የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር የኃይል መስመር ዝርፊያ ተፈፀመበት

0
718

አገልግሎቱ ወደ መደበኛ ሥራው መመለሱ ተገልጿል

የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር መስመሮች ላይ ባጋጠመው የኤሌክትሪክ መስመሮች ዝርፊያ ምክንያት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጓጉሎ መቆየቱን አስታወቀ።

በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በተፈፀመው ስርቆት ምክንያት በአገልገሎት ላይ መቆራረጥ የተከሰተ ሲሆን፣ በተለይም ከቃሊቲ እስከ ምኒልክ አደባባይ ባለው መስመር ላይ ባቡሩ ለረዥም ሰዓታት እንዲቆም ማድረጉን የከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አስታውቋል።

የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮቹን መሰረቅ ተከትሎም ባቡሩ የሚንቀሳቀስባቸው መተግበሪያዎች ከጥቅም ውጪ ሆነው እንደነበር የባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ሔኖክ ቦጋለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በርካታ ተሳፋሪዎችን እንዲማረሩ አድርጓል የተባለ ሲሆን፣ በድንገት የሚከሰተው የኤሌክትሪክ መቋረጥ ተሳፋሪዎችን ግማሽ መንገድ ላይ እንዲወርዱ አልያም ለሰዓታት በባቡሩ ውስጥ እንዲቀመጡ ያስገድዳል።

አዲስ ማለዳም ከቃሊቲ እስከ ምኒልክ አዳባባይ አገልግሎት የሚሰጠው የከተማ ቀላል ባቡር መስመር ከቃሊቲ እስከ መሿለኪያ ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ ተመልክታለች።
የአገልግሎት መቆራረጡ ቀድሞም የነበረ ችግር መሆኑን እና ባሳለፍነው ሳምንት በጎላ መልኩ መስተዋሉን የገለፁት ሔኖክ፣ የኤሌክትሪክ መስመሩ የተቋረጠበትን ቦታ ለመለየት እና ጥገና ለማድረግ ለተወሰኑ ሰዓታት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ተደርጎ እንደነበር ተናግረዋል።

አክለውም ችግሩንም በመለየት የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉ ሲሆን፣ አገልግሎቱ ወደ መደበኛ ሥራው መመለሱን ገልፀዋል። ዝርፊያውን ስለፈፀሙት አካላት እና በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮቹ ዝርፊያ ምክንያት ስለደረሰው የገንዘብ ኪሳራ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
በተጨማሪም ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የኃይል እጥረት እና መቆራረጥ በአገልግሎቱ ላይ ችግር ሲፈጥሩ እንደነበር ገልፀዋል።

የከተማ ቀላል ባቡር አገልግሎት 34 የሚሆኑ ባቡሮች በየቀኑ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያዘጅ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ኹለት ባቡሮች እንደመጠባበቂያ ይቀመጣሉ። አገልግሎቱ ወደ ሥራ ሲገባ ከ 41 በላይ የሚሆኑ ባቡሮች ወደ አገልግሎት እንደሚሰማሩ ገልጾ ነበር። ቢሆንም በባቡሮች ብልሽት እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እየሰጠ አይገኝም።

በቀን ከ20 እስከ 28 ባቡሮች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በኤሌክትሪክ መቆራረጥ እና በኃይል እጥረት ምክንያት ሁሉንም ባቡሮች በሙሉ አቅም ማሰራት እንዳልተቻለ ቀላል የከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አያይዞ ገልጿል።

በዚህ ምክንያትም ባቡሮቹ ወደ አገልግሎት ሲገቡ በተያዘላቸው በ6 ደቂቃ በእያንዳንዱ የባቡር ጣቢያ መድረስ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ጊዜያት በሚያጋጥመው በዚሁ የኃይል መቆራረጥ እና እጥረት ምክንያት ግን እስከ 15 ደቂቃ እንደሚደረሱ ተገልጿል።

የከተማ ቀላል ባቡሩ ከፍተኛ የሆነ የመለዋወጫ ችግር ያለበት ሲሆን፣ የባቡር መሰረተ ልማቱን ከገነባው የቻይና መንግሥት ጋር የተደረገው ስምምነት የመለዋወጫ ጉዳዮችን የማያካትት በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ ለጥገና እና ለመለዋወጫ ተጨማሪ ወጪ ከመንግሥት በጀት ለማውጣት እንደተገደደ ለማወቅ ተችሏል።

የአዲስ አበባ ቀላል የከተማ ባቡር አገልግሎት በሚሰጥባቸው ኹለት የጉዞ መስመሮች ከ180 ሺሕ በላይ ደንበኞችን በቀን የሚያጓጉዝ ሲሆን፣ በቀን ከ300 እስከ 350 ሺሕ ብር ገቢ ያስገኛል።

አገልግሎቱ በተጀመረበት ወቅት ተጓዦችን የጉዞ ርቀት መሠረት ባደረገ መልኩ ባለ ኹለት፣ አራት እና ስድስት ብር የጉዞ ትኬቶችን ሲያቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ የክፍያ ስርዓቱን አመቺ ለማድረግ ሁሉም ተጓዦች ወጥ በሆነ የትኬት ዋጋ እንዲስተናገዱ ከነሐሴ 11/2011 ጀምሮ አራት ብር እንዲሆን መደረጉ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here