የኢትዮጵያ ታሪክ ከሦስት ሺሕ ዓመት የሚዘልቅና የሚልቅ ነው። በእነዚህ ሁሉ፣ በምናውቃቸውም በማናውቃቸውም ዘመናት ታድያ የኢትዮጵያ ገበሬ ዝናብና በሬውን እያሞገሰና እያባበለ ሲኖር ነው የሚታወቀው። አንዳንዴ ተፈጥሮ ፊቷን ስታዞርበት ከሚያጋጥመው ድርቅና ረሃብ በላይ፣ በፖሊሲ፣ በስርዓትና በሕግ ሥም መሬቱን መነጠቁ ከሁሉም ሲያስከፋው ኖሯል።
በተለያየ ዘመን ከተሰማው የገበሬዎች አመጽ ውጪ፣ የቀለም ትምህርት የቀሰሙ የገበሬ ልጆች ‹መሬት ለአራሹ› ብለው ንቅናቄ ያካሄዱበትና ጥያቄ ያስነሱበት ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ በጉልህ ተጽፎ ይገኛል። ይህ የአርሶና አርብቶ አደሩ የመሬት ጥያቄ ከዛን ዘመን ጀምሮ ሲንከባለል፣ ዘመናዊነትን ለመላበስ ለምትዳክረው ለዛሬዋ ኢትዮጵያም ደርሷል። ጥያቄው ከዘመን ዘመን እየተለዋወጠ መሆኑ ላይ ብዙዎች ቢከራከሩም፣ ገበሬው ዛሬም ድረስ በሚገባ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ግን ሁሉም ይስማማሉ።
አሁን ላይ ደግሞ ነገሩ የከፋው፣ መሬት አልባነት እየባሰና ሥራ አጥነት እየበረታ በመምጣቱ ነው። አልፎም ወደ ኢንደስትሪ ይደረጋል የተባለው ሽግግር ከመንገድ ሲዘገይና መንገድ ሲጠፋው፣ የታሰበው እስኪሳካ ድረስ ወጣት ኃይል በመሃል እየባከነ ተገኝቷል። መሬት አልባነትን፣ የመሬት ለአራሹ አዋጅና በአሁኗ ኢትዮጵያ ስላለው የመሬት ይዞታና አስተዳደር ጉዳይ የአዲስ ማለዳዎቹ አሸናፊ እንዳለ እና ሊድያ ተስፋዬ፣ ባለሞያዎችን በማነጋገር፣ የጥናት ወረቀቶችን በማገላበጥና ከመጻሕፍት በማጣቀስ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርገውታል።
የሕይወትን የተለያዩ ገጾች ያስተናገዱበትን እድሜ ጨርሰው ዓለምን ከተሰናበቱ ከራርሟል። በደስታ የሞላው ትዳርና ቤተሰባቸው ወደማብቂያው ላይ ጨላልሞ እንደነበር ታሪኩን ለአዲስ ማለዳ ያጫወቱት ግለሰብ ይናገራሉ። እንዲህ ነበር። አባት ዐስር ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ነበራቸው። የተወሰነውን ለእርሻ የተረፈውን ደግሞ መኖሪያ ቤታቸውን ሠርተውበታል። ይዘራሉ፣ ያርሳሉ፣ ያጭዳሉ።
የባለቤታቸው ውሎ ካሉት ሠላሳ በላይ ከሚሆኑ ከብቶች ጋር ተሳስሯል። ወተትና የወተት ምርቶችን ከልጆቻቸው አልፎ ለአካባቢው ሰው ያዳርሳሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ ኑሮ ቀጥሎ ዓመታት ነጎዱ፣ ልጆች አደጉ። በድንገት ታድያ ባል ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ። መሬቱንና ሀብቱንም እናትና ልጆች ይካፈላሉ። ኑሮው ግን እንደ አጀማመሩ ጥሩና ቀለል ሆኖ አልዘለቀም።
እኚህ እናት የያዙት ቦታ ለልማት የሚፈለግ እንደሆነ ተነገራቸው፤ ለኮንዶሚንየም ቤቶች መገንቢያ። የተሰጣቸው አማራጭ የለም። ሦስት ባልሞላ የምርት ዓመት ሊያገኙ በሚችሉት ዋጋ፣ ከ130 ሺሕ ባልበለጠ የገንዘብ ካሳ፣ ሰባት ሺሕ ካሬ ቦታቸው ተወሰደ። የቀራቸው ቦታ ከሠላሳ በላይ ለነበሩትና የሕይወታቸው አንድ አካል መሆናቸውን ለተላመዱት ከብቶቻቸው ለግጦሽ እንኳ በቂ አልነበረም። እና በተገኘው ዋጋ ከብቶቹን ሸጡ፤ ኹለት ብቻ እስኪቀሩ።
በተረፈቻቸው ኩርማን መሬት ላይም አንዳች ዋስትና አልነበራቸውም። ዛሬ ባይሆን እንኳ ነገ ሊፈጠር የሚችለውን መገመት አይችሉም፣ ‹ተነሱ!› ብሎ ከቦታው የሚያስለቅቃቸው ቢመጣስ? ማንም በድንገት ካሉበት አስነስቶ መሬቱን ሊነጥቃቸው ይችላል፤ ማንም። በዚህ ጭንቅና ሰቀቀን መካከል ሆነው አልቆዩም፣ ሕይወታቸው አለፈ።
በየእለቱ ከመሳቀቃቸው ጎን ለጎን የሚያሳዝነው ደግሞ፣ ከተወሰደባቸውና በቂ ካሳ ካላገኙበት መሬት ላይ ወይ ለራሳቸው እርሻ አልያም በስርዓት ቤት መገንቢያ ሳይሆን ባዶውን የቀረ የመሬት ክፍል መኖሩ ነው። ሕይወታቸው ሲያልፍም ከእርሻ ሌላ የማያውቁ፣ የቀለም ትምህርት ቆጥረው እንኳ ኑሮን በከተማ ሊታገሉ ይችላሉ የማይባሉ የልጆቻቸው ነገር እያብሰለሰላቸው ነው።
