የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትን በቅርበት

0
931

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ፓርቲዎች 70 ሆነው ከሚቀርቡ ይልቅ ሦስት እና አራት ሆኖ መቅረብ የበለጠ እንደሚያጠናክራቸው ተናግረው ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አልጠነከሩም ተብለው እንደሚወቀሱ በመጥቀስ 70 ከሚሆኑ ይልቅ አነስ ብለው ጠንከር ቢሉ መንግሥትም ለመደገፍ እንደሚሻለው ጠቁመው ነበር።

በዚሁ ውይይት ላይ ተገኝተው የነበሩት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ሊቀመንበር አረጋዊ በርሔም (ዶ/ር) 70 እና 80 ሆነን ለሕዝብ የምናቀርበው ነገር የተንዛዛ ነው፤ ሕዝቡንም የሚያተራምስ ነገር በመሆኑ ሕዝቡ እንዲማር፣ እንዲጠይቅ እና እንዲቆጣጠረን ለማድረግ ሦስት እና አራት ሆነን በርዕዮተ ዓለም እና በሃሳብ እንጠቃለል ሲሉም የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ጠይቀው ነበር።

ምንም እንኳን ከመቶ በላይ የሆኑትን ፓርቲዎች ወደ አራት ማውረድ ያለመሳካት እድሉ ከፍተኛ የሆነ ዕቅድ እንደሆነ መገመት ቢቻልም በአሁን ጊዜ እየተካሔዱ ያሉት ጥምረቶች ግን ለወደፊት ይህ ነገር እውን ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክቱ ናቸው።

ጥምረቶችን ለመፈጸም እንቅስቃሴ ላይ ከሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እንዱ ሲሆን ለአገራዊ ምርጫው ከተለያዩ አገር አቀፍ እና የክልል ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ለመፈጸም ከወዲሁ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ የፓርቲው ቃል አቀባይ ቀጄላ መርዳሳ ለአዲሰ ማለዳ አስታውቀዋል። ጥምረቱን ለመፈጸምም አስፈላጊ የሚባለውን መረጃ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስገብተናል፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥም ቦርዱ ምላሽ ይሰጠናል ብለን እናምናለንም ብለዋል።

ኦነግ ከየኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ጋር ሊፈጽም የነበረው ጥምረት መድረክ ከሌላ ፓርቲ ጋር መጣመር እንደማይችል የሚከለክለውን መተዳደሪያ ደንቡን እስኪያሻሽል የቆየ ቢሆንም በአሁን ወቅት ይህ ሒደት ስለተጠናቀቀ ጥምረቱን ለመፈጸም አስፈላጊ መረጃዎች ተዘጋጅተው ለምርጫ ቦርድ እንደተላኩ ተናግረዋል። ጥምረቱም በምርጫ ቦርድ በኩል ጸድቆ በጋራ እንሠራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ቀጄላ ተናግረዋል።

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ ከደቡብ ክልል የሞጫ ብሔራዊ ፓርቲ፣ የከፋ አረንጓዴ ፓርቲ እና የወላይታ ብሔራዊ ፓርቲም ከእኛ ጋር ለመጣመር በዝግጅት ላይ ናቸው ብለዋል።

በቀጣይም በኮንቴ ሙሳ (ዶ/ር) ሊቀመንበርነት የሚመራው የአፋር ሕዝብ ፓርቲም በቀጣዩ ሳምንት በሰመራ በሚያደርገው ጉባኤ ላይ የጥምረቱ ጉዳይ አንዱ አጀንዳ ሲሆን ለመጣመር ይወስናሉ ብለን እየተጠባበቅን እንገናለን ብለዋል ቀጄላ።

ፓርቲዎቹን በጋራ ያገናኛቸው ነሐሴ ላይ የሚደረው አገራዊ ምርጫ በመሆኑ ይህም ለአጭር ዓላማ እና ለተወሰነ ጊዜ ስለሆነ የጥምረቱ ዓይነት ቅንጅት እንደሆነ ቀጄላ ጠቁመዋል። በሂደት ላይ ያለው ቅንጅት ‹‹ትብብር ለሕብረ ብሔረሰብ ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም›› የተባለ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ይህ ስያሜ ጸድቆ ጥምረቱ በቅርቡ ይፋ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ቀጄላ የጥምረቶቹን ፋይዳ በተመለከተ ሲያብራሩም የምርጫ ድምጽ እንዳይባክን ያደርጋል፣ በፓርቲዎች መካከል በሚኖሩ ፉክክሮች የተነሳ ግጭት ሊኖር ስለሚችል ይህን በሚገባ ይቀርፋል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጥምረቱ ፓርቲዎች ለአንድ ዓላማ የሚሠሩበት መድረክ በመሆኑ ችግሮች ይጠባሉ፤ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በጋራ ለመፍታት ያስችላል ብለዋል። ለምርጫ ቦርድም ቢሆን ሥራውን የሚያቀልለት ይሆናል ያሉት ቀጄላ ቦርዱ ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር ከሚነጋገር በተወካዮች በኩል ለመወያየት እና በጋራ ለመሥራት የፓለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት እንደሚጠቅመው ያስረዳሉ። ፓርቲዎችም ቢሆኑ በአንድ ምልክት መወዳደራቸው ምርጫውን ቢያሸንፉ በስምምነታቸው መሰረት የራሳቸውን መንግሥት ለመመሥረት ጉልህ ጥቅም እንዳለው አብራርተዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና ከኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) ጋር በጥምረት ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት በመፈራረም ‹‹ትብብር ለዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም›› የሚል ስያሜ መስጠታቸውም ይታወሳል።

