ይድረስ ለብርቱካን ሚደቅሳ!

0
1020

የኢትዮጵያ የ2012 አገራዊ ምርጫ ቀኑ ተቆርጦ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተጠበቀ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ፣ የታዩ የተለያዩ ለውጦችና መሻሻሎችም ይህን ምርጫ ፍትሐዊ ይሆናል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጎታል። ከዚህም ለውጥ አንደኛው ብርቱካን ሚደቅሳ የቦርዱ ሊቀመንበር ሆነው መሾማቸው ነው። ግዛቸው አበበ በማላዊ የ2019 ምርጫ የሆነውን በመጥቀስ፣ ሊቀመንበሯ ከወዲሁ ማድረግ አለባቸው ያሉትን ጥንቃቄ እንደሚከተለው ይድረስልኝ ብለዋል።

የማላዊውን የግንቦት 21/2019 (እ.ኤ.አ.) አጠቃላይ ምርጫ ተከትሎ ቅሬታ መሰማት የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ነው። ወዲያውኑ ሕዝባዊ ቅሬታው በማላዊ ወጣቶች “ጄን አንሻ ትወገድ!” (Jane Ansah Must Fall) የሚል አገር ዓቀፍ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ አደረገ። ወጣቶቹ ሴትየዋ ትወገድ ማለታቸው የተጣለባትን ሕዝባዊና አገራዊ አደራ ስላልተወጣች ከሥልጣን ትነሳ ማለታቸው መሆኑ ይሰመርበት። የማላዊ ወጣቶች መፈክር በዘመኑ የአገራችን የወጣቶች አነጋገር “ጃኒ አንሻ ትጫር!” ተብሎ ቢተረጉም ለመግባባት ቀላል ይሆናል።

ወጣቶቹን በመጻረር የተነሱ ሴቶች ደግሞ “እኔ ጄን አንሻ ነኝ!” (I am Jane Ansah) በማለት እንቅስቃሴ ጀመሩ። ግንቦት ላይ የተጀመሩት እነዚህ ኹለት ተጻራሪ እንቅስቃሴዎች፣ በሰኔና ሐምሌም ቀጥለዋል። ኹለቱ እንቅስቃሴዎች ጋብ ማለት የጀመሩት “ጄን አንሻ ትጫር!” የሚለው እንቅስቃሴ ሚዛን ደፍቶ የምርጫው ውዝግብ ወደ ማላዊ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በመቅረቡ ነው።

ፍልሚያው በመገናኛ ብዙኀን ላይ እና በፍርድ ቤት ውስጥ ስለቀጠለ የወጣቶቹ እንቅስቃሴ ስልቱን ቀይሮ እንቅስቃሴውን ለመጀመር ያነሳሳቸውን ነገር በመረጃና በማስረጃ የተደገፈ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጉን ተያያዙት። ይህ የወጣቶች ጥረት ከተቃዋሚ ቡድኖች ልፋት ጋር ተደምሮ ከ500 በላይ የሆነ ገጽ ያለው ወንጀል አስረጅ ሰነድ ተሠራ። የማላዊ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤትም ይህን መረጃ መሰረት አድርጎ ብይኑን ሰጠና የፕሬዝደንታዊው ምርጫ ውጤት ተሰረዘ።
ለመሆኑ ጄኒ አንሻ ማን ናት? ጄን የማላዊ ምርጫ ኮሚሽን ሊቀመንበር ናት። የማላዊ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ግንቦት 2019 በተካሄደው ምርጫ፣ የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ፒተር ሙተሪካ አሸናፊ የተባሉት የምርጫው ውጤት ስለተጭበረበረ ነው ብሎ ይወስን ዘንድ ዋና ግብአት የሆነው የድምጽ ቆጠራ ውጤት የተመዘገበባቸውና የተቀናቃኞች ወኪሎች የተፈራሙባቸው ሰነዶች በምርጫ ቦርዱ አባላት እጅ ከገቡ በኋላ፣ ተሰርዘውና ተደልዘው ውጤቱ እንዲቀየር መደረጉ ስላረጋገጠ ነው።