ይህን ታሪክ ለአዲስ ማለዳ ያጫወቱት ግለሰብ እንዲህ ያለው ታሪክ በአካባቢው የአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ስለመሆኑ ይናገራሉ። በተለያም በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ተመሳሳይ ታሪኮች ይደመጣሉ። ምርታማና ጤፍ በብዛት ይታጨድበት የነበረው መሬት አሁን የድንጋይ ፎቅ ቆሞበታል። ምርታማ መሬት የማይበቅል ድንጋይ ተተክሎበታል።
ግን ከዚህ ያተረፉ ደግሞ አሉ፤ የከተማ መሃንዲሶች። አጋጣሚውም ለእነዚህ ሰዎች የተመቻቸ እድል ሆኖ የድለላ ሥራም በመሥራት የምስኪን ገበሬዎችን መሬት በማሸጥ ሊያገኙ የማይገባውን ጥቅም ያገኛሉ። ይህንንም ተከትሎ በመንግሥት ያሳድሩት አመኔታ የቸገራቸው፣ በመንግሥት ሹመኞች ቀን ከሌት ባዶ እስኪቀሩ የሚገፈፉ እነዚህ ገበሬዎች፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚታየውን የፍርድ ቤት ክርክር ዛሬም አጨናንቀውታል።
ታሪክን የኋሊት
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መሬት ትልቅ ስፍራ አለው። የመሬት ይዞታና ባለቤትነት እንዲሁም አስተዳደር ጉዳይም በተለይ ከአምስቱ ዓመት የፋሽስት ጦርነት ማብቃት ጀምሮ አወዛጋቢ ጉዳይ ነበር ማለት ይቻላል። ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከ1874 እስከ 1983› በተሰኘ መጽሐፋቸው ይህን ታሪክ ‹እርሻና የመሬት ይዞታ› በሚል ንዑስ ክፍል ዳስሰውታል።
በዚህም መሠረት ከአምስት ዓመቱ የፋሺስት ጣልያን ጦርነት በኋላ መሬት እንደ ግላዊ ሀብት ይቆጠር እንደነበር ጠቅሰዋል። ይህም የተለያየ ገጽታ እንደነበረው የሚያነሱት ፕሮፌሰሩ፣ የግል ይዞታ የተስፋፋበት ዋናው መንገድ መንግሥት በስፋት ከያዘውና የመንግሥት መሬት ከተባለው እየቆረሰ ለአገልጋዮቹ በመስጠቱ ነው ይላሉ።
የዚህ የመንግሥት ችሮታ ዋና ተጠቃሚዎችም አርበኞች፣ ስደተኞች፣ ወታደሮችና የሲቪል ሠራተኞች ነበሩ። ቅድሚያ የሚያገኙትም በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ በታማኝነት የሚያገለግሉት ነበሩ።
ይህንንም በአሐዝ ሲያስቀምጡ፣ ‹‹ከ1933 በኋላ ከታደለው አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ለመሬት አልባ ወይም ሥራ አጥ ከሆኑት ሊያገኙ የቻሉት ጥቂትና በሺሕዎች የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው›› ይላሉ። ይህ የግል ይዞታ መስፋፋትም ለጭሰኝነት መስፋፋት ዋነኛው ምክንያት ሆነ።
በመጽሐፉም እንዲህ ሲሉ የገበሬውን ሁኔታ ገልጸውታል፤ ‹‹እንግዲህ የገበሬውን ሁኔታ ስናጠቃልል የነበረው ስዕል በአንድ ወገን በመንግሥትና በወኪሎቹ ሲገፋ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ድርቅና የአንበጣ መንጋ ለመሳሰሉ የተፈጥሮ መቅሰፍቶች ተጋልጦ በቀላል ለረሀብ የተዳረገ ሆኖ እናገኘዋለን።››
ይህን ተከትሎና በተለያዩ ኹነቶች መከሰት፣ የመሬት ለአራሹ ጥያቄ መጣ። ደርግም ይህን ጥያቄ በታኅሳስ 1967 አዋጅ መፍትሔ ሰጠው። መሬትን ከግል እና መንግሥታዊ ካልሆነ ባለቤትነት ወደ መንግሥት ወይም ሕዝብ ለወጠው። ይህ ብዙዎችን ያስደሰተ፣ በኢትዮጵያ የገበሬውና የመሬት ታሪክ ወሳኝ ምዕራፍ ሆኖ የሚገኝ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በማኅበራዊ ጥናት ፎረም የመሬት ጉዳይ ጥናት ባለሞያ ደሳለኝ ራኽመቶ፣ የአዋጁ ዓላማ ፍትህን ለገበሬው መስጠት ነበር ይላሉ። ለውጡ ስር ነቀል እንደነበርም ያስታውሳሉ። ሆኖም አዋጁ ሙሉ ለሙሉ የማውረስ መብትን ካለመፍቀዱ በተጓዳኝ ወደ ተግባር ዘግይቶ መግባቱ፣ የገበሬ ማኅበራት ከተቋቋሙና ገበሬዎች በጋራ በሰፊ መሬት ላይ እንዲያርሱ የነበረው አሠራር ከሕዝብ ብዛት ጋር ሳይመጣጠን ቀርቶ ገበሬውን አለማስደሰቱ፣ ኪራይ መከልከሉ፣ በድምሩም ጉዳዩ ግብርና መር መሆኑ ቀርቶ ፖለቲካ መር መሆኑ፣ ገበሬውን ሌላ ለውጥ ፈላጊ እንዲሆን አስገድዶታል።
በጠቅላላው አዋጁ ብዙ መሬት ካላቸው ግለሰቦች ላይ መንጠቁን እንጂ ለገበሬዎች መስጠት ላይ በሚገባ አልሠራም፣ ለገበሬውም የተረጋገጠ የመሬት ይዞታ ዋስትና አልሰጠም የሚል ሙግትም ይነሳበታል።
