ከአማራ ያለፈ ሕዝባዊ ተቀባይነት የሚማትረው አብን

0
682

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ልክ የዛሬ ሳምንት ነበር፣ በካሄደው ምርጫ የቀድሞ ሊቀመንበር የነበሩትን ደሳለኝ ጫኔን (ዶ/ር) በበለጠ ሞላ የተካው። ከዚህም ባሻገር የተለያዩ መዋቅራዊ ለውጦችን አካሂዷል። ከምክትል ሊቀመንበርነት አንድ ደረጃ ከፍ በማለት ፓርቲውን በመሪነት የተረከቡት በለጠ፣ ፓርቲውን ከመጪውን አገራዊ ምርጫ ፈተና የማሻገር የቤት ሥራ ከፊታቸው ተደቅኗል። የአዲስ ማለዳው ተወዳጅ ስንታየሁ በዚህና ተያያዥ በሆኑ የፓርቲው ጉዳዮች ላይ ከሊቀመንበሩ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፤

በቅድሚያ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ሆነው ስለተመረጡ እንኳን ደስ አለዎ?
አመሰግናለሁ

እስከአሁን ያለውን የአብንን ጉዞ እንዴት ይገመግሙታል?
አብን ከተመሠረተ አንድ ዓመት ከ8 ወር ሆኖታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ ሥራዎችን አከናውነናል። የመጀመሪያው አማራዊ ንቅናቄ መፍጠር ነው። እንደሚታወቀው የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ትርክት ውስጥ የኖረ ሕዝብ ስለነበር፣ በአማራ የብሔርተኝነት እሳቤ የተፈጠረ ፓርቲ ሲመሠረት፣ ወደዛ ለመግባት ጊዜ ያስፈልገው እንደነበር እንገነዘባለን። ከኢትዮጵያዊነት እሳቤ ወጥቶ በአንዴ የአማራ እሳቤዎችን ማምጣት አስቸጋሪ ጉዳይ ነበር።
ስለዚህ ሰፊ ሥራ ይጠይቀን ነበር። በጣም ሰፊ ሥራም ሠርተናል። ከ600 በላይ ሕዝባዊ ውይይቶችን አድርገናል፤ በአማራ ክልል፣ አዲስ አበባ እንዲሁም ከክልል ወጪ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች አድርገናል፤ ለምሳሌ እንደ ድሬዳዋና ቤኒሻንጉል። ከ600 ሺሕ በላይ አባላትን ለመመዝገብም ሞክረናል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አሉን። አሁን ላይ በርካታው የእኛ ሕዝብ የድርጅታችንን ዓላማ ተቀብሎ፣ የዚህ የትግል አካል ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በአንድ ዓመት ከስምንት ወር ውስጥ ሰፊ የሚባል ንቅናቄ ፈጥረናል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማሳረፍ ጥረት አድርገናል። በራሳችን መንገድ ከኢትዮጵያም አልፎ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት ሞክረናል። ኢትዮጵያ ውስጥና ከዛም ውጪ ያሉ ዓለማቀፍ ተቋማትን ስለአማራውና ስለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለማስገንዘብ ሠርተናል። ሰነዶች አዘጋጅተን አማራጭ ሐሳቦችን ለሕዝባችን ለማስተዋወቅ ሞክረናል። እነዚህን በማድረግ የተሻለ አማራዊ ንቃት እንዲፈጠር፣ አማራው ተደራጅቶ መታገል እንዳለበትና በዛም ጥያቄዎቹን ማስመለስ እንደሚችል ለማስገንዘብ ችለናል። እና ዛሬ ላይ አብን ሰፊ የሆነ ሕዝባዊ ተቀባይነት አለው፤ በተለይ በአማራው ዘንድ።

በአማራው ብቻ ሳይሆን፣ የአማራ ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያን አንድነት የሚፈልጉ ልኂቃን የሞራል ድጋፍ ይሰጡናል። ምክንያቱም በአማራነት ብንታገልም፣ ርዕያችን ለኢትዮጵያ የሚሆን ነው። ሕዝባችን ከደረሰበት መዋቅራዊ በደል ተላቆ፣ ራሱን ሆኖ፣ ጥያቄዎችን አስመልሶ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕቀፍ ደግሞ እኩል ከሌሎች ጋር ተሳታፊ የሚሆንበትን፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለሰላም አስተዋጽኦ የሚያደርግበትን ነገ ነው የምንፈልው። ይህን ርዕያችን በሚዲያዎችና በውይይት መድረኮች ላይ፣ ለሕዝብ እንዲሁም ለመንግሥት ለማስገንዘብ ጥረት አድርገናል።

ሌላው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጥሩ ነገር ይመጣ ዘንድ ውይይት እጅግ አስፈላጊ ነው። በውይይት ግማሽ መንገድ መጓዝ እንችላለን ብለን እናምናለን። ሁሉም ኃይሎች ወደ አንድ መድረክ በመምጣት ሀቀኛና ተከታታይ ውይይት ካደረግን፤ የተወሰኑ ጥቄዎች መልስ ያገኛሉ ብለን እናምናለን። ይህን በመገንዘብ ከአማራ እና ከኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የተውጣጡ፣ የጋራ ፎረም መንግሥት ፈጥሮላቸው ውይይት እያደረጉ ነው፣ ከአሁን በፊት ኹለት ጉባኤዎች አድርገናል። ይህም መቀጠል አለበት ብለን እናምናለን። በሠለጠነ አግባብ ልዩነታችንን ጠብቀን፣ ዞሮ ዞሮ አንድ አገር ውስጥ ነው ያለነውና፣ የተለያዩ ፍላጎቶች ቢኖሩንም፣ አንድ ሊያደርገን የሚችል ጉዳይ ላይ ተነጋግረን፣ የጋራ መቆሚያ ሠርተን ኢትዮጵያ የምትድንበትን መንገድ መፍጠር አለብን ብለን በጽኑ ስለምናምን፣ ይህንን ለማሳካት የምንችለውን እናደርጋለን።

