የኢሕአዴግ ቅኔ

0
952

ሕገ መንግሥቱን የማክበር ኃላፊነት የመንግሥት ሆኖ ሳለ ዜጎች ካሳለፉት አስቸጋሪ ጊዜ አንፃር መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ሲያከብር ውለታ እንደሠራ እንደሚቆጠርለት ያስታወሰው ገመቹ መረራ መንግሥት የገዛ ሕገ መንግሥቱን በማክበር ጦሱን ቢጋፈጠው እያለ ይመክራል።

“ታላቁ ውል”
ሥያሜው በላቲን “ማግና ካርታ” ይባላል፤ ትርጉሙ “ታላቁ ውል” ወይም “ታላቁ ሥምምነት” ማለት ነው። ይህ ሥምምነት በዓለማችን እጅግ በጣም ከሚታወቁት ታላላቅ ታሪካዊ ሰነዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው። የአገሪቱ ትላልቅ መኳንንት በተጣለባቸው ከባድ ግብር እና ሌሎች ጉዳዮች መነሻ በወቅቱ የእንግሊዝ ንጉሥ ዮሐንስ ላይ በማመፃቸው ምክንያት ነበር ይህ ሥምምነት እ.ኤ.አ. በ1215 የተፈረመው። ንጉሡ የመኳንንቱን አመፅ አቅጣጫ በማየት በጥቂቱ የተነሳው የርስበርስ ጦርነት እንዳይስፋፋ በመስጋቱ ነበር ይሄንን ሥምምነት የፈረመው።
ይህ ሥምምነት ታዲያ ንጉሥ ዮሐንስ እና በኋላ የነገሡት ነገሥታት በሕግ የበላይነት እንዲገዙ መሠረት የጣለና በአውሮፓ ታሪክ እንደ መጀመሪያው ሕገ መንግሥት የሚቆጠር ሰነድ ለመሆን ችሏል። ከዚህ ሥምምነት ፈር ቀዳጅነት በኋላ በዓለማችን የተለያዩ ክፍሎች ሕዝቦች የመንግሥታትን ሥልጣንና ኃላፊነት ሰፍረውና ለክተው በመስጠት ከገዢዎቻቸው ጋር ሥምምነት ተፈራርመዋል፤ ሥያሜውም ሕገ መንግሥት ተብሏል።
ኢትዮጵያችንም በ1923 የመጀመሪያውን ሕገ መንግሥት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት አግኝታለች። ይሁን እንጂ ይህ ሕገ መንግሥት በዜጎች ፈቃድና ፍላጎት መሠረት የገዢውን ሥልጣንና ጉልበት የሚገድብ ሳይሆን፣ ንጉሡ ከዓለም አገራት ተርታ በእኩልነት መሰለፍ ይችሉ ዘንድ ዘመናዊነትን ለመላበስ ያደረጉት ጥረት አንዱ አካል ብቻ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በመሐል የተለያዩ የሕገ መንግሥት “ለውጦችን” አስተናግደን አሁን የምንገለገልበት ሕገ መንግሥት ላይ ደርሰናል። የኢትዮጵያን ሕዝብ በማስተዳደር ሒደት የመንግሥት ሥልጣን በእርሱና በርሱ ብቻ ሊወሰን ይገባል። ሕገ መንግሥት ከሚወስናቸው ነገሮች ዋነኞቹ ደግሞ የዴሞክራሲ ምሰሦዎች ተብለው የሚታወቁት ናቸው።
“አራተኛው ምሰሦ”