ይህ የሆነው በምርጫ ኮሚሽኑ ውስጥ ባሉ ሠራተኞች አማካኝነት የመሆኑ ዕድል ሰፊ ነውና፣ ጄን ኃላፊነቷን አልተወጣችም ወይም ከፒተር ሙተሪካ ጋር ተመሳጥራ በሰነዶች ላይ የሰፈሩ ቁጥሮች እንዲቀየሩ ፈቅዳለች ብሎ ለመጠራጠር በር ከፍቷል። ይህ ድርጊት ደግሞ ተቃውሞው በእሷና በአገሪቱ ፕሬዝደንት ላይ ያነጣጠረ እንዲሆን አድርጓል። አሁንም የሕዝብ ጥሪው ቀጥሏል፤ ከምርጫ ኮሚሽን ሊቀመንበርነቷ እንድትነሳ እየተጠየቀ ነው። እሷ የምትመራው ቀርቶ እሷ ያለችበት ምርጫ ኮሚሽን ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ አይችልም የሚለው ጩኸት በርክቷል።

የኢትዮጵያውን ምርጫ ቦርድ የሚመሩት ብርቱካን ሚደቅሳን ያወቅናቸው ለሕዝብ ነጸናትና ለዴሞክራሲ አይበገሬ ጠበቃ ሆነው በመቆማቸው ነው። የብርቱካን ሚደቅሳ ወደ ምርጫ ቦርዱ መምጣት ብዙውን ኢትዮጵያዊ ‘…በዚች አገር ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትና ፓርላማ ሊታይ ነው…’ የሚል ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጎታል።

የብርቱካን ሚደቅሳ ወደ ምርጫ ቦርድ መምጣት ግልጽ ተቃውሞ የተሰማበት ከወደ ትግራይ ከዲጂታል ወያኔዎች ዘንድ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ ብርቱካን ብቻቸውን ምንም ማድረግ ስለማይችሉ በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች የሕዝብን እና የአገርን አደራ ላለመብላትና በጥቅም ላለመደለል ያላቸው ዝግጁነት እንዲሁም በፍርሃት የሌላ ወገን ጉዳይ አሰፈጻሚ ቅጥረኛ ላለመሆን ያላቸው ጽናትና ቁርጠኝነት የምርጫውን ተአማኒነትና ፍትሐዊነት የሚወስን ይሆናል።

ስለዚህ ብዙኀኑ ተስፋ ለጣለባቸው ለብርቱካን ሚደቅሳ አደራ የምንለው፣ መጭው የኢትዮጵያ ምርጫ ግልጽ፣ ታማኝና ነጻ እንዲሆን ሥራ መጀመር የሚገባቸው ከዚያው በምርጫ ቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ሊሆን እንደሚገባ በማሳሰብ ነው። ሶልያና ሽመልስ ከአሜሪካ መጥተው ወደ ምርጫ ቦርዱ እንዴት ገቡ? ሰፋ ያለ ጥሪ ተደርጎና ጥሪውን ተቀብለው ከመጡ ሌሎች ሰዎች ጋር ተወዳድረው አሸንፈው ወይስ በብቸኝነት ተጋብዘው? ብቻቸውን ጥሪ ተደርጎላቸው ወይም ተጋብዘው ከሆነ፣ በማን እና ለምን ተጠሩ/ተጋበዙ? በዚች አገር ውስጥ ሆነው ለዴሞክራሲ ብዙ ከደከሙና ዋጋ ከከፈሉ ሰዎች በምን ተሽለው ነው ለዚህ የበቁት? ሶልያና ሽመልስ ተልከው ነው ብለን ብንጠረጥርስ እንሳሳት ይሆን?

