የመስዋዕትነት ቅብብል

0
732

ሰው እገሌ ቢወልድ እገሌን፣ እገሌ ቢወልድ እገሌን እያለ የዘር ሐረጉን ይቆጥራል። የሴት የዘር ሐርግ ወደኋላ እየተመዘዘ ቢቆጠርና ይህም በሕይወት ውጣ ውረድ መልክ ቢጻፍ ምን ይመስል ይሆን?

ከአንድ የሥራ ባልደረባዬ ጋር ይህን ጉዳይ ስናነሳ፣ በመስዋዕትነት የደመቀ ነው ስትል ገለጸችው። እያንዳንዷ ሴት ከእናቷ የወረሰችውን ድካም ለሴት ልጇ ላለማውረስ፣ የራሷንም የልጇንም ሕይወት መልክ ለመቀየር ስትጥር ትታያለች። በደል አድራሽ ወንድ ብቻ ነው ብላችሁ እንዳትሳሳቱ፣ ማኅበረሰብና ባህል ጫናቸው ቀላል አይደለም። ሁሉም ሸክሙን በሴቷ ላይ ሲጥል ነው የኖረው።

የዛሬዋ ሴት ከየት መጣች ላለ፣ ትውልዷ እንዲህ ነው። አያቷ በወንድ አያቷ እንደ አቅመ ቢስ አገልጋይ እንጂ እንደ ሚስት፣ እንደ ሰው በክብር የታዩበትን ቀን እናቷ ነግረዋት አያውቅም።

እናቷ እንዲህ ይሉ ነበር፤ ‹‹ከእናቴ የተሻለ ኑሮን መኖር አለብኝ። እኔም ሰው ነኝ። እንደ ሰው ክብርን እፈልጋለሁ። በምወዳቸውና ልንከባከባቸው ቃል በገባሁላቸው ሰዎች ስር ባርያ ሆኜ መኖር አልፈልግም።›› እናም የተሻለ ትዳር፣ የተሸለ ቤተሰብና የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲኖራቸው የተቻላቸውን ሁሉ አደረጉ፤ አልተሳካም።
‹‹እርሷ ከሌላው ሴት በምን ተለይታ ነው! አርፋ ልጆቿን አታሳድግም! ቢመታትስ ባሏ ነው…አትታገሰውም! መቻል ነበረባት! ለልጆቿ ማሰብ ነበረባት፤ ጎሽ ለልጇ ስትል ይባል የለ!›› አይዞሽ ካላት ይልቅ፣ የሴትነት ደንቡን ያስታወሳት ይበዛ ነበር። ማኅበረሰቡና አካባቢዋ የለመደውን ልማድ ለመተው አልተሸነፈችም፤ ታዘዘችለት እንጂ። የተባለችውን ሆነች፣ የሚደረገውን አደረገች፣ ለልጇ ግን እንደዛ ያለ ሕይወት እንዳይገጥማት ከልቧ ትማጸን ነበር።

‹‹ምን መሆን ትፈልጊያለሽ?›› ልጇን ትጠይቃታለች፤ የዛሬዋን ሴት ልጅ። ‹‹ዶክተር›› ልጅ ትመልሳለች። ‹‹የኔ ልጅ ጎበዝ! በርትተሽ ተማሪ። እኔ አንቺን ለማሳደግ የሆንኩትን ታውቂ የለ!›› በልጅነት ለዘብ ያለው የእናቷ ምክር እያደር የመስዋዕትነት ድርሳን ሆኖ ይነበባል። ‹‹ለልጆቼ ብዬ! ለትዳሬ ብዬ! ለሰው አፍ ብዬ! ለቤተሰቤ ክብር ብዬ! ለአንቺ ብዬ!›› እናቷ ከአያቷ የተቀበሉትን መስዋዕትነት ትሰማለች፤ እስኪበቃት።

የዛሬዋ ‹የመስዋዕትነት ጉዞው በእኔ ይበቃል!› የምትል ይመስላል። ብዙዎች የሚፈርዱባት ቢሆንም፣ ብልሃትና ጥበባቸው አደባባይ ሊወጣ ሲገባ ሳይፈልጉ በቤት ውስጥ ተዘግተው የኖሩ እናትና አያቷን አይታለችና፣ ጆሮ አትሰጥም። የእናቷን መስዋዕትነት ላለመድገም፣ ትምህርትን፣ የምትወደውን ሥራ፣ ደስ የሚያሰኛትን ለማድረግ ቅድሚያ ትሰጣለች። ለልጆቿ ብላ በትዳር መታሰርን አትመርጥም፣ ለልጆቿ እናቷ የነገሯትን ተመሳሳይ ታሪክ ላለመድገም ብትተወው የምትመርጥ ናት። የመስዋዕትነት ቅብብሉ በእርሷ የሚያበቃ ይሆን? አናውቅም።

ይህቺ ሴት አሁን፣ ዛሬ የሚያበረቷት አሉ። እንዲህም በዜማ…እንዲህም በግጥም፤
እንከን የሌለብሽ…ከእግር እስከራስሽ
ሴትን አስከባሪ…እኔ ነኝ ባይ ማነሽ
አለሁ የምትይኝ…ግሩም ድንቅ የሆንሽ
ኢትዮጵያዊት ቆንጆ…ምን ትጠብቂያለሽ
ፍፁም ኢትዮጵያዊት…ዐይናማ ደማማይ
ወይዘሪት ኢትዮጵያ…ቆንጂት እኔ ነኝ ባይ
ተራመጅ ወደፊት…ውጪ በአደባባይ
እንቃወማለን…አንቺን በክፉ የሚያይ

ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here