ዳግም የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ስኳር ፋብሪካዎችን ስጋት ላይ ጥሏል

0
854

ባለፈው የዝናብ ወራት ተከስቶ ከዚያም ወደ ጎረቤት አገራት ሸሽቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ መግባት መጀመሩ የስኳር ፋብሪካዎችን አደጋ ላይ ሊጥላቸው እንደሚችል ታወቀ።

ከሦስት ሳምንት በፊት በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የሚተዳደር 240 ሄክታር የሸንኮራ ማሳ ላይ የበረሃ አንበጣ ጉዳት አድርሶ የነበረ ቢሆንም፣ የተለያዩ የመከላከል እርምጃዎች በመወሰዳቸው ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ውሏል። ነገር ግን፤ የበረሃ አንበጣ መንጋ ከኬንያ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ በድጋሚ መግባት መጀመሩ፣ በሥራ ላይ ያሉት ስምንቱ የስኳር ፋብሪካዎች አደጋ ላይ እንዲወድቁ ምክንያት ሲሆን፣ ጥቃት እንዳይደርስባቸውም ተሰግቷል።

ከነዚህም መካከል አንዱ የሆነው ጣና በለስ፣ በፋብሪካው የተተከለው 13 ሺሕ ሄክታር ሸንኮራ አገዳ የአንበጣ ጥቃት እንዳይደርስበት ተሰግቷል። የፋብሪካው የፕሮጀክት ኃላፊ አንተነህ አስጌ ከኢትዮጵያን ሄራልድ ጋር ባለፈው ሐሙስ በነበራቸው ቆይታ፣ የአንበጣው መንጋ ለግንቦት ወር ምርት እንዲሆን የተዘጋጀውን ሸንኮራ አገዳ እንዳያጠቃ ስጋት እንዳደረባቸው ጠቁመው ነበር።

በቅርቡ የአንበጣ መንጋ አደጋ በደረሰበት ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ተጨማሪ ወድመት እንዳይከሰት ፀረ ተባይ ተረጭቷል። ነገር ግን በሌሎች በሥራ ላይ ባሉ ሰባት ፋብሪካዎች እና ጣና በለስ አንድን ጨምሮ በግንባታ ላይ የሚገኙት አራት ፋብሪካዎች ውስጥ፣ ፀረ ተባይ እስከ አሁን አለመረጨቱን አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች።
ይሁን እንጂ፤ የስኳር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ የሆኑት ረታ ደመቀ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ከሁሉም አካባቢ የሚገኙ የሸንኮራ አገዳ ክፍል ኃላፊዎች ጋር በመሆኑ ጉዳዩን በጋራ በትኩረት እየተከታተሉት መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ዘብዲዮስ ፈላቶ በበኩላቸው፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ላይ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በአፋጣኝ እርምጃ ተወስዶበት ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል። ነገር ግን የበረሃ አንበጦቹ ለይቶ የሚታያቸው ከለር አረንጓዴ እና ቢጫ ተክል በመሆኑ፣ ከምሥራቅ ሐረርጌ አምልጦ የገባ የበረሃ አንበጣ ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ላይ ጉዳት አድርሶ እንደነበር ተናግረዋል።

ነገር ግን አንበጦቹ የከፋ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አውሮፕላን ተልኮ ወደ ቦታው የፀረ ተባይ ርጭቱ መካሄዱን እና ከአካባቢው እንዲርቅ መደረግ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ጨምረውም ከባህላዊ መንገዶች ባሻገር ከውጪ በኪራይ በገቡ ሦስት አውሮፕላኖች የኬሚካል ርጭት ቅድመ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ርጭቱ እየተደረገ መሆኑ ተናግረዋል። የፀረ ተባይ ርጭቱን ማከናወኛ እቃዎች እና አውሮፕላን የበረሃ አንበጣው ወደተከሰተበት አካባቢ በመላክ ከባድ ውድመት ከማስከተሉ በፊት ለመቆጣጠር እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ከጅቡቲ የሚገቡትን በድሬዳዋ፣ በኬንያ በኩል የሚገባውን ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ እና በኬልከሌ አካባቢ ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ ይህን ይበሉ እንጂ የአንበጣ መንጋው ከሶማሊያ በአምስት አቅጣጫ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ሸሽቶ የነበረው ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሰ ሲሆን፣ ይህም ስጋቱን የበለጠ እንደጨመረውና በቀጣይም ለአንበጣው መዛመት ምቹ የአየር ንብረት የሚያገኝ መሆኑ በተደጋጋሚ በተለያዩ ተቋማት ሲገለፅ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

በጣም አነስተኛ የሚባለው የበረሃ አንበጣ መንጋ እስከ ዐሥር ኪሎ ሜትር ሊረዝም እንደሚችል ዓለም ዐቀፉ የምግብ እና የግብርና ድርጅት መረጃ ያሳያል። አንድ የበርሃ አንበጣ በየቀኑ ከኹለት ግራም በላይ ወይም የራሱን ክብደት ያክል ምግብ የሚወስድ ሲሆን፣ በመንጋ ሲሆኑ በቀን 35 ሺሕ ሰዎች ሊመገቡት የሚችሉትን ያህል የመመገብ አቅም እንዳለው ተቋሙ ገልፆ ነበር።

በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስት ጊዜ እንቁላል የመጣል አቅም ያለው አንበጣው፣ በአንዴ ከ80 እስከ 120 እንቁላሎችን ከመፈልፈሉም ባሻገር አዳዲሶቹ አንበጣዎችም ከትልልቆቹ አንበጣዎች በብዙ እጥፍ የበለጠ ምግብ እንደሚመገቡ የምግብ እና የግብርና ድርጅት ባወጣው መረጃ አሳውቋል።

መቀመጫውን አዲስ አበባ ካደረገው የምሥራቅ አፍሪቃ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በምሥራቅ አፍሪቃ ሦስት የአንበጣ አይነቶች ይገኛሉ። እነዚህም የበረሃ፣ የአፍሪቃ ተዛማጅ እና የዛፍ የሚል መጠርያ አላቸው። አሁን ላይ በቀጣናው የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ሲሆን በኢትዮጵያም ከሰኔ 2011 ጀምሮ መከሰቱ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግሥት ባለፈው ረቡዕ የካቲት 11 የበረሃ አንበጣ ጉዳትን ለማቆም ቅድመ እና ድኅረ መከላከል ለኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ 8 ሚሊየን ዶላር የሰጠ ሲሆን፣ ከኹለት ሳምንታት በፊት የምግብ እና የግብርና ድርጅት ለተመሳሳይ ተግባር የሚውል 76 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለአገራቱ እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርጎ ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here