ከአማራው ውጪ ሕዝባዊ ተቀባይነት ያገኛችሁት የት ነው?
አሁን ሁሉም ነገር በሕዝብ ደረጃ ማስቀመጥ አይቻልም። በርካታ የፖለቲካ አደረጃጀቶችም አሉ። ድጋፍ የሚያደርጉልንም በድርጅት ወይም አንድ መልክ ባለው አደረጃጀት ደረጃ ሳይሆን፣ ልሂቃን የተማሩና ፖለቲካሊ አክቲቭ የሚባለው ማኅበረሰብ ነው። እኛ ከአሁን በፊት ላደረግናቸው አንዳንድ በጎ እርምጃዎች አድናቆት ሰጥተዋል፣ በርቱ ብለውናል።

እንደምናውቀው የዛሬ ዓመት ቡራዩ ላይ የተፈጠረውን እናስታውሳለን። እንዲሁም የጌዴኦ ሕዝብ መፈናቀል፣ ጣፎ ላይ የሆነውና የአዲስ አበባም ጉዳይ አለ። በእነዚህ ላይ ይዘን የወጣነው አቋም እና የወሰድናቸው እርምጃዎች፣ አማራውን ብቻ ሳይሆን ከአማራው ውጪ ያለውን ጭምር ወደ እኛ እንዲያተኩር አስችሏል። ቡራዩ ላይ የሆነውን ስናስታውስ፣ በማግስቱ ምግብና ውሃ ይዘን በዛ ተገኝተናል።

በአካባቢው ጥቃት የደረሰባቸው የጋሞ ተወላጆች መሆናቸውን እናውቃለን። ግን ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ወገኖቻችን ናቸው። ማንም በጎ ሕሊና ያለው ጥቃት ተፈጽሞባቸው ማየት አይፈልግም። እኛም እንደ ድርጅት ያንን ማየት አንፈልግም። ስለዚህ ድጋፍ አሳይተናል። በጌዴኦ መፈናቀል አሰቃቂ በነበረ ጊዜ ተደባብሶ ለስምንት ወር አካባቢ ከቆየ በኋላ፣ እኛ ይፋ አድርገናል መግለጫ ሰጥተናል። ብዙ ጩኸት ስለተፈጠረም የመንግሥት ባለሥልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በቦታው ተገኝተዋል። ያ እንዲሆን እኛ አነሳስተናል ማለት ነው። ያ ከሆነ በኋላ የጌዶኦ ተወላጅ ምሁራን፣ ልኂቃን፣ ፖለቲከኞች የወሰድነውን እርምጃና ለሕዝብ ድምጽ መሆን ስለቻልን አድናቆታቸውን ሰጥተውናል። ለገጣፎ በላያቸው ላይ ቤት የፈረሰባቸው ሰዎች አሉ። አማራ ብቻ አይደሉም፤ የሌላ አካባቢ ተወላጆችም አሉ። ጉዳዩ አግባብ እንዳልሆነ በወቅቱ መግለጫ አውጥተናል። ይህም ቅቡልነት አትርፎልናል።

ይህ ሕዝብ እንዲቀበለን ብለን የምናደርገው አይደለም። ፍትህ ፍትህ በመሆኑ ብቻ መከበር እንዳለበት ሁሉ፣ ኢ ፍትሐዊ ድርጊቶችም ኢ ፍትሐዊ ስለሆኑ ብቻ ልናወግዛቸው ይገባል። ይህን በመገንዘብ የወሰድነው እርምጃ ነው።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ብንሆንም፣ ፍላጎታችን በኢትዮጵያ ልክ ነው ያለው። አማራ በኢትዮጵያ የትኛውም ጥግ አለ። ባለበት ሁሉ መብቱ ተጠብቆ እንደ ማንኛውም ዜጋ በእኩልነት፣ የሚስተናድበትን፣ በፍትህ አደባባይ ሲቆም እኩል ሆኖ ቋንቋው፣ ባህሉን የሚያዳብርበትና ማንነቱን የሚገልጽበትን እድል ማረጋገጥ ነው የምንፈልግው። ይህን ስናደርግ ሌሎች ሕዝቦችም በኢትዮጵያ የሚገባቸውን ሳያጡ ተሳታፊ እንዲሆኑ መሻት እኛ ጋር አለ። እና ይህን የተረዱ ኃይሎች ይደግፉናል። እገሌ እገሌ ብዬ የምጠራቸው አደረጃጀት ግን አይደሉም፤ ሕዝብ ነው።