ሁሉም ሰብኣዊ መብቶች እና ነጻነቶች እኩልና የማይነጣጠሉ ናቸው። ተቀናንሰው ወይም ተቆራርሰው የማይሰጡ ወይም የማይከለከሉ ተፈጥሮኣዊ በረከቶቻችን ናቸው። እነዚህ መብቶች በሕገ መንግሥታችን እንደተቀመጠው “ሰብኣዊ”፣ “ዴሞክራሲያዊ” ወዘተ እያሉ በአንድ ወይም በሌላ ሥያሜ ሥር ማስቀመጥ ይቻላል። እነዚህ ጥቅል ሥያሜዎች እያንዳንዷን መብት በተናጠል መመልከት፣ መጠየቅ እና መተንተን የሚከለክሉ ባለመሆናቸው እንደ አስፈላጊነቱ ራሳቸውን ችለው ይገመገማሉ።
ምንም እንኳን ሁሉም መብቶች እኩል ቢሆኑም ለበርካቶች የመናገር አሊያም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የበለጠ አስፈላጊ ነው የሚሉት ኤዲት ፓተርሰን ሜዬር የተባሉ ጸሐፊ ናቸው። “ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከአንድ ሰው አፍ የሚወጡትን ቃላት ብቻ ሳይሆን፣ ከቃላቱ ጀርባ ያለውን ቃላቱ የሚወክሉትን ነገር የማሰብ፤ እንዲሁም ሐሳቡን ወረቀት ላይ የማስፈር አሊያም በሌላ መንገድ የመግለጽ ነጻነትንም ይጨምራል” በማለት መብቱ ከሌሎች የሚበልጥበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን መገደብ ኅብረተሰብ እንዳይማር፣ እንዳያድግ፣ እንዳይለወጥ፣ የተሻለ አስተሳሰብ እና ኑሮ እንዳይኖረው መገደብ ማለት ነው። በተለይ ከዚህ መብት ጋር ተያይዞ የሚታወቁት አሜሪካዊው ዳኛ ኦሊቨር ዌንደል ሆልምስ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ ነጻ የሐሳብ ገበያን የሚተክል መሠረታዊ መብት ነው ይላሉ። “አንድን እውነት መፈተኛ ምርጡ መንገድ ሐሳቡን በተወዳዳሪ የሐሳብ ገበያ እንዲቀርብ በማድረግ የሚገኘው የሐሳቡ ተቀባይነት ነው” ይላሉ። ይህ ሐሳብ እንደልብ የሚንሸራሸርበት፣ የሚገበይበት ዋነኛ መድረክ ደግሞ ብዙኃን መገናኛ ነው።
ብዙኃን መገናኛ የዓለማችን ታላቅ ኃይል ነው። ለዚህም ነው አምባገነኖች ብዙ ጊዜ ዋነኛ ትኩረታቸውና የመጀመሪያ ሥራቸው ነጻውን ሚዲያ ማፈን የሚሆነው። በዙሪያችን ያሉትን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በቀላሉ መገንዘብ የምንችለው በሚዲያ አማካኝነት ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመንግሥት ቅሌቶች በሙሉ የሚጋለጡትና ሕዝብ የሚያውቃቸው በሚዲያው በኩል ነው። ሕዝብ ሊቃወም፣ መንግሥት ሊቀይር፣ ሕግ እንዲሻሻል ሊያደርግ፣ አስተዳደር እንዲቀየር ሊጠይቅ ወዘተ የሚችለው ሚዲያው የሚሰጠውን ትክክለኛ መረጃ ተከትሎ ነው።
