የእቴጌ ጣይቱ “የሴት ሠራዊት”፤ ያልተነገረው የሴቶች ገድል በአድዋ

0
1513

የአድዋ የድል በዐል ሲታሰብ ከጥቂት ተጠቃሽ ሴቶች በስተቀር የወንዶቹ ጀግንነት ጎልቶ ይሰማል። ቤተልሔም ነጋሽ የተላያዩ መጻሕፍትንና ጽሁፎች በማጣቃስ በአድዋ ጦርነት ላይ ከ20 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ ሴቶች በመሳተፋቸውን በማስታወስ፥ ሴቶች የተጫወቱትን ዘርፈ ብዙ ዓይነተኛ ሚና ያስታውሳሉ፤ ሌላው ቢቀር “የሴቶች ሠራዊት” መሪ የነበሩትን እቴጌ ጣይቱን ማክበርና ማድነቅ የሚታይ ሐውልትና መታሰቢያ ማኖር እንደሚገባ በአጽንዎት ይገልጻሉ።

“ የምታስፎክር ሰንጋ ገለሌ
በጦር መካከል ሳይሆኑ አያሌ
በጥይት ገዳይ ነጭ ብርገድሌ
የሴት ወንድናት ሸዋረገድ ገድሌ”
ይላል በአምስት ዓመቱ የጠላት ወረራ ጊዜም አኩሪ ጀብዱ የፈጸሙትን የአርበኛዋን የሸዋረገድ ገድሌን ታሪክ የሚተርክ መጽሐፍ ለገበያ መቅረቡን አስመልክቶ በታኅሣሥ ወር 2009 ዳንኤል ክብረት “አርበኛ ሸዋረገድ ገድሌ” በሚል ርዕስ ካስነበበው መጣጥፍ የተወሰደ ግጥም።

የመጨረሻውን ስንኝ ከተፃፈበት ወቅት አንፃር ይቅርታ የሚደረግለት ሲሆን በተፃፉትና በተዘከረላቸው ጥቂት ሴት አርበኞች ታሪኮች ሁሉ ሴት ሆና የሚል ትኩረት የመስጠት ነገር ይታያል፤ በወቅቱ ከነበረው አስቸጋሪ መልክዓ ምድር፣ ሴቶች ከነበሩበት ልጅ ወልዶ የማሳደግና ደካሞችንም የመንከባከብ ኃላፊነት አንፃር ሁሉን ጣል አድርጎ ወደ ጦርነት መሄድ ቀላል ባለመሆኑ ይህ ድርብ አድናቆት ሴትን አሳንሶ የማየት ሳይሆን እውነትነትም አለው።

ፀደይ አለኸኝ የተባሉ ፀሐፊ በታዲያስ ድረ ገጽ ላይ በታተመው “ንግሥቶች፣ ሰላዮችና አገልጋዮች፡ የኢትዮጵያ ሴቶች የዓውደ ውጊያ ታሪክ” በተሰኘ ሰፋ ያለ መጣጥፍ እንዳተቱት በአድዋ ጦርነት የተሳተፈው የኢትዮጵያ ጦር ከያለበት ተሰባስቦ የመጣ ገበሬው ከወታደሩና ከከበርቴ ቤተሰብ ሆ ብሎ ሲወጣ ብቻውን አልመጣም አብዛኛው ሚስቱን ይዞ ዘምቷል። እነኝህ ባሎቻቸውን ተከትለው የመጡት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም አቅም የነበራቸው ዘማች ሴቶች በሲቪል አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ተዋጊም ሆነው ተሳትፈዋል።

ፀሐፊዋ ታሪክ አጥኝዎችን ጠቅሰው እንዳስቀመጡት ከ20 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ ሴቶች በአድዋ ጦርነት እንደተሳተፉ ሲነገር ተሳትፏቸው ስንቅ በማዘጋጀት፣ ቁስለኛ በማከም ብቻ ሳይወሰን በአማካሪነት፣ በሰላይነት፣ በአስተርጓሚነት ሲሠሩ ሌላው ቀርቶ የመሳፍንት ወገን የሚባሉ ሴቶች እኩል ከአገልጋዩች ጋር በመሰለፍ ለአገር ሲሆን የመደብ ልዩነት ቦታ እንደሌለው አስመስክረዋል።

አድስ አድማስ ጋዜጣ የካቲት 26/2006 ‘ያልተዘመረላቸው የአድዋ ጀግኖችና ዓውደ-ውጊያዎች’ በሚል ባሳተመው መጣጥፍ ለምሳሌ ካልተነገረላቸው ጀግኖች አንዷ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ናቸው ይለናል። እቴጌ የውጫሌን ውል ሲቃወሙ፣ “እኔ ሴት ነኝ፤ ጦርነት አልወድም። ግን እንደዚህ ዓይነት ውል ከምቀበል ሞትን (ጦርነትን) እመርጣለሁ” በማለት አፄ ምኒልክን ለጦርነት አነሳስተው በጦርነቱ ቦታ ስለፈጸሟቸው በርካታ ገድሎች ያለመነገሩ ያሳዝናል” ይላል። በበኩሌ ይህን የእቴጌይቱን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ስሰማ “ጦርነቱን በይፋ ያስጀመሩት/ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጁት እቴጌ ጣይቱ መሆናቸውን ምነው ሳይነግሩን” ብዬ ነበር።

