የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች ቁመና ሲፈተሽ

0
705

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ግንባር፣ ኅብረት፣ ወዘተ በሚሉ ሥያሜዎች በአገር ዐቀፍና ክልል ደረጃ 79 የፖለቲካ ማኅበራት ስለመመዝገባቸውና ባለፈው 2007 ምርጫ ስለመወዳራቸው በአዲስ አበባ የሚገኘው ፍሬድሪክ ኢበርት ስቲፍተንግ የተሰኘ የጀርመን ድርጅት በዚህ ወር ያወጣው ጥናት ያመልክታል። ኅዳር 18 ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከ81 የተቃማዊ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ ብዙ ሲባል ሰንብቷል። በአንድ በኩል ‹‹ይህን ያክል የፖለቲካ ፓርቲዎች በእርግጥ አሉ ወይ?›› የሚለው ጥያቄ ሲነሳ በሌላ በኩል በውይይቱ ላይ የተገኙት አብዛኞቹ ለበርካታ ዓመታት በፓርቲ አመራርነት ይዝለቁ እንጂ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ጠብ ያደረጉት ነገር የለም በሚልም አከራክሯል። ለዚህ ተጠያቂው የፖለቲካ ማኅበራቱ ሕዝባዊ ቅቡልነትና አደረጃጀት እንዲሁም ገዢው ኢሕአዴግ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም አብዛኞቹ ፖለቲከኞች በዕድሜ አንጋፋና ለወጣቶች ዕድል የማይሰጡ ናቸው የሚል ወቀሳም ይሰነዘራል። ከአመራሮቹ አንጋፋነት ባለፈ የዛሬ 27 ዓመት የያዙትን ‹ፕሮግራም› ባለማሻሻል በቆሞ ቀርነትም የሚወቀሱ አሉ።
ማክሰኞ፣ ኅዳር 25 ‹‹አዲሱ ውል፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ፍሬድሪክ ኢበርት ስቲፍተንግ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና የሲቪል ማኅበራት የተሳተፉበት መድረክ አካሂዷል። በውይይቱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አመሠራረት፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ቁመና፣ ቁጥርና ሕጋዊነት ላይ ተደጋጋሚ ሐሳቦች ተነስተዋል።
የመጠላለፍ ፖለቲካ
ከተሳታፊዎቹ መካከል የኦሮሞ ዴሞካራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ሌንጮ ለታ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የግራ ዘመም ፖለቲካ መለመዱን በመጥቀስ ሶቪየት ኅብረትንና የሌኒን የፖለቲካ ፍልስፍናን እንደ ጥሩ ምሳሌ ሲወስዱ ዛሬ ላይ መደረሱን ይጠቁማሉ። በአብዛኞቹ የፖለቲካ ማኅበራት ትኩረትን ከተማ ላይ የማድረጉ አባዜ ዛሬም ድረስ አለመልቀቁን ያነሳሉ። የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዘዳንት ሙሼ ሰሙ የፓርቲዎች ከተማ ላይ መንጠልጠል በተለይም ከአዲስ አበባ አለመውጣት የአርሶ አደሩን ሕይወትና ችግር እንዳይረዱትና አባላትንም እንዳያበዙ ስለማድረጉ ያነሳሉ። ሌላው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ያልተለየን አባዜ የሚሉት በሥሜትና ጥላቻ ላይ መመስረታቸውን ነው። አንዱ የብሔር ሌላው ደግሞ የአንቀጽ 39ኝን የመገንጠል ጥያቄ ይዞ እንደሚመሠረት በመጥቀስም ፓርቲዎች በትውውቅና የአገር ልጅነት ላይ መመሥረታቸውን ይጠቅሳሉ። ይህም ከሕዝብ ይልቅ ለቡድን ወይም ግለሰብ ጥቅም እንዲታገሉ ስለማድረጉ ያክላሉ። ከርዕዮት ይልቅ አስተዳደራዊና ጥቃቅን በደሎችን መነሻ አድርገው የሚቋቋሙትም ጊዜያዊ ችግሩ ሲፈታ የሚሰውለት ጠንካራ ርዕዮት ስለማይኖራቸው እንደሚበታተኑም ጠቅሰዋል። የፍረጃ ፖለቲካ ዛሬም በኢትዮጵያ ስለመለመዱም ይጠቅሳሉ። ሌላው ፓርቲዎች አንድም በጠራ ርዕዮት ላይ አለመመሥረታቸው፣ ሁለትም በጥቃቅን ልዩነት ብዙ ፓርቲዎች መፈልፈላቸው ወደመጠላለፍ አስገብቷቸዋል። በዚህም ለሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆነዋል።