በዓለም ባሉ ዴሞክራሲያዊ መንግሥታት ዘንድ፣ እንዲሁም ደግሞ በአገራችንም ጭምር ተዋቅረው የምናገኛቸው ሦስት የአንድ መንግሥት አላባውያን የሆኑት የሕግ አውጪ፣ የሕግ አስፈፃሚ እና የሕግ ተርጓሚ አካላት አሉ። እነዚህ ሦስቱ አካላት በአራተኛነት ሚዲያውን በመጨመር “አራቱ የዴሞክራሲ ምሰሦዎች” ተብለው ይጠራሉ። አንዱ ምሰሦ የጎደለበት ዴሞክራሲ ፀንቶ መቆም ብሎም መራመድ የማይችል አንካሳ ነው። የሦስቱን የመንግሥት አካላት በትክክል መሥራት በግልጽ የሚያሳየውና የሚያረጋግጠው ብዙኃን መገናኛው ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ለገጠመን እና እየገጠመን ላለው ማኅበራዊ ቀውስ አንዱና ዋነኛው መነሻ ለዓመታት ነጻ ፕሬሱ በመታፈኑ ምክንያት ሕዝቡን ሊያስረዳ፣ ሊያስገነዝብ እና ሊያስተምር የሚችለው ነጻ ሐሳብ ሳይንሸራሸር በመቅረቱ የታመቀ ቂም፣ ቁጣና አለማወቅ ተደምረው በመፈንዳታቸው ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ጥሩ መጽሐፍት በበቂ ሁኔታ በማይጻፉበት አገር፣ ቢጻፉም በብዙዎች በማይነበብበት አገር፣ ታሪክን በወቅቱ በተፈፀመበት ሁኔታ እና ዝርዝር በትክክለኛው መልኩ ዘግበው የማስቀረት ዕድል ያላቸው፣ ለሕዝቡ የተሻለና በሐሳብ ገበያ የተፈተነ እውነት ለማቅረብ አቅም ያላቸው መሣሪያዎች ጋዜጦች እና መጽሔቶች ናቸው። እነሱን ማፈን እና ጉዴን ገለጡ ብሎ መዝጋት መንግሥት ከሚፈፅማቸው እጅግ ኃላፊነት የጎደላቸው ፀረ-ትውልድ ተግባራት አንዱ ነው።
“ምኞታችን”
“‹አንድ አረብኛና ሌሎች ቋንቋዎችን የሚያውቅን ሰው ከየትኛውም ቋንቋ ምርጡ ባለቅኔ ማነው?› በልና ጠይቅ፤ መላሹ ከአንድ ሺሕ ዓመታት በፊት የኖረውን አልሙታነቢን ሊጠራልህ እንደሚችል እምነቴ ነው” በማለት ስለታላቁ የአረብ ባለቅኔ የሚነግረን ናሲም ኒኮላስ ታለብ ነው። “ኦሪጂናል የአረብኛ ግጥሞቹ የአንባቢ እና/ወይም አድማጮቹን ልብ ይሰውራሉ፣ በሩሲያዊያን ላይ ፑሽኪን የሚፈጥረው ስሜት ብቻ ይገዳደረዋል። ችግሩ፣ የሥሙ ቀጥታ ትርጉም ፣ነብይ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰው› የሆነው አልሙታነቢ፣ ብቃቱን በኩራት የሚያውቅ ሰው መሆኑ ነው።”
ይሄንን የቅኔ ልቀቱን በአንድ ግጥሙ ውስጥ ስለግጥሞቹ ምርጥነት “ዓይነ ስውራን የሚያነቡት፣ መስማት የተሳናቸው የሚያደምጡት” ግጥም ነው ሲል በጉራ ይገልጻል። በርግጥ አልሙታነቢ የወሬ ወይም የጉራ ሰው ብቻ አልነበረም፤ የተግባርም ጭምር እንጂ። በአንድ ተዓምረኛ ግጥሙ (ከብዙ እንግሊዝኛ ትርጉሞች መካከል አንዱን ወደ አማርኛ እንደመለስኩት) ሲፎክር እንዲህ ይላል፦
‘በረሃው፣ ምሽቱ፣ ጠላትና ጦሩ
ያውቁኛል ጎራዴው፣ ወረቀት ብዕሩ!’
