

ዶክተር ዳውድ ሰዒድ፣ አሜሪካ ማዲሰን ከተማ ውስጥ በሚገኘው ዩስኮንሲን ዩንቨርሲቲ ውስጥ የተላላፊ በሽታዎች ፕሮፌሰር እና የተጓዦችን ጤና በሚመለከት የሚሠራ ክሊኒክ ዳይሬክተር ናቸው። ዶክተር ዳውድ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ላይ እየተጋበዙ ስለ በሽታውና ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት ብዙ መረጃዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ዶክተሩ በኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካልን ከሚያጠቁ ስድስት ዓይነት ቫይረሶች አንዱ መሆኑን ይጠቅሱና፣ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ በደንብ የሚታወቁና 40 ከመቶ ለሚሆነው ቀላል ጉንፋን መንስኤ ናቸው። ሌሎቹ ቫይረሶች ያልተለመዱ ዓይነትና የሚያስከትሉት ችግርም ጠንከር ያለ ነው ብለዋል።
ዶክተር ዳውድ ኮሮና ቫይረስ ከዚህ ቀደምም ተከስቶ እንደነበረና በቻይና “ሳርስ” በሳውዲ ዓረቢያ “መርስ” እየተባሉ ሲጠሩ የነበሩት ሕመሞች ይኸው ቫይረስ የቀሰቀሳቸው እንደነበሩ አስታውሰዋል። ሕመሙ እንደ ማንኛውም ጉንፋን መተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ቢሆንም፣ በኮሮና የሚቀሰቀስው ሕመም አተነፋፈስን አስተጓጉሎ፣ ትንፋሽ አሳጥቶ፣ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ ሕመም ነው ብለዋል። ኮሮና ቫይረስ እንደ ብዙዎቹ የቫይረስ ሕመሞች ከእንስሰት ወደ ሰው የሚተላለፍ (በትንፋሽ፣ በመነካካት፣ በመመገብ…) እንደሆነና ኮሮና ቫይረስ ከሌሊት ወፊች ተላልፎ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳለ ዶክተሩ ተናግረዋል።

አያይዘው አዲሱን ሕመም በሚመለከት መንግሥት የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች አገራችን ያላት የመስኩ ባለሙያዎችን ብዛትና በአገር ቤት የሚገኘውን ቴክኖሎጂ መሠረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ. እንደ ችግር መታየት ያለበት የኮሮና ቫይረስ ወደ አገር ቤት መግባት ወይም አለመግባት ሳይሆን አገሪቱ ችግሩ ቢገጥማት ችግሩን ለመዋጋት የሚያስችል ቁሳቁስ በበቂ መጠን መኖርና አለመኖሩ፣ በቂ በጀት ለመመደብ መቻልና አለመቻል፣ በየክልሉና በየከተማው በቂ ባለሙያ መኖርና አለመኖሩ ነው በማለት የመንግሥት ውሳኔ ለውጭ ግንኙነት መጨነቅን ወይም የፖለቲካ ጉዳይን ተመርኩዞ ወይም ለፕሮፓጋንዳ ግብአት ሲባል መወሰን እንደሌለበት አበክረው አሳስበዋል።

ዶክተሩ በሽታው ሲጸና ተጠቂዎች ትንፋሽ እንደሚያጥራቸውና (መተንፈስ እንደማይችሉ) በሰው ሠራሽ መተንፈሻ መሣሪያዎች ካልታገዙ እንደሚሞቱ በመናገር፣ እነዚህ ስርዓተ እስትንፋስን የሚያግዙ መሣሪያዎች በአገሪቱ (በአዲሰ አበባም ሆነ በክልሎች) በበቂ መጠን አሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። አሉ የሚባሉት መሣሪያዎችም በተለያዩ ችግሮች የደከሙ ሕመምተኞችን ድጋፍ በመስጠት ጥቅም ላይ ስለሚውሉ ሥራ ፈትተው የማያውቁና ተጨማሪ ጫና ለመሸከም የሚበቁ አይደሉም ሲሉ ዶክተር ዳውድ ያስጠነቅቃሉ።

በዕለተ ሰንበት የካቲት 15/2012 አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው የአፍሪካ የጤና ሚኒስትሮች አስቸኳይ ስብሰባ፣ ቫይረሱ በአኅጉሩ ላይ ችግር እንዳያስከትል የሚረዳ ውሳኔ በጋራ እንደወሰነና የተቀናጀ የመከላከል ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ዝግጁነት ለመፍጠር እንደሚረዳ ይታመናል። የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም በትዊተር መልዕክታቸው፣ ድርጅታቸው ለአፍሪካ አገራት ተገቢውን አገዛ እንደሚደርግ ቃል ገብተዋልና ይህም ተጨማሪ ጥንካሬን ይፈጥራል። ዶክተር ዳውድን የመሳሰሉ ባለሙያዎች ሙያዊ አስተዋጽኦ ተጨምሮበትም ውጤታማ ሥራ እንደሚሠራም ይታመናል። ዶክተር ዳውድ ሰዒድ በቅርቡ ሙያዊ እገዛ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፣ ሙያዊ አበርክቶም አድርገው ወደ አሜሪካ መመለሳቸው ይታወቃልና ሊመሰገኑ ይገባል።
ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here