የፖለቲካ ማኅበራቱ ቁመና
‹‹የእውነት 80 አካባቢ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ወይ?›› የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ሆኗል። አዲስ ማለዳ በኅዳር 22 ዕትሟ ከምርጫ ቦርድ ባገኘችው መረጃ ከ22 አገር ዐቀፍ ፓርቲዎች ሕግና አሠራርን አሟልተው የሚገኙት ወይም ሕጋዊዎቹ ሰባት ብቻ ስለመሆናቸው መዘገቧ ይታወሳል። ይሁንና እነማን ሕጋዊ የትኖቹ ደግሞ ሕጋዊ ያለሆኑ ናቸው ለሚለው ጥያቄ ምርጫ ቦርድ መረጃ ለመስጠት አልፈቀደም።
የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት የሚሳስብ አይደለም የሚሉ ወገኖች 81ዱም ሕጋዊ ሆነው እየሰሩ ነው ብለው እንደማያምኑ ያነሳሉ። በ1990ዎቹ የነበሩት በርካታ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ዛሬ ቢጠፉም ከዓመታት በፊት ስለተመዘገቡ ብቻ አሁንም አሉ ማለት እንደማይቻለው ሁሉ ፓርቲዎችም እንዲሁ መታየት አለባቸው ሲሉ ያስረዳሉ። ሙሼ እንደሚያምኑት የምርጫ ቦርድ ሕግና የፓርቲዎቹ አሠራር በወጉ ከተተገበረ 82 ፓርቲዎች አይኖሩም። ሕግና አሠራሩን አክብረው የሚሄዱት ከአምስት እንደማይበልጡ ይገምታሉ።
መንግሥት የሚሠራና የሚያፈርሳቸው ፓርቲዎች ስለመኖራቸው የሚናገሩት ፖለቲከኛና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ግርማ ሰይፉ ከ80ዎቹ ስምንቱ እንኳን ለሕዝብ ጥቅም ስለመቋቋማቸው ይጠይቃሉ። ‹‹ዲያሎግ ኢትዮጵያ›› ከተሰኘ ድርጅት የመጡት አያሌው ዘገየ ውስብስብ ባሕሪይ ያላትን ኢትዮጵያ መንግሥት ሆኖ ለማስተዳደር የተቋቋሙ ፓርቲዎች የውስጥ ችግራቸውን መፍታት ሲሳናቸው እየተፈረካከሱ የየራሳቸውን አዲስ ፓርቲ ለመቋቋም ሲጣደፉ ማስተዋላቸውን በመጥቀስ እንደማያምኗቸው ይገልጻሉ። አያሌው ጋር ያለው እሳቤ ጥሩ አስረጅ ነው የሚሉት ግርማ ፓርቲዎች አንሰው እንዲታዩና እንዳይታመኑ ያደረጋቸው መንግሥት እንደሆነ ያነሳሉ። ሙሼ እንደሚሉት ከሆነ በፖለቲካ አቋም ‹‹ከሥራ መፈናቀል፣ መታሰርና መገደል›› ባለበት አገር ተቃዋሚዎች ለምን ጠንካራ ተፎካካሪ አልሆኑም የሚለው ሐሳብ በራሱ ችግር አለበት።
ከኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲ መድረክ ሰለመምጣታቸው የተናገሩት ነጋሽ ተክሉ ፓርቲዎች በመፈክራቸው የሕዝብ ቢሆኑም የሕዝቡን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ውስጠ ዴሞክራሲ እንደሌለቸው ያምናሉ። የሕግ ምሑሩ ጌታቸው አሰፋ (ዶ/ር) ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጠ ዴሞክራሲና አብሮ የመሥራት ችግር እንዳለባቸው ሲያነሱ ግርማ በበኩላቸው ውስጠ ዴሞክራሲቸው ጠንካራ የሆኑ ፓርቲዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ሌላው ችግር ውስጠ ዴሞካራሲቸው ክፍት በሆኑት ላይ ‹‹እንዳሻቸው የሚፋንኑ ሰዎች›› መኖርንም እንደ ችግር ጠቅሰዋል።
የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ቡድንን ከመሠረቱት መካከል የምትመደበው ሶሊያና ሽመልስ ፓርቲዎች ከለውጥና ጊዜው ጋር ራሳቸውን እያጣጣሙ የመሔድ ችግር እንዳለባቸው ትገልጻለች። ቁጥራቸው መብዛቱን በተመለከተ ኢሕአዴግ አንድም ዴሞክራሲ አለ ለማለት ሲጠቀምበት በሌላ በኩል ሐሳብን ከመከፋፋል አልፎም ፓርቲዎች እንዲሰነጠቁ ግፊት በማድረግ ገጽታቸውንም እያጣፋ እንደተጠቀመባቸው ጠቅሳለች። የአንድነት ለፍትሕና ዴሞክራሲ ሊቀመንበሩ ትዕግስቱ አወሉ በበኩላቸው ‹‹ከ27 ዓመታት በፊት የያዝነውን ፕሮግራም እንደያዝን ያለን አለን›› በማለት ‹‹ሪፎርም አድርገናል ወይ?›› በማለት አንዱ ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ።
መፍትሔውስ?