አልሙናተቢ በአንድ ግጥሙ ውስጥ ግን አንድን የበረሀ ነገድ አስቀየመ። ነገዱ አልሙታነቢን ሊያጠፋው ተነሳ። በቁጥር በርካቶች ነበሩና አንድ ምክንያታዊ ሰው የሚያደርገውን ነገር ማድረግ ጀመረ፤ መሸሽ። አብረውት የነበሩት ሰዎች ከላይ የጠቀስናትን ተወዳጅ ግጥሙን መልሰው ለራሱ አሰሙት። ይኼኔ አልሙታነቢ ሽሽቱን አቁሞ ወደ ተረጋገጠው ሞቱ ፊሩን መለሰ፣ ያስከፋቸውን ጎሳዎች ገጠመ። እነሆ ከሞተ ከአንድ ሺሕ ዓመታት በኋላ አልሙታነቢ ግጥሞቹን ስናነብ የቃላቱን ተግባራዊነት የምንረዳው ገጣሚ ሆኖ ይታወሳል።” ይሄንን ስንሰማ ብዙዎቻችን አንድ ነገር እንመኝ ይሆናል፤ የኢሕአዴግን ቅኔ።
የኢሕአዴግ ቅኔ
ኢሕአዴግ እንደ አልሙታነቢ የሚመካበት እና ዘወትር ሲደጋግመው የሚታወቅበት ቅኔ አለው፤ ሕገ መንግሥቱ። በመሠረቱ ውላችን ፈርሷል ወይም ተጥሷል ብሎ “ሕገ መንግሥቱ ይከበር!” ማለት ያለበት ሕዝቡ እንጂ መንግሥት አልነበረም፡፡ ሕዝቡ ይህ ኮንትራቱ ሲጣስበት ውላችን (ሕገ-መንግሥቱ) እንዲህ ይላል፤ መንግሥት እየጣሰው ነው፤ ጉልበቱን ተጠቅሞ ከሰጠነው ኃይል፣ ከፈቀድንለት ጉልበት እና ካፀደቅንለት ሥልጣኑ አልፎ እየጎዳን ነውና ውላችንን ያክብርልን ሊል የሚገባው ሕዝብ ነው። በሌላው ዓለም ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል ተብሎ የሚፈራው መንግሥት እንጂ ሕዝቡ አይደለም። ለበርካታ ዓመታት “ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ሲሞክሩ” እያለ የሚጮኸው፣ ስለ ሕገ መንግሥቱ የሚሰብከው መንግሥት ራሱ ነው። ይህ የሕዝብን ጩኸት መንጠቅ ነው።
ኢሕአዴግ ባለፉት ጥቂት ወራት ያደረገውን አበረታች “ለውጥ” ተከትሎ በይፋ በመንግሥት ባለሥልጣን አፍ “የሉም” ተብለው የተካዱት የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ ለበርካታ ዓመታት በስደት ይኖሩ የነበሩ ፖለቲከኞች ወደአገራቸው መመለሳቸው፣ ጋዜጦች እና መጽሔቶች መታተም መጀመራቸውን አይቼ እንደአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተደስቻለሁ። በመሠረቱ ኢሕአዴግ ያደረገው አስቀድሞ ያለአግባብ የነፈገውን መብትና ፍትሕ መመለስ ነው። ነገር ግን ያለፍንበት የሕይወታችን ጠባሳ መብታችንን እንድንጠይቅ ሳይሆን “እንዲህ ቢሆን” እያልን እንድንመኝ አድርጎ ቀርፆናል።
ይሁንና ኢህአዴግ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 29/2 የሰፈረውን “…ማኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነጻነቶችን» በማክበር፣ ለዓመታት ሲፎክርበትና ሲደጋግመው የነበረውን ይህንን የቅኔውን አንድ መንቶ (የሕገ መንግሥታችንን ድንጋጌ) ስንጠቅስበት ሰምቶ እንደ ባለቅኔው አልሙታነቢ ሸሽቶ ለማምለጥ ከመሞከር ይልቅ አክብሮት፣ የሚገለውም ከሆነ የክብር ሞቱን ቢጋፈጥ ብዬ ተመኝቻለሁ።

ገመቹ መረራ የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው fana@ethiopianlawgroup.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here