ሂጃብ መልበስ የማይጋርደው መብት!

0
764

‹‹እንደዚህ እንደለበስሽ ነው ሥራ የምትገቢው?›› ሲል በጥርጣሬ ዐይን ልብ ብሎ ቃኛት። ራሷን መለስ ብላ አየች፤ ያጎደለችው ነገር እንደሌለ እርግጠኛ በመሆን ሳታንገራግር፤ ‹‹አዎን! ምነው?›› ብላ መልሳ ጥያቄ አቀረበች። ‹‹ይቅርታ ለፕሮቶኮል ስለማይመች እንዲህ ለብሰሽ ደንበኛ ልታስተናግጂ አትችይም። እናም ሥራውን ለመስጠት ይከብደናል›› አላት።

ይህቺ ሴት የተጠየቀችው ልትሠራ በምትወደው ሥራ እና በሂጃቧ መካከል እንድትመርጥ ነው። ‹የማንነቴ አካል፣ የእምነቴም ማሳያ ነው› ስትል ሂጃቡን መርጣ ሥራውን ትታ ለመሄድ ተገደደች። ሂጃቧን ሳታወልቅ ህልሟን የምታሳካበትን መንገድ ስታስብ፣ ስታወጣና ስታወርድ እነሆ ዓመታት ነጎዱ።

ይህች አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻት ባለታሪክ ሥሟን መጥቀስ አልፈለገችም። ነገር ግን ሂጃብ በመልበሳቸው ምክንያት በሴቶች ላይ የሚደርስን ተጽእኖ ትቃወማለች። በኢትዮጵያ ሂጃብ በሚለብሱ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጫና ባህር ማዶ ከሚሰማው አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ነው ባይባልም፣ በተቋማትና በአሠራራቸው የሚደርስባቸው ተጽእኖ ግን በዝምታ እየታለፈ ስለመሆኑ ትስማማለች። በሂጃቧ ምክንያት በ‹ይክረም› ያቆየችውን ሕልሟንም በቁጭት ታነሳለች።

የዓለም የሂጃብ ቀን መከበር የጀመረው በተመሳሳይ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና መሠረት በማድረግ ነው። ሂጃብ በመልበሳቸው ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አገራት እንግልት የሚደርስባቸው ብዙ ሴቶች አሉ። ይህም የሥነ ልቦና እንዲሁም የአካልም ጭምር ጥቃትን ያካተተ ነው። ከፍተኛ የሚባል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ ሥራቸውን እንዳይሠሩ የተከለከሉ፣ ከአትሌቲክስ ውድድር ውጪ የሆኑ ሴቶች ታሪክም ለሰሚ አዲስ አይደሉም።

የዓለም የሂጃብ ቀን አጀማመር
ናዝማ ካኃን የባንግላዲሽ ተወላጅ ስትሆን እድገቷ አሜሪካ ኒውዮርክ ነው። ሂጃብ በመልበሷ ምክንያት በአካልና በመንፈስ በተለያየ መልክ ጫና ያደረባት ናዝማ፣ በሕይወቷ ብዙ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ግድ ብሏት ነበር። በተለይም በአሜሪካ በመንትያዎቹ ሕንጻዎች ላይ ከደረሰው የሽብር ጥቃት በኋላ፣ ሥሟን ቀይረው ‹ኦሳማ ቢላደን› የሚሏት ነበሩ።

በትምህርት ቤት፣ በሥራ ፍለጋ፣ በየእለት እንቅስቃሴና በመንገድ ላይ በምታደርገው እግር ጉዞ ሳይቀር መገለሎች አልፎም ስድቦች ደርሰውባታል። ነገር ግን ልትሰበርና አንገቷን ደፍታ የምትባለውን ልትሰማ አልፈቀደችም። ሂጃብ በመልበሷ የማንነቷ አካል የምትለውን ሃይማኖቷን አንጸባረቀች እንጂ፣ በሂጃብ ምክንያት ልታጣው የሚገባው መብት፣ ሰብአዊ ክብርና እኩልነት እንደሌለ ስለምታውቅ፣ ድምጿን ለማሰማት ሳትውል ሳታድር እንቅስቃሴ አደረገች።

እንዲህ አደረገች፤ እርሷ የሚሰማትን ጉዳት ለሌሎች ለማሳየት በማሰብና ከእርሷም በኋላ የትኛዋም ሂጃብ የምትለብስ ሙስሊም ሴት እንደዛ ያለ ፈተና እንዳይገጥማት መትጋት። እናም በ2013 በአውሮፓውያን አቆጣጠር በዓለም ላይ ሁሉ ለሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታይ ለሆኑ እንዲሁም ላልሆኑ ሴቶች ሁሉ ጥሪዋን አስተላለፈች። በዚህም ሁሉም ሂጃብን ለአንድ ቀን እንዲለብሱ ነበር የጠየቀችው።

