የጉዞ አድዋ ተጓዦች ቅዳሜ ዕንዳ አባ ገሪማ ገዳም ይደርሳሉ

0
711

የሰባተኛ ዓመት የጉዞ አድዋ ተጓዦች ዛሬ የካቲት 21/ 2012 ዕንዳ አባ ገሪማ ገዳም እንደሚደርሱ ተገለፀ።
ገዳሙ በአድዋ ዞን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ተጓዦቹ በዛሬው ዕለት ከሚደርሱበት እንዳ አባ ገሪማ ገዳም 90 ኪሎ ሜትሮችን እንደሚርቅ ለማወቅ ተችሏል።
63 ተጓዦች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ ያሉት የጉዞ አድዋ መሥራች እና አስተዳዳሪ ያሬድ ሹመቴ፣ አንድ ተጓዥ ብቻ በመንገድ ላይ በውሻ ከመነከሱ ውጪ ምንም ጉዳት የደረሰበት ተጓዥ የለም። ሕዝቡም በመልካም አቀባበል እና በልዩ እንግዳ ተቀባይነት ስሜት ሲመለከተን ነበር ብለዋል።
ቀሪዎቹን 90 ኪሎ ሜትሮች አብረውን ለመጓዝ እና የታሪኩ አካል ለመሆን 14 ሰዎች ቅዳሜ የካቲት 21 ይቀላቀሉናል ያሉ ሲሆን፣ በዛው ዕለት ተጓዥ ቡድኑ ከሚገኝበት የሃ ወደ እንዳ አባ ገሪማ ገዳም እንደሚጓዙ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ዕንዳ አባ ገሪማ ገዳም በጦርነቱ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሰውበት ስፍራ ሲሆን፣ በዓለማችን በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ቀደምት መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝበት ስፍራ በመሆኑ ቡድኑ እዛ እንደሚያድር ለማወቅ ተችሏል። ቡድኑ ከዚህ በኋላ በቀን 45 ኪሎ ሜትሮችን እንደሚጓዝ የገለጹት ያሬድ፣ ጦርነቱ በተካሄደበት ሶሎዳ ተራራ ላይ የካቲት 23 እንደሚደርስም ተናግረዋል።
በተራራው ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማስቀመጥ እና ችቦ በማብራት ከሕዝቡ ጋር በአንድነት እንደሚያከብር የተገለፀ ሲሆን፣ የዛኑ እለት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለስ ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here