የቀድሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ ፕሬዝዳንት እና የአሁን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል ሊቀ መንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተደራቢ የፖለቲካ ሥያሜ አሁን እየተንቀሳቀሰ ላለው ኢዴፓ መስጠቱ አግባብ አይደለም በሚል ክስ መሰረቱ።
ሰኞ የካቲት 23/2012 በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ኢዴፓ ሚያዚያ 21/2011 ለመክሰም መወሰኑን ገልጾ ለቦርዱ የላከውን ደብዳቤ ቦርዱ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም ሲል ያስረዳል። ነገር ግን ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ታኅሳስ 7/2012 ለኢዴፓ እውቅና መስጠቱን ገልፆ፣ ደብዳቤ መጻፉ እርስ በእርሱ የሚጋጭ እና ሕግን ያልተከተለ ድርጊት ነው ሲል ወንጅሏል።
ኢዴፓ 18 ዓመት ያስቆጠረ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥም ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው ፓርቲ ነበር የሚለው ክሱ፣ ተከሳሽ ራሱ ጭምር ለመፍታት ሲሳተፍባቸው የቆየ ተደጋጋሚ ያለመግባቶችን አስተናግዶ ያውቃል ሲል ያስረዳል።
ከዚህ ቀደምም ድርጅቱን ለማፍረስ የተደረጉ እኩይ ተግባራት እስከ መደበኛ ፍርድ ቤት ድረስ ደርሰው ነበር የሚሉት ጫኔ፣ እልባት አግኝቶ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎም በቀጣይ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ ለመገኘት በጋራ ተቀናጅቶ መሥራት ተገቢና አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፓርቲው ከስሟል፣ እንደ ጫኔ ገለፃ።
‹‹በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፓርቲው አባላት ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራ ብለው በመጠየቃቸው፣ በተጠራው ጉባኤ መጋቢት 1/2011 ስብሰባ ተካሂዷል›› ሲል ክሱ ያስነብባል። ‹‹በእለቱ ከተላለፉ ውሳኔዎች መካከልም ድርጅቱ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚያካሂውን ውህደት የፓርቲውን ጥቅም አስጠብቆ በማክሰም አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ጠቅላላ ገባኤ መጥራት ሳያስፈልግ፣ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በውክልና ይህንን እንዲያካሂድ ፈቅዷል።››
የኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 21/2011 ባካሄደው ስብሰባ፣ ፓርቲው እንዲከስም እና አዲስ በመሚመሰረት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እንዲሳተፍ ወስኗል። በክሱ ላይ እንደተጠቀሰውም፣ ለቦርዱ ይህንን ውሳኔ በተመለከተ የማስታወቂያ ደብዳቤ ተልኳል።
ጫኔ በክሳቸው ላይ እንደገለፁት፣ ምርጫ ቦርድ ተሻሽሎ በፀደቀው የምርጫ ሕግ መሰረት በ30 ቀናት ውስጥ ለደብዳቤው መልስ መስጠት ቢኖርበትም፣ ይህንን ግን ሳያደርግ ቀርቷል። ከዚህ ባለፈም ቦርዱ ከፓርቲው ፕሬዘዳንት እውቅና ውጪ ለጋራ ምክር ቤቱ ለኢዴፓ እውቅና መስጠቱን ገልፆ መጻፉ አግባብ አይደለም በሚል ወቅሷል።
‹‹ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ከስሟል ብለን ላቀረብነው ደብዳቤ በሕጉ መሰረት ምላሽ መስጠት ሲገባው፣ ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ ዞር ብሎ ኢዴፓ ለሚባል ድርጅት እውቅና መስጠቱ ሕገ ወጥ ነው›› ሲል ክሱ ያስነብባል። ‹‹በከሳሽ እና በሌሎች የፓርቲው አባላት መካከል ያለመስማማት አለ ብሎ እንኳን ቢያምን፣ በሕጉ መሰረት መፍታት ሲጠበቅበት፣ እኛ ከስመን ከሌላ ፓርቲ ጋር ተዋህደናል እያልን፣ ተከሳሽ እያወቀ በጎን ለኢዴፓ እውቅና መስጠት በማን አለብኝነት እና ሕግን በፍፁም ያለተከተለ ውሳኔ ነው።››
ይህ ተግባርም ሕግን ያልተከተለ መሆኑን በመግለጽ፣ ታኅሳስ 16/2012 ለቦርዱ በጽሑፍ ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚገልጹት ጫኔ፣ ቦርዱ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ገልፀዋል።
በዚህም መሰረት ከፍርድ ቤቱ ኹለት ዳኝነትን የጠየቁት ጫኔ፣ በአንድ በኩል የቦርዱ ተግባር ሕገ ወጥ ይባልልኝ ያሉ ሲሆን፣ ቦርዱ በሰጠው እውቅና መሰረት አሁን እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው ኢዴፓ ሕጋዊ ባለመሆኑ ሕጋዊ እውቅና የለውም እንዲባልልን ሲሉ ጫኔ ጠይቀዋል።
ጉዳዩን የሚመለከተው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጀ ፍርድ ቤትም ቦርዱ መልስ እንዲሰጥ ለየካቲት 27/2012 ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑትን ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ክሱን የመሠረቱት ግለሰቡ እንጂ ፓርቲው እንዳልሆነ ገልፀው፣ በክሱ ይዘት ላይ ግን ፓርቲያቸው እንደሚስማማ አስታውቀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012