ታድያ በ8 ቀናት ውስጥ 67 አገራት ከሚገኙ በርካታ ሴቶች ለጥያቄዋ በጎ ምላሽ አገኘች። ይህም እንቅስቃሴ አድጎ ስለ እስልምና የማያውቁ ሰዎች በደንብ እንዲያውቁ የማድረግ ሥራውንና ሂጃብ ላይ ያለውን የግንዛቤ እጥረት ለማስተካከል አጋዥ ሆናት።

በዚህ መሠረት ያኔ አንድ ብሎ መከበር የጀመረው የዓለም የሂጃብ ቀን፣ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ ተከብሯል። አሁን ላይ 190 የሚሆኑ አገራት ይህን እንቅስቃሴ እየተከተሉ ይገኛሉ። ሐሳቡንም ከተለያዩ አገራት ዜጎች በተጓዳኝ ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችና ዝነኞች ሁሉ የሚደግፉት ሆኗል።

የሂጃብ ቀን በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሂጃብ ቀን ባሳለፍነው ወር ጥር 26/2012 ነው የተከበረው። ቀኑን በዛ መልክ አስቦ ለመዋል እንቅስቃሴ ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዷ የሆኑት ሱመያ መሐመድ ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል። የሂጃብ ቀንን የማክበር ሐሳብ ከኹለት ዓመት ገደማ በፊት ታስቦ እንደነበር የሚያስታውሱት ሱመያ፣ ያኔም የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች ነበሩ ይላሉ። ተሳክቶ በአዲስ አበባ መከበር የቻለው ግን ዘንድሮ ነው።

በኢትዮጵያ ሂጃብ የሚለብሱ ሴቶች መገለል እንደሚደርስባቸው ሱመያ ሳይጠቅሱ አላለፉም። ምንአልባት ብዙዎችን ባይመስላቸውም በተለይ አካታችነት አለመኖሩ ትልቁ ችግር እንደሆነ ነው ያወሱት። ኢትዮጵያ ውስጥ በቀኑ የሂጃብ ቀን ታስቦ እንዲውል መደረጉም አንድም ይህን አካታችነትና እውቅና ማግኘት የሚገባ እንደሆነ ለማስታወስ ነው ይላሉ።

‹‹አካታችነት አይስተዋልም። ኢትዮጵያ እንዲመጣ የፈለግነውም ሂጃብ የምናደርግ ሰዎች እውቅን እንዲሰጠን ለማድረግ ነው። በዓላማም ዓለም አቀፉን ሐሳብ አንግበን ነው።›› ብለዋል። በተለይም በሂጃብ መልበስ ምክንያት የሚደርስ መገለልጋን ለመጋፋትና ለመዋጋት።

ጉዳዩን ጮክ ብሎ በይፋ ያለማውራት እንጂ ችግሩ በአገራችን ኢትዮጵያም አለ የሚሉት ሱመያ፣ ሁሌም የምንኖርበት ስለሆነ ለምደነው ዝምታን መርጠናል ይላሉ። ያም ብቻ ሳይሆን መደበኛ ተደርጎ እየተቆጠረም ሲሉ ያስረዳሉ። የሂጃብ ቀንን ማክበርም አንድም ዝምታውን መስበር አለብን ብለው የገቡበት ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
ለሂጃብ የሚሰጠው አመለካከትና ያለው አተያይ፣ ሂጃብ በሚለብሱ ሴቶች ሥነልቦና ላይ ተጽእኖ ያደርሳል። ሂጃ ለበሱ ሴቶች በሥራ ወይም የተለያየ ክህሎት የሌላቸው ተደርገው ይታሰባሉ። ይህ ደግሞ በተግባር አንዳንዱ ተቋማት ላይ በሂጃብ ምክንያት በሮች መዘጋታቸው፣ ሴቶቹ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ቢሆኑ እንኳ ገፍተው እንዳይወጡና ስኬታ ሆነው አቅማቸውን እንዳያሳዩ መሰናክል ይሆንባቸዋል።

‹‹በትምህርት ቤት ሂጃብ የለበሱ ሴቶች ወይመ ሂጃቡን ወይም ትምህርታቸውን እንዲመርጡ ይገደዳሉ›› ሱመያ እንዳሉት። በሂጃብ ምክንያትም ከትምህርት ቤት እንዲወጡ የተደረጉ ሴት ተማሪዎች ስለመኖራቸው አስታውሰው ጠቅሰዋል። ይህም ታድያ በመጀመሪያና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን፣ በከፍተኛ የትምህርተ ተቋማት ድረስም የዘለቀ ችግር ነው። የግንዛቤ እጥረት አለ ሲሉ አክለዋል።

‹‹የሴቷ ተሳትፎ ላይ ይህ ትልቅ ችግር ይፈጥራል። አካታችነት የለም። አገሪቷ ውስጥ ያሉ የአለባበስ ደንቦች/ኮዶች ሂጃብን ከግምት ያስገቡ አይደሉም።›› ሲሉ ይወቅሳሉ።

