ፖለቲካችን አጀንዳ አልባ መሆኑ ይብቃ!

0
497

በዚህ ሳምንት አነጋጋሪ ከነበሩ ነገሮች መካከል ኹለቱ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባካሄደው የሕዝብ ውይይት ላይ ታዳሚ የነበረች አንዲት ሴት “ሀበሻ” ሚስቶች ያሏቸው የኦሮሞ ወንዶች ሊፈቷቸው ይገባል ማለቷ እና ዳንኤል ክብረት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባልነትን አስመልክቶ በተወካዮች ምክር ቤት የነበረው የተቃውሞ ክብረ ወሰን ነው።

ምንም እንኳን እነዚህ ኹለት አጋጣሚዎች አነጋጋሪ ሊሆኑ ቢችሉም፣ በዋነኛነት የሚያሳዩት ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለምርጫ አምስት ወራት እንኳን እየቀሩት በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ምንም ዓይነት ትኩረት እንደማያደርግ ነው። ዋና ዋና የምርጫ መወዳደሪያ አጀንዳዎች ግልጽ በሆነ መንገድ በማይታወቁበት እና የፖሊሲ ጉዳዮች አሁንም ለአብዛኞቹ ፓርቲዎች በጭፍን ከማነሳሳት ጋር በማይወዳደር መልኩ ከኋላ በተቀመጡበት ሁኔታ፣ እንደዚህ ሳምንቶቹ ዓይነት ግለሰቦች የሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች የፖለቲካው መነጋገሪያ ይሆናሉ።

የማኅበራዊ ሚዲያዎች በስልክ ላይ በቀላሉ በየግለሰቦች እጅ ባሉበት እና የመረጃ ቴክኖሎጂው ክስተቶችን እና ኹነቶችን በቀላሉ ሊያስተላልፍ በሚችልበት በአሁኑ ጊዜ፣ የሴትየዋ ፅንፈኛ አመለካከት መነጋገሪያ መሆኑ አይገርምም። የሕዝብን ደም ያፋሰሱ ሕጎችን ይህ ነው ሊባል በማይችል ተቃውሞ ሲያሳልፍ የከረመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ግለሰብን የቦርድ አባልነት በታሪኩ ከፍተኛው የክርክር እና የተቃውሞ ማሳያ ማድረጉም ከእርሱ የሚጠበቅ ነው።

እነዚህ ነገሮች የሕዝብ መነጋገሪያ መሆናቸውም የሚደንቅ አይደለም። ነገር ግን የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንኳር መወዳደሪያ ነጥቦች እንዳሉ ሆነው፣ እነዚህ አጋጣሚዎች ቅንድብን ከፍ አድርገው የሚያልፏቸው ጉዳዮች ብቻ ሊሆኑ ይገባ ነበር። አሳዛኙ እውነታ ግን የአገሪቱ ፖለቲካ ከእነዚህ ከፍ ያለ አወቃቀር፣ እቅድ እና ቅንጅት ያለው የፖለቲካ አጀንዳዎች ፍሰት የሌለው መሆኑ ነው።
የአንድ ግለሰብም ሆነ የቡድኖች መስመር የለቀቁ እንቅስቃሴዎች የአገሪቷ የፖለቲካ አጀንዳ ሆነው በሚዲያዎች ተባባሪነት አብዛኞቹ የፖለቲካ ተዋናዮች አስተያየት ሲሰጡባቸው አይተናል። በአንጻሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ፓርቲያቸው ለሕዝብ ምን ዓይነት የፖሊሲ አማራጮችን እንዳመጣ ሲጠየቁ ‹‹እያዘጋጀነው ነው። ሲያልቅ እናሳውቃለን!›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው እየተለመደ መጥቷል። ይህም ቀደም ብለው ጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዳልሰጡ በግልፅ የሚያሳይ ነው።