በደርግ የሥልጣን ዘመን የመሬት ሪፎርምና አስተዳደር ሚኒስቴር እንዲሁም የእርሻና የመሬት አስተዳደር ሚኒስቴር በመሆን ያገለገሉት ዘገየ አስፋው፣ የያኔው የመሬት ለአራሹ አዋጅ ጊዜ ተወስዶበትና ዙሪያ ገባው ታይቶ አልተሠራም ይላሉ። ይልቁንም የተማሪዎች ንቀናቄ ግፊት ቀላል አልበረምና፣ አዋጁ የወጣው በጥድፊያ ነው ሲሉም ያስረዳሉ።
የስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ተቋም ባሳለፍነው ሐሙስ መጋቢት 28/2012 ባዘጋጀው ‹የመሬት ለአራሹ አዋጅ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አሻራ› በተሰኘ ወርሃዊ የውይይት መድረክ የተገኙት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ከ1979 እስከ 1983 ያገለገሉት ኮ/ል ፍስኃ ደስታ፣ በዚህ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል። እንዲህም አሉ፣ ‹‹አዋጁን በትላንት እንጂ በዛሬ አስተሳሰብና አውድ መገምገም ስህተት ነው። አሁን ያለው ግን ከዛ የበለጠ አስቸጋሪ ነው።››
መሬት የት ሄደ?
መሬት እንደ ውሃ ተንኖ የሚጠፋ ሀብት አይደለም። ታድያ ገበሬ አርሶ የተወሰነ ምርቱን ለገበያ፣ የቀረውን ለቤተሰቡ ቀለብ የሚያደርግበትን ዝግ ያለ እንቅስቃሴ፣ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ያወኩት ይመስላል። በሕግና በስርዓት እንዲመራ ለማስቻል ታስበው የሚዘጋጁና ተግባራዊ የሚደረጉ ፖሊሲዎችም ስርዓት ከማበጀት ጎን ለጎን ችግር መፍጠሩን ተያይዘውታል።
አንዳንድ የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሚሉት፣ ችግሩ የመጣው በአገሪቱ ባለው የመሬት ፖሊሲና አስተዳደር ምክንያት ነው። በኢትዮጵያ በራሷ የዘመን አቆጣጠር በ1974 ነበር ለመጨረሻ ጊዜ የመሬት ስርጭት ለአርሶ አደሮች በስፋት የተደረገው። ከዛ ጊዜ ጀምሮ አዳዲስ የመሬት ይዞታ ምዝገባ የተካሄደው በስጦታ አልያም በውርስ ሲመዘገብ እንጂ አዲስ የመሬት ስርጭት ወይም ክፍፍል አልነበረም።
በመሬት ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን ያካሄዱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና የደኅንነት ጥናት ተቋም ረዳት ፕሮፌሰር ፋና ገብረሰንበት፣ ለመሬት አልባነትና እሱን ተከትሎ ለተፈጠሩ ችግሮች እጅግ በርካታ ምክንያት ሊጠቀስ እንደሚችል ያነሳሉ። ዋና የሚሉት ችግር ግን ከፖሊሲ የሚመጣ ነው።
‹‹ለመሬት አልባነት ችግር በርካታ የመፍትሔ ሐሳቦች አሉ። የመጀመሪያው የመሬት ስርጭት/ክፍፍል ነው። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት የመረጠው መሬትን ለውጪ ባለሀብቶች መስጠትን እንጂ ለገበሬው ማከፋፈልን አይደለም። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ፖሊሲው በዚህ ላይ ተደርቦ ማኅበረሰብን በመንደር ማሰባሰብ በሚል ሥም መሬቱን እየወሰደ ይገኛል።›› ፋና ይላሉ።
አያይዘውም መሬት ለባለሀብት የሚሰጥ ከሆነ፣ አነስተኛ አርሶ አደር ይሁን ወይም በአደን የሚኖር አልያም አርብቶ አደር፣ ብቻ በአካባቢው ያለው ማኅበረሰብ ከኢንቨስትመንቱ ድርሻ ሊኖረው ይገባል።
ባለፉት ዐስርት ዓመታት፣ የፌዴራል መንግሥት 3.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዚህም ላይ 200 ሺሕ የሚደርስ ለስኳር ልማት በሚል ከክልል መንግሥት ወስዷል። ይህም ለውጪ ባለሀብቶች እንዲሰጥ ለመሬት ባንክ ገቢ የሆነ ነው። ከጠቅላላው መሬትም 1.7 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው ከኦሮሚያ ክልል የተወሰደ ነው።
በዚህ ላይ ፋና በሰጡት አስተያየት ተከታዩን ብለዋል። ‹‹ይህ መሬትን በእርሻ ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች በመስጠት በፍጥነት ተጠቃሚ ለመሆን የተደረገ ጥረት ነው። ይህም ምርቶችን ለዓለም ዐቀፍ ገበያ ለማቅረብ ነው። ይሁንና ይህ ግን የሩቁን ያሰበ አካሄድ አልነበረም። ምክንያቱም ይህ አካሄድ በአገሪቱ በሥራ አጥነት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የካፒታል ማግኘት፣ የምግብ ዋስትና የመሳሰሉ ችግሮችን የሚፈታ አልነበረም።››
