ሰሞኑን በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስተዋለ ያለው ወበቅ በልግ ወቅት የሚከሰት እንደሆነ እና በቀጣዮቹ ሳምንታት የበልግ ዝናብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሚጠበቅ የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።
በበልግ ወራት ወደ አገሪቱ በሚገባው እርጥበት አዘል አየር የሚፈጥረው ደመና፣ የፀሐይ ጨረር መሬት ደርሶ ወደ ላይ ሲመለስ እንዲታመቅ ስለሚያደርገው በአካባቢው ወበቃማ እና ምቹ ያልሆነ አየር እንዲኖር እንደሚያደርግ ኤጀንሲው ገልጿል።
ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት በተለይ ደግሞ በመኝታ ሰዓት ምቾት የሚያሳጣ የአየር ሁኔታ በብዛት የሚስተዋልበት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፣ አሁን ላይ የዚህ አይነት ሙቀት እና ወበቅ በደጋማ አካባቢዎችም እየተስተዋለ ይገኛል። በቆላማ አካባቢ ያሉ ሰዎች በቀኑ ክፍለ ጊዜ ከመተኛት ሊቆጠቡ ይገባል ሲልም ኤጀንሲው አሳስቧል።
ባለፉት 10 ቀናት በኤጀንሲው ግምገማ በደቡብ እና መካከለኛው የአገሪቱ አካባቢዎች እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት የተሻለ ገፅታ የነበረው ሲሆን፣ በአንዳንድ ቆላማ ተፋሰሶች ላይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር ለውሃ ትነት አስተዋጽኦ እንደነበረው ተገልጿል።
በቀጣዮቹ ሳምንታት የእርጥበት ሁኔታው እየጨመረና እየተጠናከረ እንደሚሄድ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞም አብዛኛዎቹ የበልግ ሰብል አምራች የሆኑት አካባቢዎች ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ እርጥበት ሊኖራቸው እንደሚችል እና በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ እርጥበት እንደሚኖራቸው ተተንብይዋል።
ወቅቱ የማሳ ዝግጅት ለማድረግ እና የተለያዩ የበልግ ሰብሎችን ለመዝራት አዎንታዊ ሚና የሚኖረው ሲሆን፣ አስቀድመው ለተዘሩ የተለያዩ የበልግ ወቅት ሰብሎችም ሆነ በአካባቢዎቹ ለሚበቅሉ ቋሚ ተክሎች እንዲሁም ለግጦሽ ሳር እና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦትም በጎ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
እንዲሁም ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በእነዚህ ወቅቶች የሚገኘውን ዝናብ በመሰብሰብ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሊያውሉት እንደሚገባ ኤጀንሲው አሳስቧል።
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012