ሶልያና ሽመልስ አሜሪካ ሲኖሩ በዚያች አገር በጣም ብዙ ፓርቲዎች እንዳሉ፣ በግዛት የተወሰኑና ፌዴራላዊ የሆኑ ከመቶ በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች በአሜሪካ እንዳሉ ኹለቱን ፓርቲዎች (ዴሞክራቲክና እና ሪፐብሊካን) ትልቅና ታዋቂ ያደረጋቸው ሕዝብ እና የዘመናት ጥረታቸው እንጅ የሌላ አካል ተጽዕኖ እንዳልሆነ እያወቅስ፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር በተጽዕኖ ለማሳነስ ሲባል የተጋነነ ቁጥር ያለው ፊርማ እንዲያመጡ ሲጠየቅ ለምን ዝምታን መረጡ?

በነገራችን ላይ ፓርቲ ሲቋቋም ‘የመሥራቾቹን ፎቶ አይቶ መወሰን’ ሊባል በሚችል መመዘኛ ብቻ ዐስር ሺሕ ፊርማ ማሰባሰብ ከባድ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። የፓርቲዎችን ጥንካሬ ማየትና የዓላማቸውን ቅቡልነት ማረጋገጥ የሚቻለው የመሥራቾቹን ፎቶ በማየት ወይም የተጻፉ ማንፌስቶዎችን በማንበብ ሳይሆን፣ ተግባራቸውንና ቀጣይ እንቅስቃሴዎቻቸውን በመገምገም ነው። ይህ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በዓመታት ውስጥ ነው።

አሁን ባለው የአገራችን ስርዓት አልባ ሁኔታ ከመሬት ተነስተህ ዐስር ሺሕ ፊርማ ለመሰብሰብ አክራሪ፣ ጎጠኛና ስሜታዊ ሰዎችን የሚያሰልፉ አደገኛ አጀንዳዎችን ማራገብ ግድ የሚል ነው። አንዳንድ ፓርቲዎች ፒያሳ፣ አራት ኪሎ ወዘተ… ባሉ በመንገዶችና አደባባዮች ላይ ሰዎችን አስቀምጠው ፊርማ ሲሰበስቡ አይተናል፤ ለመፈረም የሚጠይቁት የመታወቂያን ኮፒ ብቻ ነበር።

ይህን የመሰለ ቁማር እንዲካሄድ በር የከፈተው “መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር እንዴት ዐስር ሺሕ ፊርማ በዛ ይባላል!” የሚለው ኢትዮጵያ የነበረችበትንና አሁን ያለችበትን ሁኔታ ያላገናዘበ የአንዳንድ የምርጫ ቦርዱ ሰዎች አስተያየት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ይህ አቋም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲዎች ቁጥር ማነስ እንደሚገባው ደጋግመው ከመናገራቸው የተወረሰ ነው። ይህን ማሟላት ያልቻሉ በርካታ ፓርቲዎች ገና ከአሁኑ እያጉረመረሙና የምርጫ ቦርዱን ነጻና ገለልተኛ መሆን እየተጠራጠሩ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው።

ሌሎች የምርጫ ቦርድ ወሳኝ አባላት ሕዝብ (በስልክ፣ በፖስታ፣ በ-ኢሜይል ወዘተ…) ጥቆማ እንዲደርግ ተጠይቆ እንዳስመዘገባቸው፣ በሕዝብ ተጠቆሙ ከተባሉት ውስጥ ምርጫ ቦርድ ስምንቱን መልምሎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላኩን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አራቱን ለይተው የምርጫ ቦርዱ አመራር እንዳደረጓቸው ተነግሯል። ይህ አካሄድ ግልጽነት ካለው ግልጽ የሚሆነው ለምርጫ ቦርዱ ባለሥልጣናትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ነው።

