ሺሻ መጠቀም በሕግ ሊከለከል ነው

0
828

የሺሻ ምርቶችን መሸጥና ማሰራጨትም ሆነ መጠቀምን የሚከለክል ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እየተመከረበት ነው።
ማክሰኞ ኅዳር 2/2011 ምክር ቤቱ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ባቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አድርጓል። በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የአልኮል ምርቶች ላይ ከሚጣለው ገደብ ባሻገር የሺሻ ምርቶችን መጠቅም የሚከልክሉ ድንጋጌዎች መካተታቸው ታውቋል። ከዚህ ቀደም ሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ቁጥር 661/2002 የትንባሆ ምርቶች ላይ የሕግ ክፍትት ነበረበት ተብሏል። በምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳድርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕግ ባለሙያው ዳግም ዓለማየሁ እንደሚሉት ከዚህ ቀድም ሺሻን በሚመለከት የነበሩ ድንጋጌዎች አከራካሪ ሆነው ቆይተዋል።
እንደ ዳግም ማብራሪያ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ ሥር ያልተጠቀሱ የሺሻ ምርትን ወደ አገር ማስገባት፣ ማሰራጨትና ማስጠቀም ላይ ጠበቅ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች አካትቷል።
እስከ ሚቀጥለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥም ረቂቅ አዋጁን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በመላክ ለማስፀደቅ እየተሠራ እንደሆነ የሕግ ባለሙያው ጠቁመዋል። በተለይም በፍራፍሬና በሌሎች ጣፋጭ ይዘት ባላቸው ቃናዎች የሚዘጋጁ የሺሻ ምርቶቸ በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ።
በከተማዋ የሚገኙ የሺሻ ማስጨሻ ቤቶችም ሕጋዊ በሚመስል መልኩ ሥራቸውን ሲያክናወኑ እንደሚስተዋል ይገለጻል። ከወራት በፊትም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ ሺሻ ቤቶችን መዝጋቱንና ሲጠቀሙ ያገኛቸውን ሰዎች በሕግ ጥላ ሥር ማዋሉን በይፋዊ መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ሥራውን በሚሠሩ አካላት ተጠያቂ የሚያደረግ ሕግ ባለመኖሩ ሊዘጋብን አይገባም በሚል ተቃውሞ አንስተውም ነበር።
አዋጁን ለማውጣት መዘግየት ይታያል የሚሉት የውስጥ ደዌ ሐኪሙ ዶክተር አወጣኸኝ ኤፍሬም ሺሻን ጨምሮ በተለያየ ጣእምና ይዘት የሚቀርቡ የትንባሆ ምርቶች በአብዛኛው ከመተንፈሻ ስርዓት ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች እንደሚያስከትሉ አስገንዝበዋል። በዚህም ወጣቶች የችግሩ ተጠቂ መሆናቸን ጠቅሰዋል። በአዋጁ መውጣት ላይ መዘግየት ታይቷል በሚለው ሐሳብ የሚስማሙት ዳግም ከአስፈፃሚ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን አንስተዋል። ይህን ሕግ ከማውጣት ባለፈ ማስፈፀም ላይ ተደጋጋሚ እጥረቶች እንደሚግጥሙ ይነገራል። ለአብነትም ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች ሲጋራ ማጤስን የሚከለክለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቢወጣም በማስፈፀም በኩል ክፍተት በመኖሩ ዛሬም ብዙዎችን ለችግር እየዳረገ መሆኑን መረጃዎች ያመለከታሉ።
እንደ ዶክተር አወጣኸኝ ገለጻ በአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ላይ የሺሻ ምርት ስርጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ቢሆንም ጆሮ ዳባ ልበስ ተብላል።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው 80 በመቶ የሚሆኑት የትንባሆ አጫሾቸ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ አገራት ውስጥ ይገኛሉ። በተለይም የሺሻ ምርቱ ከመካከለኛው ምሥራቅ የአረብ አገራት በሕገ ወጥ መልኩ የሚገባ ነው።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት በ2007 ባስጠናው ጥናት በአገሪቱ 16 በመቶ ሕዝብ ጫት እንደሚቅም እና 41 በመቶ ዜጋ አልኮል እንደሚጠጣ ተረጋግጧል።
ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን የትንባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን መመሪያ ተቀብላ ብታፀድቅም አተገባበር ላይ ክፍትቶች እንደሚታዩ በተደጋጋሚ ይነገራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here