የገቢዎች ሚኒስቴር በየካቲት ወር 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ

0
599

የገቢዎች ሚኒስቴር በየካቲት ወር ከወጪ እና ከአገር ውስጥ ቀረጥ 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ለአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዚህ ዓመት ሊሰበስብ ካቀደው 20 ቢሊየን ብር ውስጥ በዚህ ወር ብቻ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም ገልጿል።

ሚኒስቴሩ በዓመቱ መጀመሪያ 248 ቢሊዮን ብር ለመሰብስብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ለአገር በቀል ኢኮኖሚ 20 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የመሰብሰብ ኃላፊነት በመውሰድ በዓመቱ መጨረሻ 270 ቢሊዮን ብር ገቢ የመሰብሰብ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጿል።

ከአገር በቀል የኢኮኖሚ እቅድ በፊት በየካቲት ወር ሊሰበስብ ያቀደው 18 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህን ዕቅድ መቶ በመቶ በማሳካት በተጨማሪነት ለአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚውል አንድ ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን አክሎ ጠቅሷል።

ባለፉት 8 ወራት 169 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 167 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 99 በመቶ ማከናወኑኑን በመግለፅ፣ የተሰበሰበው ገንዘብ ካለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር 36 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወይም የ28 በመቶ እድገት አሳይቷል። ከአገር ውስጥ ታክስ ብር 92 ነጥብ 5 ቢሊዮን እና ከውጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ 74 ነጥብ 1 ቢሊዮን መሰብሰቡንም አስታውቋል።

ለገቢው መገኘት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞቹን እና ግብር ከፋዮችን ያመሰገነ ሲሆን፣ ግብር በሚያጭበረብሩ እና በሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here