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣የኢትዮጵያውያን ሃገርአቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) እና ኀብር ኢትዮጵያ የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተባለ ጥምረት ማቋቋማቸው ይታወሳል። የኢዴፓው ፕሬዝዳንት አዳነ ታደሰ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እያደረጉ ያሉትን ጥምረት በተመለከተ ለአዲስ ማላዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን በምርጫው ዙሪያ እና አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ገምግሞ ከተረዳ ማንኛውም ፓርቲ ጋር በጋራ ተጣምሮ ለመሥራት ፍላጎታችንን ገልጸናል ከአንዳንዶቹም ጋር በጋራ ለመጣመር እየተንቀሳቀስን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አዳነ ቀጥለውም አሁን ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስያሜ መግለጽ ባልችልም በቅርቡ አዳዲሰ ነገሮች ይኖራሉ ሲሉ ጠቁመዋል። በጥምረቱ ዙሪያ እስከ አሁን ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ያላስገባን ቢሆንም በሚቀጥሉት ሳምንታት እንደ አስፈላጊነቱ አይተን እናስገባል ብለዋል። አዲስ ማለዳ እስካሁን እንዴት ቆያችሁ፤ ይህን ለማድረግ በቂ ጊዜስ አላቹሁ ወይ ስትል ለጠየቀቻቸው ጥያቄም አሁን ሌሎች ተጨማሪ ፓርቲዎች ጋር ተጨማሪ ውይይቶች ያሉን በመሆኑ ይህንን እንዳጠናቀቅን ለማስገባት እንሞክራለን ብለው ጊዜውም ቢሆን ይበቃናል ሲሉ ኣዳነ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ከጥምረት ጋር በተያያዘ በጥሩ መግባባት እየደረስን ነው ያሉት አዳነ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአንድ በላይ ጥምረት ሲፈጽሙ ይስተዋላል ይህም የሚሆነው የፖለቲካውን እና የአገሪቱን ሁኔታ ቆም ብሎ ካለማገናዘብ በሚመጣ መደናገር ነው ባይ ናቸው። በእኛ በኩል ይህ ዓይነት ነገር ሊከሰት አይችልም ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

በፓርቲዎቻቸው መካከል የሚፈጠረው ጥምረት ቅንጅት ሲሆን ለወደፊት ግን እንደ ግንባር ወይም እንደ ውሕደት ለመቀጠል የሚስማሙባቸው አጀንዳዎች ካሉ ሁኔታው ወደዚያ ሊቀየር እንደሚችል አዳነ አመላክተዋል። አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ያለችበትን አደጋ ያጤነ እና ያመነ ከእኛ ጋር መቀላቀል እንዲችል በራችንን ክፍት አድርገናል ብለዋል።

ኢዴፓም ይሁን አብሮነት በምርጫው ዙሪያ አቋማችንን አስቀምጠን ስንጮህ ነበር። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከ40 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ደግፈውን ምርጫው እንዲራዘም ጠይቀዋል ያሉት አዳነ ምርጫው መደረጉ የግድ ከሆነ የውድድር ሜዳውን ለፅንፈኞችና ለአክራሪ ብሔርተኞች ለቀን አንወጣም ብለዋል። በመሆኑን አደጋውን ለመቀነስ በጋራ ለመሥራት ጥምረቱ የተሻለ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከአብሮነት ጋር በጋራ ለመጣመር ፍላጎት ያለው ፓርቲ ቢኖር የሚያስፈልገው ክልል አቀፍ ፓርቲ ወይም አገር አቀፍ ፓርቲ መሆኑ ሳይሆን ዋናው ነገር ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ውስጥ ነች፣ ይህን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ መረባረብ አለብን ብሎ የሚያምን መሆኑ ብቻ ነው ብለዋል አዳነ።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው ፓርቲያቸው ከዚህ በፊት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረቱን እንዳይፈፅም ይከለክል የነበረው መተዳደሪያ ደንብ የመድረክ አባላት እና የምርጫ ቦርድ ተወካይ በተገኙበት ጥር 23/2012 ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መሻሻሉን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መረራ ከኦነግ ጋር ጥምረት ለመፈጸም ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ በመግለጽ እንደ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ይሁን እንደ መድረክ የሚለው ያልተወሰነ እና በጊዜ ሂደት የሚታወቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጥምረቱ እንዲጸድቅ ለምርጫ ቦርድ እንዳስገቡ እና የተወሰኑ የሚስተካከሉ ነገሮች ብቻ መቅረታቸውንም መረራ ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጥምረት ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ላይ የሥራ ጫና እየፈጠሩበት እንደሆነ እና አስፈላጊ የሚባሉ መስፈርቶችን አሟልተው እየቀረቡ አለመሆናቸውን የቦርዱ ሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ተናግረዋል።

ቦርዱ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግለሰቦች ስብስቦች እንዲሁም ግንባርና ቅንጅት መፍጠር የሚፈልጉ ፓርቲዎች አስፈላጊ ሰነዶቻቸውን እስከ የካቲት 30/2012 ድረስ እንዲያስገቡ መጠየቁ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here