ታድያ ፋናን ጨምሮ በዘርፉ የሠሩ ባለሞያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ለውጪ ባለሀብቶች ብሎ የፌዴራል መንግሥት ከክልል መንግሥት የወሰደው መሬት፣ ለአርሶ አደሮች ከገንዘብ አቅም እና ከቴክኖሎጂ ድጋፍ ጋር ቢሰጣቸው፣ በበለጠ ይረዳ ነበር።
ከመሬት ፖሊሲው ባሻገር
ለእርሻ መሬት እጥረት እንዲሁም ለመሬት አልባነት መጨመር፣ ከመሬት ፖሊሲው ባሻገር ምክንያት ተብሎ የሚቀመጥ ነጥብ አለ። ይህም የጥቃቅን እርሻ ሥራ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ብቻ የተለመደ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ 80 በመቶ በላይ ሕዝብ እና 34 በመቶ በላይ ዓመታዊ አጠቃላይ አገራዊ ምርትን የያዘው ግብርና፣ 20 በመቶ ታራሽ መሬት ላይ ብቻ የተንተራሰ ነው። ይህም የሆነው አነስተኛ የእርሻ ልማት ሥራ በኢትዮጵያ ማእከላዊ እና ደቡብ ክፍል ላይ ያተኮረ በመሆኑ ነው። እነዚህ ቦታዎች የሚገኘው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ለእርሻ ምቹ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ልብ ይሏል!
ደሳለኝ ራኽመቶ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየትና ቃለመጠይቅ፣ የእርሻ መሬት በኢትዮጵያ በየጊዜው እያነሰ እየሄደ ነው ብለዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ለግብርና የሚሆን የሚታረስ መሬት ውስጥ 20 በመቶውን ብቻ ትጠቀማለች። የቀረው በቆላማው አካባቢ አርብቶ አደሩ የሚጠቀምበት ነው። የሚታረስ መሬት ሳይቀር በብዛት የተከፋፈለ ነው። የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ባለበት ሁኔታ፣ ጥቅም ላይ የሚውል አዲስ መሬት የለም።›› ደሳለኝ እንዳሉት።
ሌላው፤ ለመሬት እጥረት ችግር ተጠቃሽ ምክንያት፣ በግልና በመንግሥት የተለያየ ዘርፍ የመሬት ፍላጎት መጨመር ነው። ይህም ለኢንቨስትመንት በተሰጠው ልዩ ትኩረትና ቦታ ምክንያት እንደሆነ ነው ባለሞያዎቹ የሚያስረዱት። የከተሞች መስፋፋት እንዲሁም የሥነ ሕዝብ እና የአየር ጠባይ ለውጥ፣ ለችግሩ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
‹‹ለም የሆኑ መሬቶች ለኢንዱስትሪ መትከያዎችና ለሌሎች አገልግሎቶች ከመጠቀማቸው በተጓዳኝ፣ ለከተሞች አገልግሎት እየዋሉ ነው። ይህ የሆነው የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ስለሌለን ነው። መሬት ትርፋማ ሊሆን በሚችልበት መስክ ላይ መጠቀም ወሳኝ ነው።›› በግብርና ሚኒስቴር የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ትዕግስቱ ገብረመስቀል ናቸው ያሉት።
ይህ ሁሉ ታድያ ተደማምሮ ከአባቱ የግብርና እና እርሻ ጥበብን የተማረው ወጣት፣ መሬት አልባ እንዲሆን አልፎም ያለምንም ሥራ እንዲቀመጥና፣ ከፍ ሲልም የተሻለ ሥራና ኑሮ ፍለጋ ባህር ማዶ አሻግሮ እንዲያማትር ያስገደደ ሆኗል።
የመሬት አልባነት ጦሱ
በዚህ ሐተታ መግቢያ ላይ እንደተቀመጠው ያለ ታሪክ የአንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ብዙዎች የሚጋሩት ነው። ራሳቸውንና ወገናቸውን እንዳይመግቡ እጃቸው ተሳስሮ የቆዘሙና ያዘኑ ገበሬዎች ጥቂት አይደሉም። በዛም ላይ የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋርጠው ብዙ ጊዜ ሕይወታቸውን ድርቅና ረሀብ ጎብኝቶታል። ይህ ሁሉ የሆነው በእነርሱ ብልሃትና እውቀት ማጣት ግን አልነበረም። ይልቁንም ከመሬት አያያዝና አጠቃቀም እንዲሁም አስተዳደር ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው፤ ባለሞያዎች ያስረዳሉ።