በመጀመሪያው ዓመት ጽንፈኛ በሚባል ደረጃ ነበር ሰው የሚያስባቸው። ከሆነ ጊዜ ወዲህ ግን ለዘብ እያላችሁ ይመስላል። የእውነት ለዝባችኋል? የነገሩኝ የፓርቲው ስኬት እያለ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔን መቀየር ለምን አስፈለገ? ለዘብተኝነቱ ካልተወደደ ነው እንጂ ይሄ ተለያየቶ መቅረብ ያለበት ጥያቄ ነው። ሲጀመር አብን ጽንፈኛ አልነበረም፣ አሁንም አልለዘበም። አስተሳሰቡ ለምን መጣ የሚለውን ግን ማብራራት ይቻላል። አማራ ላለፉት ሃያ በላይ ዓመታት እንደ አማራ የመደራጀት ነጻነት አልነበረውም። ለዚህም ነው በርካታ የብሔር አደረጃጃት ፓርቲዎች በፖለቲካው ማእቀፍ ተሳታፊ ሆነው ስናይ፣ የአማራ ድርጅትን ግን አላየንም። ፍላጎት ሳይኖር ቀርቶ አይደለም። ግን ስርዓቱ በራሱ አማራውን የሚገፋ ስለነበር፣ አማራው ወደፊት መጥቶ ጠንካራ ንቅናቄ እንዲመሠርት እድል አልነበረውም።

በእርግጥም የአማራ እሳቤ ከኢትዮጵያ ጋር የታሸ ነው። በኢትዮጵያ አገር ግንባታ ውስጥ፣ የሌሎችን ሚና በማሳነስ ሳይሆን፣ አማራው ሰፊ ተሳትፎ ነበረው። አገር በመገንባትና ነጻነትን ጠብቆ በማቆየት ሚና ተጫውቶ አልፏል። እናም ሕዝቡ የኢትዮጰያዊነት እሳቤ እንዲላበስ ሆኗል።

ይህን ትልቅ ማንነቱን በአገር የሚያስብ ሕዝብ፣ በአንዴ ወደ ብሔር ማንነት ውስጥ ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ነው። አማራው ራሱ አይቀበለውም ነበር። ዛሬም ድረስ ፈተናችን ነው። ብዙ ብንሠራም የሚቀር አለ። እናም ከረር ያለ አማራ ንቅናቄ ሲፈጠር ለብዙዎች አስደንጋጭ ነበር። ለስርዓቱ እንዲሁም ለአማራውም ጭምር፣ ከረርና ጠንከር ተብሎ መሠረታዊ ጥያቄዎች መስተናገድና መመለስ አለባቸው፣ አማራው በዚህ አግባብ በደል ደርሶበታል የሚል ንቅናቄ ወደ መድረክ ሲመጣ ብዙዎችን አስደንቋል።

ሰዎች ግራ መጋባታቸው አልቀርም። በርካታ የኦሮሞ ድርጅቶች እንዳሉ ይዘነጋዋል ወይም ለምዶታል። አማራው ሲደራጅ ግን እንደዛ አልሆነም። ስለዚህ የእኛ ከረር ያሉ ንግግሮች፣ ገለጻዎች ጽንፈኛ እንደሆንን እንዲያስብና በዛ እንዲፈርጀን ያደረገ ይመስለኛል። እኛ ግን እንደዛ አይደለንም። ንግግሮችም የግለሰብ ስሜት ይሆናሉ። ከዛ ውጪ ግን ርዕያችንና ውስጣዊ ፍላጎታችን የምንናፍቀውና የምንታገልለት፣ እኩልነት፣ ሰላም፣ ፍትህና ልማት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ነው ያጣው።

ከዛ ውጪ ብዙዎቻችን የፖለቲካ ልምድ የለንም፤ እኔን ጨምሮ። ወደዚህ ትግል ስንመጣ ሕዝባችን ተበድሏል፣ ልንታገልለት ይገባል ብለን ነው። ስሜታዊ ሆነን ሊሆን ይችላል። ከትላንት ዛሬ ብዙ ነገር ተምረናል፤ ከዛሬ ደግሞ ነገ ብዙ እንማራለን ብለን እንወስዳለን። ስለዚህ ትላንትና በሚዲያ ወይም በመድረክ ስንወጣ፣ አንዳንድ ነገሮች ብለን ሊሆን ይችላል። ያ ግን በጽንፈኝነት ሊያስረፍጀን አይገባም።

አንደኛ የተባለውን ነገር አውድ መረዳት መቻል አለብን። ቃላትን ነጥለን ወስደን የተባለበትን አውድ ወደጎን ከተውን ትርጉሙ ሌላ ነው የሚሆነው። በእኛም ላይ የሆነው ይህ ነው። ሰፊ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ተሠርቷል። የሚሠሩብን አካላት በርካታ ናቸው። አደረጃጀታችንን የማይደግፉና አማራ ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖረው የማይፈልጉ ነው። እና እኛ የምንናገረውን ነጥሎ በማውጣት፣ ከአውዱ በመነጠል የራሳቸውን ትርጉም በመስጠት ወይም በማጋነን ሌላ ስዕል እንዲፈጠር አድርገዋል።
እና አብን ለዘበ ከተባለ ትርክቱ ለዝቦ ሊሆን ይችላል፤ መጀመሪያ ወደ ፖለቲካው መድረክ ስንመጣ አዲስ ጉዳይ ነበርን። ወዲያው ሰፊ ንቅናቄ ፈጥረናል፣ በየእለቱ ዜና መሆን ችሎ ነበር። ዛሬም እንደዛ ነው። አብን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ክስተት ነው፤ ያኔም (ከአንድ ዓመትና 8 ወር በፊት) አሁንም። ደግሞ እንማራለን። ለዝበናል ከተባለ፣ ምንአልባት የበለጠ ማስተዋል የተመላ ፖለቲካ በመተግበራችን ነው። ኃላፊነት የሚሰማን መሆን አለብን፣ የጩኸት አካል መሆን አንፈልግም። የጩኸት አካል በመሆን የምናተርፈው ነገር እንደማይኖር እንገነዘባለን። የሰከነ ፖለቲካ መሥራት አለብን፤ ይህ አሸናፊ ያደርገናል። የሌላው ነውጥ አካል መሆን አንፈልግም፤ አልነበርንም።

