የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዜና ፎቶ እና ዜና ሹመት

0
796

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መጋቢት 1/2012 ቀትር አካባቢ በሠራው ዜና የሰሞኑ የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኑ ሰንብቷል።
‹‹ቦርዱ የምርጫ ክልሎችን ካርታ ቅዳሜ ይፋ ያደርጋል” በሚል ርዕስ በሠራው ዜና ስር የተጠቀመው ምስል የተሳሳተ መሆኑን እየገለጽን፤ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።›› ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ ይቅርታም ጠይቋል።

ይቅርታው ግን ከመነጋገሪያ አጀንዳነት አላራቀውም። እንደውም እንዴት እንደዚህ ዓይነት ስህተት ያውም አንጋፋ ከሚባል ድርጅት ይፈጠራል ሲሉ አንዳንዶች ተቆጥተዋል። ስህተቱ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተፈጠረ እንደመሆኑ፣ ሚድያው ፍጥነት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በስህተት የተፈጠረ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡ ሰዎችም ነበሩ።

‹‹ድርጅቱ ይህንን ስህተት የፈጠሩ ጋዜጠኞቹን ከሥራ ያገደ መሆኑን እየገለጽን፤ በቀጣይ የሚወሰደውን እርምጃም እናሳውቃለን። ድርጅታችን ለተፈጠረው ስህተት በድጋሜ አንባቢዎቹን ይቅርታ ይጠይቃል።›› ድርጅቱ በገጹ ላይ ያስነበበው ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ከተፈጠረው ስህተት ጋር በተያያዘ ጋዜጠኛው አመለ ሸጋ ነበር፣ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ ሲኖር ቤተኛ እንደነበርም በመመስከር ‹እንዴት እንዲህ ዓይነት ተራ ስህተት ሠራ?› ሲሉም የጠየቁ ጥቂት ሰዎች አይደሉም።

አሁን አሁን አንድ ነገር በኢትዮጵያ ሲፈጠር ተያይዞ የሚመጣው መነጋገሪያ መሆን ብቻ አይደለም። ሐሳቡ ከብሔር፣ከሃይማኖት እና ከፖቲካዊ ጉዳዮች ይታያል፣ ይብራራልም።
ከሰሞኑ የሆነውም እንዲህ ነው። አክቲቪስትና ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ የተፈጠረውን ነገር እንዲህ ሲሉ ነበር በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ያስታወቁት፤ ‹‹በትላንትናው የፕሬስ ድርጅት ጉዳይ ላይ እስከ አሁን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮም የብሮድካስት በለሥልጣን ያወጣው መግለጫ የለም!››

የፕሬስ ድርጅት ጉዳይ ከዜናነት ሳይወርድ የተወካዮች ምክር ቤት የቀረበላቸውን ሹመት ማጽደቅ ላይ ሌላ ክስተት ተፈጠረ። ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባልነታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከመፅደቁ በፊት ‹‹በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የፌስቡክ ገፅ የተፈጸመው አስነዋሪ ተግባር ‹‹ስህተት›› ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። ባትሪው የተሰካበትን ዋናውን ገመድ፣ ገመዱም የተቀጠለበትን ጄኔሬተር ፈልጎ ማግኘት፣ አግኝቶም መቁረጥ የግድ ይላል›› ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ ፅፈው ነበር።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 03/2012 ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ፣ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ሆነው ከቀረቡ ዘጠኝ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ቅሬታ ቀረበ፣ በተቃውሞ ብዙም ሥማቸው ከማይነሳው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት።

ግለሰቡ የሀይማኖት እኩልነት ላይ የማያምኑ፣ በዜጎች መካከል ክፍፍል እንዲፈጠር የሚሠሩ በማለት በሕዝብ የሚነሱባቸው ቅሬታ ወደ ጎን በመተው መቅረብ አልነበረባቸውም በሚል ቅሬታ ተሰማ። ቅሬታ የቀረበባቸው ዳንኤል ጉዳያቸው ታይቶ ድምጽ እንዲሰጥ ከተደረገ በኋላ፣ በ148 ድጋፍ በ126 ተቃውሞ እና 24 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ የቦርድ አባልነታቸው ጸደቀ። በአብላጫ ድጋፍ ድምጽ በመመረጣቸው በሕዝብ ተወካዮቹ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

በዳንኤል ላይ ቅሬታ ያሰሙ ሰዎችን አስመልክቶ ከተሰነዘሩ አስተያየቶች መካከል፣ ‹‹ዳንኤል የተለያዩ መጽሐፎችን ሲጽፉ እኮ እናንተ ስታንቀላፉ ነበር። እሳቸውን ለመተቸት ሞራል የላችሁም›› የሚል ይገኝበታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here