ምርጫው ለመካሔድ አምስት ወራት ብቻ እየቀሩት ከኹለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጪ ሌሎች ከመቶ በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎች (ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ) በአዲሱ የምርጫ አዋጅ መሠረት ያልተመዘገቡ መሆኑ ሲታሰብ ፖለቲካ ውስጥ ያሉት ሰዎች ምን ትክክል የሆነ ነገር እየሠሩ ነው ያስብላል።

ሕዝቡን ሕዝባችን ብለው የሚጠሩት አካላት ከጊዜ ወደ ጊዜ አጀንዳዎቻቸው እያነሱ መምጣቸው ብሎም መጪውን ምርጫ ለማሸነፍ እና አገር ለመምራት ሊያጠፉት የሚገባውን ጊዜ እርባና በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ማባከናቸው ከማሳሳብም አልፎ ብዙ ያጠራጥራል። በገዢውም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ፍላጎት የአገርን ቀጣይነት እና የሕዝብን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ነው ወይስ ወገኔ የሚሉት ቡድን ፊት ቆመው ሌሎች ከሚሏቸው ቡድኖች ጋር ጠብ መጫር?

በየሳምንቱ በፖለቲከኞች ንግግርም ሆነ ድርጊት ተደንቀን የምንነጋገርበት፣ አለፍ ሲልም የምንተላለቅበት ሁኔታ ሊበቃ ይገባል። ፖለቲከኞች በየጊዜው እርስ በእርስ የሚያናክሱንን ጉዳዮች ከሚግቱን በመጀመሪያ ሥራቸው ምን እንደሆነ ጠንቅቀው ለመረዳት ቢሞክሩ ይሻላል።

በሠለጠነው ዓለም ምርጫ እንዲህ ከመቅረቡ ቀደም ብሎ ፓርቲዎች የሚወዳደሩባቸው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ አጀንዳዎች ይለያሉ። በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ የኢኮኖሚ አጀንዳዎች የኑሮ ውድነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ እየተቀዛቀዘ የመጣው የኢኮኖሚ ዕድገት ወይም የውጭ ኢንቬስትመንት ፍሰት መቀነስ ሊሆኑ ይችላሉ። የፖለቲካ አጀንዳዎች ደግሞ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ የብሔር እና ግለሰብ መብቶች ንፅፅር ወይም የርዕዩተ ዓለም ክርክሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ማኅበራዊ አጀንዳዎችም በዚሁ መንገድ የሚለዩ ይሆናል።

ከዚያም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸውን አማራጭ በማቅረብ ችግሮቹን እንዴት እንደሚፈቱ ያስረዳሉ። ከዚያም መራጩ ሕዝብ የተሻሉ አማራጮች የያዘ የመሰለውን ፓርቲ ይመርጣል። በዚህ መንገድ መራጮች በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ እንዲሰጡ የፖለቲካ ስርዓቱ በሩን ይከፍትላቸዋል።

በዚህ ዓይነቱ ስርዓት ውስጥ በዚህ ሳምንት በአገራችን እንደተፈጠሩት ከላይ የጠቀስናቸው ዓይነት ነገሮች ቢከሰቱ፣ ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች በምርጫው ላይ ያላቸውን ተቀባይነት ይለውጡታል። ከመስመር የወጡ አስተያየቶችም ሆኑ ተግባራት ቢኖሩ ሕዝብ እነዚህን ለመቅጣት የሚችልበት በመረጃ የተደገፈ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ስላለ ፖለቲከኞች እንደፈለጉ መዘባረቅ አይችሉም።
በተቃራኒው በእኛ አገር ለምርጫ አጀንዳነት የሚሆኑ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች አይለዩም። ፖለቲካ ፓርቲዎችም በእነዚህ ሦስት ዘርፎች ውስጥ ባሉ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋም በተደራጀ መልክ አያዘጋጁም። አሁን እንደሚታየው ከሆነ ማዘጋጀቱ ላይ የሚያምኑትም የተወሰኑ ናቸው። እነሱም ለምርጫው ጥቂት ወራት ብቻ እየቀረ እንኳን አዘጋጅተው አልጨረሱም።
በዚህ ሁኔታ የአገራችን መራጭ ሕዝብ በመረጃ የተደገፈ ምርጫ ያደርጋል ማለት ዘበት ነው። በመሆኑም በከፍተኛ ሁኔታ ፖለቲከኞቻችን የተካኑበትን ጥላቻ መንዛት አጠናክረው ይቀጥላሉ። እኛም የእኛ ወገን የመሰለንን ቢያጠፋም እንዳላየ እያለፍን የሌላ የምንለውን ቀና ንግግር ደግሞ እያጣመምን የጦፈው የአገራችን የምርጫ ሒደት አካል እንሆናለን።