እኛ ራሳችንን እንገመግማለን። ንግግሮችን ይሁን ቅስቀሳዎችን፣ ከሕዝብ አንጻር እንዴት ታዩ የሚለውን እንገመግማለን። እርምጃም እንወስዳለን። አንድ ዓመት ከ8 ወር ቀላል ጊዜ አይደለም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ረጅም ጊዜ እንደመሄድ ነው። ልምድ እንወስዳለን። ገምግመንም የወደቅንበትን ደግመን ላለመሥራት እንሞክራለን። በዚህ ሂደት ነው የምንማረው። እና ዛሬ ላይ በትላንት አቋም ልንገኝ አንፈልግም፤ ወደፊት መምጣት አለብን። ከአማራው ውጪ ያለውን ሕዝብ ድጋፍ የሚያስገኝ ድምጸት፣ ቅርጽና አቋም ያስፈልገናል።

ያን መላበስ ስለቻልን ይመስለኛል፣ እንጂ በጥያቄዎቻችን ላይ ወደኋላ አላልንም። ጥያቄዎቻችን ትላንት የነበሩ ዛሬም እንዳሉ ናቸው። የተፈቱ አይደሉም። አብን እንደ ድርጅት ለዝቧል ከተባለ፣ ጥያቄዎቹን ጥሏል ማለት ነው። ጥያቄዎቻችን ወሳኝ ናቸው፣ ትግል ይፈልጋሉ። እየታገልንም ነው። መልስ አልተገኘም፣ ወደፊትም እስኪመጣ ቆራጥ የሆነ ትግል እያደረግን እንቀጥላለን።

ከትላንት አንዳንዶች ከጩኸት፣ ከነውጥና ጽንፈኝነት ጋር ገምተውን ይሆናል። ስህተት ነበር። ፕሮግራማችንን አላዩም። ንግግሮቻችንን አልተከታተሉም፣ ቀርበው አላወቁንም። ቀርበው ካወቁንና ያኛው አስተሳሰባቸው ተንኖ፣ አብን እንዲህም ነው ብለው በጎ ነገር ከያዙ አሸንፈናል ማለት ነው፤ ጥሩ ነው።
ሌላው ለውጥ ያስፈልገን ነበር። በፖለቲካ ውስጥ በየወቅቱ አዳዲስ ነገር ይመጣል። ከዛ ጋር ፍጥነት ጠብቀን መጓዝ አለብን። የኢትዮጵያ የፖለቲካ እርምጃ ዛሬ የሚከፍተውን አዲስ ምዕራፍ ዛሬ መያዝ ካልቻልን፣ ወደኋላ የምንቀር ከሆነ፣ አጠቃላይ የፖለቲካ አካሄዳችን ይበላሻል። በብዛት ወጣቶች ያሉበት ድርጅት ነው።
እንደሚታወቀው ከሰኔ 15 ወዲህ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይም የአማራው ፖለቲካ ትንሽ ፈተና ገጥሞታል። ይሄ የሚካድ አልነበረም። እሱ እኛ ላይ ቀጥታ ጫና አልነበረውም። ቀጣይ ምርጫ እየመጣ ነው። ተጠናክረን መጠበቅ አለብን።

አንድ ነገር ብቻ ግልጽ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ያደረግነው ሽግግር [ከደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) መለወጥ] አስደናቂ የሆነ ነው። ለውጡ ፍጹም ሰላማዊና ወንድማዊ ተግባቦት የነበረው ነው። በዛ መንፈስ ነው ለውጡ የተደረገው። በሕዝባችን ዘንድም ደስታ ፈጥሯል። አገር ወዳድ ለሆነ ዜጋም ጥሩ መንፈስ ፈጥሯል። ሰላማዊ ባይሆን ጩኸቱ ይወጣል። ግን እንደዛ አልነበረም።

በዚህ ላይ የሚነሱ ነገሮች ግን ነበሩ፤
ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚነሳው ውሃ የሚያነሳ አይደለም።

ግን እሱን ብናጠራው። ለምሳሌ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ያልሆነ ሰው ወደ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገባ የሚለውስ?
ማእከላዊ ኮሚቴ ሃምሳ አባላት አሉት። አምስቱ ተለዋጭ ይሆናሉ። ስለዚህ አስፈጻሚው ከሃምሳው ይወሰዳል። ደንባችን እንደዛ ነው። ከደንብ ውጪ የሠራነው ነገር የለም። ሌላው ነገሮች ተጋንነው እንደሚወጡ ይጠበቃል። ያልሆኑ ነገሮች ተባሉ ይባላል። ትንሹ በጣም ጉልህ ሆኖ ይወጣል።

እንጂ በመካከል ምንም አለመግባባት አልነበረም?
የሐሳብ ልዩነትኮ ሊኖር ይችላል። ፖለቲካ ውስጥ ነው ያለነው። አንድ እሳቤ ሊኖር አይችልም። ሃምሳ ሰው ካለ ሃምሳ ዐይነት እይታዎችና አስተሳሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በጎ ነገር ነው። አንድ ዓይነት እሳቤ ወይም የአንድን ሰው እሳቤ ሃምሳ ሰው ላይ በማስፈን፣ ባዶ የሆነ ፖለቲካ ነው የሚሆነው። ወደፊት አያራምድም፣ አያስጉዝም። ክርክር መኖር ደግሞ መልካም ነው፤ ፖለቲካ ውስጥ።

