የናይል ወንዝ የላይኛ ተፋሰስ አገር የሆነቸው ዩጋንዳ፣ በአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር የሃይድሮ ግድብ ለመገንባት ከፓወር ቻይና ኢንተርናሽናል ግሩፕ ሊሚትድ የመጀመሪያውን የሥራ እቅድ የተቀበለች ሲሆን፣ በመጪው ወርም የመጨረሻውን ውሳኔ እንደምትሰጥ ይጠበቃል።
የዩጋንዳ ኤሌክትክ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ባሳለፍነው ሳምንት ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የቀረበውን የሥራ እቅድ ለሕዝብ አስተያየት ክፍት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። አያጎ የሚል ሥያሜ የተሰጠው ይህ ግድብ፣ 840 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም በመያዝ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት በ40 በመቶ ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ፓወር ቻይና ለዩጋንዳ መንግሥት አቀረበ የተባለው ይህ እቅድም ከ25 በመቶ እስከ 75 በመቶ ድረስ የሚሆነውን የግድቡን ወጪ በብድር እና በኢንቨስትመንት መልኩ የማቅረብ ሐሳብ ጨምር ይዞ መምጣቱን አልጀዚራ አስነብቧል።
ዩጋንዳ 20 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ዜጎቿ አሁንም ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖሩ የዓለም ባንከ መረጃ ያሳያል። ባንኩ ከአራት ዓመት በፊት በዩጋንዳ ላይ ያሠራው ድህነትን የሚያስስ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ አገሪቱ የዜጎቿን የነፍስ ወከፍ ገቢ ብታሻሻልም በተለይም እንደ ኤሌክትሪክ፣ ትምህርት እና የንፅህና አገልገሎቶችን ለዜጎቿ በማቅረብ ረገድ ግን አሁንም ከፍተኛ ክፍተቶች አሉባት።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012