ይህ አጀንዳ አልባነት እንደ አገር የሚያዳክመን መሆኑን መገንዘብ እና ሁኔታውን ለመቀየር በፍጥነት መሥራት እንዳለብን አዲስ ማለዳ ታምናለች። በመሆኑም በየጎጡ የሚታየው የጥላቻ መርዝ የመርጨት አካሔድ ቆሞ በዘላቂ ሁኔታ የአገራችን እና የሕዝቦቿን ችግሮች ቀረብ ብለን የምንመለከትበት የምርጫ መድረክ ሊከፈት ይገባል።

ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኋን፣ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት አጀንዳ አልባነትን እንደ ችግር ሊያዩት ይገባል። ይህን ካደረጉ በኋላ በመካከላቸው ቅንጅት እንዲኖር በመሥራት አገራዊ ኃላፊነትን መወጣት ይገባል።

ይህ እስኪሆን ድረስ ግን ፖለቲከኞቻችን የፖለቲካ ሥነምግባር ሊኖራቸው ይገባል። የፖለቲካ ሥነምግባር በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትርጉም መሰረት በዋናነት በሞራል ዋጋዎች ላይ በተመሰረቱ ውሳኔዎች የሚለካ ነው። ይህም የፖለቲካ ሥነ ምግባር ከሚመራባቸው የሕግ ማእቀፎች ባለፈ የሚንቀሳቀስበትን አውድ ያማከለ የሞራል ማሰሪያ አለው።

በዩኒቨርሲቲው እንደተረቀቀው የሥነ ምግባር ኢንሳይክሎፒዲያ ማብራሪያም እንደ አንድ የጥናት ዘርፍ ተወስዶ ጥናት የሚደረግበት የፖለቲካ ሥነ ምግባር በኹለት ዋና መደቦች የተከፈለ ነው። የመጀመሪያው ፖለቲከኞች የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸውን የሚያከናውኑበት መንገድ ላይ ሲመሰረት ሌላው ግን በሚተገብሯቸው የማኅበራዊ ፖሊሲዎች ላይ ያተኩራል። በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ፖለቲከኞች በግል ተግባራቸው የሚያሳዩትን ሥነ ምግባር ሲመለከት ኹለተኛው ደግሞ የመንግሥትን ቢሮ ሲጠቀሙ በሚያጋጥሟቸው የውሳኔ አጋጣሚዎች ላይ ግንዛቤ ውስጥ የሚከቷቸው የሞራል ጉዳዮችን ይመለከታል።

ከዚህ የምንገነዘበው የእኛ አገር ፖለቲከኞች ፖለቲካዊ ሥራቸውን ብቻ ሲሠሩ ሳይሆን በግል ሕይወታቸውም ውስጥ የሥነ ምግባር ሁኔታቸው ጥሩ መሆን እንዳለበት ነው። ነገር ግን ይህንን ሁኔታ አሟልተው ሲንቀሳቀሱ ስለማይታይ የሥነ ምግባር ሁኔታቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥልጠናዎች ሊሰጣቸው ይገባል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here