እንደ ኢሕአዴግ ፓርላማ ሁሉም እጁን አውጥቶ አጽድቆ ወይም ተቃውሞ የሚወጣበት ሁኔታ ፖለቲካችንን እንደጎዳው አይተናል። የእኛ እንደዛ እንዲሆን አያስፈልግም። ብዙ ሐሳቦች ይቀርባሉ፣ የሐሳብ ግጭቶች ይኖራሉ። ክርክሮች በፖለቲካ ባህላችን ያልተለመደ ከመሆኑ አንጻር በሌላ እይታ ሊታይ ይችላል፤ እንደዛ ግን አይደለም።

ቀደም ብለው ለውጥ ያስፈልጋል ብለውኝ ነበር። ብዙ የተሳካላችሁ ነገር ካለ ለውጥ ለምን አስፈለገ
አሁን ያደረግነው ለውጥ ደሳለኝን በበለጠ መተካት አይደለም፤ የመዋቅር ለውጥ ነው። ወሳኙ ነገር እሱ ነው። መጀመሪያ የፖለቲካ ድርጅት ስንመሠርት የነበረን መዋቅራዊና የፖለቲካ ግንዛቤ፣ ዛሬ ያለን አንድ አይደለም። ትላንት የሠራነው ዛሬ ላይ ብዙ የማያስኬድ ሆኖ ያገኘነው አለ።

ለምሳሌ፣ በፊት የምክር ቤት ዓይነት መዋቅር ነበረን። ምክር ቤቱ በየትኛውም የፓርቲ መዋቅር ውስጥ የለም፤ የምክር ቤት አባል። በ3 እና 4 ወር ይሰበሰባል የአስፈጻሚውን ሥራ ይገመግማል፣ ከዛ ይበተናል፣ የራሱን ሥራ ይሠራል። የፓርቲ ሥራ ላይ አልነበረም። ይሄ መለወጥ አለበት። ቁጥሩም ማነስ አለበት፤ ከ58 ወደ 50 ወረደ። የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው የሚመጡት አስፈጻሚው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ቡድኑ ነው። የዞን አመራሮች በየአንዳንዱ ዞን ተወካይ ያስፈልጋሉ። በክልልና ክልል ከተሞች ተወክለው የማእከላዊ ኮሚቴው ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው።

እና ማእከላዊ ኮሚቴ መሬት ላይ ምን እየተሠራ እንደሆነ ዘገባ ያገኛል፤ አቅጣጫም ይሰጣል። ይሄን አሠራር እውን ለማድረግ ስለሚያግዘን የማእከላዊ ኮሚቴ መዋቅር ዘርግተናል። ወይም ምክር ቤቱን ወደዛ ለውጠነዋል። አሁን በሥራ ላይ ያለ ማእከላዊ ኮሚቴ አለን። የሥራውና የአስፈጻሚው አካል ነው። በፊት ብዙ የዞን አመራሮች የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ያልሆኑ ነበሩ። ይህን መለወጥ ነው።

ዋናው ለውጥ ይህ ነው አንጂ አንድ ሰው በሌላ ሰው መቀየሩ አይደለም። ሌላው አስፈጻሚው ራሱ ቁጥሩ 13 ነበር። አንዳንዶቹ ተከፋፍለው ቢሠሩ የተሻለ ውጤታማ ይሆናሉ ስላልን፣ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ጉዳይ በሌላ አደረጃጀት ስር እንዲሆኑ ተደርጓል። 13 የነበረውን በዚህ መልክ 9 አድርገናል።
ሌላው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ከወሰድናቸው እርምጃዎች ጋር የተገናዘበ ማሻሻያ አድርገናል። ፕሮግራማችንም ላይ አንዳንድ እርማት ሠርተናል። ከዛ ውጪ ግን የአቅጣጫ ለውጥ የለም። መነሻችንን እናውቃለን መድረሻችንንም እንደዛው። ለዚህ ለውጥ የሚያስፈልገውን የመዋቅር ለውጥ ነው ያደረግነው።
የለወጡ አካል ቢሆንም ለውጥ የምንለው መዋቅራዊውን እንጂ የግለሰብ ለውጥን አይደለም። የግለሰብ ለውጥ መቀጠልም ስላለበት ማድነቅ ነው ያለብን።

መቀጠሉ እንዳለ ሆኖ በእኛ አገር ፖለቲካ አመራር ሲቀየር የሆነ ዓይነት የሐሳብ ለውጥ ከጀርባ ያሉት ሰዎች ላይ አለ የሚል ነገር ስላለ ነው። የመሪዎች መቀየር እንደ ቀላል ነገር የሚዘለል አይደለም በሚል ነው፤ እንዲህ እንድታስብ ያደረገህ፣ የመጣንበት የፖለቲካ ሂደት ጤናማ መተካካት ስላልነበረ ነው። ተተካክተው አብረው የሚታዩ ሊቀመንበርና ምክትል አብረህ አይታዩም። እኔና ደሳለኝ አብረን ነን። ይህን ማድነቅ አለብን። ዛሬ ዋጋውን አልተገነዘብን ይሆናል ግን ትልቅ ነገር ነው። ያወቁ አድናቆት ሰጥተውናል።