በድምሩ መሬት አልባነት አባወራ ገበሬዎች ራሳቸውን በምግብ እንዳይችሉ ከማድረግ ጀምሮ፣ ለወጣቶች አገር ጥሎ መሰደድ፣ ማኅበራዊ ቀውስ፣ በኢኮኖሚውም የመዋቅር ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል/አድርጓልም።
‹መሬት፣ መሬት አልባነትና ድህነት በኢትዮጵያ› የተሰኘው የጥናት መጽሔት፣ አራት ጥናታዊ ወረቀቶችን አካትቶ በ2018 ነበር ለህትመት የበቃው። የአርትዖት ሥራውን ሙሉ ለሙሉ የሠሩት ደሳለኝ ራኽመቶ፣ መሬት አልባነት ችላ የተባለ፣ ነገር ግን በማንኛውም ሰዓት ሊፈነዳ የሚችል ቦንብ ነው ይላሉ።
በተለያዩ አጥኚ ቡድኖች፣ በአራት የተመረጡ ክልሎች የሚገኙ ከአራት እስከ ስድስት የሚደርሱ ወረዳዎችን ባዳረሰው በዚህ ጥናት፣ በትግራይ 48.8 በመቶ፣ በኦሮሚያ 38.3 በመቶ፣ በደቡብ 25 በመቶ እና በአማራ 15 በመቶው ወጣት መሬት የሌለው ነው ተብሎ ተመዝግቧል። በደቡብ የተደረገው ጥናት ከዛም አልፎ 91 ሺሕ የሚሆኑ ወጣቶች፣ ያውም ከከንባታ እና ከሐዲያ ብቻ፣ አብዛኞቹ መሬት የሌላቸው ሆነው፣ ከ2000 እስከ 2015 ባለው ዓመት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊሰደዱ ተገደዋል።
ወደተለያዩ የዓለም አገራት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ከገጠር ወደ ከተማ ለሚያጋጥመው ከፍተኛ ፍልሰትም ይህ መሬት አልባነትና እሱን የተከተለው ሥራ አጥነት ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው። ይህ የመሬት ይዞታ አልባነት ከዛም ባለፈ ለድህነት፣ ለማኅበረሰባዊ አለመረጋጋትና ለአካባቢ ችግሮች አንድምታ ሆኖ ይቀርባል፤ እንደ ደሳለኝ ገለጻ። ይህም የሥነ ሕዝብ ጫና፣ የመሬት እጥረት እንዲሁም ከእርሻ ባሻገር ያሉ ሥራዎች በቂ አለመሆን የሚያስከትሉት ነው።
ጥናቶቹ እንደሚያመላክቱት፣ በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች፣ ያላቸው የእርሻ መሬት ከክልል እና ብሔራዊ ደረጃ ካለው አማካይ የእርሻ መሬት የሚያንስ ነው። ይህ ችግር ደግሞ በደቡብ ክልል ጭራሹን የተባባሰ ሲሆን፣ ሁሉም አባወራ በሚባል ደረጃ ከ0.5 ሔክታር በታች ነው ያለው። ሌላው ቀርቶ የቤት ውስጥ ቀለብ እንኳ መሸፈን የሚያስችል አቅም የላቸውም።
በኦሮሚያም ይህ ችግር ከፍተኛ ነው የሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራራማ አካባቢዎች ይህ ችግር የዘለቀ ይመስላል። ለዚህም ትልቁ ማሳያ በእነዚህ አካባቢዎች የወጣቱ የስደት መጠን ከፍተኛ መሆን ነው።
‹‹ይህ የሆነው አሁን ላይ አዲስ የእርሻ መሬት የሚፈልግ ብዙ ቁጥር ያለው ወጣት ስላለ ነው። ለረጅም ጊዜ ጥቂት የሚባለው ወጣት መሬት ያገኝ የነበረው ከቤተሰብ በውርስ እንዲሁም አዳዲስ ደን በመመንጠር ነበር። አሁን ይህ ከበቂ በላይ ሄዷል። ሥራ አጥነት በክልላችን ልንቆጣጠረው ከምንችለው በላይ ሆኗል።›› ያሉት በኦሮሚያ ክልል የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ ሚሬሳ ፊጣ ናቸው።
አክለውም አቅምም ሆነ የሥራ ፈጠራ እንደሌለና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ እንኳ የሥራ ፈጠራ ሐሳብ ያላቸው አይደሉም ሲሉ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ምንም እንኳ እድሜያቸው ከ18 በላይ የሆኑ ዜጎች የመሬት ይዞታ እንዲኖራቸው መብት ቢሰጥም፣ በጣም ጥቂት ወጣቶች ያውም ከቤተሰብ የወረሱትን ብቻ ይዘው ይገኛሉ። እንደ ትዕግስቱ ገለጻ ከሆነ፣ ከተመዘገቡ 20 ሚሊዮን አርሶ አደሮች መካከል 15 ሚሊዮኑ ብቻ የእርሻ መሬት የምዝገባ ሰርተፍኬት አላቸው።
ከፍተኛው በገጠር የሚገኘው የሰው ኃይል ወይም 40 በመቶ የሚሆነው የገጠር ማኅበረሰብ፣ መሬት የሌለው ነው። በጣም ጥቂቱ ብቻ በስጦታ አልያም በውርስ መሬት ተቀብሏል።