ሌላው ሕዝብ ግን ተባለ፣ ተደረገ፣ ሆነ የሚለውን እየሰማ የማመንና ያለማመን ዕድል ብቻ ነው ያለው። እዚህ ላይ አስገራሚውና ጥያቄን የሚያጭረው ጉዳይ ሕዝብ መረጣቸው ተብለው ምርጫ ቦርድና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልምለዋቸው የምርጫ የቦርዱን ወሳኝ ቦታ የያዙት ሰዎች በአንጻራዊነት ሕዝብ የማያውቃቸው ሰዎች መሆናቸው ነው።

ምርጫ ቦርድ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በየአካባቢው መልምሎ ማደራጀትን የመሰለ ከባድ ሥራ ቢኖርበትም፣ ይህ ሥራ አለመጀመሩን ባሳለፍነው ቅዳሜ ለንባብ የበቃችው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ይፋ አድርጋለች። ይህን ሥራ ለመፈጸም የተቀመጠው የጊዜ ገደብ እየተጠናቀቀ ነውና ምርጫ ቦርድ በቀረው አጭር ጊዜ ይህን ወሳኝ ሥራ በጥድፊያና ያለ ጥንቃቄ እንዳይሠራው የሚል ስጋትን ያጭራል። እነዚያ በየምርጫ ጣቢያው ሲፈጸሙ የነበሩ ዐይን ያወጡ ምርጫን ለራስ ‘ድል’ የመጠምዘዝና የማስጠምዘዝ፣ ምርጫ በማን አለብኝነት የማጭበርበር ተግባራት በመጭው ምርጫ ደግመው እንዳይከሰቱ ማድረግ የሚቻለው እነዚያን የታዘዙትን ነገር ሁሉ ከመፈጸም ወደኋላ የማይሉ የስርዓት ተላላኪዎችንና መሰሎቻቸውን ከዚህ ሥራ ማራቅ ሲቻል ብቻ ነው።

በዚህ ጊዜ ከሚታየው አገራዊ ሁኔታ በመነሳት፣ እነዚህ መሰል ሰዎችን ያሰማራ ይሆን ተብሎ መጠርጠር የሚገባው ገዥው ቡድን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን የየቀበሌው፣ የየመንደሩና የየከተማው መንግሥት አድርገው የሾሙ በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖችም ጭምር ናቸው። እነዚህ የየአካባቢው ‘መንግሥታት’ በእነሱ ግዛት መንቀሳቀስ የሚችልና የማይችል ፓርቲን ለይተው የፈቃድ ሰጭና ነሺነት ሚናቸውን ሲተገብሩት እየታዩ ነው። እነዚህ የየአካባቢው ‘መንግሥታት’ ወደ እነሱ ግዛት ጎራ የሚሉ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች መስበክ ስለሚችሉት አገራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታም መመሪያና ትዕዛዝ ሲሰጡ ተስተውለዋል።

እነዚህ መንግሥታት ይህን ሥራ በአደባባይ ዛቻ በመሰንዘርና ማስጠንቀቂያ በመስጠት ጀምረውት የነበረ ቢሆንም፣ ይህ አካሄዳቸው ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል ስለተረዱ አሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ወጣቶችን በማሰማራት ፍላጎታቸውን እያስፈጸሙ ነው። የእነዚህ የጎጥና የጎራ መንግሥታት ፌስቡክን በመሳሰሉ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ፣ የመግደል ዛቻን ጨምሮ ብዙ ማስፈራያዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን በግልጽ ሲሰነዝሩ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም።

የአንዳንድ አካባቢዎች አውራወች ግጭት ፈጥረው የለኮሱት እሳት እነሱን ለሕልፈት በመዳረጉ፣ አንዳንዶቹም ባልታወቀ ሁኔታ መሞታቸው መሰማቱን ተከትሎ አዲስ አበባና በውጭ አገር ሆነው ማስጠንቀቂያና ማስፈራያ ሲነዙ የነበሩት ዋና ዋና ሰዎች ‘ከዛሬ ጀምሮ ፌስቡክ አልጠቀምም’ እያሉ ሲሰናበቱ ተስተውለዋል። በእርግጥ ይህ እውነተኛ ስንብት ነውን? አይመስልም። በሌላ ሥምና በሌላ የፕሮፋይል ምስል የጀመሩትን ሥራ እንደሚቀጥሉ መጠርጠር ተገቢ ነው።

