ከኹለት ሳምንት በፊት በኢትዮ ቴሌኮም የውስጥ ሲስተሞች ላይ የራንሰምዌር (Ransomeware) ጥቃት መድረሱን፣ ሠራተኞችም የኢ-ሜይል ልውውጣቸውን መጠባበቂያ ሳያስቀሩ ከዋና ሲስተም ጋር እንዳያገናኙ እና ይህንን ካደረጉ ልውውጦቻቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ አርብ የካቲት 10/2012 ለድርጅቱ ሠራተኞች የተላኩ መልዕክቶች አረጋገጡ።
ከድርጅቱ የዲጂታል ደኅንነት ዲቪዥን የተላከው አጭር የጽሑፍ መልዕክት አርብ ይድረስ እንጂ፣ ሠራተኞች ግን ከማክሰኞ የካቲት 10 አመሻሽ ጀምሮ ሁሉም የቴሌኮሙ ስርዓቶች ቆመው እንደነበር አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ታማኝ ምንጮች ገልጸዋል። ምንጮቻችን እንደሚሉት ሲ.አር.ኤም (Customer Relationship Management Software/CRM) ከተባለው እና የደንበኛ መረጃዎችን ከሚይዘው ሲስተሙ ውጪ ያሉ የቴሌኮሙ ስርአቶች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል።
የድርጅቱ የአስተዳደር ስርዓት (Enterprise Resource Planning Software/ERP) ጥቃቱን ማስተናገዱን ምንጮቻችን የገለፁ ሲሆን፣ ይህ ስርአት የድርጅቱን ማንኛውም እንቅስቃሴ የሚያስተዳድርበት ሶፍት ዌር ነው። ‹‹ከደመወዝ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር እና የድርጅቱን መጋዘኖች ወጪ እና ገቢ እቃዎች የሚመዘግበ ነው›› ሲሉም ያስረዳሉ።
የኢትዮ ቴሌኮም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የወረቀት ግንኙነቶችን የማይጠቀም ሲሆን፣ ከዋና ሥራ አስፈፃሚ እስከ ባለሞያዎች ትዕዛዞችን ጨምሮ መደበኛ የሥራ ትዕዛዞች የሚካሄዱበት የኢ-ሜይል ስርአቱም በራንሰም ዌር ጥቃት መድረሱን አዲስ ማለዳ ከተለያዩ የድርጅቱ ሠራተኞች አረጋግጣለች።
ራንሰም ዌር አንድ ሰው ያሉትን የዲጂታል ፋይሎች በመቆለፍ ገንዘብ እስኪከፍል ድረስ ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ አደገኛ ቫይረስ ሲሆን፣ አር.ዋይ.ኬ(RYK) የተሰኘው የራንሰም ዌር አይነት ደግሞ በ ማልዌር ሃንተር ቲም የተገኘ እና በአይነቱም እጅግ አደገኛ የሚባል ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው መጠባበቂያ ፋይሎችን ጭምር ማጥቃቱ እና ቫይረሱን ካመረቱት ሰዎች በስተቀር ማንም የተቆለፉ ፋይሎችን ሊከፍት አለመቻሉ ነው።
የራንሰምዌር ቫይረሱ አጥቂዎች ገንዘብ ከተከፈላቸው በኋላ የምስጢር ቁጥር የሚሰጡ ሲሆን፣ በዚህ መሰረትም ፋይሎቹን በድጋሚ ማግኘት ያስችላል።
ነገር ግን እነዚህ የመረጃ መንታፊዎች፣ ምንም አይነት ዋስትና በሌለበት እና በአብዛኛው በቢት ኮይን ክፍያ ስለሚፈፀምላቸው ገንዘቡን ወስደውም ቁልፉን ላይሰጡ ይችላሉ። በዲጂታል ጤና እና በዲጂታል መብቶች ላይ አትኩረው የሚሠሩት አጥናፍ ብርሃኔ እንደሚሉት፣ በተለይ ከኹለት ዓመት በፊት በመላው ዓለም የፋይናንስ ተቋማት ላይ የአር.ዋይ.ኬ ፈብራኪዎች ጥቃቶችን ሰንዝረው የነበረ ሲሆን፣ ከፍተኛ ክፍያን በተደጋጋሚ ሲጠይቁ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠው የነበሩ የድርጅቱ ስርአቶችን ቴሌኮሙ በሌሎች ጊዜአዊ ስርአቶች ተክቶ ለመጠቀም እየሞከረ እንደሆነ እና ከአንድ ሳምንት በኋላ ማለትም ከማክሰኞ የካቲት 17/2012 በኋላ፣ የድሮ የኢ-ሜይል ልውውጦችን ማግኘት አልተቻልም። ነገር ግን አዲስ ኢ-ሜይሎችን አልፎ አልፎ መለዋወጥ መቻሉን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። ከሚጠቀማቸውም አማራጮች መካከል የኢንትራ ኔት (የድርጅቱ የውስጥ የኮምፒውተር ትስስር በመጠም የሚዘረጋ የመረጃ መረብ) አንዱ መሆኑ ታውቋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የድርጅቱ ሠራተኛ፣ ከዚህ ቀደም የተላላኳቸው ኢ-ሜይሎች መጥፋታቸውን እና ይሄም በተቋሙ ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ መሆኑን ይናገራሉ። ‹‹ትልልቅ ዓለማቀፍ ግዢዎችን ጨምሮ የድርጅቱን ምስጢሮች የያዙ ኢ-ሜይሎች ናቸው›› ሲሉም ያስረዳሉ።
አዲስ ማለዳ እንዲህ አይነት ድርጊቶች በተደጋጋሚ የተከሰቱ እንደሆነ ለማጣራት ባደረገቸው ጥረት፣ ከዚህ ቀደም አጋጥሞ የማያውቅ እና ድንገቴ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ከዚህ በፊት የሚደረጉ ጥገናዎች ካሉ ቀድሞ የሚነገረን ሲሆን ሌላ ተለዋጭ ስርአት ተዘርግቶ እንጂ በድንገት ሲስተም ተቋርጦ ሙከራም ሆነ ጥገና ተደርጎ አያውቅም። ይሄኛው ግን በድንገት የተከሰተ ነው፣ በእርግጥም ጥቃት ይመስላል›› ሲሉ አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ ይናገራሉ።