‹‹መሬት አልባነት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው። በዛ ላይ መሬት ለሌለው ልንሰጠው የምንችለው መሬት የለም። ላላቸው ብቻ ነው የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እየሰጠን ያለነው።›› ያሉት በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት እና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር) ናቸው።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ኹለት ሦስተኛ የሚሆነው የገጠር ሕዝብ መሬት የለውም። ሚሬሳ ለምሳሌ ሲሉ ተከታዩን ጠቅሰዋል። አምስት የቤተሰብ አባላት ባሉበት በአንድ አርሶ አደር አባወራ ቤት፣ ቢያንስ ኹለት ልጆቹ መሬት አልባ ይሆናሉ። ምክንያቱም መሬቱን ከዛ በላይ መከፋፈል ስለማይቻል።
ይህ የሆነው ክልሎች በራሳቸው የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ያወጡ በመሆናቸው ነው። በዚህም አንድ ገበሬ ሊይዝ የሚችለው/የሚፈቀድለት ትንሹ የመሬት ስፋት መጠን 0.25 ሔክታር ነው። ‹‹መሬት ከ0.25 ሔክታር በታች ከተከፋፈለ ግብርናውን በጣም ይጎዳል። ስለዚህ እኛ የምንመዘግበው ከሩብ ሔክታር በላይ ያለውን ነው።›› ሚሬሳ እንዳብራሩት ነው።
በትግራይ እና ደቡብ ክልል ትንሹ የእርሻ መሬት ስፋት ከ0.25 ሔክታር በታች ሆኖም ይገኛል።
ቁጥሮች ይናገሩ
የመሬት ጉዳይ በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሕይወት ጉዳይ የሆነ ይመስላል። 114 ሚሊዮን ሔክታር ስፋት ያለው መሬት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከግማሽ በላይ መሬቷ ለእርሻ ተስማሚ ነው። የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ በ1997 ላይ 9.9 ሚሊዮን ሔክታር ከሆነው ጠቅላላ የሚታረስ መሬት ላይ 13.7 ሚሊዮን ሔክታሩ ብቻ ነው እህል ተዘርቶበት የተገኘው።
ጠቅላላ የሚታረስ መሬት ታድያ ከ1990 እስከ 2000 ድረስ ከነበረበት 9.9 ሚሊዮን ሔክታር፣ ከ2000 እስከ 2012 ወደ 12.7 ሚሊዮን ሔክታር አድጓል።
እስከ 2012 የሚታረስ መሬት በአንድ ሚሊዮን ሔክታር ሲጨምር፣ የግለሰብ አባወራዎች ብዛት በ3 ሚሊዮን አድጎ ወደ 15 ሚሊዮን ተጠግቷል። በድምሩ፣ አዲስ የእርሻ መሬት በ3.8 ሚሊዮን ሄክታር የጨመረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንጻሩ ቢያንስ በ35 ሚሊዮን ጨምሯል።
የሕዝብ ጥግግትም በ2000/2001 በስክዌር ኪሎሜትር 61.6 የነበረው በ2018/2019 ላይ 97.6 ደርሷል።
በማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት፣ ከ36 በመቶ በላይ አነስተኛ እርሻ ያላቸው ገበሬዎች ከ0.5 ሔክታር በታች መሬት ላይ እያረሱ ይገኛሉ። ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከአንድ ሔክታር በታች መሬት ላይ ያርሳሉ። በቁጥር 14 ሺሕ የሚጠጉ ገበሬዎች ብቻ ናቸው ከ10 ሔክታር በላይ መሬት ያላቸው።
ፋና ገብረሰንበት በዚህ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ መሬት አልባነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ አንዱ ማሳያ አማካይ የአንድ ገበሬ የእርሻ መሬት ከአንድ ሔክታር በታች መሆኑ ነው ይላሉ። ይህም ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረበት አንድ ሔክታር እንዲሁም ከዐስርት ዓመታት በፊት ደግሞ ከነበረበት ሦስት ሔክታር አንጻር የወረደ የሚባል ነው።
እስከ 2013/14 ጠቅላላ የሚታረስ መሬት በየዓመቱ በ4 በመቶ ያድግ የነበረ ሲሆን፣ ከዛ በኋላ ግን ከኹለት በመቶ በታች ነው እድገት ያሳየው። የግብርና ሚኒስቴርም በዘገባው ጠቅላላ የሚታረስ መሬት በ0.7 በመቶ ብቻ ነው ያደረገው ሲል አትቷል። እናም የመሬት መከፋፈልና ያለውን የእርሻ መሬት መበጣጠስ፣ መሬት አልባ ለሆኑ ነገር ግን መሬት ላይ ጥገኛ የሆነ ኑሮን ለሚገፉ የገበሬ ልጆችና ቤተሰቦች ብቸኛ ማምለጫ የሆነ ይመስላል።
የመሬት ለአራሹ ጥያቄ…አሁንም?
