ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ አገራትን ለመደገፍ 50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
ድርጅቱ የበሽታው መከሰት በያዝነው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖረውን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ባለፈው ዓመት ከነበረው ያነሰ እንዲሆን እንደሚያደርገው ገልጿል።
ይኸው አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ ይፋ የተደረገው በሽታው ከተከሰተባት ቻይና ወጥቶ ከ70 በላይ አገራት መሰራጨቱን ተከትሎ ነው። በያዝነው ሳምንት ውስጥ በመላው ዓለም የሚገኙ መንግሥታት እና ማእከላዊ ባንኮች የቫይረሱን ተፅዕኖ ለመግታት እርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው።
ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ድርጅት የድጋፍ የገንዘብ ድጋፉን ይፋ ያደረገው ደካማ የጤና ሥርዓት የሚገኝባቸው ድሀ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት የበሽታውን ስርጭት መግታት እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ክርስታሊና ጂኦርጂቪያ የዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመልክተው በሰጡት ሐሳብ፣ “በ2020 የሚኖረው ዕድገት ባለፈው ዓመት ከነበረው ያነሰ ነው፤ ነገር ግን ችግሩ ምን ያህል ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚለውን ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው” ብለዋል።
በተመሳሳይ በያዝነው ሳምንት ውስጥ ታዳጊ አገራት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እንዲችሉ የዓለም ባንክ የ12 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012