ሂደቱ ጥሩ ቢሆንም ምክንያቱ ሁሌም በግልጽ ያለመነገሩ ችግር ነው ብለው አያስቡም?
ዶክተር ደሳለኝ በዚህ ላይ በሰጠው መግለጫ ተናግሯል። በቃኝ ርስት አይደለም፤ ርስት እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ኻያ አምስትና ሠላሳ ዓመት የአንድ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው የሚቆዩና በዛው የሚያረጁ ሰዎችን እናውቃለን። ፖለቲካቸው ግን ወደፊት አልተራመደም። በዛም ምክንያት የኢትዮጵያ ፖለቲካም እንዳይራመድ ተጽእኖ አድርጓል። ይህን ስለምረዳና ርስት ስላልሆነ፣ ሊተካኝ የሚችል ሰው እስካለ ድረስ፣ እኔ ብተካ ለኢትዮጵያ ፖለቲካም በጎ ስለሆነ፤ ከዛ አንጻር ወስጄው ነው ብሎ በግልጽ ተናግሯል።

በእርስዎ የሊቀመንበርነት ጊዜስ አብን ምን ዓይነት ነገሮች ለማድረግ አቅዷል?
የተለየ ነገር አናደርግም። የተመሠረትንለት ዓላማ አለ። ቀጣዩ ምርጫ ነው። ለምርጫ ብቁ ቁመና ይዘን ሕዝባችን አነቃንቀን፣ ድምጽ እንዲሰጠን ማስቻል ነው። ከዚሀ በኋላ በሚመሰረት መንግሥት፣ እኛም ባገኘነው ልክ፣ የመንግሥት አካል ሆነን የሠለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የራሳችንን አስተዋጽኦ ማድረግ። የንግግር ባህልና ውይይት እንዲዳብር ማድረግ። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያጣው ይህንን ነው። አንዱ ሌላውን በመደፍጠጥ፣ ሥልጣን ላይ የወጣው ዘመኑ የእሱ ይሆንና ሌሎችን ቦታ አሳጥቶ ወይም የረባ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው አድርጎ፣ ራሱ ብቻ ባየው ልክ ነገን ለመፍጠር የሚደረገው ሁኔታ አገራችንን ጎድቷል። ይህ መሰበር አለበት። ሁሉም የኢትዮጵያ ኃይሎቸ አስተዋጽኦ አላቸው። ተከራክረው፣ ተወያይተው ከዛ የሐሳብ ፍጭት አሸናፊ የሆነው የኢትዮጵያ ሐሳብ፣ የአገር ሐሳብ ይሆናል።

አገር በዛ መንፈስ እንዲመራ ይሆናል። ይህን አተያይ ከለወጥን ብዙ ነገራችን ይለወጣል። እንዲህ ዓይነት የንግግር ባህል እንዲዳብር አብን ለውይይትና ለክርክር በዛ ልክ ክፍት ሆኖ መገኘት አለበት። ይህንን ካላደረግን ወደመጣንበት መንገድ ብቻ ሳይሆን ከዛም የባሰ ችግር ውስጥ አገራችንን እንከታለን። በዚህ አትራፊ የሚሆን የለም። ሁሉም ተጎጂ ይሆናል። ያ እንዲሆን አንፈልግም።

ሌላው በጎ ሐሳቦች አሉን ስንል፣ ለአማራው ሕዝብ ብቻ አይደለም። ቀናዒ የሆነ መንፈስ አለን፣ ለኢትዮጵያ እናስባለን። ለኢትዮጵያ ስንል ለሕዝቧ ነው። ኢትዮጵያ አንድ ሆና እንድትቀጥል፣ ሁሉም በእኩልነት በፍትህ የሚስተናገዱበትን ነገ መናፈቅ ነው እውነተኛ ፍላጎታችን። ይህ ሲሆን የመጀመሪያ ተጠቃሚ አማራው ነው፤ አይጎዳም። በዚህ አካሄድ ስንሄድ ለሌላውም ብሔር አሸናፊ የሆነ ሐሳብ ይዘን መቅረብ እንፈልጋለን።

ኦሮሞው በእኛ ላይ እምነት እንዲኖረው፣ እንዲተማመንብን እንፈልጋለን። ዝም ብሎ ምኞት ሊመስል ይችላል፣ ግን የምሬን ከእውነት ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ዘላቂ ሰላምና ጥቅሙ እንዲረጋገጥ፣ ፖለቲካው በዚህ መንገድ ነው መቃኘት ያለበት ብለን እንከራከራለን። አሁን የሚመጡበት አንዳንድ አካሄዶች ጠብ አጫሪ ከመሆናቸው የተነሳ፣ የጋራ ነገ እንዳይኖረን ያደርጋሉ። ስለዚህ የኦሮሞ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ያሰላ አካሄድ አይደለም ብለን እንነግራቸዋለን። የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅሙ በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ደግሞ እንፈልጋለን።

ሌሎች ኃይሎች የያዙት እሳቤና ስሌት ትክክል አይደለም። አሁን ለምሳሌ ሕወሓት የያዘው ስሌት ትክክል አይደለም። የአማራውን ሕዝብ ሁሉን ነገሩን ገፎታል። ለውይይት እንምጣ ስትለው ይሸሻል፣ ምክንያቱም የወሰደው ነገር አለ። ብዙ ነገራችንን ወስዷል። ባለፉት ኻያ በላይ ዓመታት እድል ነፍጎናል። ስለዚህ ትክክል እንዳልነበር ለትግራይ ሕዝብ ማስገንበዘብ እንፈልጋለን።