የመሬት ለአራሹ ጥያቄ ከሌሎች የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ጥያቄዎች ጋር ተዳምሮ መንግሥት ገልብጧል፣ የታሪክን ምዕራፍ ገልጧል። በከተማ የቀለም ትምህርትን የቀሰመውና በገበሬው ላይ የደረሰው ጫና የገባው፣ መሠረቱን ግብርና ካደረገ ቤተሰብ የወጣ ወጣት ነበር፣ ለአባቱና ለእናቱ መብት የተከራከረው። ነገር ግን ጥያቄው በየዘመኑ ሲቀየር እንጂ ምሉዕ የሆነ መልስ ሲያገኝ አልታየም።
ኮ/ል ፍስኃ ደስታ አሁን ጥያቄው መሬት ለአራሹ ዓይነት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። ከዛም የሚሰፋና የሚልቅ መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ዘገየ አስፋው የአሁኑ የመሬት ፖሊሲን ከመሬት ለአራሹ አዋጅ ጋር ሲያነጻጽሩት፣ ያኔ እንደአሁን የፈለገ ገበሬውን የሚያስነሳበትና የሚያቆይበት አሠራር እንዳልነበር አንስተዋል። ‹‹አሁን የወረዳ አስተዳዳሪዎች ሳይቀሩ መሬት ሰጪና ነሺ ናቸው። የአሁኑ ብዙ ችግር አለበት።›› ሲሉ ወቅሰዋል። በተጓዳኝ ግን ጠንካራ ጎኖችና የተመለሱ ጥያቄዎች አሉ ያሉ ሲሆን፣ መሬትን ለወራሽ ማስተላለፍ፣ በወለድ አገድ ማስያዝ መቻሉን አድንቀዋል። ‹‹የተከለከለው መሬት መሸጥ ብቻ ነው። እንኳን ተፈቅዶ ተከልክሎም ገበሬው እንዲሸጥ እየተደረገና እየተፈናቀለ ነው። መሬት የሕዝብ ሆኖ መቆየት እንዳለበት አምናለሁ።›› ሲሉ ተናግረዋል።
በኢፌዴሪ የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው፣ አሁን የመሬት ጉዳይ የግለሰብ ብቻ ወይም የአንድ ቤተሰብ ብቻ እንዳልሆነ አንስተዋል። ይልቁንም እንደ አገር ለልማትና ምጣኔ ሀብትን ለማሳደግ በሚያስችል መንገድ መጠቀም የሚለው አጽንዖት እንደተሰጠው ገልጸዋል።
ግለሰብ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ ብሎ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መሬት እንደሚወስድና እንደወሰደ የጠቀሱት ሌንሳ፣ የቱ ጋር ምን ለምቷል? የትስ ምን መሠራት አለበት? ወደ ልማት እንዴት እናስገባው? የሚለው የመሬት አጠቃቀም ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
‹‹ፖለቲካዊ ሳይሆን በኢኮኖሚው አውድ ነው ጉዳዩን የምናየው። እኛም የወሰድናቸውን እንዴት እናልማቸውን ለሚለው ነው መልስ የምናዘጋጀው። ብዙ ፖሊሲ ቢኖርም የአተገባበር ጥያቄ አለና፣ እሱ ላይ ነው እያስተካከልን ያለነው።›› ሌንሳ እንዳሉት ነው።
ታድያ የወጣቱን መሬት አልባነት በሚመለከት፣ እርሳቸው የሚመሩት ተቋም ይህን ችግር በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹እኛ ኢኮኖሚውን ያንቀሳቅሳል ብለን የያዝነውን መሬት ነው የምናስተዳድረው። ግን ይህን ጥያቄም በተዘዋዋሪ መመለሳችን አይቀርም። በኢኮኖሚው እድገት ሲመጣ ማኅበራዊ ጥቅም ያመጣል። የሥራ እድል ይፈጥራል። ይህም ቴክኖሎጂን ያማከለና ዓለም የደረሰበት ደረጃ ሊያደርሰን በሚችል ደረጃ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። በኢኮኖሚው እንዳለን ሁሉ በማኅበራዊውም ጉዳይ ተጠያቂ የምንሆንበት ነው።›› በማለት አስረድተዋል።
ምን ይደረግ?
