በ10 ዓመት ታዳጊ ላይ የግብረ ሰዶም ጥቃት የፈፀመው ግለሰብ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

0
1261

ተመሳሳይ ፆታ ካለውና ለአካለ መጠን ያልደረሰ ዕድሜው 10 ዓመት የሚሆን ሕፃን ኅዳር 29/2012 ከቀኑ በግምት 9፡30 ሰዓት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ክልል ልዩ ቦታው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን ጫካ መቃብር ስፍራ ውስጥ በመውሰድ እና በጩቤ በማስፈራራት የግብረ ሰዶም ጥቃት ያደረሰበት ግለሰብ በፅኑ እስራት ተቀጣ።

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሹ ክሱን በመካድ የተከራከረ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ አራት ምስክሮችን እንዲሁም ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀረበው የሕክምና ማስረጃ መሠረት ጥፋተኛ መሆኑ አረጋግጧል።

ፍርድ ቤቱም በክሱ አቤቱታ ላይ የተመለከተውን ድርጊት ተከሳሹ ስለመፈፀሙ ምስክሮች በዝርዝር ያስረዱ በመሆኑ፣ ተከሳሹ በተከሰሰበት ጥፋት ስር እንዲከላከልና የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቀጠሮ ቢሰጠውም፣ የመከላከያ ማስረጃ የለኝም በማለት ማቅረብ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ይከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር ጥፋተኛ ነህ ብሎታል።

ተከሳሹም በ1996 የወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 631/1/ለ/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ በፈፀመው የግብረ-ሰዶም ጥቃት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኗል።
ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ የሴቶችና ሕጻናት የወንጀል ችሎት፣ የካቲት 20 ቀን 2012 በዋለው ችሎት ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን ቅጣት የጣለ ሲሆን፣ በዚህም ተከሳሽ በ14 ዓመት ፅኑ አስራት እንዲቀጣ እንደወሰነበት ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተገኘ መረጃ አመላክቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here