ከፀሐይ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ኅዳር/2012 ተጀምሮ በስድስት ወር ለመጨረስ ታስቦ፣ ከተቋራጮች ጋር ውል ቢታሰርም፣ ከሚገነቡት 12 ፕሮጀክቶች መካከል የስምንቱ ግንባታ እስከ አሁን አልተጀመረም።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ12 ገጠራማ እና ከዋና የኤሌክትሪክ መስመሮች ርቀው የሚገኙ ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ከሦስት ወራት በፊት እንደሚጀመር ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ስምንት ያህሉ ግንባታቸው እስከ አሁን አልተጀመረም።
የኃይል ማመንጫዎቹ ግንባታ በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ይጠበቅ ነበር። ሆኖም ከባንክ ጋር በተያየዙ ችግሮች እና በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ግንባታቸው ሳይጀመር ለሦስት ወራት መዘግየቱን ለማወቅ ተችሏል።
ፕሮጀክቶቹ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ ከብሔራዊ የኃይል ማሰራጫዎች ርቀው ለሚኖሩ 68 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች ኃይል የማቅረብ አቅም ይኖራቸዋል። ፕሮጀክቶቹ በቻይና እና በስፔን ድርጅቶች የሚከናወኑ ናቸው።
የገንዘብ ክፍያ ስምምነቱ በብሔራዊ ባንክ በኩል የሚደረግ መሆኑን ተከትሎ፣ ከባንክ እና ከክፍያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስፈፀም መጓተቶች በመግጠማቸው በስምንቱ ከተሞች ላይ እስከ አሁን ግንባታው ሊጀመር እንዳልቻለ የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት የፕሮጀክቶች ክትትል ቡድን መሪ ደሞዝ ባዪ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ስምንቱ ፕሮጀክቶች ሊጀመሩ ከሚገባበት ጊዜ በሦስት ወራት ዘግይተዋል ያሉት ደሞዝ፣ የቅድመ ግንባታ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልፀው፣ አራቱ ከተሞች ላይ ያሉትን ፕሮጀክቶች ግንባታ ግን በአንድ ወር ብቻ የዘገየ በመሆኑ በተያዘለት ጊዜ መሰረት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአራቱ ከተሞች ላይ የፀሐይ ኃይል መሰብሰቢያ መሣሪያዎች ማስቀመጫዎች ግንባታ መጠናቀቁን የገለፁት ደሞዝ፣ የስምንቱ ከተሞች ፕሮጀክት መሣሪያዎቹ በቻይና በተከሰተው ኮሮና ምክንያት ወደ አገር ውስጥ ገብተው ፍተሻ ሊደረግባቸው አልቻለም ብለዋል።
በግንባታው ላይ የሚፈጠረውንም መዘግየት ለማስቀረት መሣሪያዎቹ በደረሱበት ጊዜ እንዲገጣጠሙ በማድረግ የዋስትና ጊዜውን በማስረዘም በሥራ ላይ ሆነው የሚፈተሹበትን አማራጭ ለመተግበር ከኩባንያዎቹ ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን ብለዋል።
በስምንት ክልሎች በ12 ከተሞች ላይ በመገንባት ላይ የሚገኙት ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ከ60 እስከ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖሩ 68 ሺሕ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው።
አጠቃላይ 300 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸው ሲሆን፣ በዓለም ባንክ ድጋፍ እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሸፈን ነው። በአገራችን 56 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኝ ሲሆን፣ እስከ አሁንም ታዳሽ ኃይልን መሰረት ባደረጉ ኃይል ማመንጫዎች 11 ከመቶ ለሚሆኑ ዜጎች ኤሌክትሪክ ማቅረብ ተችሏል።
ከ44 በመቶ የኤሌክትሪክ ሽፋን ውስጥም እስከ 33 በመቶ የሚደርሰውን የኃይል ፍላጎት በዋና የኤሌክትሪክ ቋቶች በማሟላት ላይ ይገኛል።
በቀጣይም በሁሉም ክልሎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች 25 ፕሮጀክቶችን ለማከናወን በዝግጅት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ120 ሺሕ በላይ ዜጎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በያዝነው ዓመት በ25 ከተሞች ላይ እስከ ኹለት ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በ20 ሚሊዮን ዶላር ለማስጀመር ጨረታ እየተከናወነ ይገኛል።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012