እቴጌይቱ በርካታ የ”ሴት ሠራዊት” አባላትን ያስከተሉ፣ ራሳቸው ባላቸውን ተከትለው የዘመቱ ሲሆን 3 ሺሕ ጠብ መንጃ 600 ፈረስ እንደነበራቸው ፀሐፍት ይጠቅሳሉ።

እዚህ ላይ መጥቀስ የሚያስፈልገው ታሪክ ፀሐፊዎች ለራሳቸው ባመቻቸው መልኩ ታሪክን ሊጽፉ መቻላቸው እንዳለ ሆኖ ከጊዜው ርቀት አንፃር በወቅቱ ሊኖር ከሚችለው የመረጃ ወሱንነትና ታሪክ ፀሐፊነት ዕውቀትና ዝግጅት የሚጠይቅ በመሆኑ የሚወጡት ታሪኮችና ጦርነቱን የተመለከቱ ገድሎች ሁሉንም ተሳትፎ ያካተቱ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። ስለሆነም ከጦርነቱ ገድልና ጀግንነት ትረካ የተረሱት ወይም ብዙ ያልተነገረላቸው ሴቶች ብቻ አለመሆናቸው ጥያቄ የለውም ።

ለምሳሌ ከአድዋ ጦርነት እጅግ አሰቃቂና ከኹለቱም ወገን ብዙ ሺዎች ያለቁበት የምንድብዳብ ውጊያ ዋና ተዋናይ የነበሩት ወጣቱ ጄነራል ፊታውራሪ ገበየሁ ምንም የሠሩት ገድል እንዳልተነገረላቸው ከላይ የጠቀስኩት የአዲስ አድማስ መጣጥፍ አስነብቧል። መጣጥፉ ጨምሮ እንዳተተው ፊታውራሪ ገበየሁ “ደረታቸውን ሰጥተው የጠላትን ጦር መግቢያ መውጪያ በማሳጣት ሲተገትጉ፣ በጥይት ተመትተው ሞቱና እዚያው ምንድብዳብ ተቀበሩ። በመቃብራቸው ላይ ምልክት ስላልተደረገ በትክክል የት እንደተቀበሩ እንኳ አይታወቅም፤ በተቃራኒው ግን ጣሊያኖች ጀኔራል ዳቦርሜዳ ሞቶ በተቀበረበት ሥፍራ በድንጋይ ላይ ሥሙን ጽፈው ስለተው፣ አሁን ድረስ ታሪኩ ይታወሳል” ብሏል።

ግለሰቦችና ጀግኖችን ትተን እንደቡድን ስናይ ግን የሴቶች ተሳትፎ በአብዛኛው “ስንቅና ትጥቅ በማቀበልና ቁስለኞችን በማከም፣ ጦር ሜዳ ድረስ አብረው በመሔድና በመዝመት ምግብ በማብሰል አገልግለዋል” በሚል ብቻ ተጠቃሎ የተቀመጠ ነው።

በኋላ ላይ የሴቶች ተሳትፎ አንሶ መቅረቡ ያስቆጫቸው ፀሐፍት የተገለፀው ውስን ተሳትፎ ራሱ ባይኖር ምናልባት በጦርነት የማሸነፍ ታሪክ ላይኖር እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ምክንያቱም ሳይበላ የሚዋጋ አልነበረምና፤ ፀሐፌ ትዕዘዝ ገብረስላሴ ሁኔታውን ሲገልፁት
“አፄ ሚኒሊክ በአዳራሽ እቴጌ ጣይቱ ባለሟሎችዋን በእልፍኝ ወይዛዝሩን ይዘው ግብሩ አንድ ቀን ሳይጎድል ይዘምታሉ። ከዘመቻ ላይ ጠጁ ማሩ አለመጉደሉ ስለምንድ ነው ያልክ እንደሆን ይህን ታሪክ መመልከት ነው። በስድስት ድንኳን እንጀራው ሲጋገር ሲያድር በአራት ድንኳን ወጡ ሲሠራ ሲያድር ግብሩ ይጎድል ይመስልሃል”
እንዳሉት ከአዲስ አበባ ተነስቶ የጠጅ በርሜልና የኩሽና ዕቃ ይዞ የዘመተው ሰልፈኛ ከአዲስ አበባ ተነስቶ 800 ኪሎ ሜትር የሸፈነ የተባለው እነኝኽ መቶ ሺሕ እንደሚጠጋ የተነገረለት የምኒልክን ጦር የመመገብ የቀን ተቀን ሥራ የሠሩ ሴቶችንም የያዘ ነው። ይህ አስተዋጽኦ ይነገር ዘንድ ያነሰ ሆኖ ያየው ማነው?
በዕውቀቱ ስዩም ለምሳሌ በአንድ መጣጥፉ “እቴጌ ጣይቱ ዘማቹን ሁሉ ብትሞት ልጆችህን እኔ አሳድግልሃለሁ” ማለታቸው ለዘማቾች ትልቅ ተስፋን ሰጥቶ እንዲዘምቱ ያደረገ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበር ጠቅሶታል።

