ዶላር እስከ 40 ብር በትይዩ (“ጥቁር”) ገበያዎች እየተሸጠ ነው

0
1072

ዶላር በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢና በሌሎች አካባቢ በሚገኙ ትይዩ (“ጥቁር”) ገበያዎች ከ36 ብር እስከ 40 ብር ድረስ እንደ መጠኑ ሁኔታ እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያደረገችው የገበያ ግምገማ አመላከተ።
በአገር ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት አስመጭ ነጋዴዎች ፍላጎታቸውን ለማሳካት ትይዩ ገበያን በብዛት መጠቀማቸው ለዶላር ዋጋ መናር እንደ ዋነኛ ምክንያት ተገልጿል።
አዲስ ማለዳ ለህትመት እስከ ገባችበት ድረስ ዶላር በባንኮች በአማካይ 27.7 ብር አካቢቢ ይሸጥና ይገዛ ነበር፡፡ ይህም በመደበኛና በኢ-መደበኛ የውጭ ምንዛሬ ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት ከ10 ብር በላይ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህን ያህል ልዩነት ሲያጋጥም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በነሐሴ ወር አካባቢ ዶላር ወደ 37 ብር ገደማ በትይዩ ገበያዎች ይሸጥ እንደነበር አይዘነጋም። ከዶላር ባሻገር ፓውንድ ከ 38 ብር እስከ 41 ብር ሲሸጥ ዮሮ ደግሞ ከ 38.50 እስከ 41 ብር ይሸጣል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ የሚገኙ የትይዩ ገበያ ነጋዴዎች እንደገለጹት ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ዶላር ፈላጊዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።
‹‹በትይዩ ገበያ ያሉ ነጋዴዎች እጅ ውስጥ ያለው ዶላር አነስተኛ መሆኑ የዶላር ዋጋ ሊጨምር ችሏል›› በማለት አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው አንድ በኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ የሚገኝ የትይዩ ገበያ ነጋዴ ገልጿል። ‹‹የበረራ አስተናጋጆች ፣ አስመጪዎችና የተለያዩ የግል ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን›› አክሏል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም የጥቁር ገበያውን ለማዳከም የተለያየ እርምጃዎችን ቢወስድም አላማውን ሊያሳካ አልቻለም። ከነዚህም መካከል፤ በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ ጠቅላይ ሚንስቴር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የውጭ ምንዛሬ ማስተካካያ ሊወስድ ይችላል ማለታቸውን ተከትሎ፤ ብር ከዶላርና ሌሎች ዋና የውጭ ምንዛሬ ጋር ሲነፃፀር ያለው ዋጋ ሊቀንስ ይችላል ተብሎ በተሰራጨ ሃሰት መረጃ ምክንያት፤ በመደበኛና በኢ-መደበኛ የውጭ ምንዛሬ ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት ከስምንት ብር ወደ 20 ሳንቲም ዝቅ ብሎ ነበር።
ነገር ግን ይህ ከሆነ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፤ እርምጃ ውሸት መሆኑን የተረዱት የትይዩ ገበያ ነጋዴዎች አንዱን ዶላር እስከ 35 ብር ድረስ ሲሸጡና ሲገዙ ነበር። ይህንን የተረዳው መንግስት በበኩሉ፤ ድንገታዊ በሆነ እርምጃ ዋና ዋና የጥቁር ገበያ ማዕከሎችን በመዝጋትለ፤ ሲገበያዩ የነበሩትን ነጋዴዎች በማሰር በሚሊየን የሚቆጠር ብሮችን ወርሶ ነበር።
ይሁን እንጂ፤ ይህ እርምጃ በተወሰደ ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፤ የትይዩ ገበያው ሊያንሰራራ ችሏል። ከ16 ዓመት በላይ በፋይናንስ ልምድ ያላቸው አብዱልመናን መሐመድ እንደገለጹት እንደዚህ ዓይነቱ እርምጃ የትይዩ ገበያው ለማዳከም ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም። ባለሙያው ለአዲስ ማለዳ እህት መፅሔት ‹‹ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው›› በሰጡት አስተያየት ‹‹መንግሥት ለዋጋ ግሽበትና ለበጀት ጉድለት የሰጠው ያነሰ ትኩረት ከአገሪቷ የላላ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ተጨምሮበት ለኢ-መደበኛ የውጭ ምንዛሬ ገበያው መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት ናቸው›› ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አሚን አብደላ የተባሉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ገለጻ የውጭና የውስጥ ንግድ ተመጣጣኝ አለመሆን ለጥቁር ገበያው መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት ነው ብለዋል። ‹‹አገሪቷ በዓለም ዐቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ባለመሆኗ የተነሳ ወደ ውጭ የተለያዩ ዕቃዎችን በመላክ የምታገኘው ገቢ ፍላጎቷን ለማሳካት በቂ አይደለም›› ብለዋል።
በርግጥ፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዕቃዎችን ወደ ውጭ በመላክ ያገኘችው ገቢ ወደ 2.9 ቢሊየን ዶላር አካባቢ ሲሆን ከተለያዪ አገራት ያስገባችው ደግሞ ወደ 15 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል። በተጨማሪም ከሐዋላ የሰበሰበችው ደግሞ ወደ 4.2 ቢሊየን ዶላር ይሆናል። ይሁን እንጂ የአገሪቷ የዶላር ክምችት የፍላጎቷን አንድ አራተኛ እንኳን መሸፈን አይችልም።
ይህንን ተከትሎ እያደገ የመጣው የጥቁር ገበያው የባንኮች የገንዘብ ክምችት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ የተለያዪ የባንክ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
አይ ኤም ኤፍ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ የወጭ ምንዛሬ ችግሯን ለመፍታት በፍላጎትና አቅርቦት የሚመራ ነፃ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ዘዴ እንድትጠቀም መክሯል።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here