ብዙ የሚባልባቸው የፖለቲካ ማኅበራት ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆኑና ጠንካራ አገር አንዲመሠረት ምን ይደረግ ሲባል አንድ ችግር ሆኖ የሚነሳው የፓርቲዎቹ አቋም መራራቅ ነው። በብሔር መደራጃት በሕግ ይከልከል የሚል አቋም ያላቸው ወገኖች የመኖራቸውን ያክል በዚህ ሐሳብ ፍጹም የማይስማሙም አሉ። የኢትዮጵየ ሃገር ዐቀፍ ንቅናቄ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ኃላፈ የሆነችው ወይንሸት ሞላ ሕገ መንግሥቱ ራሱ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው አንዱ ፈተና መሆኑን በመጥቀስ ለጎሳ አደራጆች ፍቃድ የሚሰጥ በመሆኑ ጸረ ዴሞክራሲ ነው የሚል አቋም አላት። ምክንያቷም በክርክር ማሸነፍ ለማይቻልባቸው ጉዳዮች ከለላ ይሰጣል፤ ከሐሳብ ይልቅ ጎሳ ሥልጣን ማግኛ እንዲሆን ያበረታታል የሚል ነው። ሌንጮ ለታ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። ‹‹ማንኛውም ፖለቲካ የማንነት ነው›› በማለት ራስን ሳይበይኑ መደራጀት ከባድ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ትዕግስቱ አወሉ ‹‹ችግሩ በማንነት መደራጀቱ ሳይሆን ዘረኝነት ሲከተል ነው›› ባይ ናቸው። ጌታቸው ደግሞ ሕግን እስካከበረ ድረስ በዘውጌ የሚደራጅ ፓርቲ በራሱ ችግር አይደለም ብለው ያመናሉ። በሌላ በኩል ግን አንድነትን የሚያቀነቅኑ ወገኖች የድሮ ስርዓት ናፋቂ የሚባሉ ከሆነ ችግር እንደሆነ በማስገንዘብ ለሁለቱም ሕጋዊና ነፃ የመወዳደሪያ ሜዳ ማዘጋጀቱ እንደሚበጅ ይመክረሉ።
ዋናው ችግር ‹‹የሐሳብ ነጻነት አለመኖሩ ነው›› ብለው የሚያምኑት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር መሪው አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ከኃይለሥላሴ ሕገ መንግሥት ጀምሮ እስካሁን የሐሳብ ነጻነት አለ ቢባለም አለመተግበሩን ያነሳሉ፡ አገር የሚያድገው በሐሳብ ታግሎ መሆኑን በመጥቀስም ተደራጅቶ ስርዓት የመገንባት ተግባርን መከወን አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
ሶሊያና በበኩሏ ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ሊፈተሹ፣ የርዕዮትና ፖሊሲ ጉዳዮች ላይም ሊያተኩሩ ይገባል ትላለች። ‹ኢሕአዴግ አጀንዳችንን ቀማን› ከሚለው የተለመደ ወቀሳ ሊወጡ እንደሚገባም ትመክራለች። በገዥው ፓርቲ በኩልም ፓርቲና መንግሥት በግልጽ መስመር ሊለያዩ እንደሚገባ ነው የምታምነው። ወይንሸት በበኩሏ ለዓመታት የዘለቀው ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማት የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤቶች እየሆኑ ማገልገል ሊያበቃ ይገባል ብላለች። ሙሼ በበኩላቸው ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች ከያዛቸው ያለመተማመን ‹‹አንጎቨር›› ተላቀው ስለተቋማት ግንባታና ተቋማቱ በማን ይመሩ ወደሚለው አጀንዳ መሻገር እንዳለባቸው ይመክራሉ። ፓርቲዎችንም ከጭፍን ጠላቻ እንዲወጡ ይመክራሉ። የተጀመሩ የማሻሻያ ሥራዎች ሕዝብ አሳታፊ ሆነው እንዲከወኑና በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ገቢራዊ እንዲሆኑ የመከሩት ጌታቸው በበኩላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀራርበው መሥራትና ከደጋፊዎቻቸው ጋር በመነጋገር ወደሥራ መግባት እንዳለባቸው አንስተዋል። ከደጋፊዎች ጋር ለመገናኘት በአገሪቱ የሚሰተዋሉ አለመረጋጋትና የደህንነት ሥጋቶች አሉ የተባለም ሲሆን ችግሩን ለማስወገድ ከመጠላላፍ ወጥቶ ሁሉም በጋራ ሊሠሩበት የሚገባ ኃላፊነት ነው ተብሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 4 ኅዳር 29 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here