የሴቶች ታሪክ አልተነገረም በሚለው ተስማምተን ከተነገረላቸው ጥቂቶች መካከል የተወሰኑትን ጽሁፌን ላብቃ።
“ቀሪን ገረመው ፤ የአርበኞች ታሪክ” በቀኛዝማች ታደሠ ዘወልዴ ተጽፎ በ1960 ታትሞ የነበረና እንደገና በ2008 በድጋሚ የታተመ ራሳቸው ፈረንሳይ ለትምህርት ከነበሩበት መጥተው ወደ አርበኝነት የተቀላቀሉ ታሪክ ፀሐፊ በተወሰነ መልኩ ስለ ሴት አርበኞችና አስተዋጽኦ አበርካቾች ጠቅሰዋል። ለምሳሌ በአንድ ምዕራፍ በመጽሐፉ (ገጽ 369 – 378) የሸዋረገድ ገድሌን ታሪክ አስቀምጠዋል።
በመፅሐፉ መጨረሻ በአባረነት ከያዙዋቸው ፎቶና መግለጫዎች መካከልም ሴቶችን ያነሱበት የሚከተሉት ይገኙበታል።

“የጠላት ተገዥ በመምሰል ለአርበኞች ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስ ጥይትና ሌላም መሣሪያ በማቀበል የሚረዱ የውስጥ አርበኞች ነበሩ። ከእነዚህም መከከል ለዕለት መተዳሪያቸው እየሠሩ በሚያገኙት ገንዘብ ምግብና ልብስ መድኀኒትና የሩቅ ማሳያ መነጽር እየገዙ ለአርበኞች ይልኩ የነበሩት አቶ አምዴ ፈሪድና ባለቤታቸው ወይዘሮ እሌኒ ይገኙባቸዋል።”

“የጠላት ግልምጫና ቁጣ ሳያስደነግጣቸው ለአገራቸው ነፃነት በቆራጥነት የተዋጉና የአዲስ ዓለምን የፋሽስት ምሽግ ያፈራረሱት የአርበኞች መሪ ነበሩ” ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ “ፆታዋ እንስት ቢሆንም ሙያዋ ግን የእውነተኛ ወንድ ተግባር የሆነው የመንዝና የተጉለት አርበኛዋ ወይዘሮ ዘውዲቱ ግዛው።”
አልፎ አልፎም ቢሆን እንደሚጠቀሰው በጦርነቱ ሴት አርበኞች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ከባሎቻቸው ጋር ወደ ጦርነቱ ከመጡት ሴቶች በተጨማሪ እቴጌ የሴቶች ሠራዊት አስተባብራ ምግብ፣ መጠጥ እና ሕክምና ለተዋጊዎቹ ያቀርቡ ነበር። ከዛ ባለፈም ጣልያኖች ባረፉበት አካባቢ በመሔድ ይሰልሉና መረጃ ያቀብሉ ነበር። ለኢትዮጵያውያን ድል ማድረግ ትልቅ ኣስተዋጽዖ ያደረገው የጠላቶችን የውሃ ምንጭን ማቋረጥ የእቴጌ ጣይቱን ብልሀት ያሳየ ድርጊትም ነበር። ፉከራ፣ ሽለላ፣ ቀረርቶ በማዜም ተዋጊዎች በርትተው ዓላማቸውን ሳይዘነጉ እንዲዋጉ ሴቶቹ ድጋፍ ይሰጡ ነበር። ይህ ሁሉ ጦሩን ተቀላቅለው የተዋጉትን ሴቶች ሳንዘነጋ ነው።

ዛሬ ላይ ሆኖ የእያንዳንዷን ሴት የጦርነቱ ቀጥታና ተዘዋዋሪ ተሳታፊ ታሪክ ለማሰባሰብም ይሁን ለመፃፍ ጊዜው የረፈደ ቢመስልም፣ አንድ ነገር ማድረግ ግን ይቻላል “የሴቶች ሠራዊት” መሪ የነበሩትን እቴጌ ጣይቱን ማክበርና ማድነቅ የሚታይ ሐውልትና መታሰቢያ ማኖር፥ ይህን ማድረግ በዚያ ጦርነት ላይ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱትን ሴቶች ሁሉ ማክበርና ማድነቅ ስለሚሆን።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here