የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የንግድ ሚኒስቴር ለዓመታት ሲያወዛግብ የቆየውን የነዳጅ ስርጭት ችግሮችን ለመቆጣጠር የተቋመውን የነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንዲመሩ አሕመድ ቱሳ ተሾሙ።
መቋቋሚያ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ ከወራት በኋላ የሰው ኃይሉን መልምሎ ወደ ሥራ የገባው ተቋሙ፣ ለንግድ ሚኒስቴር ተጠሪ ሲሆን ራሱን ችሎ እስኪወጣ ድረስ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር እንደሚቆይ የንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እሸቴ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹ነዳጅ ትልቅ የአገር ሀብት የሚወጣበት እና ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በዓመት የሚፈጅ ግብይት እንደመሆኑ፣ ስርጭት እና ሂደቱ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ አስፋለጊ እንዲሆን አድርጎታል›› ያሉት እሸቴ፣ አያይዘውም ‹‹ይህ ባለሥልጣንም ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ በሚታየው የክትትልና ቁጥጥር ችግር ምክንያት በወር መግቢያና መውጫ ላይ የሚያጋጥመውን ተደጋጋሚ እጥረት ለመግታት ያግዛል።›› ብለዋል።
ባለሥልጣኑ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭቱን በባለቤትነትና በተጠያቂነት በመምራት አፈፃፀሙን የሚከታተልና የሕግ ጥሰት ተፈፅሞ ሲገኝ እርማት የሚወስድ እንደሆነም ተገልጿል።
ተቋሙ ግብይቱ ተገቢ በሆነ የንግድ አሰራር መመራቱ እና ለኅብረተሰቡ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ፣ ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶችን በማጣራት፣ በማቅረብ፣ በማከማቸት፣ በማጓጓዝ፣ በማከፋፈል፣ በመቸርቸር እና ከእነዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ተግባራትም የሚቆጣጠር ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች በተደጋጋሚ በሚያጋጥሙ የቤንዚን እጥረት ክስተቶች፣ የመአድን ሚኒስቴር፣ የንግድ ሚኒስቴር እና የየከተማ አስተዳደሮቹ የቁጥጥር ሥራዎችን አንዱ ወደ ሌላው ሲያንከባልል ቆይቷል። የተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ መቋቋም፣ በአገር ውስጥ በተገቢው መንገድ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት እንዲሁም ግብይት እንዲኖር እና እነዚህን የቁጥጥር መበታተን ሰብስቦ በመፈጸም ዋነኛው የባለሥልጣኑ የመቋቋሚያ ምክንያት እንደሆነ ተጠቁሟል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሚኒስቴሮች ሥር የነበረው የነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች ስርጭት፣ በርካታ ክፍተቶችና የመልካም አስተዳደር እጦት ይስተዋልበት እንደነበር በተለያየ ጊዜ አስተያየቶች ሲሰጡ ስነብተዋል።
ባለሥልጣኑ በነዳጅ እና ነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ሥራ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችን ከስርጭትና አቅርቦት ጋር በተገናኘ ሕጋዊ ባልሆነ ተግባር ሲሳተፉ፣ ተገቢውን የቅጣት እርምጃ በራሱ የመውሰድ እና የማስወሰድ ኃላፊነት አለው። ከዚህም ጋር ተያይዞም ባለሥልጣኑ የነዳጅ የመጠባበቂያ ክምችት መጠን በዓይነት እንዲወሰን የማድረግ ሥልጣን ይኖረዋል።
የነዳጅ ዋጋ ቁጥጥር የሚደረግበትና በየወሩም ክለሳ የሚደረግበት ሲሆን፣ አግባብ ባላቸው ሕጎች መሰረት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን ከመስጠት ባሻገር የተሰጡ ሥራ ፈቃዶችን ለተገቢው ዓላማ መዋላቸውን ይቆጣጠራል።
ለነዳጅ አቅርቦት እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አሕመድ ቱሳ፣ ከዚህ ቀደም የሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን አገልግለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012