እንደ ሌንሳ ገለጻ፣ አዲስ የመሬት ስርጭት ወይም ክፍፍል እንደ መፍትሔ ሐሳብ የሚቀርብ አይደለም። ይልቁንም ባለውና በተያዘው ሀብት ላይ የሥራ እድል በዘላቂነት እንዲፈጠርና ቀጣይት እንዲኖረው ማድረግ ነው የተያዘው ግብ።
ትዕግስቱ ብቸኛው በእጅ ያለ አማራጭ የመሬት ኪራይ ነው ባይ ናቸው። የመሬት አስተዳደር ስርዓቱን ለማዘመን መረጃዎቻችን በዘመናዊ የመረጃ ቋት ማስቀመጥ ላይ እንዲሁም ለአርሶና አርብቶ አደሩ ብድር ለመስጠት የሚያስችለውን ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የመጨረሻው ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል።
ከዚህ በላይ ደግሞ የብድር አገልግሎት አሠራር እንደ ትዕግስቱ ገለጻ፣ ባንኮች መጀመሪያ የመሬትን ምርታማነት፣ የምርት ዓይነት እና የአየር ጸባይ እንዲሁም ገበያውን እንዲተነብዩ የሚያስችላቸው ነው። ከዛም ለመሬቱ ባለይዞታ ብር ሊያበድሩ ይችላሉ። ገበሬው ታድያ ብድሩን በሦስት ዓመት ውስጥ መክፈል ካልቻለ፣ ባንኩ መሬቱን በመውረስ አከራይቶ ገንዘቡን ካስመለሰ በኋላ ለባለይዞታው ይመልሳል። ትዕግስቱ እንደጠቆሙት፣ መንግሥት በተያዘው ዓመት በመሬት ዋስትና 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የብድር መጠን አዘጋጅቷል።
ይህን አሠራር ለመደገፍም የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በዝግጅት ሥራ ላይ ነው ተብሏል። በተጨማሪም የክልል መንግሥታት መሬት አልባነትን ለማስቀረት እና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የየራሳቸውን እቅድ አዘጋጅተው በዛ መሰረት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ሚሬሳ በዚህ ላይ ተከታዩን ሐሳብ አካፍለዋል፤ ‹‹በደጋማ አካባቢዎች በግማሽ ሔክታር መሬት ላይ የተትረፈረፈ ምርት ማምረት እንደሚቻል የግብርና እቅዳችን ያምንበታል። ይህም የሚሆነው አርሶ አደሩ በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት ከቻለ ነው። ሌላው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተያዘው እቅድ የመሬት ኪራይን ማስተዳደሪያ ሕጋዊ መዋቅር ማበጀት ነው። ይህም በመሬት ዋስትና ላይ በ20 ወረዳዎችና በኹለት ጥቃቅን እና አነስተኛ የብድር ተቋማት ከጀመርነው የዳሰሳ ምልከታ ጎን ለጎን ነው።›› ብለዋል።
ዳሳለኝ ራኽመቶ ግን በዚህ ምክረ ሐሳብና አካሄድ አይስማሙም። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በደጋማ አካባቢ ያለው መሬት ያለእረፍት የታረሰና አፈሩም እንዲያገግም እንክብካቤ ያልተደረገለት በመሆኑ የተባለውን ምርታማነት ማግኘት አይቻልም።
‹‹የመሬት ጉዳይ በጣም ውስብስብ በመሆኑ በቀላል ይፈታል ብዬ አላምንም። ለአሁኑ ለመንግሥት አንዳንድ የመፍትሔ ሐሳቦችን ጠቁመናል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አማራጭ መንገድ ተፈልጎ ከሆነ፣ ኢንቨስትመንትን ወደ ቆላማ አካባቢ እንዲወርድ ማድረግ፣ አሁን ያለው አስተዳደር እየሄደበት ያለው መንገድ። ይህ ጥሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል።›› ይላሉ ደሳለኝ። አክለውም ‹‹ነገር ግን ገበሬዎችን ከደጋማ አካባቢ ወደ ቆላማው እንዲሰፍሩ ማድረግ፣ ካለው የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር ከባድ ነው።››
በደሳለኝ እይታ ለረጅም ጊዜና ለዘለቄታው መፍትሄ የሚሆነው፣ መንግሥት ባለው አቅም ሁሉ የአገሬውን ገበሬ ማገዝና ማበረታታት ላይ መሥራቱ ነው። ገበሬው መሬቱን እንዲይዝ ዋስትና መስጠት እንጂ የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ አይደለም ወሳኙ ሲሉም ይሞግታሉ።
‹‹አሁን እርሻ ላይ ያለውን ቅጥር ለመቀነስና ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ቀጣሪ እንዲሆን ለማስቻል፣ ከዚህ በኋላ ከ15 ዓመት በላይ ይወስዳል። በዚህ መካከል ኢትዮጵያ ጥሩ የሚባል፣ ግልጽ፣ ተለዋዋጭ፣ በሕግ የሚያግባባና አርሶ አደሩን የሚደግፍ የመሬት ፖሊሲ ማውጣት ከቻለች፣ ራሳቸው አርሶ አደሮች ከመሬት አልባነት የሚወጡበትን መንገድ ሊያገኙ ይችላሉ።›› በደሳለኝ አመለካከት።
‹‹በቀጣይ አምስት እና ዐስር ዓመት ውስጥ የመሬት ስርዓቱን እና አጠቃቀምን በሚመለከት አሠራሩን ዘመናዊ ለማድረግ፣ አስፈላጊውን የሰው ኃይል ልማት ላይ መሠራት አለበት። መሬት በፖለቲካዊ መንገድ መመራት አለበት፣ በፖለቲከኞች ግን መሆን የለበትም።›› በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት እና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር) እንዳሉት ነው።
ሌንሳ በበኩላቸው፣ ዛሬ ላይ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ ከትላንት መንከባለላቸውና አዳዲስ ጥያቄዎችም መወለዳቸው፣ የቀደሙ ጥሩና መጥፎ ልምዶች ቀምሮ አዲስ ሐሳቦችን ማምጣት ባለመቻል ነው ይላሉ። በዚህም ምክንያት ብዙ ጠፍቷል የሚሉት ሌንሳ፣ የቀደመውን ልምድ ከዛሬው ሐሳብ ጋር አቀናብሮ፣ በመደማመጥና በመነጋገር የራሳችን የሆነ መፍትሔ ማምጣት እንዳለብንም እናምናለን ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012