የእነዚህ መንግሥታት ግልጽና ስውር ሥራ በምርጫው ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እንደሚኖረው መጠራጠር አይገባም። ‘በመንደሬ ኢትዮጵያ እያልክ አትሰብክም’ እያለ ለግብግብ የተጋበዘ ግለሰብ ወይም ቡድን ‘በመንደሬማ ለምርጫ አትወዳደርም’ ብሎ አይከለክልም ብሎ ማሰብ አይቻልም። የሽንፈት ውጤትን በጸጋ መቀበልማ የማይታሰብ ነው። የእነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች በየአካባቢው መኖር ችግር መፍጠር የሚጀምረው የየአካበቢውን የምርጫ አስፈጻሚዎች ማደራጀቱ ላይ እንደሚሆን ማሰብ ይቻላል። ጀሌዎቻቸውን አስርጎ ከማስገባት ጀምሮ ለእነሱ ስሜታዊ አካሄድ የማይበጁ ሰዎች ወደ አስፈጻሚነት እንዳይመጡ እስከማድረግ የሚዘልቅ ትርምስ ሊፈጥሩ ይችላሉ።

ከዚህ ሌላ መሣሪያ አቀባብለው ስብሰባ ሲከለክሉና የተጀመረን ስብሰባ ሲበትኑ የታዩ ወጣቶች ያንኑ መሣሪያ ይዘው በምርጫ ወቅት ችግር እንደማይፈጥሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ሌሎች መብታቸውን እንዳይጠቀሙ ከልካይ ሲሆኑ፣ በዝምታ ያያቸው የየአካባቢው አስተዳደርና የፖሊስ ኃይል በምርጫ ወቅት ችግር እንዳይፈጥሩ ያስቆማቸዋል ብሎ ተስፋ ማድረግ አይቻልም። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢ የፖሊስ አዛዦችና የአካባቢው አስተዳደሮች ችግር መፈጸሙን እንዳላወቁ ሆነው ሲክዱና፣ የባሰባቸው ደግሞ ጥፋቱን የተበዳዮቹ ለማስመሰል ሲጥሩ ተስተውለዋል።

ምርጫ ቦርዱ በሺዎች የሚቆጠሩ አስፈጻሚዎቹን ከመመልመሉ በፊት የየአካባቢው ሰላምና ደኅንነት በማንኛውም ግለሰብና ቡድን እጅ ውስጥ አለመሆኑን ማረጋገጥ ይገባዋል። ባለፉት ምርጫዎች ከምርጫ ሕግና ድንብ ውጭ የተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ሕዝብ የሚመሰክርባቸው ግለሰቦች፣ በዚህኛው ምርጫ የገዥው ቡድን ወይም የሌሎች መሣሪያ ሆነው በለመደ እጃቸው ምርጫውን ማጭበርበርና በግላዊና ቡድናዊ ተጽዕኖ ስር ማስገባት እንዳይችሉ ማድረግ የሚቻለው ወደ እዚህ የሥራ ቦታ ድርሽ እንዳይሉ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው።

ይህን ማድረግ ደግሞ ጊዜን የሚጠይቅ ሥራ ነው። የምርጫውን ጊዜ መወሰን የሚገባውም ይህን መሰሉን የጥንቃቄ ሥራ ለመስራት የሚያስፈልገው ጊዜ ሊሆን ይገባል። ይህን ጥንቃቄ ማድረግና አለማድረግ መጭውን ምርጫ ለማካሄድና ላለማካሄድም መሰረታዊ ነጥብ መሆን ይገባዋል። ይኸኛው ምርጫ እንደ ቀደምቶቹ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ምርጫዎች ቅርጫ ሊሆን አይገባውምና!
ግዛቸው አበበ / gizachewabe@gmail.com

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here