ለዚህም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጀምሮ በግል ዘርፎች ሁሉ የሚታይ ነው። አካታችነት አለመኖሩም በፖሊሲ፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤት፣ በመገናኛ ብዙኀን ወዘተ የሚቀርቡ ደንቦች ማነቆዎች ናቸው፤ እንደ ሱመያ ገለጻ። እነዚህ ተቋማት ቢሆኑም በውስጣቸው የሚገኙ የማኅበረሰቡ ነጸብራቅ የሆኑ ሰዎች ናቸውና፣ ለማኅበረሰቡም ግንዛቤ ማስጨበጥና በቋሚነት በጉዳዩ ሐሳቦችን መስጠት ተገቢ እንደሚሆን አውስተዋል። የተለያዩ መገለሎችና መገፋቶች አሉ።

ታድያ የተቋማት አካታችነት ስርዓት መፍጠርና ግንዛቤ መስጠት ወሳኝ የሆነው፣ ሂጃብ መልበስ ላይ ክልከላ ማድረግ አንደኛ የሰውን መብት መጋፋት ስለሆነ ነው። ሱመያ ከዚህ ጋር አያይዘው ሂጃብ ሃይማኖታዊ መሠረት እንዳለው ይጠቅሳሉ። ‹‹ሂጅብ እንደ አምልኮ ነው የሚታየው። አንዲት ሴት ለፈጣሪዋ ያላትን ታዛዣነት የምታሳይበት መንገድ ነው። እናም የእስልምና እምነት ተከታይ ሴቶች ሂጃብ እንዳይለብሱ መከልከል የሃይማኖት መብትንም የሚጋፋ ነው።›› ሲሉ አብራርተዋል።
ታድያ የሂጃብ ቀንን ወደ ኢትዮጵያ ያመጡበት ምክንያትም ግንዛቤን ለማሳደግና ንግግር እንዲጀመር ማድረግ በመፈለግ መሆኑን ሱመያ ደጋግመው ጠቅሰዋል።

አንድም ቀን ጉዳይ ሆኖ አያውቀምናም፣ ለተቸገሩት ሴቶች ድምጽ መሆን መቻልንም አስበውበት ነው። በተጨማሪም በሴቶች መብት ላይ የሚሠሩ እንቅስቃሴዎች ወይም አክቲቪዝሞች ላይ ለሙስሊም ሴት መብትና እኩልነት መጠየቂያ ተጨማሪ አውድ ሆኖ ያገለግላል በሚል እምነት ነው።

ጥናታዊ ወረቀቶች ምን አሉ?
በኢትጵያ የሂጃብ ቀን ለመጀመሪያ በተከበረበት ክዋኔ፣ ሦስት ጥናታዊ ሥራዎች ቀርበዋል። እነዚህም በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ታድያ ወረቀቶቹ አንድም ለመድረኩ ይመጥናል፣ አንድም ለታዳሚ ከምሉዕ የሚጠጋጋ መልዕክት ያስተላልፋሉ በሚል የተመረጡ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል አንዱ ወረቀት የሂጃብን መሠረት የሚቃኝ ሲሆን፣ ሂጃብን እንደ መጤ አድርጎ መውሰድ ትክክል እንዳይደለ ያስረዳ ነው። በተለይም የአረብ ባህል ነው የሚል እምነት ቢኖርም፣ በኢትዮጵያም ባህል እንደሆነ ጥናቱ ለማስረዳት ሞክሯል። በዚህም በኢትዮጵያ የኖሩና የተለመዱ ሻሽና ነጠላን አሉና፣ ሂጃብም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ዘመናትን የኖረና የተሻገረ ነው እንጂ እንግዳ ባህል አይደለም፤ እንደ ጥናት ወረቀቱ። ‹‹እናም መጤ ነው ብሎ ማሰብ አይገባም። ሂጃብ የኖረና የነበረ፣ ያለም ነው። መገፋት የሚጀምረው የአረብ ባህል አመጣችሁብን በሚል ስለሆነ።›› ሱመያ አሳስበዋል።

የቀሩት በመድረኩ የቀረቡ ጥናቶች በአንድ ጎን ሂጃብ እንዳይለበስ መከልከል ከሕግ አንጻር ምን ዓይነት መብቶችን ይጋፋል የሚለው የተነሳ ሲሆን፣ በሦስተኛው ጥናታዊ ወረቀት ሂጃብና ሂጃብ የሚለብሱ ሴቶች በመገናኛ ብዙኀን እና በጥበቡ ዘርፎች እንዴት ተስለዋል የሚለው ነው።

ሱመያ የመጀመሪያው በኢትጵያ የሂጃብ ቀን የተሳካ እንደነበር በማታወስ፣ ምንም እንኳ በአዲስ አባ ብቻ የተከበረ ቢሆንም፣ በቀጣይ አገር አቀፍ የማድረግ እቅድ እንዳለ ጠቅሰዋል። በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ መፍጠርና ሴቶችም ሂጃብ በመልበሳቸው ከሕልማቸው የሚገድባቸውና ከተቋማት የሚያስገፋቸው እንዳይሆን ለማድረግ፣ በዚሁ ንቅናቄና ጥረቱ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here