እስከዛሬ ድረስ ጸረ ቫይረስ የሚጫነውም ከዋና መሥሪያ ቤት ሲሆን፣ አሁን ግን በየሪጅኑ በአካል ባለሞያዎች ተልከው ፀረ ቫይረስ እንዲጫን እየተደረገ መሆኑንም እኚሁ ምንጭ ጨምረው ገልፀዋል።
የጥንቃቄ ጉድለቶች በቴሌኮሙ ዘንድ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥርጣሬአቸውን የሚያስቀምጡት አጥናፍ በበኩላቸው፣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያለ ትልቅ ተቋም የዲጂታል ደኅንነት ኦዲት በየወቅቱ ማድረግ እንዳለበት እና ይህ በአግባቡ ተደርጎ ቢሆን ቢያንስ እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች ሲደርሱ መጠባበቂያ ያስቀምጥ ነበር ይላሉ።
‹‹ማንኛውም ኦዲት በዋናነት ለጥቃት የሚያጋልጡ ክፍተቶችን ከመሙላት ባሻገር በድንገት ወሳኝ መረጃዎቻችንን ብናጣ እንኳን እንዴት መልሰን እናገኛቸዋለን ለሚለው መልስ መስጠት አለበት›› እንደ አጥናፍ ገለጻ።
ለፋይናንሱ ዘርፍ ይህ ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን እና እንዲህ አይነት ጥቃቶችን ከግምት ውስጥ የሚከተው እንዳልነበር ጠቅሰዋል። አሁን ግን አገሪቷ እየዘመነች እና በጥሬ ብር ከመገበያየት ይልቅ የዲጂታል ግብይት መስፋፋቱ ስለማይቀር፣ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ።
‹‹እንዲህ አይነት ጥቃቶች የሚደርሱት ብዙ ጊዜ በኢ-ሜይል በሚላኩ መልክቶች ሲሆን ቴሌኮሙ ሠራተኞቹን የዲጂታል ደኅንነት ሥልጠናዎች ቢሰጥ ይህንን የመቀነስ እድል ይኖረው ነበር›› ይላሉ። ‹‹እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ከፍተኛ የሕዝብ ጥቅም ያለባቸውን ተቋማት የዲጂታል ደኅንነት በተመለከተ ደግሞ፣ ኢንሳ ቀድሞውንም አቅም መገንባት ይጠበቅበት ነበር።››
ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ ችግር ለመውጣት ሦስት አማራጮች እንዳሉት የሚናገሩት አጥናፍ፣ ብቃት ያላቸው የተለያዩ ባለሞያዎችን አሰባስቦ ፋይሉን ለማስከፈት መሞከር ቀዳሚው ነው ይላሉ። ለዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ተቋሙ ብቃት አለው ብለው እንደማያምኑ እና ቴሌኮሙ በራሱ ባለሞያዎችን በማምጣት ይህንን ማድረግ ተጓዳኝ አማረጩ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተቃራኒ በአር.ዋይ.ኬ ላይ የተጻፉ የተለያዩ ጽሑፎች እንደሚያስረዱት፣ እነዚህን የተቆለፉ ፋይሎች ለመንካት መሞከር ፋይሎቹ ከመንታፊዎቹ የሚሰጡ የይለፍ ቃሎች ራሱ የማይከፍቷቸው እንዲሆኑ እና ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ የሚያደርጉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
ሌላው በዓለም ላይ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውለው በአፀፋው መንታፊዎቹን በመመንተፍ የይለፍ ቃሎችን መውሰድ ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛ ባለሞያና ሙያ ይጠይቃል። የመጨረሻው አማራጭ ግን ከመንታፊዎች ጋር ተነጋግሮ እና የሚጠይቁትን ክፍያ ሰጥቶ መረጃውን መልሶ ማግኘት ነው።
‹‹እነዚህ መንታፊዎች የሚጠይቁት ገንዘብ እንደ ተቋሙ አቅም እና እንደቆለፉት መረጃ አይነት እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ይሄንን ያህል ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ መንታፊዎች ጋር መደራደር ከሽብርተኛ ጋር ከመደራደር ስለማይተናነስ ማንም ይሄንን ያህል ከፈልኩ አይልም›› ያሉት አጥናፍ ‹‹በግሌ ግን ቴሌኮሙ ይሄንን ችግር እንዴት ይፈታዋል የሚለው አጓጊ አድርጌ አየዋለሁ›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም እጅግ አትራፊ እና የውድ መሠረተ ልማቶች ባለቤት የሆነ ድርጅት በመሆኑ፣ እንዲህ ባሉ ጥቃቶች ዋጋውን ይቀንሰዋል ብለው እንደማያምኑ የሚገልጹት አጥናፍ፣ ቴሌኮሙ በቅርቡ ለሚያካሂደው የከፊል ወደ ግል የመዞር ሂደት ጫናው እንብዛም ነው ብለዋል።
የቴሌኮሙ ዋላ ስራ አሰፈፃሚ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጨረር አክሊሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልፀዋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012



