እንኳን ደኅና መጡ!

0
634

በአቅምና በበጀት አቅሙ ካላቸው ግን መሪ ከማይወጣላቸውና ካልታደሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መካከል የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ። ተቋሙ የተሾሙለት ሚኒስትሮች ይሄ ነው የሚባል ሥራ ሲሠሩበት አይታይም። አልፎም የፖለቲካ ማጫወቻ አድርገውት፣ ‹እገሊት ሥልጣን እስኪገኝላት የት ትቆይ?› ለሚለው ጥያቄ መልስ ሆኖ የከረመ ይመስላል።
አሁን ግን ለውጥ የምንፈልግበት ሰዓት ነው። ለዚህ ለውጥ ያደርሱናል በሚል ተስፋና እምነት፣ አዲሷንና ወጣቷን የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ፊልሰን አብዶላሂን እንኳን ደኅና መጡ እንላለን/እላለሁ።

ዛሬ ከትላንት ይሻላል። የተለየ ተዓምር ኖሮ አይደለም፣ ትላንት ያለፈ ቀን ስለሆነና ዛሬ በእጃችን የሚገኝ ስለሆነ ነው። ለዛም ነው ዛሬ ላይ የመጡትን ፊልሰንን እንኳን ደኅና መጡ ለማለት የወደድኩት።
እርግጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ፣ ሁሉም ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት እንደማይሆን ይገመታል። እንዲህ ያሉ ቦታዎች ደግሞ ለውጥ ለማምጣትና ታሪክ ለመሥራት ወሳኝ ናቸው። አዲሷ ሚኒስትርም ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ለራሳቸውም፣ አገልግሎታቸውን ለሚፈልጉ ይልቁንም ሕጻናትና ሴቶችም በሚችሉት እንደሚሠሩ እምነቴ ነው።

ፊልሰን የቀደመ የትምህርት ቆይታቸውንና የሕይወት ልምዳቸውን ስንመለከት፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ወጣቶችን በማስተባበር እንዲሁም የእርቅና የሰላም ኮንፈረንስ በማዘጋጀት ሥማቸው ተነስቷል። ከዚህም በተለይ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለማረጋጋትና ሰላምን ለማስፈን የሚያስችል ሙያዊ አስተዋጽኦ አበርክተው በዛም ውጤታማ ሥራ መሥራታቸው ይጠቀሳል።

ለዚህም ከኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት ማዕረግ እንደተበረከተላቸው ሰምተናል።
በግሌ ፊልሰን ለውጥ ለማምጣት ብዙ እድል እንዳላቸው አምናለሁ። በአንድ በኩል የወጣትነት እድሜ ላይ በመሆናቸው የለወጥ ፈላጊው ማኅበረሰብን ስሜት ከማንም በላይ እንደሚረዱ በማመን ነው። የልጅ እናት መሆናቸውም ከዚህ ጋር ተዳምሮ ለውጤት ያበቃቸዋል ብዬ አስባለሁ። የተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ለማጽደቅ ካገላበጠው የትምህርትና የልምድ ማስረጃቸው በላይ፣ ይህ ሚዛን እንደሚደፋም እገምታለሁ።

እንደ አንድ ተራ ግለሰብ፣ ሚኒስትሮች ሲሾሙና ሲለወጡ ታዝቤአለሁ። ዘገባዎችንና መረጃዎችን ተመልክቻለሁ። ሁሉም ተሿሚ ሚኒስትሮች የየራሳቸውን ጥረት አድርገው ይሆናል፤ ግን ለውጥ አላየንም። ሌላው ቀርቶ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደጃፍ ተኝተው ማስቲሽ እየሳቡ ለሚያድሩ ሕጻናት መፍትሔ አልተሰጠም። መች አይዋቸውና!
ሴቶች ሲጠለፉና ሲደፈሩ፣ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሲሆኑ፣ ከጩኸቶች መካከል ድምጻቸው የሚገኘው በፍለጋ ነው። ሰልፍ እንውጣ ቢባል አያስተባብሩም፣ ሕግ እንዲሻሻል የሚያደርጉት ተጽእኖ አይታይም። ‹ቀኝህ ሲሰጥ ግራህ አይመልከት!› እንዲል ጽድቅን ብለው ዝምታን መርጠው ከሆነ አላውቅም፣ ግን ጠብ ያለ ሥራ ሰምተን አናውቅም።

ክብርት ሚኒስትር ፊልሰን ይህን እንደሚቀይሩ፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሊሠራ የሚችለውን ሥራና ያለውን አቅም እንደሚያሳዩ፣ ያልተነገረላቸውና ብርቱ የሆኑ የተቋሙን ሠራተኞች ይዘው ከፍ እንደሚሉ፣ በለመዱት በመሮጥ ወር እየጠበቁ ደሞዝ፣ ድግስ እየጠበቁ ድምቀት የሚወዱትንም እንደሚያርሙ እጠብቃለሁ።
‹‹ሥራዬ ማስተባበር ብቻ ነው›› እያለ ጥፋትን የሚታገስ ሳይሆን፣ ከክልል ቢሮዎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሕጻናትና ሴቶችን የሚጠብቅ፣ የሚያገለግል ተቋም ነው የሚፈልገው። ፊልሰን ያንን ሆነው እንደሚገኙም ነው የምጠብቀው።
መልካም የሥራ ዘመን!
መቅደስ /ቹቹ/

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here