በየትኛውም አገር ከልማት ሥራዎች ጋር ተያይዞ የከተሞች መስፋፋት ይከሰታል። የአገራት ዕድገት ከሚገለጹባቸው መንገዶችም አንዱ ይኸው የከተሞች መስፋፋት ነው። ችግሩ፣ ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ በከተሞች ዙሪያ የሚገኙ አርሶ እና አርብቶ አደሮች በተስፋፊዎቹ ከተሞች ተፅዕኖ ሥር መውደቃቸው ነው።
በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የከተሞች የልማት እንቅስቀሴዎችም ከነባራዊው ዓለም ሁኔታዎች የተለዩ አይደሉም። በተለይ አዲስ አበባን በመሳሰሉ ትልልቅ ከተሞች የሚታዩት መስፋፋቶች ዙሪያ ገባውን ባሉ አርሶ አደሮች ሕይወት ላይ ዘላቂ ተፅዕኖ ማሳደራቸው የአደባባይ ምሥጢር ከሆነ ውሎ አድሯል። በተለይ ከአዲስ አበባ ከተማ ማስፋፋት ጋር በተያያዘ ተፅዕኖዎቹ ከአዲስ አባባና ዙሪያው አልፎ የአገሪቱ ዋናኛ የማኅበረ ፖለቲካን ዕጣ ፈንታ ሲወስኑ ተስተውሏል።
ለምሳሌ መንግሥትን በማናወጥ አሁን ለሚስተዋለው ፖለቲካዊ ለውጥ መነሻ የሆኑት የቅርብ ዓመታቱ ሕዝባዊ አመፆች መነሻ ያደረጉት የአዲስ አበባ ‘ማስተር ፕላን’ በአጎራባቾቹ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞኖች የሚኖሩትን ገበሬዎች ያፈናቅላል በሚል ነው።
ስለዚህም ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዙ የሚነሱ ጉዳዮች በሕግ አግባብ ብቻ ሳይሆን በአተገባበርም ረገድ በጥንቃቄ መታየት አለባቸው። ይሁን እንጂ ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ያለው ቅሬታ በከፍተኛ ድምፅ ቢደመጥም በኢትዮጵያ ባሉ ከተሞች መስፋፋት ሳቢያ በከተሞቹ ዙሪያ ያሉት አርሶ አደሮች ለብዙ እንግልቶች እየተዳረጉ ነው።
የጉዳዩን ሕጋዊ አንድምታ የተመለከትን እንደሆን፣ አሶር አደሮች ከመሬታቸው መፈናቀል እንደሌለባቸው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ ተደንግጎ ይገኛል፦
አንቀጽ 40/4፡ “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው።…”
ይሁን እንጂ በዚሁ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ፣ ንዑስ አንቀጽ 8 እንደተመለከተው “የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ካሣ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ ይችላል።”
ይሁንና በኢትዮጵያ ባሉ የከተሞች መስፋፋት ሳቢያ ከእርሻ መሬታቸው እና ከቤታቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች የሚከተሉት ተግዳሮቶች ተጋርጠውባቸዋል፦
– ተመጣጣኝ ወይም የወቅቱን ገበያ ከግምት ውስጥ ያስገባ ካሣ እየተከፈላቸው አይደለም፣
– የአርሶ አደሮቹን ሥነ ልቦና እና ማኅበራዊ ግንኙነት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ምትክ ቦታ እና አሰፋፈር እየተመቻቸላቸው አይደለም፣
– ከእርሻ ቦታቸው የሚነቀሉት አርሶ አደሮች በጉዳዩ ላይ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጊዜ እየተሰጣቸው አይደለም፣
– በመመሪያዎች ዙሪያ ክፍተቶች እና አለመናበቦች አሉ፤ የሕግ አተገባበሩም ፍትሓዊነት ይጎድለዋል።
እነዚህ ዋነኞቹ ችግሮች ቢሆኑም ቅሉ፣ ሌሎችም በርካታ ችግሮች አሉባቸው። ከነዚህም ውስጥ የከተማ ኑሮ ባለማወቃቸው እና የተሰጣቸውን ካሣ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ክኅሎት ባለማዳበራቸው ወይም እንዲያዳብሩ የሚመለከተው አካል ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ምክንያት ገንዘባቸውን በማባከን ለችግር እየተዳረጉ ነው። በሌላ በኩል የከተማ የገጠር አስተዳደሮች የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች ከነዋሪዎቹ ጋር በመመካከር ባለማድረጋቸው ምክንያት እርምጃዎቹ በጥርጣሬ እየታዩ ጠቃሚ መሆን አለመሆናቸው ሳይረጋገጥ ገና የግጭት መንስዔ እስከመሆን እየደረሱ ነው።
በመሆኑም ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩትን ችግሮች ለዘለቄታው ለመፍታት፦
– የሚመለከታቸውን አካላት ባግባቡ ያሳተፈ የልማት ዕቅድ መንደፍ፣
– የተነሺዎችን ማኅበራዊ ኑሮ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ምትክ ቦታ መስጠት፣
– የሚከፈላቸው ካሣ የወቅቱን የገበያ ዋጋ ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ተመጣጣኝ መሆኑን ማረጋገጥ፣
– ለተነሺዎች ከቦታቸው ከመነቀላቸው በፊት በቂ የዝግጅት ጊዜ እንዲኖራቸው ማድረግ፣
– የተነሺዎችን ዕድሜ፣ ዕውቀት፣ ክኅሎት እና ሌሎችንም ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥልጠና እና የማደራጀት ሥራ ማከናወን ከብዙ አስፈላጊ የመፍትሔ እርምጃዎች ጥቂቶቹ ናቸው።
በመሆኑም አዲስ ማለዳ በከተሞች መስፋፋትና ልማት ሰበብ በሚደረጉ የልማት ተነሺዎች ጉዳይ፣ መንግሥት ከላይ የጠቀስናቸውን የመፍትሔ ጥቆማዎች ካልተከለ እና ወጥ አገር ዐቀፍ ፖሊሲ ካልተገበረ፣ የልማት እርምጃዎቹ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አመዝኖ ለሕዝባዊ ቅሬታ መንስዔ እንደሚሆኑ ታሳስባለች።
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011