የደቡብ ክልል የማዳበሪያ እዳ 5 ቢሊዮን ብር ደረሰ

0
640

በክልሉ የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ እስከ 10 ቀን ይዘገያል

በደቡብ ክልል ለአርሶ አደሮች የሚሰራጭ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ የክልሉ መንግሥት ከኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ የወሰደው ብድር በወቅቱ ሳይከፈል እየተጠራቀመ ሲሆን፣ እስከተያዘው ወር ድረስም የብድር መጠኑ አምስት ቢሊዮን ብር መሻገሩ ታወቀ።

ከ 2006 ጀምሮ በብድር ሲሰራጭ የነበረው የማዳበሪያ አቅርቦት እዳ አለመክፈሉ፣ እዳው እያሻቀበ እንዲሄድ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የማዳበሪያ አቅርቦት ብድሩ የክልሉን በጀት ዋስትና በማድረግ የሚሰጥ በመሆኑ ክልሉን ለተደራራቢ ወለድ እና ሌሎች ቅጣቶች እየዳረጉት እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

የክልሉ የማዳበሪያ ብድር ዕዳ በየቀኑ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወለድ በማስመዝገብ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ፣ ክልሉ በዓመት ከ 600 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ እዳ እያስተናገደ ይገኛል። የ2012 የምርት ዓመት ሳይጨምር፣ የክልሉ አጠቃላይ የእርሻ ማዳበሪያ የብድር እዳ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።
የክልሉ የግብርና ቢሮ እና የኅብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት በመለየት ማዳበሪያውን ያቀርባሉ። የደቡብ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የገንዘብ አቅርቦቱን የሚያመቻች ሲሆን፣ የኦሞ ማይከሮ ፋይናንስ ተቋም ደግሞ የብድር ስርጭቱን እና አሰባሰቡን የመቆጣጠር ኃላፊነት ነበረባቸው።
‹‹ተቋማቱ የተሰራጨውን ብድር ለመሰብሰብ ያላቸው ፍላጎት እና ተነሳሽነት አናሳ ነው›› የሚሉት የክልሉ የኅብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ የማዳበሪያ አቅርቦት እና ብድር ክትትል ባለሙያ ታመነ ጌታቸው ናቸው። ‹‹አርሶ አደሮች የወሰዱትን ብድር በወቅቱ የመክፍል ችግር አለባቸው›› ብለዋል።

ተቋማቱ በተቀናጀ መልኩ የተሰጠውን ብድር ለማስመለስ በተሰጣቸው ደንብ እና መመሪያ መሰረት እየሠሩ አይደለም የሚሉት ባለሞያው፣ ሥራው ለሦስት እና አራት ተቋማት የተከፋፋለ በመሆኑ ለተቋማቱ እንደ ተጨማሪ ሥራ እንጂ ሥራውን በኃላፊነት የሚሠራ የለም ይላሉ።

‹‹የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ የማዳበሪያ ብድሩን የማስመለስ ቀጥተኛ ኃላፊነት አይደለም፤ ብድሩን ለአርሶ አደሮች ያቀረበው ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ብድሩን ተከታትሎ አላስመለሰም። የሚመለሰውንም ቢሆን የራሱን ኮሚሽን ከመውስድ ውጪ የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ አይደለም›› ሲሉ ጠንከር ያለ ትችታቸውንም አቅርበዋል።

ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ በበኩሉ ብድሩን የማቅረብ ኃላፊነት ቢኖርበትም ብድሩን ተከታትሎ የማስመለስ ኃላፊነቱ ግን የእኔ አይደለም ሲል ለአዲስ ማለዳ ምላሹን ሰጥቷል።

አብዛኛው የብድር መጠን በአርሶ አደሮች እጅ የሚገኝ ነው የተባለ ሲሆን፣ ለተከታታይ ዓመታት ሲከማች መቆየቱ ብድሩን ለመሰብሰብ አስቸጋሪ አድርጎታል።
የክልሉን ብድርም ለማጣጣት የብድር ማካካሻ በጀት እንደሚታጠፍ የገለፁት ታመነ፣ ለ2012/2013 የምርት ዓመት የፀደቀው አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የማዳበሪያ ግዢ የባንክ ብድር ክልሉ ባለበት ተደራራቢ ዕዳ ምክንያት እንዳይለቀቅ መደረጉን ገልፀዋል።

‹‹የማዳበሪያ ስርጭቱ እንዳይቆም ለማድረግ አቅራቢዎች ክፍያ ሳይፈፀምላቸው አሁንም በማቅረብ ላይ ይገኛሉ›› ያሉት ታመነ፣ በክልሉ የገንዘብ እጥረት በግልፅ እየታየ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ሥራዎችም እየተስተጓጎሉ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የገንዘብ እጥረቱን ተከትሎ የክልሉ መንግሥት የካፒታልና መደበኛ ወጪዎችን ለመሸፈን የጥሬ ገንዘብ እጥረት አጋጥሞታል የተባለ ሲሆን፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያትም የተጀመሩ መንገዶችን ለማጠናቀቅ፣ የሠራተኞችኝ ደሞዝ ለመክፈል ችግር አጋጥሟል ተብሏል።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደተናገሩት፣ ክልሉ አዳዲስ ሠራተኞች ቅጥርም ሆነ የሥራ ዕድገት እንዳይከናወን ተደርጓል። በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በማስፈለጉ፣ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ መደረጉንም ገልፀዋል።
በክልሉ ከመንግሥት በጀት ውጪ ካሉ የልማት ድርጅቶች ከሚገኝ የገንዘብ ዕርዳታ ውጪ የመንግሥት በጀት አለ ማለት አስቸጋሪ ነው ያሉ ሲሆን፣ የክልሉ ኃላፊዎች ችግሩን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ጥረት እንደሌለ በመስተዳድሩ ውስጥ የሚሠሩ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹በየዓመቱ ክልሉ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት በተደጋጋሚ ገልፀናል፤ ጥያቄዎችንም አንስተናል። ነገር ግን መፍትሔ ሊያገኝ ያልቻለ ጉዳይ ነው›› ሲሉ የደቡብ ክልል የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ተፈሪ አባተ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የማዳበሪያ ብድርን በተመለከተ የክልሉ ግብርና ቢሮ ጉዳዩን እየተከታታለው እንደሚገኝም ገልፀዋል። በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ አዲስ ማለዳ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊን በስልክ አግኝታ ብትጠይቅም ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ በድጋሚ እንዳትደውሉልኝ›› በማለት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here