የአብን እሳቤ እንዲህ ቢሆን የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ሊያረጋግጥ ይችላል በሚል፣ መገናኘት ይፈልጋል። ስለዚህ ለአማራው ብቻ ሳይሆን ለሌላውም እውነተኛ አማራጭ ሆነን እንድንታሰብ እንፈልጋለን። ስለዚህ በዛ ድምጸት ፖለቲካችንን መሠራት አለበት። ለወደፊትም የምናደርገው ይህን ነው።

ኢዴፓ እና ባልደራስ ጋር ጥምረት ለመመሥረት የጀመራችሁት ሂደት አለ፤ ምን ደረሰ?
ገና በሂደት ላይ ነው። አሁን ይፋ አናደርገውም። ጥረቶች አሉ፣ እየተነጋገርን ነው። የተወሰነ እና የተጠናቀቀ ነገር የለም። በቅርቡ ዜና ልትሰሙ ተችላላችሁ። የካቲት 30 ላይ ለምርጫ ቦርድ ጥምረት የሚፈጥሩ ኃይሎች፣ ያንን የሚያስረጃ ሰነድ ይዘው መቅረብ አለባቸው። እና ቀጣይ ሳምንት ላይ አንድ ነገር ይኖራል። ብዙ ነገሮች ይቀራሉ። የቀረን 10 ቀን ቢሆንም፣ በዐስር ቀን ውስጥ ብዙ ነገር ይሠራል። ወሳኙ ውሳኔ ገና ነውና አሁን መናገር አልችልም።

ለእናንተ ባለ እይታ ምክንያት በሌላ ክልል ያሉ የአማራ ተወላጆች ለጥቃት ያመቻቸና ያባሰ እንደሆነ ይነገራል። ይህን እንዴት ያዩታል?
ከክልል ውጪ ያሉ የአማራ ተወላጆች ጉዳይ ያሳስበናል። ድርጅቱ እንዲመሠረት አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ እንደውም ከክልል ውጪ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እጣ ፋንታም ጭምር ነው። ትግላችን በኢትዮጵያ ልክ ነው ስንል እነሱን በማሰብ ነው። የእኛ ተደራጅቶ መታገል ግን የእነሱን አጣፋንታ አወሳስቧል፣ ችግር ፈጥሯል ብለን አናምንም። እርግጥ ነው፤ ንግግሮቻችን ላይ ኃላፊነት ሊሰማን ይገባል። በየትኛውም ጊዜ ቢሆን እነርሱን አስበን ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት የሚሰማው ፖለቲካ ማራመድ ስላለብን ነው። የሚበጀው ይሄ ስለሆነ።

ግን ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፤ እውነት ነው፤ ያሳስበናል። ይህ የሆነው ግን በእኛ ሳይሆን አማራ ጠል የሆኑ ኃይሎች ስላሉና ጥቃት ሊፍጽሙባቸው ስለሚፈልጉ ነው። ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ ወደሥልጣን ከመጡ በኋላ ኦሮሚያ ክልል ላይ ያለ አማራ ተፈናቅሏል። ያ እንዲሆን ያደረገው በአብን ንግግር ምክንያት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈልገውት አይደለም፤ እዛ ያሉ ጸረ አማራ የሆኑ ኃይሎች ናቸው። በስርዓቱ ውስጥ ያሉ ኃይሎች፣ የመንግሥት አካላት የሆኑ የሆነ መደበቂያ ይፈልጋሉ። ለዚህም አማራውን መቀስቀስ አማራውን ማፈናቀልና መግደል አለባቸው። ያ ምክንያት ምንድን ነው ስንል፣ ወደ አብን መምጣት የለብንም። ምን አድርገን ምን ብለን? እዛ የጸረ አማራነት መንፈስ የተላበሱ ኃይሎችና በቡድን ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም አሉ፤ ያልገባቸው።

እኛ ወለጋ እና ኢሉባቡር ላይ ለሚፈናቀል አማራ ምን ስላደረግን ነው? ይሄ የተሳሳተ እይታ ነው። እንደዛ የሚሉ እንዳሉ አውቃለሁ ግን ስህተት ነው። ዛሬም ድረስ የተደራጀ ፀረ አማራነት መንፈስ ያለው፣ አማራ ጨቋኝ ነው የሚል ኦዴፖ ውስጥ አለ። ቀላል ቁጥር አይደለም ያለው።

ከፋኖ ጋር ግንኙነት እንዳላችሁ ይነገራል። ግንኙነት አላችሁ? ካላችሁስ ምን ዓይነት ነው?
ይሄ ግምት ነው። እንደተባለው ብዙ ግምት አለ። ሐቁ እኛ የመንግሥት ስለላ ውጪ አይደለንም። የአማራ ብሔርተኝነት ትግል ጉልበት እንዳይኖረው ለማድረግ ብዙ ዓይነት ነገሮች እኛ ላይ እንደሚቀነቀኑ እናውቃለን። እኛን ከብዙ ወንጀሎች ጋር ለማገናኘት ጥረት ይደረጋል፣ ይባላል፣ ይነገራል። ይሄ ለምን እንደሆነ ይገባናል። ይህ ማለት ጠንከር ማለትና ማሸነፍ ችለናል፣ ሕዝባችንን ከሌሎች እጅ ቀምተን ወደ እኛ ወስደናል ማለት ነው። ይህ እንዳይሆን የሚፈልግ ኃይል አብን ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቅና እምነት እንዲታጣበት ለማድረግ ከብዙ ነገሮቸ ጋር ያገናኙናል።

አብን በሰላማዊ ሁኔታ የተመሠረተ፣ እውቅና ያለው ፓርቲ ነው። መንግሥት ያውቀዋል። ከዛ ውጪ እኛ በሰላማዊ የትግል ሂደት አሸኛፊ ልንሆን እንደምንችል ፅኑ እምነት አለን። መስመራችን ይሄ ነው፣ ከዚህ ውጪ ሌላ መስመር የለንም፤ እንደ ድርጅት።

ግን አብንን ለመምታት ሲፈለግ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በጎ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለውን የፖለቲካ ትግላችንን በበጎ የማያዩ ሰዎች ወይም ኃይሎች፣ እኛ ሌላ መልክ እንዳለን በመሳል ለመምታት ፍላጎት አለ። እውነታውን ግን አጥተውት አይደለም። ከዛ ውጪ ሌላ መልክ የለውም።

አንዳንድ ፓርቲዎች በአማራ ክልል ተንቀሳቅሰው ስብሰባ ለማድረግ ሞክረው ከፍተኛ ተቃውሞ እያጋጠማቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ ጀርባ ያለው ደግሞ አብን ነው የሚል አስተያየት አለ፡፡ እንዴት ያዩታል? እኛ አይደለንም የሚሉም ከሆነ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ሒደት በአማራ ክልል እንዲኖር ምን እየሰራችሁ ነው?
በአንድነት ሥም ጸረ አማራ ኃይል ወይም ግለሰቦች አይጠፉም። አማራ ክልል ሄደው ሕዝባዊ ተቀባይነት ከሌላቸው ሰበብ ይፈልጋሉ። አብን ይላሉ። አብን እንዲህ ባለ እንቅስቃሴ አትራፊ እንደማይሆን እናውቃለን። ኃላፊነት የሚሰማው ፖለቲካ ማራመድ አለብን። እኛ ኦሮሚያ ላይ በነጻነት መሥራት እንፈልጋለን። ያንን ለማድረግ አማራ ላይ አይምጣ የሚል ነገር ሊኖረን አይገባም/የለንም።

ወጣቱ ሊቃወማቸው ላይቀበላቸው ይችላል። እና በዚህ ላይ ምን ሚና መውሰድ እንችላለን? እኛ የምናደረገው በእኛ መዋቅር ውስጥ ያለ አባላችንን ማሠልጠን ነው። ለሕዝብ ግንዛቤ መስጠትን በሚመለከት እስከዛሬ በመገናኛ ብዙኀን የምንናገረው ለብዙኀኑ ይደርሳል። ይህን ጥረት ሁሌም እናደርጋለን። በዋናነት ግን በእኛ መዋቅር ስር ያለውን እንዲበቃ እናሠለጥናለን፣ ኃላፊነት የሚሰማው ትግል ማድረግ እንዳለብን እናስገነዝበዋለን። ከዚህ የሚያመልጥ ሰው ካለ፤ በፓርቲ አካሄድ በምንጠይቀው አግባብ ልንጠይቀው እንችላለን።

ከዚህ ባለፈ የፖለቲካ ድርጅቶች በአማራ ክልል ሲሄዱ ለሚገጥማቸው ማናቸውም ፈተና አብን ሰበብ ሆኖ መቅረቡ ትልቅ ስህተት ነው።

የድርጅታችሁ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምን ይመስላል?
ይህን ሌላ ጊዜ በሰፊው እናንሳው። እስከ አሁን ስንጠቀምበት የነበረው ሰነድ ላይ አንዳንድ እርማቶች እያደረግን ስለሆነ አጠናክረን የፖለሲ አማራጫችን ምን ይመስላል የሚለውን እንገልጻለን። ሰነድ እያዘጋጀን ነው። ወደ ምርጫ ስንቀርብ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦች ይህን ይመስላሉ የምንለውን በተለያየ ረገድ እናቀርባለን። አማራጮች አሉ፤ ግን አላለቁምና አሁን ባለው ደረጃ ከማብራራ ተስተካክለው ሲያልቁ ይሻላል፡፡

ይህን ግን የዘገየ ነው ሊያስብላችሁ አይችልም?
ሐሳቦቹ የነበሩ ናቸው። ለዘብተኛ ሊብራሊዝም ዋና መመሪያ አቅጣጫችን ነው ብለናል። እሱ ደግሞ ኢኮኖሚው ላይ የራሱ የሆነ እይታ አለው። የዚህን ዝርዝር ወደ ፖሊሲ ማምጣት ላይ ነን። ለምርጫ ክርክርም የምናቀርበው እሱን ነው። ሲያልቁ ለሕዝብ አቅርበነው ይተቻል፤ በዛም መሠረት አድርገን አጠናቀን እናቀርባለን።

የትኛውን የፍልስፍና ዘውግ ነው የሚወዱት?
ሰፊ ነው የሚሆነው። ሶቅራጠስ እና ፕሌቶ የጥንት ፈላስፎች ናናው፤ እነርሱ መሠረት ናቸው። እኔን በጣም ከሚገዙኝ ፈላስፎች መካከል አንዱ የጀርመኑ ፈላስፋ ማርቲን ሃይዲገር ነው። የእርሱ ፕሮጀክት ከአርስቶትል ጊዜ ጀምሮ ያለውን ፍልስፍና ይገመግምና ወይ በበቂ ሁኔታ ጠልቆ አልገባም ወይም ኅላዌ ላይ አልደረሰበትም ይላል። ይህ ባህል፣ ቋንቋ፣ ፖለቲካና ሌላውም ላይ ይመነዘራል። ሙሉ ሆኖ የማገኘው በማርቲን ፍልስፍና ላይ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here